በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የርት—የመካከለኛው እስያ ተንቀሳቃሽ ቤት

የርት—የመካከለኛው እስያ ተንቀሳቃሽ ቤት

የርት—የመካከለኛው እስያ ተንቀሳቃሽ ቤት

ለስላሳ ሽፋንና ክብ ቅርጽ አለኝ፤ ክረምት ላይ ሰዎች እንዲሞቃቸው አደርጋለሁ፤ በጋ ላይ ደግሞ ቀዝቀዝ ያለ አየር እንዲያገኙ አደርጋለሁ፤ እኔ ማን ነኝ? በመካከለኛው እስያ ለሚኖሩ ዘላን ሕዝቦች ይህ እንቆቅልሽ ቢቀርብላቸው “የርት” የሚል መልስ እንደሚሰጡ ጥርጥር የለውም። ድሮ ድሮ በሞንጎሊያና በካዛክስታን ከሚገኙት አውላላ ሜዳዎች አንስቶ በኪርጊስታን እስከሚገኙት ተራሮችና ሸለቆዎች ድረስ እነዚህን መኖሪያ ቤቶች ማየት የተለመደ ነበር።

የርት ክብ ቅርጽ ያለው ድንኳን የሚመስል ቤት ሲሆን ከደንገል በተሠራ ኬሻ ቄንጠኛ በሆነ መንገድ ይሸፈናል። ከዚያም ከሱፍ የተሠራ ጨርቅ እንዲለብስ ይደረጋል። የርቶች ለመሸከም የማይከብዱና በቀላሉ የሚገጣጠሙ ቢሆኑም ጥንካሬ አላቸው፤ እንዲሁም በሞቃትም ሆነ በቀዝቃዛ ወቅቶች የሚመቹ ናቸው። ኪርጊስታኖች የርትን ‘ግራጫ ቤት’ ብለው ሲጠሩት ካዛክስታኖች ደግሞ ‘የጨርቅ ቤት’ ይሉታል፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሞንጎሊያውያን ጌር ብለው የሚጠሩት ሲሆን ትርጉሙም “ቤት” ማለት ነው።

የርቶች እንደተሠሩበት የሱፍ ዓይነት ቀለማቸው ፈዛዛ ቡኒ ወይም እንደ ወተት የነጣ ሊሆን ይችላል። ብዙውን ጊዜ የኪርጊስታንና የካዛክስታን የርቶች፣ በአካባቢው የንድፍ ጥበብ በተሠሩ የሱፍ ጨርቆች ያጌጡ ናቸው፤ ደማቅ በሆኑ ቀለማት በተነከሩ ፈትሎች የሚሠሩት እነዚህ ጨርቆች የበግ ቀንድ ምስል አለባቸው። ቀደም ባሉት ዘመናት አንድ ቤተሰብ የሚያማምሩ ብርድ ልብሶችና ከሱፍ የተሠሩ የወለል ምንጣፎች ካሉት፣ ባለጸጋና የተከበረ እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር።

የጣሪያው ወራጆች በሙሉ የሚገናኙበት በየርት አናት ላይ የሚገኘው ቀለበት የቤቱ ወሳኝ ክፍል ነው። ጠንካራና ክብደት ያለው ይህ ቀለበት ቤቱ ቀጥ ብሎ እንዲቆም ይረዳዋል። ድንኳኑን ማናፈስ ሲያስፈልግ ድምድማቱ ላይ የሚገኘውን ይህን ቀለበት የሚሸፍነው የጨርቅ ልባስ ሊነሳ አለዚያም በቅዝቃዜና በዝናብ ወቅት ወደ ቦታው ሊመለስ ይችላል። ሌሊት ላይ ሰማዩ የጠራ በሚሆንበት ጊዜ የቀለበቱን ሽፋን በማንሳት በከዋክብት ያሸበረቀውን ሰማይ በክፍተቱ በኩል መመልከት ይቻላል።

