በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እምነት ልትጥል የምትችልባቸው ሰዎች

እምነት ልትጥል የምትችልባቸው ሰዎች

እምነት ልትጥል የምትችልባቸው ሰዎች

በአርጀንቲና የሚኖር ሳንቲያጎ የሚባል የታክሲ ሾፌር አንድ ተሳፋሪ በታክሲው ውስጥ ረስቶት የወረደውን ቦርሳ ሲያገኝ ምን ማድረግ እንዳለበት ማሰብ አላስፈለገውም። ቦርሳውን ምንም ሳያመነታ ለባለቤቱ መለሰለት። እርግጥ ነው፣ ሳንቲያጎ ያደረገው ነገር ቀላል ሊመስል ይችላል፤ ይሁንና ቦርሳው ውስጥ የነበረው ገንዘብ ከ32,000 የአሜሪካ ዶላር በላይ ነበር!

እምነት በሚጣልባቸው ሰዎች የተሞላ ዓለም በዓይነ ሕሊናህ መሳል ትችላለህ? ሕይወት እንዴት የተለየ ይሆን ነበር! ምንም የምትፈራው ነገር ሳይኖር ልጅህን ለማንኛውም ሰው እንዲጠብቅልህ ትተህ መሄድ ትችል ነበር። ቤትህን መቆለፍም ሆነ መቀርቀር አያስፈልግህም ነበር። ይህ እንዲያው ሕልም ብቻ ሆኖ ይቀር ይሆን?

የሥነ ምግባር መመሪያዎች የሚያስገኙት ውጤት

ሐዋርያው ጳውሎስ ራሱንና የእምነት አጋሮቹ የሆኑትን ክርስቲያኖች አስመልክቶ ሲናገር “በሁሉም ነገር በሐቀኝነት ለመኖር [እንመኛለን]” ብሏል። (ዕብራውያን 13:18) የይሖዋ ምሥክሮችም በሐቀኝነት ለመኖር ጥረት ያደርጋሉ። የይሖዋ ምሥክሮች ዓላማ መጽሐፍ ቅዱስ በኢሳይያስ 33:15 ላይ “በጽድቅ የሚራመድ፣ ቅን ነገር የሚናገር፣ በሽንገላ የሚገኝ ትርፍ [“ተገቢ ያልሆነ ጥቅም፣” NW] የሚንቅ፣ መማለጃን ላለመቀበል እጁን የሚሰበሰብ” በማለት የተናገረለትን ሰው መምሰል ነው። አንዳንዶቹ የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህን ባሕርያት በማንጸባረቅ እምነት የሚጣልባቸው እንደሆኑ ያሳዩት እንዴት ነው?

“ቅን ነገር የሚናገር።” በፊሊፒንስ የሚኖረውና የይሖዋ ምሥክር የሆነው ዶሚንጎ የሚሠራው በአንድ የኮኮናት እርሻ ላይ ነው። ዶሚንጎ እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ ሰዎች ለአሠሪዎቻቸው ሐቀኞች አይደሉም። ለምሳሌ ያህል፣ ኮኮናት በሚሰበስቡበት ጊዜ ስንት ጆንያ እንደሰበሰቡ ለአሠሪያቸው አይነግሩም። ስለዚህ አንዳንዶቹን ጆንያዎች ደብቀው በጎን ይሸጧቸዋል።”

ዶሚንጎና ቤተሰቡ አሠሪያቸውን ለመጥቀም ሲሉ ስለ ድርጅቱ የምርት መጠን ለመዋሸት ፈቃደኞች ስላልሆኑ ከሥራቸው ሊባረሩ ነበር። ዶሚንጎ እንዲህ ብሏል፦ “ከሥራ መባረር ሊያስከትልብን ቢችልም እንኳ እንደማንዋሽ ለአሠሪያችን ነገርነው። በመጨረሻም አሠሪያችን የይሖዋ ምሥክሮች እምነት ሊጣልባቸው የሚችሉ ጥሩ ሰዎች እንደሆኑ የተናገረ ከመሆኑም ሌላ የምንሠራበት ተጨማሪ የእርሻ ቦታ ሰጠን።”

