“እውነትም ነፃ ያወጣችኋል”!
“እውነትም ነፃ ያወጣችኋል”!
ኢየሱስ ክርስቶስ የተናገረውና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዮሐንስ 8:32 ላይ የሚገኘው ይህ ሐሳብ ምንጊዜም ቢሆን እውነት ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ከአጉል እምነቶችና አምላክን ከሚያሳዝኑ እንዲሁም እኛን ከሚጎዱ ልማዶች ነፃ ያወጣናል። የሚከተሉት ምሳሌዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ሰዎችን ከገና ጋር ተያያዥነት ካላቸው ሸክም የሚሆኑ ልማዶች እንዴት ነፃ እንዳወጣቸው ያሳያሉ።
የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ነፃ አውጥቷቸዋል!
አርጀንቲና፦ ኦስካር “ቤተሰባችን ከመጠን በላይ መብላትና መጠጣት እንዲሁም ከአቅማችን በላይ የሆኑ ስጦታዎችን መግዛት ከሚያስከትሏቸው ችግሮች ነፃ ወጥቷል” ብሏል።
ማርዮ፣ ገና በውሸት ላይ የተመሠረተ በዓል መሆኑን ሲገነዘብ ትልቅ እፎይታ እንደተሰማው ይናገራል። “አሁን በዓመቱ ውስጥ በማንኛውም ወቅት አቅሜ በፈቀደልኝ ጊዜ ለሌሎች
ስጦታ በመስጠት ለእነሱ ያለኝን አድናቆት መግለጽ ስለምችል በጣም ደስተኛ ነኝ” ብሏል።ካናዳ፦ ኤልፊ “ስጦታ መስጠትም ሆነ መቀበል ደስ ይለኛል” በማለት ጽፋለች። “ሆኖም ሰዎች ግዴታ እንደሆነ ተሰምቷቸው ስጦታ ሲሰጡኝ ደስ አይለኝም። ቤተሰባችን የገና በዓልን ማክበር ሲያቆም ትልቅ እፎይታ ተሰማኝ!”
ከኤልፊ ልጆች አንዷ የሆነችው ኡሊ እንዲህ ብላለች፦ “ወላጆቼ ገናን ማክበር ካቆሙ በኋላ በዓመቱ ውስጥ በተለያዩ ጊዜያት ያዝናኑን እንዲሁም ስጦታዎች ይሰጡን የነበረ ሲሆን እኛም በዚህ በጣም እንደሰት ነበር! አብረውን የሚማሩት ልጆች ወላጆቻችን ስጦታ የሰጡን ምንን አስመልክተው እንደሆነ ሲጠይቁን ‘ደስ ስላላቸው ነው!’ በማለት በኩራት እንመልስላቸዋለን። ያም ቢሆን ወላጆቻችን፣ በመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች መሠረት ሕይወታቸውን ለመምራት ሲሉ ለውጥ በማድረጋቸው ዘመዶቻችን ይቃወሟቸውና ጫና ያደርጉባቸው ስለነበር ሁኔታው ቀላል አልሆነላቸውም። ይሁን እንጂ ሁኔታውን በጽናት ተቋቁመውታል። ይሖዋ አምላክን እሱ በሚፈልገው መንገድ ለማምለክ ያላቸውን ቁርጠኝነት ማየቴ በእኔ ላይ በጎ ተጽዕኖ አሳድሯል።”
ሲልቭያ የገናን በዓል ማክበር ስታቆም “ትልቅ እረፍት” እንዳገኘች ገልጻለች። “በጣም ደስ አለኝ! ይሖዋ አምላክን እያስደሰትኩ እንደሆነ ማወቄ ገናን ሳከብር ይሰማኝ ከነበረው የላቀ ደስታ እንዲኖረኝ አድርጎኛል።”
ኬንያ፦ ፒተር እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ገናን አከብር በነበረበት ጊዜ ስጦታዎችን ለመግዛትና ድል ያለ ድግስ ለማዘጋጀት ስል በዕዳ እዘፈቅ ነበር። ይህን ዕዳ ለመክፈል ደግሞ ትርፍ ሰዓት ለመሥራት ስለምገደድ ከቤተሰቤ ጋር የማሳልፈው ጊዜ አይኖረኝም። ከዚህ ሁሉ ነፃ በመውጣቴ ደስታዬ ወደር የለውም!”
