በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በጣም አስፈሪው የ19ኛው መቶ ዘመን በሽታ

በጣም አስፈሪው የ19ኛው መቶ ዘመን በሽታ

በጣም አስፈሪው የ19ኛው መቶ ዘመን በሽታ

ወቅቱ 1854 ሲሆን ለንደን በኮሌራ ወረርሽኝ ዳግመኛ እየታመሰች ነው። በሽታው አስደንጋጭ በሆነ ፍጥነት ይዛመታል። ጠዋት ከእንቅልፋቸው ሲነሱ ጤነኛ የነበሩ በርካታ ሰዎች ምሽት ላይ ይሞታሉ። በሽታው መድኃኒት አልተገኘለትም።

በክፍለ ዘመኑ እጅግ አስፈሪ የነበረው የዚህ በሽታ መንስኤ እንቆቅልሽ ሆኖ ነበር። አንዳንዶች ኮሌራ (ኃይለኛ ተቅማጥ የሚያስከትልና የሰውነትን ፈሳሽ የሚያሟጥጥ የአንጀት በሽታ) የሚመጣው የበሰበሱ ነገሮችን በማሽተት እንደሆነ ያስቡ ነበር። ደግሞም እንዲህ ብሎ ለማሰብ በቂ ምክንያት ያላቸው ይመስል ነበር። የለንደንን ከተማ አቋርጦ ከሚያልፈው የቴምዝ ወንዝ የሚወጣው ሽታ ይከረፋ ነበር። በሽታውን የሚያመጣው ይህ ግማት ይሆን?

ከአምስት ዓመት በፊት ጆን ስኖው የተባለ ሐኪም ኮሌራ የሚመጣው ከተበከለ አየር ሳይሆን ከተበከለ ውኃ እንደሆነ የሚገልጽ ሐሳብ ሰንዝሮ ነበር። ዊልያም በድ የተባለ ሌላ ሐኪም ደግሞ በሽታው የሚተላለፈው ፈንገስ በሚመስሉ ረቂቅ ተሕዋስያን አማካኝነት እንደሆነ ያምን ነበር።

በ1854 በተከሰተው ወረርሽኝ ወቅት ስኖው ግምቱ ትክክል መሆኑን ለማጣራት በለንደን ከተማ ሶሆ በሚባለው አካባቢ ኮሌራ በያዛቸው ሰዎች አኗኗር ላይ ጥናት አካሄደ። እነዚህን ሰዎች የሚያመሳስላቸውን ነገር ለማወቅ ጥረት አደረገ። የስኖው ምርምር ያስገኘው ውጤት አስደንጋጭ ነበር። በዚያ አካባቢ ኮሌራ የያዛቸው ሰዎች በሙሉ የመጠጥ ውኃ የሚያገኙት ከአንድ መስመር ሲሆን ውኃው ደግሞ የኮሌራ ባክቴሪያ ባለበት ፍሳሽ የተበከለ ነበር! *

በዚያው ዓመት ፊሊፖ ፓቺኒ የተባለ ጣሊያናዊ ሳይንቲስት ኮሌራ አምጪ ስለሆነው ረቂቅ ተሕዋስያን የሚገልጽ የጥናት ጽሑፍ በማውጣቱ በሕክምናው መስክ አዲስ ምዕራፍ ተከፈተ። ይሁን እንጂ የፓቺኒም ሆነ የስኖውና የበድ ግኝቶች እምብዛም ትኩረት አልተሰጣቸውም። የኮሌራው ወረርሽኝ እስከ 1858 ድረስ መዛመቱን ቀጠለ።

“ታላቁ ግማት”

ፓርላማው የቴምዝን ወንዝ ጽዳት ለመጠበቅ አዲስ የፍሳሽ ማስወገጃ በማሠራት ረገድ ዳተኛ ሆኖ የቆየ ቢሆንም በ1858 የበጋ ወቅት የነበረው ከፍተኛ ሙቀት እርምጃ እንዲወሰድ አስገደደው። በምክር ቤቱ ሕንፃ በኩል የሚያልፈው ወንዝ ግማት ፖለቲከኞቹን መቀመጫ ስላሳጣቸው ሽታው እንዲቀንስ በማለት ጀርም በሚገድል ፈሳሽ የተነከሩ መጋረጃዎችን መስኮቶቻቸው ላይ ለማንጠልጠል ተገደው ነበር። ታላቁ ግማት ተብሎ የተጠራው ይህ ክስተት ፓርላማው እርምጃ እንዲወስድ አነሳሳው። አዲስ የፍሳሽ ማስወገጃ እንዲሠራ የሚያዝ ሕግ በ18 ቀን ውስጥ ወጣ።

