የገና በዓል ተወዳጅ እየሆነ የመጣው ለምንድን ነው?
የገና በዓል ተወዳጅ እየሆነ የመጣው ለምንድን ነው?
ገና በጉጉት የምትጠብቀው በዓል ነው? ወይስ በዓሉ እየተቃረበ ሲመጣ ጭንቅ ጭንቅ ይልሃል? በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የገና በዓል ሲቃረብ እንደሚከተሉት ያሉት ጥያቄዎች በአእምሯቸው ይመላለሳሉ፦ ‘ስጦታ የምሰጠው ለእነማን ነው? ምን ብገዛ ይሻላል? ይህን ለማድረግ አቅሜ ይፈቅድልኛል? ዕዳዬን ከፍዬ ለመጨረስ ምን ያህል ጊዜ ይወስድብኝ ይሆን?’
የገና በዓል እነዚህን ሁሉ ጭንቀቶች አስከትሎ የሚመጣ ቢሆንም በጣም ተወዳጅ በዓል መሆኑ አልቀረም። እንዲያውም ይህ በዓል ክርስቲያን ባልሆኑ አገሮች ውስጥ እንኳ ዘልቆ ገብቷል። አሁን አሁን በጃፓን አብዛኞቹ ሰዎች ገናን ያከብራሉ፤ ይህን የሚያደርጉት ግን ከሃይማኖት ጋር አያይዘውት ሳይሆን በበዓሉ ወቅት የሚኖረው ግርግር ደስ ስለሚላቸው ነው። ዘ ዎል ስትሪት ጆርናል በቻይና “በዋና ዋና ከተሞች በሚገኙ ሱቆች ውስጥ የገና አባት ፎቶ ይታያል” ይላል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ በመካከለኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ቻይናውያን፣ ገበያ ለመውጣት ብሎም ለመብላትና ለመፈንጠዝ አጋጣሚ ስለሚከፍትላቸው ገናን ማክበርን ተያይዘውታል።”
የገና በዓል በብዙ የዓለም ክፍሎች ለኢኮኖሚው እድገት ትልቅ እገዛ አድርጓል። ይህ በተለይ በቻይና በግልጽ እየታየ ነው፤ ከላይ የተጠቀሰው ጋዜጣ እንደገለጸው በአሁኑ ጊዜ ቻይና “የፕላስቲክ ዛፎችን፣ ብልጭልጭ ወረቀቶችን፣ ብልጭ ድርግም የሚሉ መብራቶችንና ሌሎች የገና ጌጣጌጦችን ወደ ሌሎች አገሮች በገፍ እየላከች ነው።”
ሙስሊሞች በሚበዙባቸው አገሮችም ቢሆን ታኅሣሥ 25 ላይ ባይሆንም እንኳ ከገና ጋር የሚመሳሰል ክብረ በዓል ይደረጋል። በአንካራ፣ ቱርክ እንዲሁም በቤሩት፣ ሊባኖስ በሚያብረቀርቁ ወረቀቶች ያጌጡ ዛፎችንና በስጦታ ወረቀት የተጠቀለሉ ዕቃዎችን በሱቆች ውስጥ ማየት የተለመደ ነገር ነው። በኢንዶኔዥያ፣ ሆቴሎችና ትላልቅ የገበያ አዳራሾች የበዓል ዝግጅት የሚያደርጉ ሲሆን ልጆች ከገና አባት ጋር ይመገባሉ ወይም ፎቶግራፍ ይነሳሉ።
“ክርስቲያን” በሆኑ አገሮችም የገና በዓል ከሃይማኖት ጋር የተያያዘ መሆኑ ቀርቶ የካናዳው ሮያል ባንክ ሌተር እንደገለጸው “በቀጥታ በልጆች ላይ ያነጣጠሩ” በርካታ ማስታወቂያዎች የሚዥጎደጎዱበት በንግድ ላይ ያተኮረ በዓል እየሆነ ነው። እርግጥ ነው፣ ዛሬም ቢሆን ለገና በዓል በሚዘጋጁ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓቶች ላይ የሚገኙ ሰዎች እንዳሉ አይካድም። ይሁንና ብዙዎች በገና በዓል ወቅት ይበልጥ ትኩረት የሚያደርጉት በመንፈሳዊ ነገሮች ላይ ሳይሆን ገበያ በመውጣትና ስጦታ በመለዋወጥ ላይ ነው። እንዲህ ያለ ለውጥ የመጣው ለምንድን ነው? ምክንያቱ ከገና በዓል አመጣጥ ጋር ተዛማጅነት ይኖረው ይሆን? የገና በዓል ምንጩ ምንድን ነው?
የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ከመመልከታችን በፊት ከገና በዓል ጋር በተያያዘ ለሚሳሉት ሥዕሎች መሠረት እንደሆኑ የሚነገርላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች እስቲ እንመርምር።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
የወንጌል ጸሐፊዎች ምን ይላሉ?
ሐዋርያው ማቴዎስ፦ “በንጉሥ ሄሮድስ ዘመን ኢየሱስ በይሁዳ በምትገኘው በቤተልሔም ከተወለደ በኋላ ኮከብ ቆጣሪዎች ከምሥራቅ አገር ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው፣ ‘የተወለደው የአይሁድ ንጉሥ የሚገኘው የት ነው? በምሥራቅ ሳለን ኮከቡን ስላየን ልንሰግድለት መጥተናል’ አሉ። ንጉሥ ሄሮድስ ይህን ሲሰማ ተደናገጠ።” ስለዚህ ሄሮድስ “የሕዝቡን የካህናት አለቆች . . . መሲሑ የት እንደሚወለድ” ጠየቃቸው። መሲሑ የሚወለደው “በቤተልሔም” እንደሆነ ሲያውቅ ኮከብ ቆጣሪዎቹን “ሄዳችሁ ሕፃኑን በደንብ ፈልጉ፤ ባገኛችሁትም ጊዜ . . . መጥታችሁ ንገሩኝ” አላቸው።
“እነሱም . . . ጉዟቸውን ቀጠሉ፤ በምሥራቅ ሳሉ ያዩት ኮከብም ሕፃኑ ባለበት ቦታ እስከቆመበት ጊዜ ድረስ ከፊት ከፊታቸው ይሄድ ነበር። . . . ወደ ቤትም ሲገቡ ሕፃኑን ከእናቱ ከማርያም ጋር አዩት።” ለኢየሱስ ስጦታ ካቀረቡ በኋላ “ወደ ሄሮድስ ተመልሰው እንዳይሄዱ በሕልም መለኮታዊ ማስጠንቀቂያ ስለተሰጣቸው በሌላ መንገድ ወደ አገራቸው ተመለሱ።”
“እነሱ ከሄዱ በኋላ የይሖዋ መልአክ ለዮሴፍ በሕልም ተገልጦ ‘ተነስ፣ ሕፃኑንና እናቱን ይዘህ ወደ ግብፅ ሽሽ . . .’ አለው። ስለዚህ ዮሴፍ ተነሳ፤ ሕፃኑንና እናቱን ይዞ በሌሊት ወደ ግብፅ ሄደ። . . . ከዚያም ሄሮድስ ኮከብ ቆጣሪዎቹ እንዳታለሉት ሲያውቅ በጣም ተናደደ፤ . . . ሰዎች ልኮ በቤተልሔምና በአካባቢዋ ሁሉ የሚገኙትን ሁለት ዓመትና ከዚያ በታች የሆኑትን ወንዶች ልጆች በሙሉ አስጨፈጨፈ።”—ማቴዎስ 2:1-16
ደቀ መዝሙሩ ሉቃስ፦ “[ዮሴፍ] በገሊላ ከምትገኘው ከናዝሬት ከተማ ተነስቶ በይሁዳ ወዳለች ቤተልሔም ተብላ ወደምትጠራ የዳዊት ከተማ ሄደ፤ ወደዚያ የሄደውም . . . ከማርያም ጋር ነበር፤ . . . በዚያም እንዳሉ . . . የበኩር ልጇ የሆነውን ወንድ ልጅም ወለደች፤ በእንግዶች ማረፊያ ቦታ ስላላገኙም ልጁን በመጠቅለያ ጠቅልላ በግርግም ውስጥ አስተኛችው።”
“በዚያው አገር፣ ሌሊት ሜዳ ላይ መንጎቻቸውን ሲጠብቁ የሚያድሩ እረኞች ነበሩ። በድንገት የይሖዋ መልአክ መጥቶ አጠገባቸው ቆመ፤ . . . በዚህ ጊዜ በታላቅ ፍርሃት ተዋጡ። መልአኩ ግን እንዲህ አላቸው፦ ‘አትፍሩ፣ እነሆ ለሰዎች ሁሉ ታላቅ ደስታ የሚያስገኝ ምሥራች እነግራችኋለሁ፤ ምክንያቱም በዛሬው ዕለት በዳዊት ከተማ አዳኝ ተወልዶላችኋል፤ እሱም ጌታ ክርስቶስ ነው።’” በዚህ ጊዜ እረኞቹ “በፍጥነትም ሄደው ማርያምንና ዮሴፍን አገኙ፤ ሕፃኑም በግርግም ተኝቶ ነበር።”—ሉቃስ 2:4-16