በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

‘የሰዓቶችን ንጉሥ’ ማየትና መስማት

‘የሰዓቶችን ንጉሥ’ ማየትና መስማት

‘የሰዓቶችን ንጉሥ’ ማየትና መስማት

የዌስትሚንስተር ቤተ መንግሥት በ1834 ከተቃጠለ በኋላ የብሪታንያ ፖለቲከኞች አዲስ ለሚሠራው የፓርላማ ሕንፃ የሚሆን ከሁሉ የላቀ ንድፍ ለማቅረብ ተወዳድረው ነበር። በውድድሩ ያሸነፈው ሰር ቻርልስ ቤሪ ያቀረቡት ንድፍ ነበር፤ ጎቲክ የሚባለውን የመካከለኛው ዘመን የሕንፃ አሠራር በተከተለውና የሚያምር ቅርጽ ባለው በዚህ የቤተ መንግሥት ንድፍ ላይ አራት ማዕዘን የሆነ ግዙፍ የሰዓት ማማ ተካትቶ ነበር። ሥራ አስፈጻሚው ቢሮ “ዓለም አይቶት የማያውቅ ግዙፍ ሰዓት፣ የሰዓቶች ንጉሥ” እንዲሠራ አዘዘ።

ይህ ሰዓት ዝነኛ ከሆኑት የለንደን ገጽታዎች አንዱ ሲሆን ደወሉ የሚያሰማው ለየት ያለ ድምፅ በመላው ዓለም የታወቀ ሆኗል። ሰዓቱ ቢግ ቤን ይባላል፤ በእርግጥ ይህ ስም መጀመሪያ የሚያመለክተው ትልቁን ደወል ብቻ ነበር። ከፍተኛ ዝና ያተረፈው ይህ ሰዓት አስደናቂ የሆነ የምሕንድስና ጥበብ ተንጸባርቆበታል።

እልህ አስጨራሽ ሥራ

የ96 ሜትር ከፍታ ያለው የሰዓት ማማ መሠራት የጀመረው በ1843 ነበር። ከሦስት ዓመት በኋላ፣ በሰዓት ከአንድ ሴኮንድ በላይ የማያዛንፍ ትክክለኛ ሰዓት የሚሠራ ባለሙያ ማፈላለግ ተጀመረ። የዚህ ሰዓት ሥራ እልህ አስጨራሽ ነበር። ሰዓቱ የሚቀመጠው ረጅም በሆነ ማማ ላይ ሲሆን መከለያም የለውም፤ በዚህም የተነሳ የሰዓቱ ቆጣሪዎች ለነፋስና ለበረዶ የተጋለጡ ከመሆናቸውም ሌላ ርግቦች ሊያርፉባቸው ይችላሉ! እነዚህ ነገሮች በፔንዱለሙ እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ሲሆን ሰዓቱ በትክክል እንዲሠራ ደግሞ ፔንዱለሙ ወጥ የሆነ እንቅስቃሴ ማድረጉ እጅግ አስፈላጊ ነው። ባለሙያዎቹ ይህን ችግር እንዴት እንደሚወጡ በመወያየት ላይ እያሉ የሰዓት ሥራ ባለሙያ የሆነው ኤድመንት ቤከት ዴኒሰን ተቀባይነት ያለው ንድፍ አቀረበ፤ ከዚያም አንድ እውቅ የሆነ ሰዓት ሠሪ ሥራውን እንዲጀምር ተደረገ።

ከሁለት ዓመት በኋላ ሰዓቱ ተሠርቶ ቢጠናቀቅም የማማው ሥራ ስላላለቀ ለአምስት ዓመታት ያህል ከሰዓት ሠሪው ቤት አልተንቀሳቀሰም። በዚህ ጊዜ ውስጥ ዴኒሰን በፔንዱለሙ እንቅስቃሴ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ነገሮችን ለመከላከል የሚያስችል ዘዴ አገኘ፤ ይህ ደግሞ ሰዓቱ ይበልጥ በትክክል እንዲሠራ አስተዋጽኦ አድርጓል።

