ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
የካናዳ ተመራማሪዎች የብልግና ምስሎችና ጽሑፎች በወንዶች ላይ ስለሚያስከትሉት ውጤት ጥናት አካሂደው ነበር። አንድ የቡድኑ አባል እንዲህ ብለዋል፦ “በጥናታችን መጀመሪያ ላይ የብልግና ምስሎችንና ጽሑፎችን ጨርሶ አይተውም ሆነ አንብበው የማያውቁ በሃያዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ወንዶች ለማግኘት ጥረት አድርገን ነበር። [ይሁን እንጂ] አንድም ሰው ልናገኝ አልቻልንም።”—የሞንትሪያል ዩኒቨርሲቲ፣ ካናዳ
በርዝመቱ ከዓለም አንደኛ የሆነው ቡርጅ ከሊፋ የተባለው ሕንፃ ባለፈው ጥር ወር በዱባይ ተመርቋል። ሕንፃው 828 ሜትር ከፍታ ሲኖረው ከ160 በላይ ፎቆች አሉት፤ ይህን ሕንፃ ከ95 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ሆኖ ማየት ይቻላል።—ገልፍ ኒውስ፣ ዩናይትድ ዓረብ ኢሚሬትስ
“የአይሁድ እምነት ተሐድሶ በየጊዜው ከሚካሄደው ለውጥ ጋር አብሮ ካልሄደ ምንም ትርጉም አይኖረውም። ፆታቸውን ለመለወጥ ቀዶ ሕክምና ለሚያደርጉ ሰዎች የሚቀርብ ልዩ ጸሎት በቅርቡ በአይሁድ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል።”—ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ መጽሔት፣ ዩናይትድ ስቴትስ
ሐሳባቸውን መግለጽ የማይችሉ ልጆች
በዛሬ ጊዜ ያሉ ወላጆች ቀደም ባሉት ዘመናት የነበሩትን ወላጆች ያህል ልጆቻቸውን በምግብ ሰዓት አያዋሯቸውም ወይም በሚያስተኟቸው ጊዜ አያነቡላቸውም። ዘ ታይምስ የተሰኘው የለንደን ጋዜጣ እንደዘገበው “አንዳንድ ልጆች የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ሲጀምሩ የመናገር ችሎታቸው፣ ዓመት ከስድስት ወር ከሆናቸው ሕፃናት የማይሻል ነው፤ እንዲሁም ቀላል ዓረፍተ ነገሮችን መሥራት የማይችሉ ልጆች ቁጥር እየጨመረ ነው።” በብሪታንያ “አምስት ዓመት ከሆናቸው ልጆች መካከል 18 በመቶ የሚሆኑት (ከ100,000 ይበልጣሉ) ሐሳባቸውን የመግለጽ ችሎታቸው በእነሱ ዕድሜ ከሚጠበቀው ያነሰ ነው።” በመሆኑም መሠረታዊ የሆኑ መመሪያዎችን መረዳት ወይም የሚፈልጉትን ነገር መናገር የማይችሉ ብዙ ልጆች በክፍል ውስጥ ምን እየተከናወነ እንዳለ መረዳት ስለማይችሉ “እንደ ባዕድ አገር ሰዎች ይሆናሉ።”
ቀሳውስት የሌሏቸው የአየርላንድ አብያተ ክርስቲያናት
ዚ አይሪሽ ታይምስ “በካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የቀሳውስት ቁጥር እየቀነሰ” መሆኑን ዘግቧል። ከሃምሳ ዓመት በፊት አየርላንድ ከየትኛውም አገር በላይ በርካታ ቀሳውስት ታፈራ ነበር። ዛሬ ዛሬ ግን የአየርላንድ ቀሳውስት በዕድሜ እየገፉ በመሆኑ በቅርብ ጊዜ ውስጥ እነዚህ ቀሳውስት 75 ዓመት ሞልቷቸው ጡረታ ሲወጡ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት ቄስ አይኖራቸውም። አንዳንዶች እንደሚሉት ለዚህ ችግር መነሻ የሆነው በ1968 የወጣው ሰው ሠራሽ የእርግዝና መከላከያ ዘዴዎችን የሚከለክለው ሂውማናኤ ቪታኤ የተባለ የርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ድንጋጌ ነው። ታይምስ በመቀጠል እንደገለጸው ይህ ድንጋጌ ሰዎች “የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርቶች መጠራጠር እንዲጀምሩ” እንዲሁም “በቤተ ክርስቲያን አመራር ላይ ያላቸው እምነት” እየተዳከመ እንዲሄድ አድርጓል።
የሰሜኑ መግነጢሳዊ ዋልታ ከቦታው በመንቀሳቀስ ላይ ነው
የሰሜኑ መግነጢሳዊ ዋልታ ያለበት ቦታ በ1831 ለመጀመሪያ ጊዜ ሲታወቅ በሰሜናዊ ካናዳ የነበረ ሲሆን “ከጂኦግራፊያዊው የሰሜን ዋልታ 2,750 ኪሎ ሜትር ያህል ይርቅ ነበር” ይላል ለ ፊጋሮ የተባለው የፈረንሳይ ጋዜጣ። እስከ 1989 ባለው ጊዜ የሰሜኑ መግነጢሳዊ ዋልታ በየዓመቱ ከ5 እስከ 15 ኪሎ ሜትር ወደ ጂኦግራፊያዊው የሰሜን ዋልታ ሲጠጋ ቆይቷል። የፓሪሱ ግሎባል ፊዚክስ ተቋም እንደገለጸው የሰሜኑ መግነጢሳዊ ዋልታ በአሁኑ ጊዜ “በዓመት 55 ኪሎ ሜትር” በሚደርስ ፍጥነት ወደ ጂኦግራፊያዊው የሰሜን ዋልታ እየተጠጋ ሲሆን በ2007 ከጂኦግራፊያዊው የሰሜን ዋልታ ያለው ርቀት 550 ኪሎ ሜትር ብቻ ነበር። የሰሜኑ መግነጢሳዊ ዋልታ በዚህ ፍጥነትና አቅጣጫ መንቀሳቀሱን ከቀጠለ ይህ ዋልታ ባለበት አካባቢ የሚታየው አውሮራ ቦሪያሊስ ወይም የሰሜኑ ውጋገን በ2020 “ከካናዳ ይልቅ በሳይቤሪያ ይበልጥ ደምቆ ይታያል” በማለት ጋዜጣው አክሎ ገልጿል።