የወጣቶች ጥያቄ
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ግብረ ሰዶም ምን እንደሚል እንዴት ማስረዳት እችላለሁ?
በሽልማት አሰጣጥ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ታዋቂ የሆኑ ሁለት ሴት ተዋንያን ከመድረክ ሆነው ከንፈር ለከንፈር በመሳሳም ሰላምታ ሲለዋወጡ የተሰበሰበው ሕዝብ አድናቆቱን በታላቅ ጩኸት ገለጸ! አንዳንዶች በድንጋጤ አፋቸውን ከፍተው ቀሩ፤ በኋላ ላይ ግን እነሱም ሌሎቹን በመደገፍ ደስታቸውን መግለጽ ጀመሩ። ግብረ ሰዶማውያን ይህን ሁኔታ እንደ ታላቅ ድል ይቆጥሩታል። አንዳንዶች ደግሞ ትኩረት ለመሳብ የተደረገ እንደሆነ ያስባሉ። ያም ሆነ ይህ፣ ተዋንያኑ ሲሳሳሙ የሚያሳየው ቪድዮ በተደጋጋሚ በቴሌቪዥን ዜናዎች ላይ የሚታይ ሲሆን በቀጣዮቹ ቀናት ደግሞ በኢንተርኔት ላይ ስለሚለቀቅ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሚያዩት ይጠበቃል።
ከላይ የቀረበው ምሳሌ እንደሚያሳየው ታዋቂ የሆኑ ሰዎች ግብረ ሰዶማውያን እንደሆኑ አሊያም ለሁለቱም ፆታዎች የፍቅር ስሜት እንዳላቸው የሚያሳይ ነገር በይፋ ካደረጉ በመገናኛ ብዙኃን የእነሱን ያህል ሰፊ ሽፋን የሚሰጠው ነገር የለም ማለት ይቻላል። አንዳንዶች እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ደፋር እንደሆኑ በመቁጠር አድናቆታቸውን ሲቸሯቸው ሌሎች ግን ድርጊታቸው ጸያፍ እንደሆነ በመግለጽ ያወግዟቸዋል። በሁለቱ ጽንፍ መካከል የሚገኙ አብዛኞቹ ሰዎች ደግም ግብረ ሰዶማዊነትን የሚመለከቱት አማራጭ የአኗኗር ዘይቤ እንደሆነ ብቻ አድርገው ነው። “በትምህርት ቤት ሳለሁ” ይላል የ21 ዓመቱ ዳንኤል፣ “ፍቅር የሚይዛቸው ከተቃራኒ ፆታ እንደሆነ የሚናገሩ ልጆችም እንኳ ግብረ ሰዶማዊነትን ከተቃወምክ ጭፍን ጥላቻ እንዳለብህና ለመፍረድ እንደምትቸኩል ይሰማቸዋል።” *
ሰዎች ለግብረ ሰዶማዊነት ያላቸው አመለካከት ከትውልድ ትውልድ ወይም ከአገር አገር ሊለያይ ይችላል። ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች ‘በማንኛውም የትምህርት ነፋስ ወዲያና ወዲህ አይሉም።’ (ኤፌሶን 4:14) ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መመሪያ በጥብቅ ይከተላሉ።
ታዲያ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ግብረ ሰዶማዊነት ምን ይላል? በመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር ደንብ የምትመራ ከሆነ ጭፍን ጥላቻ ያለብህ፣ በሌሎች መፍረድ የሚቀናህ፣ አልፎ ተርፎም ግብረ ሰዶማውያንን የምትጸየፍ ሰው እንደሆንክ በመቁጠር ያለ ስምህ ስም ለሚሰጡህ ሰዎች መልስ መስጠት የምትችለው እንዴት ነው? ቀጥሎ የቀረቡትን ጥያቄዎችና ልትሰጥ የምትችላቸውን መልሶች ተመልከት።
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ግብረ ሰዶማዊነት ምን ይላል?
አምላክ ከፆታ ጋር በተያያዘ ያለው ዓላማ፣ የፆታ ግንኙነት በተጋቡ ወንድና ሴት መካከል ብቻ እንዲፈጸም መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። (ዘፍጥረት 1:27, 28፤ ዘሌዋውያን 18:22፤ ምሳሌ 5:18, 19) መጽሐፍ ቅዱስ ዝሙትን ሲያወግዝ ተመሳሳይ ፆታ ባላቸውም ሆነ ተቃራኒ ፆታ ባላቸው ሰዎች መካከል የሚፈጸመውን የፆታ ብልግና ማመልከቱ ነው። *—ገላትያ 5:19-21
አንድ ሰው እንዲህ ቢልህ፦ “ስለ ግብረ ሰዶም ያለህ አመለካከት ምንድን ነው?”
እንዲህ ልትል ትችላለህ፦ “ግብረ ሰዶማውያንን አልጠላቸውም፤ ይሁን እንጂ ተግባራቸውን አልደግፍም።”
ኢያሱ 24:15) ባለህ አመለካከት አትፈር።—መዝሙር 119:46
✔ ልብ በል፦ በመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር ደንብ የምትመራ ከሆነ ይህ አንተ የመረጥከው የአኗኗር ዘይቤ ነው፤ ደግሞም መብትህ ነው። (ሰዎች የፆታ ዝንባሌያቸው ምንም ይሁን ምን፣ ክርስቲያኖች ሁሉንም ሰው በአክብሮት መያዝ አይገባቸውም?
