ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
በየዓመቱ ከሚጠመዱት 95.2 ሚሊዮን ቶን የሚያክሉ የባሕር ፍጥረታት መካከል 38.5 ሚሊዮን ገደማ የሚሆኑት የማይፈለጉ ናቸው። በወርልድ ዋይልድላይፍ ፈንድ ውስጥ የሚሠሩት ካሮሊነ ሻክት የተባሉ የዓሦች ኤክስፐርት “ከምናጠምዳቸው የባሕር እንስሳት ውስጥ 40 በመቶ የሚሆኑት እንደ ቆሻሻ የሚጣሉ እስከሆነ ድረስ የዓሦቹ ቁጥር ሊያንሰራራ አይችልም” ብለዋል።—በርሊነር ሞርገንፖስት፣ ጀርመን
“ላሞች፣ በጎችና ፍየሎች የሰውን ልጅ የሥጋ ፍላጎት ለማርካት መሥዋዕት የሚደረጉ ሰለባዎች እንደሆኑ አድርገን እናስብ ይሆናል። ይሁን እንጂ . . . ለዓለም ሙቀት መጨመር ምክንያት ከሚሆኑት ጋዞች ውስጥ [በተለይ ሚቴይን] 18 በመቶ የሚሆነው የሚወጣው እንስሳት በሚያገሱበት ጊዜ ነው። ይህ ደግሞ ከሁሉም የመጓጓዣ ዓይነቶች ከሚለቀቀው የጋዝ መጠን ይበልጣል።”—ኒው ሳይንቲስት፣ ብሪታንያ
ጥንታዊ ኃይለኛ ማጣበቂያ
በኩዋዙሉ ናታል፣ ደቡብ አፍሪካ የሚሠሩ ሳይንቲስቶች በሺህ ዓመታት የሚቆጠር ዕድሜ ያለው ኃይለኛ ማጣበቂያ አግኝተዋል። ዘ ስታር የተባለ በጆሃንስበርግ የሚታተም ጋዜጣ “ማጣበቂያው ዛሬ በሕንጻ መሣሪያ መሸጫዎች ውስጥ ከሚገኙት ማጣበቂያዎች በምንም አይተናነስም” ብሏል። የጥንት አዳኞች የጦራቸውን ወይም የቀስታቸውን እጀታ ከጫፉ ጋር ለማጣበቅ በዚህ ማጣበቂያ ይጠቀሙ እንደነበር ይታመናል። ሳይንቲስቶቹ ቀይ አፈር፣ ስብ፣ የግራር ሙጫና አሸዋ ከቀላቀሉ በኋላ ከእሳት ጎን አስቀምጠው ተገቢውን ሙቀት እንዲያገኝ በማድረግ የጥንቱን ማጣበቂያ ለመሥራት ሙከራ አድርገው ነበር፤ ሳይንቲስቶቹ ማጣበቂያውን ለመሥራት ብዙ ልፋት የጠየቀባቸው መሆኑ ጥንታዊውን ማጣበቂያ ለሚጠቀሙት ሰዎች ከፍተኛ ከበሬታ እንዲኖራቸው አድርጓል።
የእንቅልፍ ማነስና ጉንፋን
በፒትስበርግ፣ ፔንስልቬንያ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው ካርንጊ ሜለን ዩኒቨርሲቲ ያወጣው አንድ ሪፖርት “ማታ ማታ ከሰባት ሰዓት በታች የሚተኙ ሰዎች በጉንፋን የመያዝ አጋጣሚያቸው በአማካይ ስምንት ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ ከሚተኙ ሰዎች ወደ ሦስት እጥፍ ገደማ ይበልጣል” ብሏል። “አልጋ ላይ ሆነው ከሚያሳልፉት ጊዜ ውስጥ 8 በመቶ የምታክለውን ጊዜ እንኳ እንቅልፍ ሳይወስዳቸው የሚቀሩ ሰዎች” ድብን ያለ እንቅልፍ ከሚወስዳቸው ሰዎች በጉንፋን የመያዝ አጋጣሚያቸው “በአምስት ተኩል እጥፍ” ይበልጣል። የዚህ ጥናት መሪ የሆኑት ሼልደን ኮኸን “እንቅልፍ በሽታን ከመከላከል አቅም ጋር ዝምድና እንዳለው የታወቀ ቢሆንም ጥቂት የእንቅልፍ መረበሽ እንኳ ሰውነትን ለጉንፋን ቫይረሶች እንደሚያጋልጥ የሚያሳይ መረጃ ሲገኝ ይህ የመጀመሪያው ነው” ብለዋል። “ሰዎች ሌሊቱን ሙሉ ለመተኛት የሚያስችላቸውን ፕሮግራም ማውጣት የሚኖርባቸው ለምን እንደሆነ ይህ ተጨማሪ ምክንያት ይሰጣል።”
የተትረፈረፈ የእርሻ መሬት
ኒው ሳይንቲስት የተሰኘው መጽሔት “ዓለማችን፣ በቁጥር እየጨመረ ለሚሄደው ሕዝብ ቀለብ የሚሆን ተጨማሪ ምግብ ለማምረት የሚያስችል በቂ ቦታ አላት” ብሏል። “ከሚታሰበው በተቃራኒ አብዛኛውን ምግብ በአፍሪካ ማምረት ይቻላል።” መጽሔቱ የኢኮኖሚያዊ ትብብርና ልማት ድርጅት እንዲሁም የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት፣ እርሻን በተመለከተ ስላወጡት ትንበያ የሚናገረውን ሪፖርት ይጠቅሳል። በዚህ ሪፖርት መሠረት በአሁኑ ጊዜ በመላው ዓለም ለእርሻ የሚውለውን መሬት ስፋት ከእጥፍ በላይ እንዲያድግ ማድረግ ይቻላል። ለእርሻ “ሊውል ከሚችለው ተጨማሪ መሬት ውስጥ ከግማሽ የሚበልጠው የሚገኘው በአፍሪካና በላቲን አሜሪካ ነው።”