አምላክ አካል አለው?
መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?
አምላክ አካል አለው?
ብዙ ሰዎች በተፈጥሮ ውበት በጣም ከመደመማቸው የተነሳ ከሰው በላይ የሆነ አንድ ኃይል ወይም አምላክ አለ ብለው ለማመን ተገደዋል። አንተስ በአጽናፈ ዓለም ውስብስብነት ተገርመህ ታውቃለህ? የሰው ልጆች አካል የተራቀቀ ንድፍና በፕላኔታችን ውስጥ ያሉት የተፈጥሮ መስህቦች የአድናቆት ስሜት አሳድረውብህ አያውቁም?
እንዲህ ከሆነ እነዚህ ነገሮች አንተንም አንድ መለኮታዊ ኃይል አለ ብለህ እንድታምን ሳያደርጉህ አይቀሩም። አንዳንድ ሃይማኖቶች ይህ መለኮታዊ ኃይል በተራሮች፣ በዛፎች፣ በሰማይና በሌሎች የአጽናፈ ዓለም አካላት ላይ ይኖራል ብለው ያስተምራሉ። ሌሎች ደግሞ የቀድሞ አባቶች መናፍስት (ደጎቹም ሆኑ ክፉዎቹ) ሚስጥራዊ በሆኑ ኃይላት አማካኝነት እርስ በርስ ተቀላቅለው አንድ ታላቅ ኃይል ይኸውም አምላክ እንደሚሆኑ ያምናሉ።
ከዚህ መመልከት እንደምንችለው ሁለቱም አስተሳሰቦች ከሰው በላይ የሆነው ይህ ኃይል አካል የለውም የሚል የጋራ እምነት አላቸው። አንዳንድ ሰዎች አምላክ ያስባል አልፎ ተርፎም ስሜት፣ ዓላማና ፍላጎት አለው የሚለውን ሐሳብ መቀበል ይከብዳቸዋል። ታዲያ አምላክ አካል አለው? በጣም ጥንታዊ ከሆኑት ቅዱስ መጻሕፍት መካከል አንዱ የሆነውና በዛሬው ጊዜ በስፋት የተሰራጨው መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ግልጽ የሆነ መልስ ይሰጣል።
የሰዎች አፈጣጠር የአምላክን ማንነት ይገልጣል
መጽሐፍ ቅዱስ ሰው የተፈጠረው የአምላክን ባሕርያት እንዲያንጸባርቅ ተደርጎ እንደሆነ ያስተምራል። ዘፍጥረት 1:27 አምላክ “ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው” በማለት ይናገራል።
ይህ ጥቅስ፣ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ቃል በቃል አምላክን ይመስላሉ እያለ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ በዓይን የማይታይ መንፈሳዊ አካል እንደሆነና የሰው ልጆች ደግሞ ሊታዩና ሊዳሰሱ ከሚችሉ የምድር ንጥረ ነገሮች እንደተሠሩ ይናገራል። (ዘፍጥረት 2:7፤ ዮሐንስ 4:24) በሰው ልጆችና በአምላክ መካከል ያለውን ይህን መሠረታዊ ልዩነት ወደጎን አድርገን የሰዎችን ባሕርያት ልብ ብለን ብንመለከት ስለ አምላክ ማንነት የተወሰነ ፍንጭ ማግኘታችን አይቀርም።
ሰዎች ኃይላቸውን ተገቢ በሆነ መንገድ የመጠቀም ብሎም የታሰበባቸውና የታቀዱ ተግባራትን የማከናወን ችሎታ አላቸው። እነዚህን ተግባራት እንዲፈጽሙ የሚያነሷሷቸው እንደ ደግነት፣ ጥበብና ፍትሕ የመሳሰሉ ባሕርያት ናቸው፤ በተጨማሪም ያላቸው የማመዛዘን ችሎታ ለዚህ ይረዳቸዋል። ሰዎች እጅግ ጥልቅ የሆነ የመውደድ ስሜት ሊኖራቸው፣ በሌላው ጽንፍ ደግሞ የጥላቻና የቁጣ ስሜት ሊያድርባቸው ይችላል። በእነዚህ መሃል የሚፈጠሩት የተለያዩ ባሕርያት አንዳችን ከሌላው በተወሰነ መጠንም ቢሆን የተለየን እንድንሆን ያደርጉናል። አዎን፣ እያንዳንዳችን የየራሳችን ማንነትና ስብዕና አለን።
አምላክ ዝም ብሎ በየቦታው የሚንሳፈፍና እውን የሆነ አካል የሌለው መንፈሳዊ ኃይል ቢሆን ኖሮ እኛን ውስብስብ ስብዕና እንዲኖረን አድርጎ ይፈጥረናል ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው? ሰዎች በአምላክ አምሳል የተሠሩ ከሆኑ አምላክ በብዙ መንገድ ከሰዎች ጋር ይመሳሰላል ማለት ነው። እስቲ የሚከተለውን ተመልከት።
አምላክ የግል ስም አለው። መጽሐፍ ቅዱስ በዘፀአት 6:3 [የ1879 ትርጉም] ላይ “ለአብርሃምም ለይስሐቅም ለያዕቆብም ሁሉን እንደሚችል አምላክ ተገለጥሁ በስሜም እግዚእ [ይሖዋ] አልታወቅሁላቸውም” ይላል። አምላክ ስሙ እንዲታወቅ ይፈልጋል። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “ከአሁን እስከ ዘላለም፣ የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ስም የተመሰገነ ይሁን። ከፀሓይ መውጫ እስከ መግቢያው ድረስ፣ የእግዚአብሔር [“የይሖዋ፣” NW] ስም የተመሰገነ ይሁን።” (መዝሙር 113:2, 3) እንግዲያው የአምላክ አገልጋዮች ስሙን አዘውትረው በመጠቀም በእርግጥ እውን አካል ያለው እንደሆነ አድርገው እንደሚያዩት ያሳያሉ።
አምላክ የተለየ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ በእርግጥም የተለየ እንደሆነ ያስተምራል። (1 ቆሮንቶስ 8:5, 6) “ልዑል እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ሆይ፤ እንዴት ታላቅ ነህ! ከቶ የሚመስልህ ማንም የለም፤ በጆሮአችን እንደሰማነው ሁሉ፣ ከአንተ በቀር አምላክ የለም” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (2 ሳሙኤል 7:22) በተጨማሪም ቅዱሳን መጻሕፍት ይሖዋ ‘በሰማይ፣ በታችም በምድር እርሱ አምላክ እንደሆነና ሌላም እንደሌለ’ ይገልጻሉ።—ዘዳግም 4:39
ይሖዋ ክፋትን ይጠላል። ለአንድ ነገር የጥላቻ ስሜት ሊኖረው የሚችለው አካል ያለው ነገር ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፈጣሪ “ትዕቢተኛ ዐይን፣ ሐሰተኛ ምላስ፣ ንጹሕ ደም የሚያፈሱ እጆች፣ ክፋትን የሚያውጠነጥን ልብ፣ ወደ ክፋት የሚቻኰሉ እግሮች፣ በውሸት ላይ ውሸት የሚጨምር ሐሰተኛ ምስክር፣ በወንድማማቾች መካከል ጠብን የሚጭር ሰው” እንደሚጠላ ይናገራል። (ምሳሌ 6:16-19) አምላክ፣ ሌሎችን የሚጎዱ ሰብዓዊ ባሕርያትን እንደሚጠላ ልብ በል። ከዚህ መረዳት እንደምንችለው አምላክ የእኛ ደኅንነት የሚያሳስበው ከመሆኑም በላይ ጉዳት የሚያደርሱብንን ነገሮች ይጠላል።
ይሖዋ አፍቃሪ አምላክ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ “በዚህ ዓለም ላይ የሚኖሩ ሰዎችን” በጣም እንደሚወዳቸው ይናገራል። (ዮሐንስ 3:16 ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርሽን) በተጨማሪም ቅዱሳን መጻሕፍት አምላክን ልጆቹ ምንጊዜም የተሻለ ነገር እንዲያገኙ ከሚፈልግ ደግ አባት ጋር አመሳስለውታል። (ኢሳይያስ 64:8) የሰው ልጆች አምላክን እንደ አፍቃሪ አባታቸው አድርገው የሚቀበሉት ከሆነ ምንጊዜም በረከትን ማጨድ ይችላሉ።
የአምላክ ወዳጅ መሆን ትችላለህ
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ፈጣሪ የራሱ የሆነ መጠሪያ ስምና ባሕርያት እንዳሉት በግልጽ ይናገራል። አምላክ ኃይሉን በተገቢው መንገድ የመጠቀም ችሎታ ያለው ከመሆኑም ባሻገር እንደ ደግነት፣ ጥበብና ፍትሕ ባሉት መልካም ባሕርያቱ ተነሳስቶ የታሰበባቸውና የታቀዱ ተግባራትን ያከናውናል። ከእኛ በጣም የራቀ ወይም ሊቀረብ የማይችል አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ ‘እኔ አምላክህ “አትፍራ፤ እረዳሃለሁ” ብዬ ቀኝ እጅህን እይዛለሁ’ በማለት ተናግሯል።—ኢሳይያስ 41:13
አምላክ የሰው ልጆችን በተመለከተ ያወጣው ዓላማ አለ። መጽሐፍ ቅዱስ “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” ይላል። (መዝሙር 37:29) ይሖዋ የተለየና የራሱ የሆነ ማንነት ያለው መሆኑን ማወቃችን በግለሰብ ደረጃ ከእሱ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት ቀላል እንዲሆንልን ያደርጋል፤ ይህ ደግሞ ወዳጁ ለሚሆኑት ሰዎች የዘረጋላቸውን በረከት እንድናጭድ ያስችለናል።—ዘዳግም 6:4, 5፤ 1 ጴጥሮስ 5:6, 7
ይህን አስተውለኸዋል?
● አምላክ የግል ስም አለው?—ዘፀአት 6:3 የ1879 ትርጉም
● ብዙ አማልክት አሉ?—1 ቆሮንቶስ 8:5, 6
● ሰዎች ከእውነተኛው አምላክ ጋር በግለሰብ ደረጃ ወዳጅነት መመሥረት ይችላሉ?—1 ጴጥሮስ 5:6, 7
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አምላክ እውን የሆነ አካል የሌለው ቢሆን ኖሮ እኛን ውስብስብ ስብዕና እንዲኖረን አድርጎ ይፈጥረን ነበር?