ይህ ምንም ጥርጥር የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ “ሁሉንም ዓይነት ሰው አክብሩ” ወይም እንደ 1954 ትርጉም “ሁሉን አክብሩ” ይላል። (1 ጴጥሮስ 2:17) ስለዚህ ክርስቲያኖች ለግብረ ሰዶማውያን ጥላቻ የላቸውም። ከዚህ ይልቅ ግብረ ሰዶማውያን ለሆኑት ጨምሮ ለሁሉም ሰው ደግነት ያሳያሉ።—ማቴዎስ 7:12
አንድ ሰው እንዲህ ቢልህ፦ “ስለ ግብረ ሰዶማውያን ያለህ አመለካከት ሌሎች ለእነሱ ጭፍን ጥላቻ እንዲኖራቸው የሚያበረታታ አይመስልህም?”
እንዲህ ልትል ትችላለህ፦ “በጭራሽ። እኔ የምጠላው ግብረ ሰዶማውያን የሚፈጽሙትን ተግባር እንጂ ሰዎቹን አይደለም።”
✔ አክለህ እንዲህ ልትል ትችላለህ፦ “ለምሳሌ እኔ ሲጋራ ማጨስ አልፈልግም። እንዲያውም ገና ሳስበው ራሱ ይቀፈኛል። አንተ ግን አጫሽ እንደሆንክና ከእኔ የተለየ አመለካከት እንዳለህ አድርገን እናስብ። ባለኝ አቋም የተነሳ በእኔ ላይ ጭፍን ጥላቻ እንደማያድርብህ እርግጠኛ ነኝ፤ ተሳሳትኩ እንዴ? እኔም አንተ ባለህ አመለካከት ምክንያት በአንተ ላይ ጭፍን ጥላቻ አያድርብኝም። ስለ ግብረ ሰዶም ባለን የአመለካከት ልዩነት ረገድም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።”
ኢየሱስ ስለ መቻቻል አስተምሮ የለም እንዴ? ታዲያ ክርስቲያኖች ግብረ ሰዶምን በተመለከተ የከረረ አቋም ሊይዙ ይገባል?
ኢየሱስ ማንኛውም ዓይነት የአኗኗር ዘይቤ ተቀባይነት እንዳለው ለተከታዮቹ አላስተማረም። ከዚህ ይልቅ የመዳን መንገድ የሚከፈተው በእሱ “እንደሚያምን በተግባር ለሚያሳይ ሁሉ” እንደሆነ አስተምሯል። (ዮሐንስ 3:16) በኢየሱስ እንደምናምን በተግባር ማሳየት ሲባል አምላክ ካወጣቸው የሥነ ምግባር ደንቦች ጋር ተስማምቶ መኖር ማለት ነው፤ ይህ ደግሞ ግብረ ሰዶማዊነትን ጨምሮ መጽሐፍ ቅዱስ ከሚያወግዛቸው አንዳንድ ምግባሮች መራቅን ያጠቃልላል።—ሮም 1:26, 27
አንድ ሰው እንዲህ ቢልህ፦ “ግብረ ሰዶማውያን የፆታ ዝንባሌያቸውን መለወጥ አይችሉም፤ ይህ አብሯቸው የተወለደ ነገር ነው።”
እንዲህ ልትል ትችላለህ፦ “መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ባሕርያት ለመላቀቅ ከባድ እስኪሆኑ ድረስ ሥር ሊሰዱ እንደሚችሉ ቢናገርም ስለ ግብረ ሰዶማውያን የተፈጥሮ ሁኔታ የሚገልጸው ነገር የለም። (2 ቆሮንቶስ 10:4, 5) አንዳንዶች እንደ እነሱ ዓይነት ፆታ ላለው ሰው የፍቅር ዝንባሌ ቢኖራቸውም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖችን ከግብረ ሰዶማዊነት እንዲርቁ ያዝዛል።”
✔ ለጥቆማ ያህል፦ ሰዎች የግብረ ሰዶማዊነት ስሜት እንዲያድርባቸው ስለሚያደርገው ምክንያት በማንሳት አጉል ክርክር ውስጥ ከመግባት ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ ግብረ ሰዶም መፈጸምን እንደሚከለክል ጎላ አድርገህ ግለጽ። ነገሩን በንጽጽር ለማስረዳት ያህል እንዲህ ልትል ትችላለህ፦ “ብዙ ሰዎች የግልፍተኛነት ባሕርይ በዘር ውርስ ሊመጣ እንደሚችልና በዚህም የተነሳ አንዳንድ ሰዎች በቁጣ መገንፈል እንደሚቀናቸው ይናገራሉ። (ምሳሌ 29:22) ይህ አስተያየት እውነት ነው እንበል። ይሁንና አንተ እንደምታውቀው መጽሐፍ ቅዱስ በቁጣ መገንፈልን ያወግዛል። (መዝሙር 37:8፤ ኤፌሶን 4:31) አንዳንድ ሰዎች በቁጣ መገንፈል ስለሚቀናቸው ብቻ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርት ፍትሐዊነት የጎደለው ነው ሊባል ይችላል?”
