በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የምድርን አናት በመርከብ ማቋረጥ

የምድርን አናት በመርከብ ማቋረጥ

የምድርን አናት በመርከብ ማቋረጥ

የጥንት መርከበኞች የአትላንቲክና የፓስፊክ ውቅያኖሶችን በሰሜን ዋልታ በኩል የሚያገናኝ አቋራጭ የባሕር መስመር የማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው፤ ይሁን እንጂ በበረዶ ግግር የተሸፈነው የአርክቲክ ውቅያኖስ ሊወጡ የማይችሉት ጋሬጣ ሆኖባቸው ነበር።

ያም ሆኖ በምድር አናት ላይ የሚያልፍ አቋራጭ መስመር እንዲፈልጉ የሚያነሳሷቸው ምክንያቶች ነበሩ። በ16ኛው ምዕተ ዓመት፣ በአፍሪካና በደቡብ አሜሪካ ደቡባዊ ጫፍ ዞረው ወደ ሩቅ ምሥራቅ የሚያደርሱት የንግድ መስመሮች ሙሉ በሙሉ በፖርቹጋልና በስፔን ቁጥጥር ሥር ነበሩ። የሌላ አገር ነጋዴዎች ከምሥራቁ ንግድ ድርሻ እንዲኖራቸው ከፈለጉ በሰሜን ዋልታ በኩል የሚያልፍ የባሕር መስመር ማግኘት ነበረባቸው። ከዚህ በታች የተጠቀሱትን ጨምሮ ብዙዎች ይህን ለማድረግ ሞክረዋል።

እንግሊዞች፦ በ1553 ሰር ሂዩ ዊለቢ እና ሪቻርድ ቻንስለር ወደ ሰሜን ዋልታ የተደረገውን የመጀመሪያውን የእንግሊዝ የባሕር ጉዞ መርተዋል። ሆኖም በባሕር ሞገድ ምክንያት መርከቦቻቸው በተለያየ አቅጣጫ በመሄዳቸው ዊለቢ በሩሲያ ሰሜናዊ ጫፍ በምትገኘውና ጠፍ ምድር በሆነችው በኮላ ባሕረ ገብ መሬት የበረዶውን ወራት ለማሳለፍ ተገደደ። የሚያሳዝነው ግን ዊለቢም ሆነ አብረውት የነበሩት ሰዎች ብርዱን ለመቋቋም በቂ ዝግጅት ስላላደረጉ ሁሉም አለቁ። ቻንስለር ግን አርካንገልስክ ወደብ መድረስ ቻለ። ከዚያም የሩሲያው ዛር ኢቫን አራተኛ ቫሲሊቪች (ኢቫን ጨካኙ) ያደረጉለትን ግብዣ በመቀበል ወደ ሞስኮ ተጓዘ። ቻንስለር ወደ እስያ የሚያሻግር መስመር ማግኘት አይቻል እንጂ በእንግሊዝና በሩሲያ መካከል የንግድ ግንኙነት እንዲከፈት አስችሏል።

ደቾች፦ በ1594 ቪለም ባረንትስ መጀመሪያ ወደ ኖቨያ ዘምሊያ በመርከብ ተጓዘ። በ1596 ለሦስተኛ ጊዜ ባደረገው ጉዞ ላይ ግን በሩሲያ ሰሜናዊ ጫፍ የነበሩትን ትናንሽ ደሴቶች ለማቋረጥ ሲሞክር መርከቡ በረዶ ውስጥ በመቀርቀሩ ሊጠገን በማይችል ሁኔታ ተጎዳ። ባረንትስና የመርከቡ ሠራተኞች ባሕር ላይ ተንሳፈው ባገኟቸው እንጨቶች መጠለያ የሠሩ ሲሆን የድብ ሥጋ እየበሉ ከባድ የነበረውን የበረዶ ወቅት አሳለፉ፤ ከዚያም በሁለት ትናንሽ ጀልባዎች ተመለሱ። ይሁንና ባረንትስ በጉዞ ላይ እንዳለ ሕይወቱ አለፈ።

