በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አምላክ የለሾች ዘመቻ እያካሄዱ ነው

አምላክ የለሾች ዘመቻ እያካሄዱ ነው

አምላክ የለሾች ዘመቻ እያካሄዱ ነው

ዲስ ዓይነት አምላክ የለሽነትን የሚያስፋፋ ቡድን በኅብረተሰቡ ውስጥ ብቅ ብሏል። የዚህ ቡድን አባላት አመለካከታቸውን ለራሳቸው ብቻ ይዘው ዝም አላሉም። ከዚህ ይልቅ “ሃይማኖተኛ ሰዎች የእነሱን አመለካከት እንዲቀበሉ ለማሳመን በትጋት፣ በቁጣ ስሜትና በግለት” ዘመቻ እያካሄዱ መሆኑን የአንድ ጋዜጣ አምድ አዘጋጅ የሆኑት ሪቻርድ በርንስታይን ጽፈዋል። አዲስ ዓይነት አምላክ የለሽነትን የሚያስፋፉት እነዚህ ሰዎች፣ አምላክ መኖር አለመኖሩን በእርግጠኝነት ማወቅ እንደማይቻል የሚናገሩ ግለሰቦችን አስተሳሰብ እንኳ ለማስቀየር ይጥራሉ፤ ምክንያቱም እንደነሱ አመለካከት አምላክ አለመኖሩ ምንም የሚያጠራጥር ጉዳይ አይደለም። አምላክ የሚባል ነገር የለም፤ አበቃ!

“ዓለም ለዘመናት ከዘለቀው ሃይማኖታዊ ቅዠት መንቃት ያስፈልገዋል” በማለት የኖቤል ተሸላሚ የሆኑት ስቲቨን ዋይንበርግ ተናግረዋል። “እኛ የሳይንስ ሊቃውንት፣ ሕዝቡን እንደ ማነቆ ከሆነበት የሃይማኖት ተጽዕኖ ለማላቀቅ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ አለብን፤ ይህ ለሥልጣኔ የምናበረክተው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ይሆናል።” የሃይማኖትን ተጽዕኖ ለማዳከም ከሚያገለግሉት መሣሪያዎች መካከል ጽሑፎች ይገኙበታል፤ አዲስ ዓይነት አምላክ የለሽነትን የሚያስፋፉት ሰዎች ካዘጋጇቸው መጻሕፍት አንዳንዶቹ ከፍተኛ ሽያጭ እያገኙ መሆኑ አመለካከታቸው የብዙዎችን ትኩረት እየሳበ እንዳለ የሚጠቁም ሊሆን ይችላል።

ሃይማኖትም የአዲሶቹ አምላክ የለሾች አመለካከት እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ አድርጓል፤ ምክንያቱም ዓለምን እያመሳት ያለው ሃይማኖታዊ ጽንፈኝነት፣ ሽብርተኝነትና ግጭት ብዙዎችን አንገሽግሿቸዋል። አምላክ የለሽነትን የሚያራምዱ አንድ ታዋቂ ሰው “ሃይማኖት ሁሉን ነገር ይመርዛል” በማለት ተናግረዋል። ከዚህም በላይ ‘መርዝ’ የሆነው የጽንፈኞች አመለካከት ብቻ ሳይሆን ሃይማኖታዊ እምነት በአጠቃላይ እንደሆነ ሲገለጽ ይሰማል። እነዚህ አምላክ የለሾች ዋና ዋናዎቹ ሃይማኖታዊ እምነቶች ሊጋለጡ፣ ሊወገዱ ብሎም በምክንያታዊነትና በእውነታ ላይ በተመሠረተ አስተሳሰብ ሊተኩ እንደሚገባ ይናገራሉ። ሰዎች ቅዱሳን በሚባሉ የተለያዩ መጻሕፍት ውስጥ ስለሚገኙት “ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሕይወትን የሚያበላሹ እርባና ቢስ ትምህርቶች” ምንም ሳይሸማቀቁ በግልጽ መናገር መቻል እንደሚኖርባቸው በአምላክ መኖር የማያምነው ሳም ሃሪስ ጽፏል። አክሎም አምላክ የለሽ የሆኑ ሰዎች፣ ሃይማኖተኛ ሰዎችን ላለማስከፋት ሲሉ አመለካከታቸውን ከመግለጽ ወደኋላ ማለታቸው አደገኛ እንደሆነ ተናግሯል።

አዲስ ዓይነት አምላክ የለሽነትን የሚያስፋፉት ሰዎች ሃይማኖትን ቢያንቋሽሹም ሳይንስን ግን ያወድሳሉ፤ እንዲያውም ከመካከላቸው አንዳንዶቹ፣ ሳይንስ አምላክ እንደሌለ ያረጋግጣል ብለው ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ይህ እውነት ነው? ደግሞስ ሳይንስ አምላክ እንደሌለ ማረጋገጥ ይችላል? ሃሪስ “በቂ ጊዜ ከተሰጠው በዚህ ውዝግብ ላይ አንደኛው ወገን በእርግጠኝነት ድል ማድረጉና ሌላኛው በማያሻማ ሁኔታ መረታቱ የማይቀር ነው” ብሏል።

ታዲያ በጊዜ ሂደት ትክክለኛነቱ የሚረጋገጠው የትኛው ወገን ይመስልሃል? ስለዚህ ጉዳይ ስታስብ ራስህን እንደሚከተለው እያልህ ጠይቅ፦ ‘በፈጣሪ ማመን በራሱ ጎጂ ነው? ሁሉም ሰው አምላክ የለሽ መሆኑ የተሻለ ዓለም ያስገኛል?’ ተደማጭነት ያላቸው አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንትና ፈላስፎች ስለ አምላክ የለሽነት፣ ስለ ሃይማኖትና ስለ ሳይንስ ምን እንደተናገሩ እስቲ እንመልከት።