በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

እርግጠኛ የሆነ ተስፋና መመሪያ ምንጭ

እርግጠኛ የሆነ ተስፋና መመሪያ ምንጭ

እርግጠኛ የሆነ ተስፋና መመሪያ ምንጭ

ከአጋንንት በተለየ መልኩ ይሖዋ በጥበቡም ሆነ በኃይሉ ተወዳዳሪ የሌለው አምላክ ነው። በተጨማሪም እሱ የፍቅር ተምሳሌት ነው። (1 ዮሐንስ 4:8) የሚሰጠን ምክር ምንጊዜም ጠቃሚ ከመሆኑም ሌላ ምክሩን የሚሰጠን በነፃ ነው፤ እንዲሁም ስለ ደኅንነታችን ከልቡ ያስባል። ይህ ከሰው በላይ የሆነ ኃይል አላቸው የሚባሉ ግለሰቦችና ጠንቋዮች ከሚሰጡት ምክር ምንኛ የተለየ ነው! አምላክ እንዲህ ይላል፦ “እናንት [በመንፈሳዊ] የተጠማችሁ ሁሉ ኑ፤ እናንት ገንዘብ የሌላችሁ፣ ወደ ውሆች ኑ፤ ኑና ግዙ፤ ብሉም፤ ኑና ያለ ገንዘብ፣ ያለ ዋጋ፣ የወይን ጠጅና ወተት ግዙ። ገንዘባችሁን እንጀራ ባልሆነ ነገር ላይ ለምን ታጠፋላችሁ? በማያጠግብስ ነገር ላይ ለምን ጕልበታችሁን ትጨርሳላችሁ? ስሙ፤ እኔን ስሙኝ፤ መልካም የሆነውንም ብሉ፤ ነፍሳችሁም በጥሩ ምግብ ትደሰታለች።”—ኢሳይያስ 55:1, 2

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አፍቃሪ በሆነው ፈጣሪያችን መንፈስ መሪነት የተጻፈ በመሆኑ ተስፋ ይሰጠናል፣ መንፈሳዊ ጥበቃ ያስገኝልናል፣ የሕይወት ዓላማ እንዲኖረን ይረዳናል፤ እንዲሁም በሕይወታችን ውስጥ የምንመራበት ከሁሉ የተሻለ መመሪያ ይሰጠናል። ጥቂት ጊዜ ወስደህ የሚከተሉትን ጥያቄዎችና ከጥያቄዎቹ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እንድታስብባቸው እንጋብዝሃለን።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

እውነተኛ ውስጣዊ ሰላም ላገኝ የምችለው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል፦ “የተቤዠህ፣ የእስራኤል ቅዱስ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እኔ እግዚአብሔር አምላክህ፣ የሚበጅህ ምን እንደ ሆነ የማስተምርህ፣ መሄድ በሚገባህ መንገድ የምመራህ ነኝ። ትእዛዜን ሰምተህ ብቻ ቢሆን ኖሮ፣ ሰላምህ እንደ ወንዝ፣ ጽድቅህም እንደ ባሕር ሞገድ በሆነ ነበር።’”—ኢሳይያስ 48:17, 18

ክፋት የሚወገድበት ጊዜ ይኖር ይሆን? “ቅኖች በምድሪቱ ይቀመጣሉና፤ ነቀፋ የሌለባቸውም በእርሷ ላይ ጸንተው ይኖራሉ። ክፉዎች ግን ከምድሪቱ ይወገዳሉ፤ ታማኝነት የጐደላቸውም ከእርሷ ይነቀላሉ።” (ምሳሌ 2:21, 22) አዎን፣ ክፉ ሰዎችም ሆኑ ክፉ መላእክት እሳት የበላቸው ያህል ለዘላለም ይጠፋሉ።—ራእይ 20:10, 14

በሽታና መከራ የማይኖርበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? “እነሆ፣ የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር ነው፤ እሱም ከእነሱ ጋር ይኖራል፤ እነሱም ሕዝቦቹ ይሆናሉ። አምላክ ራሱም ከእነሱ ጋር ይሆናል። እሱም እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች [በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ ችግሮች] አልፈዋል።”—ራእይ 21:3, 4

ከአጋንንት በተለየ መልኩ አምላክ ጨርሶ አይዋሽም። እንዲያውም ‘ሊዋሽ አይችልም።’ (ቲቶ 1:2) ከዚህም በላይ የሚቀጥለው ርዕስ እንደሚያሳየው ከአምላክ የምናገኘው እውነት ነፃ የሚያወጣና ሕይወት የሚሰጥ ነው።—ዮሐንስ 8:32፤ 17:3