አምላክ ለተመሳሳይ ፆታ የፍቅር ስሜት የሚያድርባቸውን ሰዎች ከግብረ ሰዶማዊነት እንዲርቁ እንዴት መንገር ይችላል? ይህ ጨካኝ አያስብለውም?
እንዲህ ያለው አመለካከት የመነጨው ሰዎች የፆታ ስሜታቸው ከተነሳሳ ግንኙነት መፈጸም አለባቸው ከሚለው የተሳሳተ አስተሳሰብ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ተገቢ ያልሆነ የፆታ ስሜት ቢቀሰቀስባቸውም ከልብ እስከፈለጉ ድረስ ለስሜታቸው ላለመሸነፍ የራሳቸውን ምርጫ ማድረግ እንደሚችሉ በማረጋገጥ አክብሯቸዋል።—ቆላስይስ 3:5
አንድ ሰው እንዲህ ቢልህ፦ “ግብረ ሰዶማዊ ባትሆንም እንኳ ስለ ግብረ ሰዶማዊነት ያለህን አመለካከት መለወጥ ይኖርብሃል።”
እንዲህ ልትል ትችላለህ፦ “እንበልና እኔ ቁማር መጫወትን አልደግፍም፤ አንተ ግን ትደግፋለህ። በሚሊዮን
የሚቆጠሩ ሰዎች ቁማር ለመጫወት ስለሚመርጡ ብቻ እኔ አመለካከቴን እንድለውጥ ብትጎተጉተኝ ምክንያታዊ ይሆናል?”✔ ይህን ልብ በል፦ አብዛኞቹ ሰዎች (ግብረ ሰዶማውያንን ጨምሮ) ለአንዳንድ ነገሮች ለምሳሌ ለማጭበርበር፣ ለፍትሕ መዛባት ወይም ለጦርነት ጥላቻ እንዲያድርባቸው የሚያደርጋቸው የሆነ ዓይነት የሥነ ምግባር ደንብ አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስም እነዚህን ነገሮች ያወግዛል፤ እንዲሁም ግብረ ሰዶማዊነትን ጨምሮ ከፆታ ጋር የተያያዙ አንዳንድ ምግባሮችን ይከለክላል።—1 ቆሮንቶስ 6:9-11
መጽሐፍ ቅዱስ ምክንያታዊነት የጎደለው ወይም ጭፍን ጥላቻን የሚያስፋፋ አይደለም። የአምላክ ቃል ለተመሳሳይ ፆታ የፍቅር ስሜት ለሚያድርባቸው ሰዎች የሚሰጠው መመሪያ ከተቃራኒ ፆታ ፍቅር ለሚይዛቸው ሰዎች ከሚሰጠው መመሪያ የተለየ አይደለም፤ ይህም “ከዝሙት ሽሹ” የሚለው ነው።—1 ቆሮንቶስ 6:18
ክርስቲያኖች ብዙኃኑ ከሚቀበለው የተለየ አመለካከት ለመያዝ ድፍረቱ አላቸው
ሐቁ እንደሚያሳየው ግን ለተቃራኒ ፆታ የፍቅር ስሜት ያላቸው በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ጋር ተስማምተው መኖር ስለሚፈልጉ ምንም ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታ ቢያጋጥማቸውም ራስን የመግዛት ባሕርይ አሳይተዋል። ከእነዚህም መካከል የማግባት አጋጣሚያቸው የመነመነ በነጠላነት የሚኖሩ በርካታ ሰዎችና በደረሰበት የአካል ጉዳት የተነሳ የፆታ ግንኙነት መፈጸም የማይችል የትዳር ጓደኛ ያላቸው ብዙ ያገቡ ሰዎች ይገኙበታል። እነዚህ ሰዎች የፆታ ስሜታቸውን ማርካት ባይችሉም በደስታ መኖር ችለዋል። የግብረ ሰዶማዊነት ዝንባሌ ያላቸው ሰዎችም ቢሆኑ በእርግጥ አምላክን ማስደሰት ከፈለጉ እንዲሁ ማድረግ ይችላሉ።—ዘዳግም 30:19
^ አን.4 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች ተቀይረዋል።
^ አን.7 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተሠራበት “ዝሙት” የሚለው ቃል የሚያመለክተው የግብረ ሥጋ ግንኙነት መፈጸምን ብቻ ሳይሆን የሌላን ሰው የፆታ ብልት እንደ ማሻሸት ወይም በአፍና በፊንጢጣ የፆታ ግንኙነት እንደ መፈጸም ያሉ ድርጊቶችን ጭምር ነው።
ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነጥቦች
-
አምላክ ሰዎች የሥነ ምግባር ሕጎችን እንዲያከብሩ የሚጠብቅባቸው ለምንድን ነው?
-
የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ሕጎች በጥብቅ መከተልህ ምን ጥቅም ያስገኝልሃል?