ካሮላይን “ለቤተሰቦቼና ለወዳጆቼ በማንኛውም ጊዜ ስጦታ የምሰጣቸው ሲሆን እነሱም እንዲሁ ያደርጋሉ” ብላለች። “እንዲህ ያለው ያልተጠበቀና ከልብ የሚሰጥ ስጦታ ትልቅ ቦታ እንዳለው ይሰማኛል።”
ጃፓን፦ ሂሮሺ እና ሪ እንዲህ ብለዋል፦ “ልጆቻችን ስጦታ እንዲሰጣቸው የመጠበቅ ወይም የሚሰጣቸውን ስጦታ አቅልለው የመመልከት ዝንባሌ አይታይባቸውም። ስጦታ ከልብ የመነጨ መሆን እንዳለበት እንደተገነዘቡ ማወቃችን ያስደስተናል።”
ኬኮ እንዲህ በማለት ታስታውሳለች፦ “ቤተሰባችን የገናን በዓል ያከብር ነበር። እኔና ባለቤቴ፣ ልጃችን እንቅልፍ እንደወሰደው ካረጋገጥን በኋላ አልጋው አጠገብ ስጦታ እናስቀምጥለት ነበር። በማግስቱም ‘ጥሩ ልጅ ስለሆንክ የገና አባት ስጦታ አምጥቶልሃል’ እንለዋለን። ስለ ገና በዓል እውነቱን ካወቅኩ በኋላ የተማርኩትን ለልጄ ስነግረው በጣም ደነገጠ፤ በነገሩ ስሜቱ በመጎዳቱ አለቀሰ። የገና በዓል የሚነገርለትን ያህል አስደሳች ነገር እንዳልሆነ የተገነዘብኩት ያን ጊዜ ነበር። ይህ በዓል በውሸት ላይ የተመሠረተ ሲሆን እኔም ይህን ውሸት ለልጄ በመናገሬ እንዳታለልሁት ተሰማኝ።”
ፊሊፒንስ፦ ዴቭ እንዲህ ይላል፦ “ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው ንጹሕ እውነት አማካኝነት ምን ያህል ደስተኞች እንድንሆን እንደረዳን በጽሑፍ መግለጽ በጣም ያስቸግራል። ቤተሰባችን ለሌሎች ስጦታ ሲሰጥ በምላሹ ስጦታ ለማግኘት አይጠብቅም። ስጦታ የምንሰጠውም ከልባችን ነው።”
ከላይ የተጠቀሱት ግለሰቦች የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ሰዎችን ነፃ እንደሚያወጣ ከግል ተሞክሯቸው ከተገነዘቡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። ከሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ነገር ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር በሚስማማ መንገድ ስንኖር የአምላክን ልብ የምናስደስት መሆኑ ነው። (ምሳሌ 27:11) ኢየሱስ ክርስቶስ “እውነተኛ አምላኪዎች አብን በመንፈስና በእውነት [ያመልኩታል]፤ . . . ምክንያቱም አብ እንዲህ ዓይነት ሰዎች እንዲያመልኩት ይፈልጋል” በማለት ተናግሯል። (ዮሐንስ 4:23) አምላክ ልብህን በሚመረምርበት ጊዜ እውነትን ለማወቅ ጉጉት እንዳለህ ይመለከታል? መልስህ አዎን እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን!
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ክርስቲያኖች ስጦታ የሚሰጡት በፍቅር ተነሳስተው ሲሆን ይህንንም ለማድረግ የተወሰነ ጊዜ አይጠብቁም