በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ሜይዴይ! ሜይዴይ! ሜይዴይ!”—ሕይወት አዳኝ ጥሪ

“ሜይዴይ! ሜይዴይ! ሜይዴይ!”—ሕይወት አዳኝ ጥሪ

“ሜይዴይ! ሜይዴይ! ሜይዴይ!”—ሕይወት አዳኝ ጥሪ

በእሳት የተያያዘችው የዓሣ ማጥመጃ መርከብ በጭስ ታፍናለች! መርከቧ ላይ ያሉት በሙሉ ከባድ አደጋ ተጋርጦባቸዋል። አንድ የባሕር ዳርቻ ጥበቃ ኃላፊ “ካፒቴኑ የሜይዴይ ጥሪ ባያሰማ ኖሮ ‘ኖቲካል ሌገሲ’ የተባለችው መርከብ ምኗም አይገኝም ነበር” ብሏል። የካናዳ የባሕር ዳርቻ ጥበቃ አባላት ለጥሪው ፈጣን ምላሽ በመስጠታቸው የመርከቧን ሠራተኞች ሕይወት መታደግ ችለዋል። *

“ሜይዴይ! ሜይዴይ! ሜይዴይ!” ይህ በሬዲዮ የሚሰማ መልእክት የሰዎች ሕይወት አደጋ ላይ እንደወደቀ የሚያሳውቅ የድረሱልን ጥሪ ነው። የሜይዴይ ጥሪ ምን ያህል ውጤታማ ነው? በ2008 የዩናይትድ ስቴትስ የባሕር ዳርቻ ጥበቃ ተቋም 24,000 የሚሆኑ ሕይወት አድን ተልእኮዎችን ተወጥቷል። ተቋሙ 4,910 ሰዎችን ከሞት ያዳነ ሲሆን በአማካይ በቀን የ13 ሰዎችን ሕይወት ታድጓል ማለት ነው። ከዚህም በላይ ከ31,000 ለሚበልጡ በጭንቅ ላይ ለነበሩ ሰዎች እርዳታ ሰጥቷል።

ይሁን እንጂ “ሜይዴይ” የሚለውን ቃል የምንጠቀመው ለምንድን ነው? መልእክት በሬዲዮ መተላለፍ ከመጀመሩ በፊት መርከቦች የድረሱልን ጥሪ ያሰሙ የነበረው እንዴት ነው?

የጥንቶቹ የድረሱልን ጥሪ ማስተላለፊያ ዘዴዎች

በ1588 ሳንታ ማርያ ደ ላ ሮሳ የተባለችው የስፔን የጦር መርከብ በጣም ኃይለኛ በሆነ ማዕበል መወሰድ ስትጀምር የተኩስ ድምፅ በማሰማት የድረሱልኝ ጥሪ አቀረበች። ሆኖም መርከቧ የሰመጠች ሲሆን በውስጧ ከነበሩት ሰዎች መካከል ማንም ሊተርፍ አልቻለም። ጥንት የነበሩ ሌሎች ባሕረተኞች ደግሞ የድረሱልን ጥሪ ለማቅረብ የሚያገለግሉ ባንዲራዎችን ይሰቅሉ ነበር። ዛሬም ቢሆን መርከቦች የሚጠቀሙበት ትልቅ ቀይ የኤክስ ምልክት ያለበት ነጭ ባንዲራ፣ የእርዳታ ጥሪ ለማስተላለፍ የሚያገለግል ዓለም አቀፋዊ ምልክት ነው።

በ1760ዎቹ ዓመታት ባሕረተኞች ሴማፎር የሚባለውን በምልክት መልእክት የመለዋወጥ ዘዴ መጠቀም ጀመሩ። በዚህ የመልእክት መለዋወጫ ዘዴ የሚጠቀም ሰው ሁለት ባንዲራዎችን በሰዓት ላይ እንደሚገኙት መቁጠሪያዎች አድርጎ ይይዛል። መልእክት አስተላላፊው “የሰዓት መቁጠሪያዎቹን” ቦታ በመለዋወጥ የሚያሳየው እያንዳንዱ ምልክት የተለየ ፊደል ወይም ቁጥር ያመለክታል።

ይሁን እንጂ በባንዲራ፣ በመድፍ ተኩስና በምልክት መልእክት የማስተላለፍ ዘዴዎች የታሰበላቸውን ዓላማ ሊያከናውኑ የሚችሉት መልእክቶቹን ሊያዩ ወይም ሊሰሙ የሚችሉ ሰዎች በቅርብ ካሉ ብቻ ነው። በመሆኑም አብዛኛውን ጊዜ በሞት አፋፍ ላይ የሚገኙ ባሕረተኞች እርዳታ ሳያገኙ ይቀራሉ። ታዲያ ይህ ሁኔታ እንዴት ይሻሻል ይሆን?

