በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰዎች መናፍስታዊ ነገሮች የሚስቧቸው ለምንድን ነው?

ሰዎች መናፍስታዊ ነገሮች የሚስቧቸው ለምንድን ነው?

ሰዎች መናፍስታዊ ነገሮች የሚስቧቸው ለምንድን ነው?

የዚህ ጥያቄ መልስ በአብዛኛው የተመካው ሰዎች በሚኖሩበት አካባቢ፣ በሃይማኖታዊ እምነታቸው ወይም በአስተዳደጋቸውና በባሕላቸው ላይ ሊሆን ይችላል። አንተ በምትኖርበት አካባቢ ሰዎችን ወደ መናፍስታዊ ነገሮች የሚስባቸው ምንድን ነው? ከዚህ በታች ከተዘረዘሩት ምክንያቶች አንዱ ሊሆን ይችላል።

የማወቅ ጉጉት፦ መናፍስታዊ ነገሮች ሚስጥራዊ ናቸው፤ ሰዎች ደግሞ በተፈጥሯቸው ድብቅ ስለሆኑ ነገሮች የማወቅ ጉጉት አላቸው። ስለሆነም አንዳንዶች ‘ከመናፍስታዊ ነገሮች በስተጀርባ አንድ ስውር ኃይል ይኖር ይሆን?’ ብለው ያስባሉ። ሌሎች ደግሞ ለመናፍስታዊ ድርጊት በሚያገለግል ሰሌዳ ወይም በኮከብ ቆጠራ አማካኝነት የሚነገሩት ትንቢቶች እውነት መሆናቸውን ለማየት ሲሉ በእነዚህ ነገሮች ይጠቀሙ ይሆናል። ወይም ደግሞ ቡና ከጠጡ በኋላ ሲኒው ላይ የቀረውን አተላ በማየት ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለማወቅ ይሞክራሉ። አንዳንዶች ወደ ሙታን ሳቢ ይሄዳሉ አሊያም ከሰው በላይ የሆነ ኃይል አላቸው የሚባሉ ግለሰቦችን ያማክራሉ።

መዝናኛ፦ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ መናፍስታዊ ነገሮችንና የጥንት አረማዊ እምነቶችን መሠረት ያደረጉ --መጻሕፍት፣ ፊልሞችና የኮምፒውተር ጨዋታዎች ተበራክተዋል። ከእነዚህ መዝናኛዎች አንዳንዶቹ ዓመፅና የፆታ ብልግና በገሐድ የሚታዩባቸው ናቸው።

ስለ ወደፊቱ ጊዜ መጨነቅ፦ መጽሐፍ ቅዱስ “በመጨረሻዎቹ ቀኖች ለመቋቋም የሚያስቸግር በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን እንደሚመጣ” ተንብዮአል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) በእርግጥም የምንኖረው አስቸጋሪ በሆነ ዘመን ነው፤ በዚህም ምክንያት ብዙዎች ኮከብ ቆጣሪዎችን፣ የእጅ መዳፍ የሚያነቡ ሰዎችን፣ ጠንቋዮችን፣ ከሰው በላይ የሆነ ኃይል አላቸው የሚባሉ ግለሰቦችንና እንደነዚህ ያሉትን መናፍስታዊ ድርጊቶች የሚያከናውኑ ሰዎችን ያማክራሉ። ስለ ወደፊቱ ጊዜ ማወቅ እንደሚችል የሚናገር አንድ ሰው “ይህ ሥራ የኢኮኖሚ ውድቀት ተጽዕኖ ከማያሳድርባቸው መስኮች አንዱ ነው” ብሏል። “ብዙውን ጊዜ ሰዎች ደስተኛ ሲሆኑ ወደ እኛ አይመጡም” በማለትም ተናግሯል። ተመሳሳይ ሙያ ያላት በካናዳ የምትኖር አንዲት ሴት “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ታላላቅ የንግድ ሰዎች በግል የስልክ መስመራቸው ወይም በሞባይላቸው ደውለው ሰው እንዳይሰማቸው እየተጠነቀቁ ምክር ይጠይቁኛል” በማለት ተናግራለች። አክላም “እነዚህ ሰዎች ከሰው በላይ የሆነ ኃይል ባላቸው ግለሰቦች እምብዛም የማያምኑና እንደነዚህ ያሉ ሰዎችን ማማከር የማይፈልጉ ነበሩ” ብላለች።

በሽታ፦ በአንዳንድ አገሮች ከባድ ሕመም ያለባቸው ሰዎች በሕክምና ዶክተሮች ተስፋ ሲቆርጡ መናፍስታዊ ድርጊቶችን ወደሚፈጽሙ ባሕላዊ ፈዋሾች ዘወር ይላሉ። እዚያ ሲሄዱ ደግሞ የታመሙት መድኃኒት ወይም መተት ስለተደረገባቸው እንደሆነ ይነገራቸዋል። የታማሚው ወዳጆችና ዘመዶች ግለሰቡን ለማስፈታት ወደ ጠንቋይ የሚሄዱ ሲሆን ጠንቋዩም ከፍተኛ ገንዘብ ሊጠይቃቸው ይችላል።

