ሃይማኖት ለሰላም የቆመ ኃይል የሚሆንበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?
ሃይማኖት ለሰላም የቆመ ኃይል የሚሆንበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?
“ዓለምን የተሻለች ቦታ እናድርጋት። ሃይማኖትን እናስወግድ።” ይህን ሐሳብ ያቀረቡት ፍሎሪስ ቫን ደን በርግ የተባሉ የደች ፈላስፋ ሲሆኑ ሐሳቡን የተናገሩት “ሃይማኖትን የምናስወግደው እንዴት ነው? ለምንስ?” በሚል ርዕስ ታትሞ በወጣው ንግግራቸው ላይ ነበር። በተመሳሳይም በመላው ዓለም በተለያዩ የትምህርት መስኮች የተሰማሩ ጠበብት ሃይማኖትን ማጥፋት አስፈላጊ መሆኑን በመግለጽ እያበረታቱ ነው።
የኖቤል ተሸላሚና የፊዚክስ ሊቅ የሆኑት ስቲቨን ዋይንበርግም “ዓለም ለረጅም ዘመናት ሲያቃዠው ከነበረው በሃይማኖት የማመን ቅዥት መባነን ያስፈልገዋል” በማለት ተናግረዋል። ሃይማኖትን በማጥፋት በዚህ ዓለም ላይ የሚፈጸሙትን ክፉ ነገሮች በእጅጉ መቀነስ ይቻላል የሚለው አስተሳሰብ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በግልጽ እየተስተጋባ ነው። ሃይማኖትን የሚቃወሙ መጻሕፍት እንደ አሸን የፈሉ ሲሆን በሕዝብ ዘንድም ተወዳጅነትን እያተረፉ ነው።
ታዋቂ የሳይንስ ሊቃውንት፣ ለነገ ይደር የማይባል ጉዳይ ነው ብለው ስላሰቡት ሃይማኖትን የማጥፋት ጉዳይ ለመወያየት ተሰብስበው ነበር። ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ አምላክ የለሾች ለሃይማኖት ያላቸውን ጥላቻ በግልጽ በመገናኛ ብዙኃን እየተናገሩ ነው። በእርግጥ የእነዚህ ሰዎች አስተሳሰብ ትክክል ነው?
እውነተኛ ሃይማኖት ይኖር ይሆን?
ሁሉም ሃይማኖቶች ውሸት ከሆኑና አንዳንዶች እንደሚሉት አምላክ ከሌለ ሃይማኖትን ማጥፋቱ ምክንያታዊ ሊሆን ይችላል። ሆኖም አምላክ ካለስ? አምላክን በትክክል የሚወክሉ ሕዝቦችን ያቀፈ አንድ እውነተኛ ሃይማኖት ቢኖርስ?
በሃይማኖት ታሪክ ላይ የተደረገ ጥንቃቄ የተሞላበት ጥናት እንደሚጠቁመው ከሌሎቹ ሃይማኖቶች በሙሉ ለየት ብሎ የሚታይ አንድ ሃይማኖት አለ። በዛሬው ጊዜ ያሉት የዚህ ሃይማኖት ተከታዮች ቁጥር በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ በጣም ጥቂት ነው። ይህ ሃይማኖት የተመሠረተው በኢየሱስ ክርስቶስና በሐዋርያቱ ነበር። ይሁን እንጂ ሕዝበ ክርስትና ለብዙ መቶ ዘመናት ስትፈጽም የኖረችው ነገር ይህን እውነተኛ ሃይማኖት አይወክልም።
ታዲያ በሕዝበ ክርስትና እና ኢየሱስ ክርስቶስ በተመሠረተው እውነተኛ ሃይማኖት መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? በብዙ መንገድ ይለያያሉ። ከእነዚህ ልዩነቶች ውስጥ አንዱን እንመልከት።
‘የዚህ የዓለም ክፍል አይደሉም’
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ከፖለቲካ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ አንዱን ወገን ደግፈው አይቆሙም ነበር። ይህ ደግሞ ኢየሱስ ራሱ ከነበረው የገለልተኝነት አቋም ጋር የሚስማማ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ፣ ኢየሱስ ቢያንስ በሁለት አጋጣሚዎች ፖለቲካዊ መሪ እንዲሆን የቀረበለትን ግብዣ በጥብቅ እንደተቃወመ ይናገራል። (ማቴዎስ 4:8-10፤ ዮሐንስ 6:15) እንዲያውም ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ እሱ እንዳይያዝ ኃይል ለመጠቀም በሞከሩበት ጊዜ ገሥጿቸዋል።—ማቴዎስ 26:51, 52፤ ሉቃስ 22:49-51፤ ዮሐንስ 18:10, 11