ይበልጥ ውጤታማ የሆኑ የድረሱልን ጥሪ ማስተላለፊያ ዘዴዎች

በ1840ዎቹ ዓመታት የመገናኛ ቴክኖሎጂው ዘርፍ ትልቅ እመርታ አሳየ። ሳሙኤል ሞርስ፣ የቴሌግራም ኦፕሬተሮች በሽቦ መስመር በተገናኘ በእጅ የሚሠራ መሣሪያ አማካኝነት መልእክት ማስተላለፍ የሚችሉበትን ዘዴ ፈለሰፈ። ኦፕሬተሩ የመልእክት ማስተላለፊያውን መሣሪያ ቁልፍ ተጭኖ ሲቆይ በሽቦው ሌላኛ ጫፍ በኩል ያለው ግለሰብ የኤሌክትሪክ ንዝረት መኖሩን ማወቅ ይችላል። በሞርስ ኮድ መሠረት አጭሩ ንዝረት ነጥብን፣ ረጅሙ ንዝረት ደግሞ ሰረዝን የሚያመለክት ሲሆን እያንዳንዱ ፊደልና ቁጥር በተለያየ የነጥቦችና የሰረዞች ቅንብር ይወከላል።

መርከበኞች በባሕር ላይ የሞርስ ኮድን ሥራ ላይ የሚያውሉት እንደ ቴሌግራም ኦፕሬተሮች የድምፅ ኮድ በመላክ ሳይሆን ደማቅ የብርሃን ጨረሮችን በመጠቀም ነበር። መልእክት አስተላላፊው ነጥብን ለማመልከት ጨረሩን ለአጭር ጊዜ የሚለቅ ሲሆን ሰረዝን ለማመልከት ደግሞ የብርሃኑን ጨረር ረዘም ላለ ጊዜ ይለቀዋል። ብዙም ሳይቆይ መልእክት አስተላላፊዎች ኤስ ኦ ኤስ * (SOS) የሚሉትን የእንግሊዝኛ ፊደላት የሚወክሉ ሶስት ነጥቦች፣ ሶስት ሰረዞችና ሌሎች ሶስት ነጥቦች (... --- ...) በመጠቀም ቀላልና ልዩ በሆነ መንገድ የድረሱልን ጥሪ ማስተላለፍ ጀመሩ።

የድረሱልን ጥሪዎችን ለማስተላለፍ የሚያገለግሉት ዘዴዎች በዚህ ብቻ አልተገደቡም፤ ከጊዜ በኋላ የተፈለሰፉት ዘዴዎች ይበልጥ ውጤታማና ረጅም ርቀት የሚሸፍኑ መሆን ችለዋል። ጉልየልሞ ማርኮኒ በ1901 የሬዲዮ መልእክት ለመጀመሪያ ጊዜ ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ባሻገር ማስተላለፍ ቻለ። በዚህ ጊዜ የኤስ ኦ ኤስ መልእክቶችን በብርሃን ጨረር ሳይሆን በሬዲዮ ሞገድ መላክ ተቻለ። ይሁን እንጂ በዚህ ጊዜም ቢሆን ኦፕሬተሮች የሰው ድምፅ በመጠቀም የድረሱልን ጥሪዎችን ማስተላለፍ አልቻሉም። “ሜይዴይ! ሜይዴይ! ሜይዴይ!” የሚለው የድረሱልን ጥሪ ገና አልተጀመረም ነበር።

ረጂናልድ ፌሰንደን በ1906 የሰዎችን ንግግርና ሙዚቃ የያዘ ፕሮግራም ለመጀመሪያ ጊዜ ባስተላለፈበት ወቅት የሰዎችን ድምፅ በአየር ሞገድ አማካኝነት መስማት ተቻለ። የሬዲዮ መቀበያ መሣሪያ የነበራቸው መርከበኞች የፌሰንደንን ስርጭት ከ80 ኪሎ ሜትር ርቀት መስማት ችለዋል። በ1915 ብዙ ሰዎች በፈረንሳይ፣ በፓሪስ ከተማ በሚገኘው አይፍል ታወር አካባቢ ሆነው 14,000  ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው ከኦርሊንግተን፣ ቨርጂኒያ ዩናይትድ ስቴትስ የተላለፈውን ንግግር በቀጥታ ስርጭት ማዳመጥ በመቻላቸው ተደንቀው ነበር። በ1922 ደግሞ ኤስ ኤስ አሜሪካ የተባለችው መርከብ ሠራተኞች እነሱ ካሉበት 600 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ካለችውና ኒው ጀርሲ ውስጥ ከምትገኘው የዲል ቢች ወደብ ጋር በሬዲዮ መገናኘት ችለው ነበር፤ ከባሕር ወደ ወደብ መልእክት በመለዋወጥ የመጀመሪያዎቹ በመሆናቸው ምን ያህል እንደተደሰቱ መገመት ይቻላል።