ሩሲያውያን፦ ሩሲያውያን አሳሾች ሳይቤሪያንና የሩሲያን ሩቅ ምሥራቃዊ ዳርቻ ለማሰስ የተጠናከረ ጥረት አድርገዋል። ከ1581 እስከ 1641 በነበሩት 60 ዓመታት ውስጥ ብቻ ከዩራል ተራሮች እስከ ፓስፊክ ውቅያኖስ ተጉዘዋል። በዚህ ጊዜ ኮሳኮች በሳይቤሪያ ወንዞች አድርገው ወደ አርክቲክ ውቅያኖስ ተጓዙ። ኮሳኮች፣ ሳይቤሪያ የሩሲያ ግዛት እንድትሆን ከማድረጋቸውም በላይ በሳይቤሪያ ሰሜን ምሥራቅ ዳርቻዎች በኩል የባሕር መስመር ከፈቱ። በ1648 የሩሲያ መርከቦች፣ ቪቶስ ቤሪንግ በተባለ ዴንማርካዊ መርከበኛ የተሰየመውን የቤሪንግ ባሕረ ሰላጤ አቋርጠው አልፈዋል።

ተጨማሪ የባሕር ጉዞዎች

ከ1733 እስከ 1743 ባሉት ዓመታት በቤሪንግ የሚመሩ አንድ ሺህ የሚያህሉ ሰዎች በሰባት ቡድኖች ተከፋፍለው በሩሲያ በኩል የሚገኙትን የአርክቲክና የፓስፊክ የባሕር ዳርቻዎች ለማሰስ ተጉዘዋል። መርከቦቻቸው በተደጋጋሚ በበረዶ የተያዙባቸው ሲሆን በርካታ ባሕረተኞችም ሞተዋል። ያም ቢሆን ተጓዦቹ ሙሉውን የአርክቲክ የባሕር ዳርቻ ካርታ ማንሳት ችለዋል። እነሱ ያጠናቀሯቸው መረጃዎች (ስለ ባሕሩ ዝርዝር መረጃዎችን የያዙ ካርታዎች እንዲሁም ስለ ውቅያኖሱ ጥልቀትና ስለ በረዶው ሁኔታ የሚናገሩ መግለጫዎች) ከዚያ በኋላ በአርክቲክ ላይ ለሚጓዙ ባሕረተኞች በጣም ከፍተኛ ጥቅም አስገኝተዋል።

በአርክቲክ ውቅያኖስ ላይ የተጓዙት እነዚህ ሁሉ ሰዎች የተጠቀሙት ከእንጨት በተሠሩ መርከቦች ነበር። ይሁን እንጂ ከእንጨት የተሠሩ መርከቦች ሰሜናዊውን የባሕር መስመር ለማቋረጥ ፈጽሞ እንደማያስችሉ ቤሪንግ ያደረገው አሰሳ አረጋግጧል። ብሪታንያዊው አሳሽ ጄምስ ኩክም በ1778 ተመሳሳይ መደምደሚያ ላይ ደርሷል፤ ጄምስ ኩክ በቤሪንግ ባሕረ ሰላጤ አልፎ ወደ ምዕራብ ለመጓዝ ሲሞክር በረዶ መንገዱን ስለዘጋበት ጉዞው አልተሳካም። ከአንድ ምዕተ ዓመት በኋላ የፊንላንድ ተወላጅ የሆነው ኒልስ አዶልፍ ኤሪክ ኖርደንሾልድ፣ በእንፋሎት የሚሠራ ሞተር ባለው መርከብ በመጠቀም ሰሜናዊውን የባሕር መስመር ማቋረጥ ቻለ።

ሩሲያውያን የነበራቸው እውቀትና ብቃት

በ1917 ከተካሄደው የሩሲያ አብዮት በኋላ በሩሲያ ክልል በሚገኘው የአርክቲክ ውቅያኖስ ላይ ከሩሲያ መርከቦች በስተቀር ሌሎች መርከቦች እንዳይጓዙ ተከለከለ። ከ1930 ወዲህ ባሉት ዓመታት ሶቪየት ኅብረት ሰሜናዊውን የባሕር መስመር ይበልጥ በማሻሻል አዲስ ለተቋቋሙ ኢንዱስትሪዎች አገልግሎት የሚሰጡ ወደቦችን ገነባች። በዚህ መንገድ ሩሲያ በአርክቲክ ውቅያኖስ ላይ በሚደረገው ጉዞ ረገድ ከፍተኛ እውቀትና ብቃት አዳበረች።

በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ሰሜናዊው የባሕር መስመር ለሌሎች አገሮች መርከቦች ዝግ ነበር። ይሁን እንጂ የፖለቲካ ለውጥ በመካሄዱና ወደ ገበያ ኢኮኖሚ ሽግግር በመደረጉ በአሁኑ ጊዜ የሩሲያ ባለሥልጣናት የሌሎች አገሮች መርከቦች በዚህ መስመር እንዲያልፉ እያበረታቱ ነው። ይህ ለውጥ ያስገኘውን ጥቅም ከሚከተለው ምሳሌ መመልከት ይቻላል።

በ2009 የበጋ ወቅት ሁለት የጀርመን ዕቃ ጫኝ መርከቦች በቤሪንግ ባሕረ ሰላጤ አልፈው በስተምዕራብ እምብዛም በረዶ በሌለባቸው የእስያና የአውሮፓ ሰሜናዊ ዳርቻዎች ከተጓዙ በኋላ ኔዘርላንድ ደርሰዋል። ንብረትነቱ የሩሲያ ያልሆነ መርከብ መላውን ሰሜናዊ ምሥራቅ የባሕር መተላለፊያ * ሲያቋርጥ ይህ የመጀመሪያው ጊዜ ነው። መርከቡ በዚህ መተላለፊያ በመጠቀሙ 5,560 ኪሎ ሜትርና የአሥር ቀን የባሕር ጉዞ መቀነስ ችሏል። የዚህ መርከብ ባለቤት የሆነው ኩባንያ አርክቲክን ለመሻገር በሚያስችለው በዚህ አቋራጭ መስመር በመጠቀሙ በእያንዳንዱ መርከብ 300,000 ዩሮ (በወቅቱ 450,000 የአሜሪካ ዶላር) እንደቆጠበ ገምቷል።

በአሁኑ ጊዜ የአርክቲክ ውቅያኖስ በረዶ በከፍተኛ ፍጥነት በመቀነስ ላይ ይገኛል። በዚህ ምክንያት በበጋው ወራት ሰፋ ያለ የባሕሩ ክፍል ለመርከብ ጉዞ አመቺ እየሆነ መጥቷል። * የበረዶው መቅለጥ አሳሳቢ ቢሆንም ይህ ሁኔታ እየቀጠለ ከሄደ መርከቦች ብዙ ጥልቀት በሌላቸው የሩሲያ የባሕር ዳርቻዎች መጓዛቸውን ትተው ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ወደ ፓስፊክ ውቅያኖስ መሃል ለመሃል መሻገር በሌላ አባባል የምድርን አናት ማቋረጥ ይችላሉ።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.13 “ሰሜናዊ ምሥራቅ የባሕር መተላለፊያ” የሚለው አገላለጽ በሩሲያኛ “ሰሜናዊ የባሕር መስመር” ለሚለው መጠሪያ የተሰጠ ሌላ ስም ነው።

^ አን.14 በዚህና በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ ለመርከብ ጉዞ አመቺ የሆኑት ወራት ርዝመት በምሥራቃዊው አርክቲክ በሦስት እጥፍ ገደማ ሲጨምር በምዕራባዊው አርክቲክ ከሁለት እጥፍ በላይ ጨምሯል።

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

. . . የተጓዙባቸው መስመሮች

ሰር ሂዩ ዊለቢ እና ሪቻርድ ቻንስለር

ቪለም ባረንትስ

ቪቶስ ቤሪንግ

ኒልስ አዶልፍ ኤሪክ ኖርደንሾልድ

የበረዶ ድንበር

[ካርታ]

አርክቲክ ውቅያኖስ

ሰሜን ዋልታ

ቋሚ የበረዶ ድንበር

በሞቃት ወቅት የበረዶው ድንበር

በቅዝቃዜ ወቅት የበረዶው ድንበር

የአርክቲክ ክልል

ስዊድን

ግሪንላንድ

ካናዳ

አላስካ

ቤሪንግ ባሕረ ሰላጤ

ሩሲያ

ሳይቤሪያ

የዩራል ተራሮች

ኖቨያ ዘምሊያ

ኮላ ባሕረ ገብ መሬት

አርካንገልስክ

ሞስኮ

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአርክቲክ ውቅያኖስ በረዶ በፍጥነት እየቀለጠ ነው

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]

Library and Archives Canada/Samuel Gurney Cresswell collection/C-016105