ሮማዊው የይሁዳ ገዥ፣ ኢየሱስ ፖለቲካዊ ሥልጣን የሚፈልግ ሰው እንደሆነ ተነግሮት ስለነበር ስለዚህ ጉዳይ ቀጥተኛ ጥያቄ በጠየቀው ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ በማለት በግልጽ መልስ ሰጥቶታል፦ “መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም። መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል ቢሆን ኖሮ በአይሁዳውያን እጅ እንዳልወድቅ አገልጋዮቼ ይዋጉልኝ ነበር። አሁን ግን መንግሥቴ ከዚህ አይደለም።” (ዮሐንስ 18:36) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ኢየሱስ በዘመኑ በነበረው ፖለቲካዊና ወታደራዊ እንቅስቃሴ አልተካፈለም።
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም የእሱን አርዓያ ተከትለዋል። በዚህ ተከታታይ ርዕሰ ትምህርት ውስጥ የተጠቀሰው የተመራማሪዎች ቡድን ሃይማኖት በጦርነት ውስጥ የነበረውን ሚና አስመልክቶ ያካሄደው የጥናት ውጤት እንደሚከተለው በማለት ይገልጻል፦ “የጥንቶቹ ክርስቲያኖች ኃይል በመጠቀም አያምኑም ነበር። . . . አብዛኞቹ ክርስቲያኖች በጦር ሠራዊት ውስጥ ገብተው ለመዋጋት ፈቃደኞች አልነበሩም።” ኢየሱስና ሐዋርያቱ ያስተማሩት ትምህርት እንግዶችን እንዲሁም የተለየ ጎሣና ዘር ያላቸውን ሰዎች ጨምሮ ሁሉንም ዓይነት ሰው መውደድን የሚያበረታታ ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 10:34, 35፤ ያዕቆብ 3:17) እንዲህ ዓይነቱ ሃይማኖት በእርግጥም ለሰላም የቆመ ኃይል ነበር።
ውሎ አድሮ ግን የመጀመሪያው የክርስትና አስተሳሰብ ከፋፋይ ኃይሎች በሆኑት በፍልስፍና፣ በባሕል እና በብሔራዊ ስሜት ተበከለ። ቀደም ሲል የተጠቀሰው የተመራማሪዎች ቡድን ሃይማኖት በትጥቅ ትግል ውስጥ የነበረውን ሚና አስመልክቶ ያካሄደው የታሪክ ጥናት ውጤት እንደሚከተለው ይላል፦ “[ሮማዊው ንጉሠ ነገሥት] ቆስጠንጢኖስ ወደ ክርስትና መለወጡ ክርስቲያናዊው እንቅስቃሴ ወደ ወታደራዊ ኃይል እንዲለወጥ ስላደረገ ከዚያ በኋላ ክርስትና ርኅራኄ በተላበሱት የክርስቶስ ትምህርቶች መመራቱን አቁሞ ንጉሠ ነገሥቱ ፖለቲካዊና መልክዓ ምድራዊ መስፋፋትን ግብ አድርጎ በሚያራምደው ፖሊሲ መመራት ጀመረ። ንጉሠ ነገሥቱን ጨምሮ ክርስቲያኖች ጦርነትን ትክክል ለማስመሰል ሃይማኖታዊ ምክንያቶችን መፈለግ ግድ ሆነባቸው።” በዚህ መንገድ አስመሳይ ክርስትና ተወለደ።
‘የተለየ’ ቡድን
ታዲያ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የተቋቋመው ክርስትና ጠፍቷል ማለት ነው? በጭራሽ። በዛሬው ጊዜ ልዩ ትኩረት ሰጥተን ልንመለከተው የሚገባ አንድ ቡድን አለ። የይሖዋ ምሥክሮች ከሌሎቹ ሃይማኖተኛ ሰዎች በተለየ መልኩ የመጀመሪያዎቹን ክርስቲያኖች ምሳሌ ይከተላሉ። በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ካለ ከማንኛውም ሃይማኖት ጋር ግንኙነት የላቸውም። ዚ ኢንሳይክሎፒድያ ኦቭ ሪሊጅን የይሖዋ ምሥክሮች “የተለዩ” እንደሆኑ አድርጎ ገልጿቸዋል፤ የዚህን ምክንያት ሲናገር ትምህርቶቻቸው በሙሉ የተመሠረቱት “ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን ወግ ሙሉ በሙሉ በተካው በመጽሐፍ ቅዱስ” ላይ እንደሆነ ተናግሯል።
እንደ መጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮች በፖለቲካዊ ግጭቶች ውስጥ ገብተው አንዱን ወገን አይደግፉም። በዩክሬን ብሔራዊ የሳይንስ አካዳሚ የተዘጋጀ አንድ ጽሑፍ፣ የይሖዋ ምሥክሮች “የዘር፣ የብሔር፣ የሃይማኖት፣ የማኅበራዊና የኢኮኖሚያዊ ልዩነቶችን” የማስወገድ ዓላማ አንግበው እንደሚንቀሳቀሱ ተናግሯል። ጥናቱ የይሖዋ ምሥክሮች “በፀረ መንግሥት እንቅስቃሴ” ውስጥ እንደማይካፈሉ እንዲሁም “የአገራቸውን ሕግ የሚያከብሩ ዜጎች” እንደሆኑ ገልጿል።
