በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ግቦቼ ላይ መድረስ የምችለው እንዴት ነው?

ግቦቼ ላይ መድረስ የምችለው እንዴት ነው?

የወጣቶች ጥያቄ

ግቦቼ ላይ መድረስ የምችለው እንዴት ነው?

ከሚከተሉት ውስጥ ቢሳካልህ ደስ የሚልህ የትኛው ነው?

በራስ የመተማመን ስሜትን ማሳደግ

ተጨማሪ ጓደኞች ማፍራት

የበለጠ ደስተኛ መሆን

እንደ እውነቱ ከሆነ ሦስቱም ነገሮች ሊሳኩልህ ይችላሉ! እንዴት? ግቦችን በማውጣትና ያወጣሃቸው ግቦች ላይ በመድረስ ነው። ቀጥሎ የቀረቡትን ሐሳቦች ተመልከት።

በራስ የመተማመን ስሜትን ማሳደግ፦ ትንንሽ ግቦችን አውጥተህ ከተሳካልህ ትልልቅ ግቦችን ብታወጣም ሊሳካልህ እንደሚችል ትተማመናለህ። እንዲሁም እንደ እኩዮች ተጽዕኖ ያሉ በየዕለቱ የሚያጋጥሙህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ስትቋቋም በራስ የመተማመን ስሜትህ እያደገ ይሄዳል። በምላሹም ሰዎች ያለህን በራስ የመተማመን ስሜት ሊያስተውሉ አልፎ ተርፎም ሊያከብሩህ ይችላሉ። አንዳንዶች ደግሞ የሚያሳድሩብህን ተጽዕኖ ይቀንሱ ይሆናል። እንዲያውም አንተን ማድነቅ ሊጀምሩ ይችላሉ።—ከማቴዎስ 5:14-16 ጋር አወዳድር።

ተጨማሪ ጓደኞች ማፍራት፦ ብዙዎች መቀራረብ የሚያስደስታቸው ምን እንደሚፈልጉ ከሚያውቁና የፈለጉትን ለማግኘት አስፈላጊውን ጥረት ሁሉ ከሚያደርጉ ሰዎች ጋር ነው። ያለህን ግብ አውቀው የሚቀርቡህ ሰዎች ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ያሰብከው ግብ ላይ እንድትደርስ ይረዱሃል።—መክብብ 4:9, 10

የበለጠ ደስተኛ መሆን፦ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ለነገሮች ፍላጎት ማጣት ወይም የሆነው ይሁን ብሎ ዝም ብሎ መኖር ደስ የሚል ነገር አይደለም። በሌላ በኩል ግን ግብ ስታወጣና ያወጣኸው ግብ ላይ ስትደርስ ስኬት የሚያስገኘውን ደስታ ታጣጥማለህ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረው ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ በአንድ ወቅት “እኔ ግብ እንደሌለው ሰው በከንቱ አልሮጥም” ብሎ የተናገረው ለዚህ ነው። (1 ቆሮንቶስ 9:26 አ.መ.ት.) በተጨማሪም ግብህ ትልቅ በሆነ መጠን ግብህ ላይ በመድረስ የምታገኘው እርካታና ደስታ የዚያኑ ያህል ከፍተኛ እንደሚሆን አስታውስ!

ታዲያ ለመጀመር ተዘጋጅተሃል? አሁን የሚቀጥለውን ገጽ ቆርጠህ እጠፈው፤ ከዚያም የተዘረዘሩትን እርምጃዎች ተከተል። *

www.watchtower.org/ype በሚለው ድረ ገጽ ላይ “Young People Ask” በሚል አምድ ሥር ተጨማሪ ርዕሶችን ማግኘት ይቻላል።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.11 እዚህ ላይ የቀረቡት ሐሳቦች፣ በጥቂት ሳምንታት ወይም ወራት ውስጥ የሚደረስባቸው ግቦችን ለማሳካት የሚረዱህ ቢሆኑም መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ለትልልቅ ግቦችም ይሠራሉ።

ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች

● በአንድ ጊዜ ብዙ ግቦች ማውጣት ይቻላል? —ፊልጵስዩስ 1:10

● ግብ ማውጣት ማለት ለእያንዳንዱ የሕይወትህ እንቅስቃሴ እቅድ ማውጣት ማለት ነው?—ፊልጵስዩስ 4:5

መስመሩን ተከትለህ ቁረጠው

[በገጽ 25 እና 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ግቦችህ ላይ መድረስ የምትችልበት መንገድ ግብህን እወቅ

