በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እምነት መጣል ይቻላል?

እምነት መጣል ይቻላል?

እምነት መጣል ይቻላል?

ሥቃይን ለማስታገሥ በሚሰጠው የሕክምና ዘርፍ ፈር ቀዳጅ እንደሆነ ተደርጎ ይታይ ነበር። ሆኖም በዚህ ሙያ ስመ ጥር የሆነው ይህ ዶክተር ከ1996 አንስቶ ከ10 ለሚበልጡ ዓመታት በታወቁ የሕክምና መጽሔቶች ላይ ሲያወጣቸው የነበሩት የጥናት ውጤቶች የውሸት ግኝቶች ነበሩ።

ክተር ስቲቨን ሼፈር አኒስቲዚዮሎጂ ኒውስ በተሰኘ ጽሑፍ ላይ ይህን ጉዳይ አስመልክተው ሲናገሩ “አንድ ሰው ለምን እንዲህ እንደሚያደርግ አይገባኝም” ብለዋል።

አንድ የተከበረ ባለሙያ ሰዎችን እንዲያታልል የሚያነሳሳው ምንድን ነው? ምክንያት ይሆናሉ ተብለው የሚታሰቡ አራት ነገሮችን እንመልከት።

ስግብግብነት። ዘ ኒው ኢንግላንድ ጆርናል ኦቭ ሜዲሲን የተባለው መጽሔት አዘጋጅ የነበሩት ዶክተር ጄሮም ካሲረር በኒው ዮርክ ታይምስ ላይ እንዲህ በማለት ተናግረዋል፦ “ተመራማሪዎች ገቢያቸው በአብዛኛው የተመካው መድኃኒት አምራች ኩባንያዎች በሚያገኙት ትርፍ ላይ በሚሆንበት ጊዜ እነዚህ ተመራማሪዎች ለኩባንያው ጥቅም የሚያስገኝ የምርምር ውጤት ለማግኘት የመፈለግ ከፍተኛ አዝማሚያ ይታይባቸዋል።”

ለስኬት መቋመጥ። በጀርመን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በዚያች አገር የስኬት ምልክት የሆነውን ዶክቶር የሚለውን ማዕረግ “ለማግኘት” ለአስተማሪዎቻቸው በሺህ የሚቆጠር ዩሮ ጉቦ እንደሚሰጡ ይታመናል። የሐቀኝነትን ድንበር የሚጥሱ ብዙ ተማሪዎች፣ የሚፈልጉት ስኬት ላይ ከደረሱ በኋላ “ጥብቅ የሥነ ምግባር ደንቦችን የመከተል ፍላጎት እንዳላቸው” መናገራቸውን ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ላይ የወጣ አንድ ጥናት ገልጿል።

አርዓያ የሚሆኑ ሰዎች መጥፋታቸው። ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ አንድ ፕሮፌሰር የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን አስመልክተው የተናገሩትን ሐሳብ ጠቅሶ እንዲህ ብሏል፦ “የሥነ ምግባር ኮምፓሳቸው ጠፍቷል ለማለት እንገደዳለን። . . . አስተማሪዎች፣ አማካሪዎችና የተቀረው ኅብረተሰብ ወጣቶች መጀመሪያም ቢሆን የሥነ ምግባር ኮምፓስ እንዲኖራቸውና በዚያ እንዲጠቀሙ ረድተዋቸው አያውቁም ማለቱ ሳይሻል አይቀርም።”

የሥነ ምግባር መመሪያዎች ቸል መባላቸው። ወደ 30,000 የሚጠጉ ተማሪዎችን ያካተተ አንድ ጥናት እንዳመለከተው 98 በመቶ የሚሆኑት፣ ሰዎች እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት ሐቀኝነት በጣም አስፈላጊ መሆኑን ያምናሉ። ይሁን እንጂ ከ10 ተማሪዎች መካከል 8ቱ ወላጆቻቸውን እንደዋሹ 64 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ቀደም ባለው ዓመት በፈተና ወቅት እንደኮረጁ አምነዋል።

ከፍተኛ የሆኑ የሥነ ምግባር መመሪያዎች

በዚህ ገጽ ላይ ባለው ሣጥን ውስጥ እንደሚጠቁመው ሰዎች በሌሎች ላይ እምነት እንዲጥሉ ተደርገው የተፈጠሩ ይመስላል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ሰው ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ሐሳቡ ወደ ክፋት ያዘነበለ” መሆኑን በመናገር እውነታውን በግልጽ አስቀምጦታል። (ዘፍጥረት 8:21) ታዲያ ይህን ዝንባሌ በመዋጋት በዛሬው ጊዜ በጣም ተስፋፍቶ የሚገኘው እምነት የማጉደል አባዜ እንዳይጠናወትህ ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? የሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ሊረዱህ ይችላሉ፦