ቢግ ቤን ተወለደ

ሰዓቱ ተሠርቶ ከተጠናቀቀ በኋላ ቀጣዩ እርምጃ ደወሎቹን መሥራት ነበር። በሰሜን ምሥራቅ እንግሊዝ የሚገኝ አንድ የብረታ ብረት ማቅለጫ፣ ሙሉ ሰዓት ላይ የሚደውለውን ትልቁን ደወል ሠራ። ደወሉ ከተጠበቀው በላይ ግዙፍ ሲሆን ክብደቱ 160 ኩንታል ይመዝን ነበር! ደወሉ በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ ወደ ለንደን እንዲያጓጉዘው በተጫነበት መርከብ ላይ ጉዳት አድርሶ ነበር። ከጊዜ በኋላ መርከቡ ለንደን ደረሰ። ደወሉ ከመርከብ ከወረደ በኋላ በ16 ነጫጭ ፈረሶች በሚጎተት ልዩ ሠረገላ ተጭኖ ተወሰደ። ከዚያም ደወሉን ለመሞከር፣ በፓርላማው ፊት ለፊት በተሠራ መስቀያ ላይ እንዲንጠለጠል ተደረገ።

ብዙ ትላልቅ ደወሎች ስም ይሰጣቸዋል፤ ይህ ግዙፍ ደወልም ቢግ ቤን የሚል ስያሜ ተሰጠው። ለምን? ይህን በእርግጠኝነት የሚያውቅ ሰው የለም። አንዳንዶች ደወሉ ሰር ቤንጃሚን ሆል በተባሉ ግዙፍ ሰውነት ያላቸው የፓርላማ ሠራተኛ ስም ተሰይሞ ሊሆን እንደሚችል ይናገራሉ። ሌሎች ደግሞ በዘመኑ ዝነኛ በነበረው ቤንጃሚን ኮንት በተባለ የከባድ ሚዛን ቦክሰኛ ስም እንደተሰየመ ይገልጻሉ። ደወሉ ስያሜውን ያገኘው ከየትም ይሁን፣ መጀመሪያ ላይ የሰዓቱን ደወል ብቻ ያመለክት የነበረው ቢግ ቤን የሚለው መጠሪያ ዛሬ ሰዓቱንና ማማውን በአጠቃላይ ለማመልከት ይሠራበታል።

ሁለት ጊዜ አደጋ አጋጠመው

የቢግ ቤን የመጀመሪያ መደወያ ቀላል እንደሆነ ስለታሰበ 660 ኪሎ ግራም ክብደት ያለው ትልቅ የደወል መምቻ ተቀየረለት። ይሁን እንጂ ደወሉ ለተወሰኑ ወራት ከተሞከረ በኋላ አደጋ አጋጠመው፤ ሊጠገን በማይችል ሁኔታ ተሰነጠቀ። በዚህ የተነሳ ቢግ ቤን ከመስቀያው እንዲወርድ ተደረገ። ከዚያም ብረቱ ቀልጦ 137 ኩንታል የሚመዝን ሌላ ደወል ተሠራ። አዲሱን ደወል የጫነው ሠረገላ ወደ ፓርላማው ሕንፃ ሲያመራ ሕዝቡ በድጋሚ በመንገዱ ዳር ተሰብስቦ ይመለከት ነበር።

ከጥቂት ወራት በኋላ ማማው ተጠናቀቀ። ቢግ ቤንን ማማው ላይ ለመስቀል በርካታ ሰዎች በቡድን ተከፋፍለው ያለመታከት ሥራውን ተያያዙት። ይህ ግዙፍ ደወል በየሩብ ሰዓቱ ከሚደውሉት አራት አነስተኛ ደወሎች ጋር አብሮ ተሰቀለ። ከዚያም ትልቁ ሰዓት ተገጠመ። በመጨረሻም “የሰዓቶች ንጉሥ” ሥራውን ለመጀመር ዝግጁ የሆነ ይመስል ነበር።

በሐምሌ ወር 1859 ቢግ ቤን በየሰዓቱ የደወል ድምፅ ማሰማት ጀመረ። ይሁን እንጂ የተገኘው ድል በአጭሩ ተቀጨ። በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ትልቁ ደወል እንደገና ተሰነጠቀ! ደወሉን ከማማው ላይ ማውረድ የማይታሰብ ነገር ነበር። በዚህ ፋንታ ሠራተኞቹ የደወሉ መምቻ ስንጥቁ ላይ እንዳያርፍ የደወሉን አቅጣጫ በትንሹ አዞሩት። ከዚያም ደወሉ ዳግመኛ እንዳይሰነጠቅ ቀለል ያለ መምቻ ተገጠመለት። በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ቢግ ቤን እንደገና ሥራውን ጀመረ! ስንጥቁ እንዳለ ሲሆን ደወሉ ጎርነን ያለ ልዩ ድምፅ የሚያሰማው በዚህ ምክንያት ነው።