የድረሱልን ጥሪውን አንድ ወጥ ማድረግ

በ1920ዎቹና በ1930ዎቹ ዓመታት በርካታ ቁጥር ያላቸው ኦፕሬተሮች በሬዲዮ አማካኝነት መልእክት መለዋወጥ ጀመሩ። የመርከብ ሠራተኞች የተለያየ ቋንቋ ሊኖራቸው ስለሚችል አንድ ካፒቴን የሚያሰማውን የድረሱልን ጥሪ ሁሉም ሰው እንዲረዳው ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? የሬዲዮ ቴሌግራም ዓለም አቀፍ ጉባኤ በ1927 “ሜይዴይ” ዓለም አቀፋዊ የድረሱልን ጥሪ እንዲሆን በወሰነ ጊዜ ይህ ችግር መፍትሔ አገኘ። *

የመገናኛ ዘዴዎች እየተሻሻሉ በመሄዳቸው አመስጋኞች መሆን ይገባናል። ለምሳሌ የመድፍ ተኩስና የባንዲራ ምልክት በራዳርና በጂ ፒ ኤስ (ከሳተላይት በሚመጡ መልእክቶች አማካኝነት አንድ ነገር ያለበትን ቦታ ለማወቅ የሚያስችል መሣሪያ) ተተክተዋል። በተጨማሪም ሬዲዮ በማንኛውም መርከብ ላይ የሚገጠም መሣሪያ እንዲሆን በመደረጉ ሕይወት አድን ተቋማት በአየር ሞገዶች አማካኝነት የሚመጡትን መልእክቶች በንቃት መከታተልና እርዳታ ለመስጠት ሁልጊዜ ዝግጁ መሆን ይችላሉ። ከኖቲካል ሌገሲ ሁኔታ መመልከት እንደሚቻለው አንድ አደጋ በየትኛውም ቦታ ሆነ በማንኛውም ጊዜ ቢደርስ ሰዎች “ሜይዴይ! ሜይዴይ! ሜይዴይ!” የሚለውን የድረሱልን ጥሪ እስካሰሙ ድረስ ምላሽ የማግኘታቸው አጋጣሚ ሰፊ ነው። ዛሬ ባሕር ላይ ሆነህ አደጋ ቢያጋጥምህ እንደቀደሙት ትውልዶች ተስፋ ከመቁረጥ ይልቅ እርዳታ እንደምታገኝ በእርግጠኝነት መጠባበቅ ትችላለህ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2 ትሩ ስቶሪስ ኦቭ ረስክዩ ኤንድ ሰርቫይቫል—ካናዲያንስ አንኖውን ሂሮስ በተባለው መጽሐፍ ላይ የቀረበ ዘገባ

^ አን.11 ኤስ ኦ ኤስ የተባሉት ፊደላት የተመረጡት ለመላክም ሆነ ለመለየት ቀላል ስለሆኑ ነበር። ከዚህ ውጪ እነዚህ ፊደላት ምንም ትርጉም የላቸውም።

^ አን.15 “ሜይዴይ” ከማንኛውም ሌላ ቃል ጋር እንዳይምታታና ግራ እንዳያጋባ ጥሪ የሚያስተላልፈው ሰው ይህን ቃል ሦስት ጊዜ መጥራት ይኖርበታል።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በእሳት የተያያዘችው “ኖቲካል ሌገሲ” በጭስ ታፍና

[ምንጭ]

Courtesy Fisheries and Oceans Canada, reproduced with the permission of © Her Majesty the Queen in Right of Canada, 2010

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

መርከበኞች በባሕር ላይ የሞርስ ኮድን ሥራ ላይ የሚያውሉት እንደ ኦፕሬተሮች የድምፅ ኮድ በመላክ ሳይሆን ደማቅ የብርሃን ጨረሮችን በመጠቀም ነበር

[ምንጭ]

© Science and Society/SuperStock