ከየቤቱ የሚወጣውን ፍሳሽ ወደ ወንዙ ከመድረሱ በፊት ተቀብለው ወደ ምሥራቅ ለንደን የሚወስዱ ትላልቅ ቦዮች የተገነቡ ሲሆን ፍሳሹ ወደ ባሕር ይለቀቃል። ይህ ለውጥ ያስገኘው ውጤት አስደናቂ ነበር። መላው የለንደን ከተማ በአዲሱ የፍሳሽ ማስወገጃ መጠቀም ከጀመረ በኋላ የኮሌራው ወረርሽኝ አቆመ።

በዚህ ጊዜ፣ ኮሌራ የሚመጣው በተበከለ አየር ሳይሆን በተበከለ ውኃ ወይም ምግብ እንደሆነ በሚገባ ተረጋገጠ። ኮሌራን ለመከላከል ቁልፉም ንጽሕናን መጠበቅ እንደሆነ በግልጽ ታወቀ።

ከዘመኑ የቀደመ ሕግ

ለንደንን ያመሳት የኮሌራ ወረርሽኝ ከመከሰቱ በሺህ ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት ሙሴ የእስራኤልን ሕዝብ እየመራ ከግብፅ አውጥቶ ነበር። እስራኤላውያን 40 ለሚያህሉ ዓመታት በሲና ምድረ በዳ ሲጓዙ ቢቆዩም ኮሌራን የመሰለ ወረርሽኝ አንድም ጊዜ አላጋጠማቸውም። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው?

የሰው እዳሪ የመኖሪያ አካባቢዎችንና የውኃ ምንጮችን እንዳይበክል ሕዝቡ ከሰፈር ውጭ ራቅ ባለ ቦታ እንዲቀብሩት ታዘው ነበር። ይህ ትእዛዝ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ዘዳግም 23:12, 13 ላይ ተመዝግቦ ይገኛል፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦

“የምትጸዳዱበትን ልዩ ስፍራ ከሰፈር ውጭ አዘጋጁ፤ በምትጸዳዱበት ጊዜ እዳሪ ለመቈፈርና መልሶ ለመድፈን የሚያገለግላችሁን አንካሴ ከጦር መሣሪያችሁ ጋር ያዙ።”—የ1980 ትርጉም

ይህ ቀላል መመሪያ እስራኤላውያንን በአካባቢያቸው የሚኖሩትን ብሔራት ያሠቃዩዋቸው ከነበሩት በሽታዎች ጠብቋቸው ነበር። በቅርብ ጊዜያትም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል የንጽሕና አጠባበቅ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ታድጓል። * እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት።

‘ወረርሽኝ አጋጥሞን አያውቅም’

በ1970ዎቹ ዓመታት በማላዊ የሚገኙ በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች በደረሰባቸው ከባድ ስደት ምክንያት አገራቸውን ጥለው ለመሸሽ ተገድደው ነበር። አጎራባች አገር በሆነችው በሞዛምቢክ መጠለያ ማግኘት የቻሉ ሲሆን በአሥር የስደተኛ ሰፈሮች ውስጥ 30,000 የሚያህሉ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ይኖሩ ነበር። ብዙውን ጊዜ በስደተኞች ሰፈር ውስጥ ውኃ ወለድ በሽታዎች በፍጥነት እንደሚሰራጩ የታወቀ ነው። ታዲያ የይሖዋ ምሥክሮች ሁኔታ ምን ይመስል ነበር?