“አንተን ተማምኖ በአጠገብህ በተቀመጠ፣ በጐረቤትህ ላይ ክፉ አትምከርበት።”—ምሳሌ 3:29

ለጎረቤታችን ወይም ለሰዎች ያለን ፍቅር እነሱ የጣሉብንን እምነት ከማጉደል ይልቅ ለእነሱ የሚበጀውን እንድንሻ ይገፋፋናል። ሰዎች ይህን መሠረታዊ መመሪያ ቢከተሉ ኖሮ ቀደም ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሰውን የውሸት መድኃኒቶችን መሸጥን ጨምሮ ብዙዎች በስግብግብነት ተነሳስተው የሚፈጽሟቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው የማጭበርበር ድርጊቶች ባልኖሩ ነበር።

“እውነት ግን ጸንታ ትኖራለች። ሐሰት ዘላቂነት የለውም።”—ምሳሌ 12:19 የታረመው የ1980 ትርጉም

በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ሐቀኝነት ለኪሳራ እንደሚያጋልጥ ይሰማቸዋል። ይሁን እንጂ እንዲህ ብለህ ራስህን ጠይቅ፦ ‘ይበልጥ ጠቃሚ የሆነው የትኛው ነው? ጊዜያዊ ጥቅም ማግኘት ወይስ ለራስ አክብሮት ማትረፍን ጨምሮ ዘላቂ ጥቅም ማግኘት?’ አንድ ተማሪ ፈተና በመኮረጅ ስለ እውቀቱ ወይም ስለ ችሎታው ሌሎችን ማታለል ይችል ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ወደ ሥራው ዓለም ሲገባ ሥራውን እንዴት ሊወጣው ይችላል?

“ጻድቅ ነቀፋ የሌለበት ሕይወት ይመራል፤ ከእርሱም በኋላ የሚከተሉት ልጆቹ ቡሩካን ናቸው።”—ምሳሌ 20:7

ወላጅ ከሆንክ ‘ነቀፋ የሌለበት ሕይወት በመምራት’ ወይም ንጹሕ አቋምህን በመጠበቅ ለልጆችህ ጥሩ ምሳሌ ሁን። የታማኝነት ጎዳና በመከተልህ እንዴት እንደተጠቀምክ ግለጽላቸው። ልጆች ወላጆቻቸው ንጹሕ አቋማቸውን ጠብቀው እንደሚመላለሱ ሲመለከቱ እነሱም የታማኝነትን ጎዳና ለመከተል ሊመርጡ ይችላሉ።—ምሳሌ 22:6

ከላይ የተገለጹት የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ናቸው? በዛሬው ጊዜ እምነት የሚጣልባቸው ሰዎች ማግኘት ይቻላል?

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ለ ፊጋሮ የተሰኘው ጋዜጣ እንደገለጸው ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ የፈረንሳይ ዜጎች “በኅብረተሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ ያላቸው ማለትም በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊ ሕይወትና በባሕሉ መስክ ታዋቂ የሆኑ ሰዎች ጥሩ ምግባር እንደሌላቸው ስለሚሰማቸው እነሱም ቢሆኑ ጥሩ ምግባር የሚያሳዩበት ምክንያት አይታያቸውም።”

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የተፈጠርነው በሌሎች ላይ እምነት እንድንጥል ተደርገን ነው?

ጀርመን በሚገኘው የፍራንክፈርት ዩኒቨርሲቲ የንግድ ሥራ አስተዳደር ፕሮፌሰር የሆኑት ሚካኤል ኮስፌልት ባካሄዱት ጥናት፣ በሌሎች ላይ እምነት መጣል “የሰው ተፈጥሯዊ ባሕርይ ክፍል” ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። ኮስፌልት፣ በሁለት ሰዎች መካከል ቅርርብ ሲፈጠር የሰው አንጎል አንዱ በሌላው ላይ እምነት እንዲጥል የሚገፋፋውን ኦክሲቶሲን የሚባል ሆርሞን እንደሚያመነጭ ደርሰውበታል። “ይህ እንዲያውም የሰውን ዘር ልዩ ከሚያደርጉት ገጽታዎች መካከል አንዱ ነው። በሌሎች ላይ እምነት መጣል ካልቻልን ከተፈጥሯችን አንድ አስፈላጊ ነገር ጎድሎናል ማለት ነው” በማለት ኮስፌልት ተናግረዋል።