ፖላንድ በሚገኘው ዋርሶ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚሠሩት ፕሮፌሰር ቮይቼክ ሞጀለስኪ ፓሲፊዝም ኤንድ ቪሲኒቲ በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ “በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ላይ ጦርነትን የሚቃወም ትልቅ ማኅበረሰብ አቋቁመዋል” ብለዋል። የይሖዋ ምሥክሮች የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችን አርዓያ በጥብቅ ስለሚከተሉ በክርስቶስና በሐዋርያቱ ተመሥርቶ የነበረውን ዓይነት ሃይማኖት መልሶ በማቋቋም ረገድ ተሳክቶላቸዋል ሊባል ይችላል። እንዲህ ዓይነቱ ክርስትና በእርግጥም ለሰላም የቆመ ኃይል ነው።—በሚቀጥለው ገጽ ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።
ብሩህ ተስፋ
እርግጥ ነው፣ ቅን ልቦና ያላቸው በርካታ ሃይማኖተኞች አልፎ ተርፎም ብዙ የሃይማኖት መሪዎች በራሳቸው ሃይማኖት ውስጥ የሚያዩት ግብዝነት ያስደነግጣቸዋል። በዓለም ላይ ሰላምና ስምምነትን ለማስፈን ሲሉ ተግተው የሚሠሩ በርካታ ሃይማኖተኛ ሰዎች ተገቢው እውቅና ሊቸራቸው ይገባል።
ይሁንና የሰው ልጆች በቅን ልቦና ተነሳስተው የቱንም ያህል ጥረት ቢያደርጉ የዓለምን ችግር ለማስተካከል ያላቸው አቅም ውስን ነው። በጥንት ጊዜ የኖረው ነቢዩ ኤርምያስ “የሰው ሕይወት በራሱ እጅ እንዳልሆነች፣ አካሄዱንም በራሱ አቃንቶ ሊመራ እንደማይችል ዐውቃለሁ” በማለት ጽፏል።—ኤርምያስ 10:23
ይሁን እንጂ ብሩህ ተስፋ አለ። የአምላክ ቃል፣ በምድር ላይ ሰላማዊ የሆነ አዲስ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ እንደሚቋቋም ያስተምራል። ይህ አዲስ ኅብረተሰብ እውነተኛ ወንድማማችነት ይመሠርታል። ከዚያ በኋላ የሰው ዘር በድንበር፣
በጎሣ ጥላቻ ወይም በሃይማኖታዊ አመለካከት ስለማይከፋፈል ሁሉም የሰው ልጅ በስምምነት ይኖራል። የሰውን ዘር አንድ አድርጎ የሚያስተሳስረው መሠረታዊ ነገር የይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ነው።በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ለአምላክ ክብር የማይሰጥ ሃይማኖት እንደሚጠፋ ትንቢት ይናገራል። ኢየሱስ “እርስ በርሱ የሚከፋፈል መንግሥት ሁሉ ይጠፋል፤ እንዲሁም እርስ በርሱ የሚከፋፈል ከተማ ወይም ቤት ሁሉ ጸንቶ አይቆምም” ብሏል። (ማቴዎስ 12:25) አምላክ ይህ ትንቢት በሐሰት ሃይማኖቶች ሁሉ ላይ ፍጻሜውን እንዲያገኝ ያደርጋል።
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ከረጅም ጊዜ በፊት “በሕዝቦች መካከል ይፈርዳል፤ የብዙ ሰዎችን አለመግባባት ያስወግዳል” በማለት ስለ አምላክ ትንቢት ተናግሮ ነበር። ይህ ትንቢት ሰዎች የሚያደርጉትን ነገር በተመለከተ ቀጥሎ ሲናገር “ሰይፋቸውን ቀጥቅጠው ማረሻ ጦራቸውንም ማጭድ ያደርጋሉ። ሕዝብ በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፤ ጦርነትንም ከእንግዲህ አይማሩም” ይላል። (ኢሳይያስ 2:4) ይህ ትንቢት በዛሬው ጊዜ ፍጻሜውን እያገኘ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች ተግባራዊ የሚያደርጉት እውነተኛው ሃይማኖት አሁንም እንኳ ለሰላም የቆመ ኃይል ሆኗል።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
የይሖዋ ምሥክሮች በፍቅር ተሳስረዋል
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የይሖዋ ምሥክሮች ከሌሎች የሚለዩት እንዴት ነው?