እጠፈው ምሳሌ 4:25, 26

“ትልልቅ ግቦችን ለማውጣት አትፍራ። ከዚህ ቀደም ሌሎች አንተ ያወጣሃቸው ግቦች ላይ መድረስ ከቻሉ አንተም ትችላለህ።”—ሮበን

1. የትኞቹን ግቦች ማውጣት እንደምትችል አስብ። ይህን በምታደርግበት ጊዜ መጨነቅ አያስፈልግህም። ትንታኔ ውስጥ አትግባ፤ ብቻ የመጣልህን ግብ በሙሉ ጻፍ። ቢያንስ 10 ወይም 20 አማራጮችን ለመጻፍ ሞክር።

2. የጻፍካቸውን ግቦች ገምግም። ይበልጥ አስደሳች የሚሆኑልህ የትኞቹ ግቦች ናቸው? በጣም ተፈታታኝ የሆኑትስ? ብትደርስበት ትልቅ ስኬት እንዳገኘህ እንዲሰማህ የሚያደርግህ ግብ የትኛው ነው? ምርጥ ናቸው የምትላቸው ግቦች ለአንተ ትልቅ ትርጉም ያላቸው ግቦች መሆን እንደሚገባቸው አትዘንጋ።

3. ቅደም ተከተል አውጣ። መጀመሪያ በጥቂት ቀናት ልትደርስባቸው የምትችላቸውን የአጭር ጊዜ ግቦች ምረጥ። ቀጥሎ (በብዙ ሳምንታት ወይም ወራት ውስጥ ሊደረስባቸው የሚችሉ) የረጅም ጊዜ ግቦችን ምረጥ። ከዚያም ግቦችህን እንደ አስፈላጊነታቸው በቅደም ተከተል ቁጥር ስጣቸው።

ናሙና

ጓደኝነት፦ በዕድሜ ከእኔ ከሚበልጥ ሰው ጋር ጓደኝነት መመሥረት። ከድሮ ጓደኛዬ ጋር የነበረኝን ግንኙነት እንደገና ማጠናከር።

ጤንነት፦ በየሳምንቱ በድምሩ ለ90 ደቂቃ ያህል ስፖርት መሥራት። በእያንዳንዱ ሌሊት ለስምንት ሰዓት ያህል መተኛት።

ትምህርት ቤት፦ በሒሳብ ትምህርት ውጤቴን ማሻሻል። እኩዮቼ ፈተና እንድኮርጅ የሚያደርጉብኝን ግፊት መቋቋም።

መንፈሳዊነት፦ በየቀኑ መጽሐፍ ቅዱስን ለ15 ደቂቃ ማንበብ። በዚህ ሳምንት ለአንድ የክፍል ጓደኛዬ ስለ እምነቴ መንገር።

እቅድ ምሳሌ 21:5

“ግብ ማውጣት ጥሩ ነው፤ ይሁን እንጂ ግቦችህ ላይ ለመድረስ እቅድ ማውጣት ያስፈልግሃል። አለበለዚያ ግብ ሆነው ይቀራሉ እንጂ መቼም ቢሆን አትደርስባቸውም።”—ዴሪክ

ለመረጥከው ለእያንዳንዱ ግብ የሚከተለውን አድርግ፦

1. ግብህን መዝግብ።

2. ቀነ ገደብ አብጅ። ደግሞም ቀነ ገደብ ያልተበጀለት ግብ ሕልም ሆኖ ይቀራል!

3. የምትወስዳቸውን እርምጃዎች መዝግብ።

4. የሚያጋጥሙህን እንቅፋቶች አስብ። ከዚያም እንዴት እንደምትወጣቸው አስብ።

5. የዓላማ ጽናት ይኑርህ። ግብህ ላይ ለመድረስ የቻልከውን ሁሉ እንደምታደርግ ለራስህ ቃል ግባ። ከዚያም ፊርማህንና ቀኑን አስፍር።

ወላይትኛ እማራለሁ ምክንያቱም ወላይታ ሶዶ እሄዳለሁ። ሐምሌ 1 እጀምራለሁ።

እርምጃዎች

1. ወላይትኛ መማሪያ መጽሐፍ ማግኘት።

2. በየሳምንቱ አሥር አዳዲስ ቃላትን መማር።

3. ሌሎች ሰዎች ወላይትኛ ሲናገሩ ማዳመጥ።

4. አንድ ሰው የሰዋስውና የቃላት አጠቃቀሜ ትክክል መሆኑን እንዲነግረኝ መጠየቅ።

እንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች

ወላይትኛ የሚናገር ሰው በአካባቢዬ የለም

እንቅፋቶቹን ማስወገድ የምችለው እንዴት ነው?