ለዘላን ኑሮ የሚስማማ

እንደ ካዛክስታን፣ ኪርጊስታንና ሞንጎሊያ ባሉት አገሮች ውስጥ በሚገኙ አንዳንድ ገጠራማ አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎች አሁንም ድረስ የዘላንነት ሕይወት ይመራሉ። ቤኪ ኬሜሪ የተባሉ ሴት የርትስ—ሊቪንግ ኢን ዘ ራውንድ በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ የሞንጎሊያ ግመሎች አሁንም ድረስ ድንኳኖችን ለማጓጓዝ እንደሚያገለግሉ ሲናገሩ እንደሚከተለው ብለዋል፦ “ቤቱ የሚዋቀርባቸው እንጨቶች እንዳያጋድሉ ተደርገው በአንድ ግመል ላይ ይጫናሉ። በመጨረሻ የሚጫነው የጣሪያው ቀለበት ሲሆን በግመሉ ሻኛ ላይ ተስተካክሎ ይቀመጣል። ልባሶቹ ደግሞ በሌላ ግመል ላይ ይጫናሉ። ግመል በሌለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ አርብቶ አደሮች ደግሞ የርቶቻቸውን ወደ አዲሱ ማረፊያ ቦታቸው የሚያጓጉዙት ያክ በሚባለው የእስያ በሬ ወይም በፈረስ የሚጎተት ሠረገላ በመጠቀም ነው፤ ካልሆነ ደግሞ በሩሲያ የጭነት መኪና ሊጠቀሙ ይችላሉ።”

ሞንጎላውያን የርቶቻቸውን ለመሥራት የሚጠቀሙባቸው ቋሚዎች ከሌሎቹ በተለየ ቀጥ ያሉ ናቸው፤ ጣሪያዎቻቸው ደግሞ ይበልጥ ጠፍጠፍ ያሉ ናቸው። ይህ ደግሞ በገላጣ ሜዳዎች ላይ የሚከሰተው ኃይለኛ ነፋስና መብረቅ ጉዳት እንዳያደርስ ይረዳል። በኪርጊስታንና በካዛክስታን የሚገኙት የርቶች ሾል ያለ ቅርጽ ያላቸው ከመሆኑም ሌላ በሌሎች አካባቢዎች ካሉት ይበልጥ ክብ ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ የርቶች የሚተከሉት መግቢያቸው በፀሐይ መውጫ በኩል እንዲሆን ተደርጎ በመሆኑ የፀሐይ ብርሃን ወደ ውስጥ እንዲገባ ያስችላል። ወደ ውስጥ ሲገባ ተጣጥፈው የተቀመጡ በደማቅ ቀለማት ያጌጡ የሱፍ ስጋጃዎችና ብርድ ልብሶች ከበሩ ትይዩ ባሉ የእንጨት ሣጥኖች ላይ ይታያሉ። በባሕሉ መሠረት አንድ የክብር እንግዳ ወይም በቤተሰቡ ውስጥ በዕድሜ አንጋፋ የሆነው ወንድ በቀለማት ያሸበረቁት ጨርቆች ከተደረደሩበት ሣጥን አጠገብ ይቀመጣል።

ከየርቱ መግቢያ በስተቀኝ ያለው ቦታ ለሴቶች የተመደበ ነው። ምግብ ለማብሰል፣ ለጽዳት፣ ለልብስ ስፌትና ለሱፍ መሥሪያ የሚያገለግሉት ቁሳቁሶች በሙሉ የሚቀመጡት እዚህ ነው። በስተግራ በኩል ያለው ቦታ ደግሞ ለወንዶች የተመደበ ነው። ኮርቻና የፈረስ አለንጋ እንዲሁም ለአደንና እንስሳትን ለመንከባከብ የሚያገለግሉ ሌሎች ቁሳቁሶች በዚህ ስፍራ ይቀመጣሉ።

ፖለቲካዊ ለውጦች ቢኖሩም የየርቶች ሕልውና ቀጥሏል

በ1917 ከፈነዳው የኮሚኒስት አብዮት በኋላ የዘላኖች አኗኗር በከፍተኛ ሁኔታ ተለውጧል። ሩሲያውያን በመላው መካከለኛ እስያ ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችንና መንገዶችን በመሥራት ዘላኖቹ ይበልጥ የተደላደለ ኑሮ እንዲጀምሩ አደረጉ።

ጊዜያት እያለፉ ሲሄዱ ብዙዎቹ የአገሬው ሰዎች በመንደሮችና በከተሞች ለመኖር ሲሉ የዘላንነት አኗኗራቸውን እየተዉ መጡ። የተለያዩ ሰዎች ንብረት የሆኑ በጎችን፣ ላሞችንና ፈረሶችን በአንድነት የሚያግዱ እረኞች፣ ከብቶቹን ለግጦሽ በሚያሰማሩባቸው ስፍራዎች ላይ አሁንም ድረስ በሞቃታማ ወቅቶች የርቶችን ይጠቀማሉ።