ሌመን ካብዋዚ 17,000 ከሚያህሉ ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጋር በምላንጄኒ በሚገኘው ትልቁ የስደተኞች ሰፈር ይኖር ነበር። ሁኔታውን ሲያስታውስ እንዲህ ብሏል፦ “ካምፑ ሁልጊዜ ንጹሕ ነበር። ከሰፈር ውጭ የመጸዳጃ ጉድጓዶች የተቆፈሩ ሲሆን ማንም ሰው በካምፑ ውስጥ የራሱን የመጸዳጃ ጉድጓድ እንዲቆፍር አይፈቀድለትም። የቆሻሻ መጣያ ጉድጓዶችም ከሰፈሩ ራቅ ተደርገው ይቆፈሩ ነበር። የንጽሕና ጉዳዮችን የሚከታተሉ ፈቃደኛ ሠራተኞች የነበሩ ሲሆን እነዚህ ሠራተኞች ከሰፈሩ ውጭ በሌላ አካባቢ ከተቆፈሩ ጉድጓዶች የሚቀዳውን ውኃ ንጽሕናም ይቆጣጠሩ ነበር። በጣም ተጣብበን እንኖር የነበረ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ንጽሕና የሚሰጣቸውን መመሪያዎች በጥብቅ እንከተል ስለነበር ከበድ ያለ ወረርሽኝ አጋጥሞን የማያውቅ ከመሆኑም በላይ አንድም ሰው ኮሌራ አልያዘውም።”

የሚያሳዝነው ግን በአንዳንድ የዓለም ክፍሎች ዛሬም ቢሆን ተገቢ የሆነ የፍሳሽ ማስወገጃ የሌላቸው ቤቶች አሉ። ከእዳሪ ጋር ተያይዘው በሚመጡ በሽታዎች ምክንያት በየቀኑ 5,000 የሚያህሉ ሕፃናት ይሞታሉ።

ኮሌራና ተመሳሳይ የሆኑ ሌሎች በሽታዎችን መከላከል እንደሚቻልና የሰው ልጅ ንጽሕናን ለመጠበቅ ያደረጋቸው ጥረቶች ከፍተኛ ውጤት እያስገኙ እንደሆነ አይካድም፤ መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ በቅርቡ በሽታ ሁሉ የሚጠፋበት ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ ይሰጣል። በአምላክ መንግሥት ግዛት ሥር “ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም” በማለት ራእይ 21:4 ይናገራል። በተጨማሪም በዚያን ጊዜ “‘ታምሜአለሁ’ የሚል አይኖርም።”—ኢሳይያስ 33:24

የአምላክ መንግሥት ለሰው ልጆች ስለሚያደርጋቸው ነገሮች የበለጠ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን 8ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 3ን እና 8ን ተመልከት።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.5 በ1854 ዘመናዊ መጸዳጃ ቤቶች የነበሩ ቢሆንም የፍሳሽ ማስወገጃዎቹ በማርጀታቸው ምክንያት የሰው እዳሪ ወደ ቴምዝ ወንዝ ይገባ ነበር፤ ይህ ወንዝ ለመጠጥነት የሚያገለግለው ውኃ ዋነኛ ምንጭ ነበር።

^ አን.15 ኮሌራ የሚተላለፈው በተበከለ ምግብ ወይም ውኃ በመሆኑ በሽታውን ለመከላከል ቁልፉ በምንበላው ወይም በምንጠጣው ነገር ረገድ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ነው። ውኃን ማጣራትና ምግብን በደንብ ማብሰል ሊወሰዱ የሚገባቸው አስፈላጊ እርምጃዎች ናቸው።

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የቴምዝ ወንዝ የለንደንን ከተማ አቋርጦ የሚያልፍ ሲሆን በ19ኛው መቶ ዘመን በተሠሩ በርካታ ሥዕሎች ላይ እንደሚታየው ወንዙ የኮሌራ ባክቴሪያ ባለበት ፍሳሽ የተበከለ ነበር

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከ30,000 የሚበልጡ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች በሞዛምቢክ በሚገኙ አሥር የስደተኛ ሰፈሮች ይኖሩ የነበረ ሲሆን ካምፑ ሁልጊዜ ንጹሕ ነበር

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Death on Thames: © Mary Evans Picture Library; map: University of Texas Libraries