“ተገቢ ያልሆነ ጥቅም የሚንቅ።” በካሜሩን የአንድ ክልል ግብር ተቀባይ ቢሮ ኃላፊ የሆነው ፒየር በቀላሉ ገንዘብ ማግኘት የሚችልባቸው ብዙ አጋጣሚዎች ነበሩት። መጀመሪያ ላይ ለጊዜያዊ ሠራተኞች ደመወዛቸውን እንዲከፍል በተመደበ ጊዜ የሆነ ስህተት እንዳለ ተገነዘበ። “ኮንትራታቸውን በጨረሱ ወይም በሞቱ ሰዎች ስም ደሞዝ ይከፈል ነበር” በማለት ፒየር ይናገራል። “ይህን ገንዘብ ወስጄ ለመጠቀም ከማሰብ ይልቅ ትክክለኛ የሂሳብ መዝገብ ካዘጋጀሁ በኋላ ገንዘቡን በጥንቃቄ ማስቀመጥ ጀመርኩ።”

ውጤቱስ ምን ሆነ? ፒየር እንዲህ ብሏል፦ “ከሁለት ዓመት በኋላ ይህን ሁኔታ ለማረጋገጥ የሒሳብ ምርመራ ተደረገ። እኔም ትክክለኛውን መዝገብ ማቅረብና በወቅቱ ተጠራቅሞ የነበረውን ብዙ ገንዘብ ማስረከብ በመቻሌ ኩራት ተሰማኝ። የሒሳብ መርማሪዎቹም ላሳየሁት ሐቀኝነት በጣም አመሰገኑኝ።”

ጉቦ ወይም ‘መማለጃ የማይቀበል።’ ሪዮ ዴ ጄኔሮ፣ ብራዚል የሚኖረው የውልና ሰነድ አዋዋይ የሆነው ሪካርዶ በሥራ ዘመኑ ሁሉ ጉቦ ይቀርብለት ነበር። ሪካርዶ እንዲህ በማለት ያስታውሳል፦ “በአንድ ወቅት አንድ ጠበቃ ጉቦ ሊሰጠኝ ሞክሮ ነበር። እኔ ሳላውቅ የሲዲ ማጫወቻ ወደ ቤቴ ልኮ ነበር። በጊዜው የሲዲ ማጫወቻ አዲስ የመጣ የቅንጦት ዕቃ ነበር።”

ታዲያ ሪካርዶ ምን አደረገ? ሁኔታውን ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “እኔና ባለቤቴ ዕቃውን ከፍተን እንኳ ማየት አልፈለግንም። ወደ ጠበቃው ቢሮ ሄጄ የላከልንን ዕቃ እንደታሸገ ጠረጴዛው ላይ ሳስቀምጥለት በጣም ተገረመ። ይህ ሁኔታ ዕቃውን ለምን እንደመለስኩ ለማስረዳት ጥሩ አጋጣሚ ፈጠረልኝ። በተለይ ደግሞ ጸሐፊው በወሰድኩት እርምጃ በጣም ተደነቀች።”

በቅንነት ለመመላለስ የሚጥሩት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ባይሆኑም በቡድን ደረጃ እምነት የሚጣልባቸው ሰዎች በመሆን ረገድ መልካም ስም አትርፈዋል። በፖላንድ ብዙ የልብስ ሱቆች ያሉት አንድ ድርጅት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የይሖዋ ምሥክሮችን ብቻ ለመቅጠር የተነሳሳው በዚህ ምክንያት ነው። የድርጅቱ የሽያጭ ክፍል ኃላፊ “የትም ቦታ ሐቀኛ ሰዎች አሉ፤ ሆኖም የይሖዋ ምሥክሮች በጥብቅ የሚከተሏቸው መመሪያዎች አሏቸው” በማለት ተናግራለች።

ድሆች ቢሆኑም እምነት የሚጣልባቸው ሰዎች

በብዙ ሰዎች አስተሳሰብ አንድ ሰው ድሃ ከሆነ ሐቀኛ መሆን አይጠበቅበትም። ለምሳሌ ሲ ኤን ኤን፣ ሰዎችን በኢንተርኔት ሲያጭበረብር ስለሚውል ስለ አንድ የ14 ዓመት ናይጄሪያዊ ዘግቦ ነበር። ይህ ልጅ ራሱን ከጥፋተኝነት ነፃ ለማድረግ “ታዲያ ምን ላድርግ? እህቴን፣ እናቴንና [አባቴን] ቤተሰቤን በሙሉ የምመግበው እኔ ነኝ። እንግዲህ አንሞት” ብሏል።