በርካታ ሰዎች፣ የይሖዋ ምሥክሮች ክርስቶስን እንከተላለን ከሚሉ ሌሎች ሃይማኖቶች በሙሉ ፈጽሞ የተለዩ መሆናቸውን ሲያውቁ በጣም ይገረማሉ። የይሖዋ ምሥክሮችን ልዩ ከሚያደርጓቸው ነገሮች መካከል ጥቂቶቹ የሚከተሉት ናቸው፦
አደረጃጀት
● የይሖዋ ምሥክሮች የቀሳውስት ቡድን የላቸውም።
● ሽማግሌዎቻቸው፣ አስተማሪዎቻቸውና ሚስዮናውያኖቻቸው ደመወዝ አይከፈላቸውም።
● የመንግሥት አዳራሽ ተብለው በሚጠሩ የመሰብሰቢያ ቦታዎቻቸው ላይ ሰዎችን አሥራት አይጠይቁም፤ እንዲሁም ሙዳየ ምፅዋት አያዞሩም።
● ለሚያከናውኗቸው ሥራዎች የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኙት ስማቸው የማይገለጽ ለጋሾች በሚሰጡት መዋጮ ነው።
● በፖለቲካ ጉዳዮች ጣልቃ አይገቡም።
● ሰላምን አጥብቀው የሚደግፉ ሲሆን በጦርነትም አይሳተፉም።
● እምነታቸውም ሆነ የሚያስተምሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በዓለም ዙሪያ አንድ ስለሆነ ዓለም አቀፋዊ አንድነት አላቸው።
● በመካከላቸው በኑሮ ደረጃ፣ በጎሣ፣ በዘር ወይም በመደብ ክፍፍል የለም።
● ከማንኛውም ሌላ ሃይማኖት ጋር ማለትም ከካቶሊክ፣ ከኦርቶዶክስ፣ ከፕሮቴስታንት ወይም ከሌሎች ሃይማኖቶች ጋር ኅብረት የላቸውም።
መሠረተ ትምህርት
● ስሙ ይሖዋ የሆነ አንድ እውነተኛ አምላክ ብቻ እንዳለ ያምናሉ።
● ኢየሱስ ክርስቶስ ሁሉን ቻይ አምላክ ነው ብለው አያምኑም፤ እንዲሁም አምላክ ሥላሴ ነው በሚለው ትምህርት አያምኑም።
● የኢየሱስን ትምህርቶች የሚከተሉ ሲሆን ኢየሱስም የአምላክ ልጅ እንደሆነ በማመን ያከብሩታል።
● ለመስቀል አምልኮታዊ ክብር አይሰጡም፤ ወይም ምስሎችን ለአምልኮ አይጠቀሙም።
● መጥፎ ሰዎች ሁሉ ከሞቱ በኋላ እሳታማ ሲኦል ውስጥ ገብተው ይቃጠላሉ በሚለው እምነት አያምኑም።
● አምላክ ታዛዥ ለሆኑ የሰው ልጆች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ፍጹም የሆነ ዘላለማዊ ሕይወት በመስጠት እንደሚባርካቸው ያምናሉ።
የይሖዋ ምሥክሮች በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኢየሱስ ሐዋርያት ተግባራዊ አድርገውት የነበረውን የክርስትና እምነት መልሰው በማቋቋም ረገድ እንደተሳካላቸው ያምናሉ።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሰርቢያዊ፣ ቦስኒያዊና ክሮኤሺያዊ