በወላይትኛ የተቀዱ ካሴቶችንና በዚህ ቋንቋ የሚተላለፉ ፕሮግራሞችን ማዳመጥ።

․․․․․ ․․․․․

ፊርማ ቀን

እርምጃ ውሰድ! ዮሐንስ 13:17

“ሌሎች ነገሮች ትኩረትህን ሊሰርቁት ስለሚችሉ ግቦችህን በቀላሉ ልትረሳቸው ትችላለህ፤ በመሆኑም ምንጊዜም በግቦችህ ላይ ማተኮርና ግብህን ለማሳካት ጥረት ማድረግህን መቀጠል ይኖርብሃል።”—ኤሪካ

ቶሎ ጀምር። ‘ግቤ ላይ ለመድረስ ዛሬን ምን ማድረግ እችላለሁ?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። እርግጥ ነው፣ ዝርዝር ሐሳብ አልጻፍክ ይሆናል፤ ያም ቢሆን እንዲህ አለማድረግህ ወደ ግብህ የሚያደርስህን እርምጃ መውሰድ እንዳትጀምር እንቅፋት ሊሆንብህ አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጸው “ነፋሱና አየሩ ጥሩ እስኪሆን ድረስ የምትጠባበቅ ከሆነ ምንም ነገር አትዘራም፤ መቼም ቢሆን አታጭድም።” (መክብብ 11:4 ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን) ትንሽ ነገር ቢሆንም እንኳ ዛሬ ልታደርገው የምትችለውን ነገር ፈልገህ አድርግ።

ግቦችህን በየቀኑ ገምግም። እያንዳንዱ ግብ ለአንተ አስፈላጊ የሆነበትን ምክንያት መለስ ብለህ አስብ። እያንዳንዱን እርምጃ ስታጠናቅቅ ከአጠገቡ ምልክት አድርግ ወይም “በቀኑ የተጠናቀቀ” በማለት ጻፍ።

ግትር አትሁን። በዝርዝር ያወጣኸው እቅድ የቱንም ያህል ጥሩ ቢሆን እየሠራህበት ስትሄድ መስተካከል ሊያስፈልገው ይችላል። እንዲህ መሆኑ ችግር የለውም። እቅዴን ሙሉ በሙሉ ካልተከተልኩ ብለህ መጨናነቅ የለብህም። ዋናው ነገር የመጨረሻው ግብህ ላይ የሚያደርስህን እርምጃ መውሰድህን መቀጠልህ ነው።

በዓይነ ሕሊናህ ተጠቀም። በዓይነ ሕሊናህ በፍጥነት “ወደፊት አጠንጥነህ” ግብህ ላይ እንደደረስክ አድርገህ አስብ። ስኬቱ የሚያስገኝልህን ደስታ አጣጥም። ከዚያም “ወደኋላ እያጠነጠንክ” እያንዳንዱን እርምጃ በሐሳብህ ቃኘው። በመጨረሻም “ተጫወት” የሚለውን ቁልፍ ተጫንና እያንዳንዱን እርምጃ እያጠናቀቅህ ግብህ ላይ ስትደርስ ምን ያህል ልትደሰት እንደምትችል በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። በል አሁን ግብህ ላይ ለመድረስ ታጥቀህ ተነሳ!

[ሥዕል]

ግቦች ከንድፍ ጋር ይመሳሰላሉ፤ ግብንም ሆነ ንድፍን እውን ለማድረግ ሥራ ይጠይቃል!

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

እኩዮችህ ምን ይላሉ?

“ትኩረት የምታደርግበት ወይም የምትጠባበቀው ነገር ከሌለ በቀላሉ ተስፋ ልትቆርጥ ትችላለህ። ይሁን እንጂ ግብ አውጥተህ ግብህ ላይ ስትደርስ ስለ ራስህ ጥሩ አመለካከት ይኖርሃል።”—ሪድ

“ግብህን ሙሉ በሙሉ አሊያም ባሰብክበት ጊዜ ማሳካት ባትችል ራስህን አትኮንን። ራስህን መኮነንህ የሚፈይደው ነገር የለም። ጥረት ማድረግህን ቀጥል!”—ኮሪ

“የአንተ ዓይነት ግብ የነበራቸውና ግባቸው ላይ የደረሱ ሰዎችን አነጋግር። ለሥራ እንድትነሳሳ ሊያደርጉህ አልፎ ተርፎም ተግባራዊ ምክር ሊሰጡህ ይችላሉ። በተጨማሪም ቤተሰቦችህ ድጋፍ እንዲሰጡህ ስላወጣሃቸው ግቦች ንገራቸው።”—ጁሊያ

[በገጽ  24 ላይ የሚገኝ ሥዕላዊ መግለጫ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ቁረጠው

እጠፈው