ጥበቃ ለማግኘትና ገድ እንዲቀናቸው፦ በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ሰዎች ክፉ መናፍስትን ከአካባቢያቸው እንዲያርቅላቸው ሲሉ በተአምራዊ ፈውስ ከሚያምኑ አብያተ ክርስቲያናት አንድ “ነቢይ” ይቀጥራሉ። ይህ “ነቢይ” የሚያከናውነው ሥርዓት መድኃኒትና “ጸበል” መጠጣትን ያካትታል። በሌሎች አካባቢዎች ሰዎች ገድ እንዲቀናቸው ሲሉ በአዲስ ቤት፣ በቤት እንስሳት፣ በእርሻቸው፣ በሰብላቸው፣ በትዳራቸው ወይም በትምህርታቸው ሌላው ቀርቶ በመቃብር ላይ እንኳ የመናፍስት ጠሪዎችን ቡራኬ ይጠይቃሉ። አንዳንዶች ደግሞ “ቡዳ” እንዳይበላቸው ሲሉ ክታብ ያስራሉ።

ልጆችን ከአደጋ ለመጠበቅ፦ በፓፑዋ ኒው ጊኒ አንዲት እናት አራስ ልጇን ይዛ በምሽት ከቤት አትወጣም። ለምን? ክፉ መናፍስት በሕፃኑ ላዩ ጉዳት ያደርሱበታል ብላ ስለምትፈራ ነው። በኡጋንዳ የሚገኙ እናቶች፣ አንዳንድ ጊዜ ጨሌና ዶቃ በክር አድርገው በልጃቸው እግርና እጅ ላይ ያስራሉ፤ ይህን የሚያደርጉት ልጁን ከጉዳት ይጠብቀዋል ብለው ስለሚያምኑ ነው።

የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት፦ ሰር አርተር ኮናን ዶይል የተባሉት ብሪታንያዊ ደራሲ በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ልጃቸውን፣ ወንድማቸውን፣ የባለቤታቸውን ወንድምና የእህታቸውን ልጅ በሞት አጥተዋል። በከፍተኛ ሐዘን የተዋጡትና የሚያደርጉት የጠፋቸው ዶይልና ባለቤታቸው የሞተውን ልጃቸውን እንደሚያነጋግሩ በማሰብ ሙታን ሳቢዎች ዘንድ ሄዱ። ዛሬም ቢሆን በሞት የተለያቸውን ሰው ለማነጋገር ሲሉ ወደ ሙታን ሳቢ የሚሄዱ ብዙዎች ናቸው። በአንዳንድ አገሮች ባሕላዊ ሃይማኖቶችና ክርስቲያን ነን ባይ አብያተ ክርስቲያናት፣ ሰው የሚሞተው የተቆጡ መናፍስት በሚሰነዝሩት ጥቃት ምክንያት እንደሆነ ያስተምራሉ። አብያተ ክርስቲያናቱ፣ የአንድን ሰው ሞት ተከትሎ በማኅበረሰቡ ውስጥ ሌሎች ሰዎችም እንዳይሞቱ ለመከላከል በሚል ብዙ ወጪ የሚጠይቅ ሥርዓተ አምልኮ መከናወን እንዳለበት ይገልጻሉ።

ሙታንን መፍራት፦ ከሞትና ከሙታን ጋር የተያያዙ እምነቶች በሰው ልጅ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድረዋል። ስለሆነም በብዙ አገሮች ሰዎች የሞቱ ዘመዶቻቸውን ለማስደሰት ወይም ምን ያህል እንደሚወዷቸው “ለማሳየት” ሲሉ በራስ ላይ ጉዳት ማድረስን ጨምሮ ብዙ ዓይነት የአምልኮ ሥርዓቶችን ያከናውናሉ። በፓስፊክ ደሴቶች በሚኖሩ አንዳንድ ማኅበረሰቦች ውስጥ የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ ሰዎች ለበርካታ ወራት ጥቁር ለብሰው ሐዘን እንዲቀመጡ የሚገደዱ ከመሆኑም በላይ የሞተው ሰው ይወደው የነበረውን ምግብ ሳይመገቡ በአንድ ቤት ውስጥ ተዘግተው እንዲቆዩ ይደረጋሉ። እንዲህ ያለውን ባሕል የሚከተሉ ሰዎች በመንፈስ ጭንቀት ሊዋጡ፣ በረሃብ ምክንያት ሊታመሙ አልፎ ተርፎም ሊሞቱ ይችላሉ።

ሰዎች ወደ መናፍስታዊ ነገሮች እንዲሳቡ የሚያደርጓቸው ምክንያቶች በርካታ እንደሆኑ ግልጽ ነው። በመሆኑም መናፍስታዊ ድርጊቶች ምንጫቸው ምን እንደሆነ መረዳታችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! እንግዲያው ስለዚህ ጉዳይ የተሟላ ግንዛቤ ሊሰጠን የሚችለውን ብቸኛ መጽሐፍ ይኸውም መጽሐፍ ቅዱስን እንመርምር።