እርግጥ ነው፣ መጽሐፍ ቅዱስ በቅንነት የሚመላለሱ ሰዎች ሀብት ያገኛሉ የሚል ተስፋ አይሰጥም፤ ይሁን እንጂ ለመኖር የሚያስፈልጓቸውን መሠረታዊ ነገሮች እንደሚያገኙ ዋስትና ይሰጣል። ኢሳይያስ 33:16 እንደሚገልጸው “እንጀራ ይሰጠዋል፣ ውሃውም አይቋረጥበትም።”

ይሁን እንጂ አንዳንዶች እንዲህ ብለው ይጠይቁ ይሆናል፦ ‘በከፋ ድህነት ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ሐቀኛ መሆናቸው ምን ይጠቅማቸዋል? የዕለት ጉርሳቸውን እንኳ ማግኘት ከባድ የሆነባቸው ሰዎች ምን ይሁኑ?’

በካሜሩን የምትኖረውን በርት የተባለች ባሏ የሞተባትን ሴት ሁኔታ እንመልከት፤ ይህች ሴት ትንሽ በሆነችው መደቧ ላይ ሚአንዶ የሚባል ከካሳቫ የሚሠራ ምግብ ትሸጣለች። በርት እንዲህ ብላለች፦ “እንደ ደንቡ ከሆነ እያንዳንዱ እሽግ 20 ሚአንዶ ይይዛል፤ ባለ ሱቆቹ ግን በአብዛኞቹ እሽጎች ውስጥ 17 ወይም 18 ሚአንዶ ማድረጋቸው የተለመደ ነው። ይሁን እንጂ እኔ በዚህ መንገድ ሌሎችን በማታለል ገንዘብ ማግኘት አልፈልግም።”

ታዲያ በርት ሁልጊዜ ገበያ ታገኛለች? አታገኝም። በርት እንዲህ በማለት ተናግራለች፦ “ብዙውን ጊዜ ቀኑን ሙሉ ምንም ሳልሸጥ እውላለሁ። ይሁን እንጂ ምግብ የሚሸጡትን ሰዎች ምንም ነገር ስላልሸጥኩ ምግብ በዱቤ እንዲሰጡኝ እጠይቃቸዋለሁ። እነሱም ገንዘብ እንዳገኘሁ ወዲያውኑ እንደምከፍላቸው ስለሚያውቁ ምግቡን ይሰጡኛል። ይህ የሆነው በጊዜ ሂደት በመካከላችን መተማመን ስለተፈጠረ ነው።”

እምነት ልንጥልበት የሚገባ አምላክ

አንድ ሰው ቃሉን የማያጥፍ መሆኑን ስንመለከት በእሱ ላይ ያለን እምነት እያደገ ይሄዳል። በጥንት ጊዜ የእስራኤል መሪ የነበረው ኢያሱ ስለ አምላክ ሲናገር “እግዚአብሔር . . . ከሰጠው መልካም የተስፋ ቃል አንዳችም አልቀረም፤ ሁሉም ተፈጽሞአል” ብሏል። (ኢያሱ 21:45) እኛስ በአምላክ ላይ እምነት እንድንጥል የሚያደርጉን በቂ ምክንያቶች አሉን?

አምላክ የሚሰጣቸው ተስፋዎች እምነት የሚጣልባቸው ከመሆናቸው የተነሳ ቃሉን ከዝናብ ጋር አመሳስሎታል። (ኢሳይያስ 55:10, 11) ዝናብ እንዳይዘንብ፣ መሬትን እንዳያርስና ዕፅዋትን እንዳያበቅል ሊያግደው የሚችል ምን ነገር አለ? ምንም ነገር ሊኖር አይችልም! በተመሳሳይም አምላክ ቃል የገባቸውን ነገሮች እንዳይፈጽም ሊያግደው የሚችል ምንም ነገር የለም።