አሁን በ30ዎቹ ዕድሜ መገባደጃ ላይ የሚገኘው ማክሳት የሚባል ኪርጊስታናዊ እንዲህ ብሏል፦ “በአሥራዎቹ ዕድሜ ላይ ሳለሁ አባቴን በእሱ ኃላፊነት ሥር ያሉ መንጎችን በመጠበቅ እረዳው ነበር። ሐምሌ ላይ በረዶው በሚቀልጥበትና የተራራው መንገዶች በሚከፈቱበት ጊዜ እንስሶቹን ተራራው ላይ ወደሚገኙ የግጦሽ ስፍራዎች ይዘናቸው እንወጣ ነበር።

“እዚያም ለምግብና ለመተጣጠቢያ የሚያስፈልገንን ውኃ እንደልብ በምናገኝበት በአንድ የተራራ ጅረት አጠገብ የርታችንን እንተክል ነበር። የቅዝቃዜው ወቅት እስከሚጀምርበት እስከ ጥቅምት ወር መጀመሪያ ድረስ እዚያው እንቆይ ነበር።” ስለዚህ የርት አሁንም ቢሆን በዘመናዊው ኅብረተሰብ ዘንድ ተፈላጊ ነው።

ዘመናዊው የርት

እንደ ኪርጊስታን ባሉ አገሮች ውስጥ በመንገድ ዳርና ዳር የርቶችን ማየት የተለመደ ነው። እነዚህ ቤቶች እንደ ሱቅ ሆነው ሊያገለግሉ አሊያም ጎብኚዎች ባሕላዊ ምግቦችን የሚመገቡባቸው ሻይ ቤቶች ሊሆኑ ይችላሉ። በተጨማሪም እንግዶች በኪርጊስታን ተራራማ አካባቢዎች ወይም ኢይሲክ ከል በሚባለው ኩልል ባለው ሐይቅ ዳርቻ ላይ በተሠሩ የርቶች ውስጥ በማደር የኪርጊስታንን ሰዎች ባሕላዊ አኗኗር ሊቀምሱ ይችላሉ።

የርቶች በመካከለኛው እስያ ውስጥ ከሚካሄዱ አንዳንድ ባሕላዊ የለቅሶ ሥነ ሥርዓቶች ጋር በተያያዘም ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። ማክሳት “በኪርጊስታን ባሕል መሠረት አስከሬኑ በየርቱ ውስጥ እንዲቀመጥ ከተደረገ በኋላ ቤተሰቦችና ወዳጆች ወደ የርቱ እየገቡ በሚወዱት ሰው ሞት የተሰማቸውን ሐዘን ይገልጻሉ” ብሏል።

የርት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በምዕራባውያን አገሮች ውስጥም መታየት ጀምሯል። አንዳንድ ሰዎች የርት ጠቃሚና የአካባቢውን ገጽታ የማያበላሽ እንደሆነ በመግለጽ ሲያስተዋውቁት ይስተዋላል። ያም ሆኖ ዘመናዊ የሆኑት አብዛኞቹ የርቶች በቀድሞ ዘመን ይሠሩ ከነበሩት በጣም የተለዩ ናቸው። የርቶችን ለመሥራት የሚያገለግሉት ቁሳቁሶች የረቀቀ ቴክኖሎጂ ውጤት ሲሆኑ በአብዛኛው የሚሠሩት በአንድ ቦታ ላይ ረዥም ጊዜ እንዲቆዩ ተደርገው ነው።

የርት ለመጀመሪያ ጊዜ የተሠራው የት እንደሆነ በእርግጠኝነት ማወቅ ባይቻልም ጠቃሚ መሆኑ ግን አሌ የሚባል አይደለም። የርት በመካከለኛው እስያ ለሚኖሩ ዘላን ሕዝቦች ተስማሚ መኖሪያ ከመሆኑም ሌላ መንፈሰ ጠንካራና ከሁኔታዎች ጋር መላመድ የሚችሉትን የእነዚህን ሕዝቦች ብልህነት የሚያሳይ ቋሚ ማስረጃ ነው።

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በታዋቂው ኢይሲክ ከል ሐይቅ ዳርቻ ላይ የተተከሉ የርቶች