ታሪካዊ ምዕራፎች

በ1924 ቢቢሲ የተባለው የብሪታንያ ዜና ማሰራጫ ኮርፖሬሽን ሰዓቱ በሚገኝበት ማማ ላይ በቋሚነት የድምፅ ማጉያ በመግጠም ሰዓቱን የሚያሳውቅ ደወል በመላ አገሪቱ ማሰራጨት ጀመረ። ከስምንት ዓመት በኋላ በብሪታንያ የጋራ ብልጽግና አባል አገራት ውስጥ የሚኖሩ አድማጮች በሙሉ ይህን ደወል እንዲሰሙት የተደረገ ሲሆን ዛሬ በቢቢሲ ዓለም አቀፍ አገልግሎት አማካኝነት የቢግ ቤን ማራኪ ደወል በመላው ዓለም ይደመጣል።

ሰዓቱና ደወሎቹ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት የቦምብ ድብደባ ቢተርፉም በ1976 ከመደወያ መሣሪያዎቹ ጋር በተያያዘ በተፈጠረው ብልሽት የተነሳ ሰዓቱ ካለበት ክፍል አብዛኛው ጉዳት ደረሰበት። ሆኖም ትልቁ ደወል ምንም ስላልሆነ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ በየሰዓቱ መደወሉን ቀጠለ። መላው ሰዓት እንደ ቀድሞው እንዲሠራ ለማድረግ ግን ዘጠኝ ወር ፈጅቷል።

ለተወሰነ ጊዜ ያህል ቢግ ቤን በትልቅነቱ በዓለም ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ሰዓት ሆኖ ቆይቷል፤ ዛሬም ቢሆን ዝንፍ የማይል አውቶማቲክ የሕዝብ ሰዓት በመሆኑ ይታወቃል። ብዙዎች ለየት ያለውን የቢግ ቤን ደወል የኮረጁ ሲሆን በበርካታ አገራት የሚገኙ ትላልቅም ሆኑ ትናንሽ ሰዓቶች እንዲህ ዓይነት ድምፅ አላቸው። ከዚህ አንጻር ቢግ ቤን የእንግሊዝና የዋና ከተማዋ መለያ መሆኑ ምንም አያስደንቅም። በእርግጥም ቢግ ቤን “የሰዓቶች ንጉሥ” ነው!

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕሎች]

ሰዓቱ በትክክል እንዲሠራ የሚደረገው እንዴት ነው?

በሳምንት ሦስት ጊዜ አንድ ቴክኒሽያን 300 የሚያህሉ ጠመዝማዛ ደረጃዎችን ይወጣና ለሰዓቱ ኃይል የሚሠጠውን ክብደት የተሸከመውን ገመድ በእጁ ይጠቀልለዋል። በተጨማሪም ቴክኒሽያኑ ሰዓቱ ትክክል መሆን አለመሆኑን ያረጋግጣል። አራት ሜትር ርዝመት ያለው ፔንዱለም በየሁለት ሴኮንዱ ይወዛወዛል። በፔንዱለሙ አናት ላይ በሚገኝ ማስቀመጫ ላይ ትናንሽ የድሮ ሳንቲሞች ይቀመጣሉ። ቴክኒሽያኑ ሰዓቱ ወደኋላ እየቀረ እንዳለ ካስተዋለ አንድ ሳንቲም ይጨምራል። ሰዓቱ እየፈጠነ ከሆነ ደግሞ አንድ ሳንቲም ይቀንሳል።

[ሥዕል]

ትናንሽ የድሮ ሳንቲሞች ሰዓቱን ለማስተካከል ይረዳሉ

[ምንጮች]

Winding clock: AP Photo/Lefteris Pitarakis; coins on ledge: Parliamentary copyright images are reproduced with the permission of Parliament

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

137 ኩንታል የሚመዝነው ትልቅ ደወል (ቢግ ቤን) በየሙሉ ሰዓቱ ይደውላል

[ምንጭ]

Popperfoto/Getty Images