አምላክ ከሰጣቸው ተስፋዎች መካከል አንዱ በ2 ጴጥሮስ 3:13 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘው ነው፤ ጥቅሱ እንዲህ ይላል፦ “አምላክ በገባው ቃል መሠረት አዲስ ሰማያትና አዲስ ምድር እንጠባበቃለን፤ በእነዚህም ውስጥ ጽድቅ ይሰፍናል።” በመሆኑም አምላክ ባልንጀሮቻቸውን የሚበዘብዙ ሰዎችን ያቀፈውን አሁን ያለውን ምድር በሌላ አባባል ክፉውን ኅብረተሰብ የማጥፋት ዓላማ አለው። አምላክ ይህን ዓላማውን የሚፈጽመው እንዴት እንደሆነ ማወቅ ትፈልጋለህ? ከሆነ በአቅራቢያህ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮችን ማነጋገር ወይም በዚህ መጽሔት ገጽ 5 ላይ ከተዘረዘሩት አድራሻዎች አመቺ ወደሆነው መጻፍ ትችላለህ።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ሐቀኝነት ወሮታ አስገኘ

በፊሊፒንስ የሚኖረው ሉስዮ የሚባል የይሖዋ ምሥክር እምነቱን እንዲያጎድል የሚፈትን አንድ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። የአለቃውን ቢሮ እንዲያጸዳ ታዝዞ ሳለ በአንድ አሮጌ የፋይል ማስቀመጫ ሣጥን ውስጥ 27,500 የአሜሪካ ዶላር አገኘ። የገንዘቡ ባለቤት ለሥራ ጉዳይ ወደ ሌላ ቦታ ሄዶ የነበረው አለቃው ነበር። ሉስዮ “ዶላር ለመጀመሪያ ጊዜ ማየቴ ነበር!” ብሏል።

አለቃው ከጉዞ ሲመለስ ሉስዮ ገንዘቡን ሰጠው። ውጤቱስ ምን ነበር? ሉስዮ “የሥራ እድገት አገኘሁ” ብሏል። አክሎም “እንዲያውም አለቃዬ ከቤተሰቤ ጋር የምኖርበት አንድ ክፍል ሰጠኝ። ምንም እንኳ በመላው ፊሊፒንስ ኑሮ ከባድ ቢሆንም ይሖዋ ሕጉን የሙጥኝ ስላልን እንደተንከባከበን ይሰማኛል” ብሏል።

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ትክክለኛ ሚዛኖች

በካሜሩን፣ ዱዋላ በሚገኝ አንድ ትልቅ ገበያ ውስጥ የሞኢዝ ዓሣ መሸጫ ሱቅ በጣም የታወቀች ናት። ሞኢዝ እንዲህ ብሏል፦ “ትንሿን ሱቄን ‘ሚዛኖቹ’ ብዬ ሰይሜያታለሁ። ለሱቄ ይህን ስም የሰጠኋት የእኔ ሚዛኖች በገበያው ውስጥ አሉ ከሚባሉት ጥቂት ትክክለኛ ሚዛኖች መካከል ስለሚመደቡ ነው። ሰዎች ሚዛኔ ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ እንደሚሞክሩ አውቃለሁ። አንድ ኪሎ ዓሣ ስጠን ካሉኝ የጠየቁኝን እሰጣቸዋለሁ። ከእኔ የገዙትን ዓሣ ምንጊዜም ሌላ ቦታ ሄደው ያስመዝኑታል። እንዲህ ሲያደርጉ ደግሞ ከአንድ ኪሎ የበለጠ ሆኖ ያገኙታል! በዚህ መንገድ እንዳላታለልኳቸው ያውቃሉ! ብዙ ሰዎች ‘ወዳንተ የምንመጣው ሐቀኛ ስለሆንክ ነው’ ይሉኛል።”

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ከሥራ መባረር ሊያስከትልብን ቢችልም እንኳ እንደማንዋሽ ለአሠሪያችን ነገርነው።” —ዶሚንጎ፣ ፊሊፒንስ

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“የሒሳብ መርማሪዎቹም ላሳየሁት ሐቀኝነት በጣም አመሰገኑኝ።”—ፒየር፣ ካሜሩን

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“በአንድ ወቅት አንድ ጠበቃ ጉቦ ሊሰጠኝ ሞክሮ ነበር። . . . እኔና ባለቤቴ ዕቃውን ከፍተን እንኳ ማየት አልፈለግንም።”—ሪካርዶ፣ ብራዚል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በርት ቀኑን ሙሉ ምንም ሳትሸጥ የምትውልባቸው በርካታ ጊዜያት አሉ። ይሁን እንጂ ምግብ የሚሸጡ ሌሎች ሰዎች ገንዘብ እንዳገኘች ወዲያውኑ እንደምትከፍላቸው ስለሚያውቁ ምግብ በዱቤ ይሸጡላታል።