እጅግ አስደሳች ሕይወት አሳልፌያለሁ
እጅግ አስደሳች ሕይወት አሳልፌያለሁ
ሄረዋቲ ኖይሃርት እንደተናገረችው
በደማቅ ቀለማትና በእጅ በተሳሉ ንድፎች ያጌጠ የባቲክ ጨርቅ በማምረት በምትታወቀው ቺረቦን በምትባል የኢንዶኔዥያ ከተማ ተወለድኩ። ሚስዮናዊ ሆኜ ያሳለፍኩት ሕይወት በደቡባዊ ምሥራቅ እስያና በደቡብ ፓስፊክ አካባቢ ካሉ የተለያዩ አስደናቂ ባሕሎች ጋር ስላስተዋወቀኝ በአንዳንድ መንገዶች ሲታይ ሕይወቴ ከባቲክ ጨርቅ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። እስቲ ታሪኬን ልግለጽላችሁ።
በ1962 የአሥር ዓመት ልጅ ሳለሁ እናቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመረች። ከጊዜ በኋላ በኢንዶኔዥያ የተወለዱትና ቻይናውያን የሆኑት እናቴና አባቴ እንዲሁም እኔን ጨምሮ አምስቱ ልጆቻቸው የይሖዋ ምሥክሮች ሆኑ።
ሚስዮናውያንና ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች መንፈሳዊ ማበረታቻ ለመስጠት ጉባኤያችንን ሊጎበኙ ሲመጡ ብዙ ጊዜ በቤታችን ያርፉ ነበር። መልካም ምሳሌነታቸውና የሚያንጽ ጭውውታቸው በጎ ተጽዕኖ አሳድሮብኛል። ዕድሜዬ 19 ዓመት ሲሆን የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር ወሰንኩ። ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ በ1968 ሚስዮናዊ ሆኖ ከጀርመን ወደ ኢንዶኒዥያ የመጣውን ጆሴፍ ኖይሃርትን አገባሁ። የጫጉላ እረፍታችንን ስንጨርስ በኢንዶኔዥያ ካሉት ከ17,000 የሚበልጡ ደሴቶች ውስጥ በትልቅነቷ ሁለተኛ ወደሆነችው ወደ ሱማትራ ተዛወርን። እዚያም ጆሴፍ የይሖዋ ምሥክሮችን ጉባኤዎች እየተዘዋወረ የመጎብኘት ኃላፊነት ስለነበረው እኔም አብሬው መጓዝ ጀመርኩ።
በሱማትራ ማገልገል
ወረዳችን ወይም የምናገለግልበት ክልል ሞቃታማ ከሆነውና ሕዝብ ከሚበዛበት በምዕራባዊ ሱማትራ ከሚገኘው ከፓዳንግ ከተማ አንስቶ በስተ ሰሜን ሱማትራ ተንጣሎ እስከሚታየው ቶባ የሚባል እሳተ ገሞራ የፈጠረው ትልቅና የሚያምር ሐይቅ ድረስ ያለውን ክልል ያጠቃልል ነበር። ከጊዜ በኋላ ደግሞ በደሴቲቱ ደቡባዊ ክፍል ጭምር እንድናገለግል ተመደብን። እኛም ጥንዚዛ የሚል ቅጽል ስም ባላት አሮጌ ቮልስዋገን መኪናችን በተቆፋፈሩ መንገዶች ላይ እየተንገጫገጭን፣ በኮከናት ግንዶች የተሠሩ ያረጁ ድልድዮችን እያቋረጥንና ዋልጌ ወይም ንቅ እሳተ ገሞራ ባለባቸው ረጃጅም ተራሮች ዳር ዳሩን እየዞርን ዘወትር እንጓዝ ነበር። ኤሌክትሪክ፣ የቧንቧ ውኃ ወይም ባኞ ቤት በሌላቸው ጫካ ውስጥ በሚገኙ አነስተኛ ቤቶች ውስጥ መሬት ላይ አንጥፈን እናድር ነበር። ገላችንን የምንታጠበውም ሆነ ልብሳችንን የምናጥበው በሐይቅና በወንዝ ውስጥ ነበር። ኑሯችን ቀላል የነበረ ሲሆን ሕዝቡንም እንወደው ነበር። ሕዝቡ ሞቅ ባለ ስሜት ይቀበለንና ምግብ ያቀርብልን ነበር፤ ብዙዎቹም መጽሐፍ ