በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከተራራው ማርሞት ጋር ተዋወቅ

ከተራራው ማርሞት ጋር ተዋወቅ

ከተራራው ማርሞት ጋር ተዋወቅ

ኃይለኛ ፉጨት አየሩን ሰንጥቆ አለፈ። ድምፁ በጣም ኃይለኛ ከመሆኑ በስተቀር አንድ ልጅ ጓደኛውን ለመጥራት የሚያሰማውን ፉጨት ይመስላል። ፉጨቱ ከተራሮቹ ጋር ሲጋጭ ስለሚያስተጋባ ድምፁ ከየት እንደመጣ ማወቅ አይቻልም። ድንገት ፀጉር ያላት አይጥ የምትመስል አንዲት ትንሽ ፍጥረት በአቅራቢያዬ ወዳለው ጉድጓድ ተስፈንጥራ ስትገባ ተመለከትኩ። በዚህ ጊዜ ስለ አካባቢው የሚናገረውን መጽሐፍ አውጥቼ ስመለከት ወደ ጉድጓዱ ስትገባ ያየኋትና ስታፏጭ የነበረችው እንስሳ ማርሞት እንደሆነች ተገነዘብኩ።

ቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት ውስጥ ስለ እነዚህ ፀጉራማ የፍልፈል ዝርያዎች ይበልጥ ለማወቅ ቻልኩ። ፀሐይ ለመሞቅ የሚመርጧቸው ዐለቶች የትኞቹ እንደሆኑ፣ የሚኖሩባቸው ጉድጓዶች የት እንደሚገኙ እንዲሁም በተራራማ ቦታው ላይ ያለውን አስቸጋሪ የአየር ሁኔታ እንዴት ተቋቁመው እንደሚኖሩ ተገነዘብኩ።

የማርሞቶች ቤተሰባዊ ትብብርና ንቃት

ከዓመት ዓመት በበረዶ ከሚሸፈነው የተራራ ጫፍ በታች ባለ ዐለታማ ስፍራ መኖር ለማርሞቶች ቀላል አይደለም። የክረምቱ ወቅት በጣም ቀዝቃዛ ከመሆኑም በላይ አካባቢው ለወራት በበረዶ ሊሸፈን ይችላል። በተጨማሪም እነሱን ለማደን በሰማይ የሚያንዣብቡና በመሬት አድፍጠው የሚጠብቁ ፍጥረታት አሉ። በመሆኑም የማርሞቶች ሕልውና የተመካው እርስ በርስ በመተባበራቸው፣ አስቀድመው ዝግጅት በማድረጋቸውና ንቁ በመሆናቸው ላይ ነው።

ማርሞቶች የሚኖሩት በቤተሰብ መልክ ነው፤ በሌላ አባባል ተጓዳኞችና ልጆቻቸው አብረው ይኖራሉ። እያንዳንዱ ቤተሰብ በርካታ ጉድጓዶች የሚኖሩት ሲሆን አንደኛው ጉድጓድ ለመላው ቤተሰብ መኖሪያ ሆኖ ሲያገለግል ሌሎቹ ደግሞ በአደጋ ጊዜ መሸሸጊያ ሆነው ያገለግላሉ። አንዳንድ ጊዜ ማርሞቶች ጉድጓዳቸውን የሚቆፍሩት በትላልቅ ቋጥኞች ሥር በሚገኝ ክፍት ቦታ ላይ ነው። እንዲህ ባለው ቤተ መንግሥት የመሰለ መኖሪያ ውስጥ መኖራቸው ጠላቶቻቸውን ከሩቅ ለማየትና ዘና ብለው ፀሐይ ለመሞቅ ያስችላቸዋል።

ማርሞቶች ንጽሕናቸውን ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። የሚጸዳዱበት የተለየ ጉድጓድ ስላላቸው የሚኖሩበት ጉድጓድ ሁልጊዜ ንጹሕ ነው። በመኖሪያ ጉድጓዳቸው የመጨረሻ ጥግ ላይ ሰፋ ያለ ጎሬ ያዘጋጁና ሣር ይጎዘጉዙበታል። እንስቷ ልጆቿን የምትወልደው እንዲህ ባለው ምቹና ከአደጋ የተጠበቀ ቦታ ነው። በተጨማሪም ይህ ቦታ ቤተሰቡ በክረምት ወቅት ሙቀት አግኝቶ የሚያሳልፍበት አስተማማኝ ስፍራ በመሆን ያገለግላል፤ በዚህ ወቅት ማርሞቶች በጣም ተጠጋግተው ለረጅም ወራት ይተኛሉ።

ከሁሉም ከባድ የሆነው ኃላፊነት ቤተሰቡን ከአደጋ መጠበቅ ሳይሆን አይቀርም። ሌሎች የቤተሰብ አባሎች ምግብ ፍለጋ በአካባቢው በሚሰማሩበት ጊዜ ለአካለ መጠን የደረሰ አንድ ማርሞት ለጥበቃ ይቆማል። ይህ ማርሞት አደጋ መኖር አለመኖሩን ለማረጋገጥ አንዳንድ ጊዜ በኋላ እግሮቹ ቀጥ ብሎ የሚቆም ሲሆን ይህ ደግሞ አካባቢውን በተሻለ ሁኔታ ለመቃኘት ያስችለዋል። ብዙውን ጊዜ በተራራ ማርሞቶች ላይ ስጋት የሚፈጥሩት ንስሮች፣ ቀበሮዎችና ሰዎች ናቸው። ጠባቂው ማርሞት፣ ከእነዚህ ጠላቶች አንዱን ወይም የትኛውንም አዳኝ ወፍ ካየ የማስጠንቀቂያ ጩኸት ያሰማል። የሚገርመው ደግሞ ማርሞቶች ዋነኛ ጠላታቸው የሆነውን ንስር ሲያዩ የሚያሰሙት ድምፅ ከሌላው ጊዜ ለየት ይላል። የማስጠንቀቂያው ድምፅ እንደተሰማ ማርሞቶቹ በፍጥነት ወደ ጉድጓዳቸው ጥልቅ ይላሉ፤ በቅጽበት ድራሻቸው ይጠፋል!

በተለይ የወርቃማ ንስሮች ጣፋጭ ቀለብ ለሆኑት የማርሞት ግልገሎች ታዛዥነት የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነው። ጠባቂው ማርሞት፣ የመጣው አደጋ አጣዳፊ እንደሆነ ከተሰማው እሱም አጠገቡ ወዳለው ጉድጓድ ገብቶ ይሸሸጋል። ከዚያም ጥቂት ደቂቃዎች ቆይቶ ጭንቅላቱን በቀስታ ብቅ ያደርግና አደጋው ማለፍ አለማለፉን ያጣራል።

ሙቀትን መቋቋምና ብዙ መተኛት

የተራራ ማርሞቶች በሚኖሩበት ስፍራ ብዙ ግጦሽ የሚገኝ ከመሆኑም በላይ የበጋው ወቅት በጣም ሞቃት ወይም በጣም ቀዝቃዛ አይደለም። አየሩ ቀዝቀዝ በሚልበት ጊዜ ማርሞቶች ምቹ ቋጥኝ ፈልገው ፀሐይ ይሞቃሉ። አየሩ በሚሞቅበት ጊዜ ግን በጣም ይቸገራሉ፤ ምክንያቱም ሰውነታቸው ሙቀት በሚሰጥ ፀጉር የተሸፈነ ነው። በዚህም የተነሳ ማርሞቶች የበለጠ ንቁ የሚሆኑት አብዛኛውን ጊዜ ማለዳና አመሻሹ ላይ ነው።

የተራራ ማርሞቶችን የእንቅልፍ ችግር አያውቃቸውም፤ ምክንያቱም በዓመት ውስጥ ስድስት ወር ገደማ የሚሆነውን ጊዜ የሚያሳልፉት ተኝተው ነው። ሆሪ ማርሞት የሚባሉት ሌሎቹ የፍልፈል ዝርያዎች ለዘጠኝ ወራት ያህል ሊተኙ ይችላሉ። የተራራ ማርሞት በእንቅልፍ በሚያሳልፋቸው ወራት የልቡ ምት ቀንሶ በደቂቃ አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ብቻ የሚመታ ሲሆን የሰውነቱ ሙቀት ደግሞ እስከ 5 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ዝቅ ሊል ይችላል። ይህን ያህል ጊዜ ሳይበሉ ለመቆየት ብዙ ዝግጅት ማድረግ እንደሚጠይቅ ምንም ጥርጥር የለውም። ማርሞቶች ረጅሙን የክረምት ወቅት ለማሳለፍ የሚያስችላቸውን በቂ ስብ ለማከማቸት በበጋ ወራትና በመጸው ወቅት መጀመሪያ ላይ በብዛት ይመገባሉ።

ግልገሎቹ ማርሞቶች ብዙውን ጊዜ አንዳቸው ሌላውን እያባረሩ ክብ ሠርተው ይጫወታሉ። አንድ ጊዜ ለጨዋታ ሲታገሉ የነበሩ ሦስት ግልገሎች በሣር በተሸፈነው ቁልቁለት ላይ ተያይዘው ሲንከባለሉ ተመልክቻለሁ። በማንኛውም ዕድሜ ላይ የሚገኙ ማርሞቶች አፍንጫ ለአፍንጫ በመነካካት ሰላምታ ይለዋወጣሉ። የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ ማርሞቶች አንዳቸው የሌላውን ፀጉር የሚያጸዱ ከመሆኑም በላይ በቅዝቃዜ ወቅት ደግሞ ሙቀት ለማግኘት ተቃቅፈው ይተኛሉ።

ማርሞቶች ለሚጠብቃቸው አስቸጋሪ ጊዜ አስቀድመው የሚዘጋጁ ከመሆኑም ሌላ አደገኛ ሁኔታዎችን ነቅተው ይጠብቃሉ። (ኢዮብ 12:7) ሰብዓዊ ቤተሰቦች ከእነዚህ እንስሳት ትምህርት ማግኘት ይችሉ ይሆን?

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

ማርሞቶች በተራራማ ቦታ ለሚገኙ መስኮች ውበት የሚጨምሩ ከመሆኑም በላይ ያላቸው ቤተሰባዊ ትብብር ፈጣሪያቸው ምን ያህል ጥበበኛ እንደሆነ ይመሠክራል።—መዝሙር 50:10

[ከገጽ 12 የተቀነጨበ ሐሳብ ]

ሌሎች የቤተሰብ አባሎች ምግብ ፍለጋ በአካባቢው በሚሰማሩበት ጊዜ ለአካለ መጠን የደረሰ አንድ ማርሞት ለጥበቃ ይቆማል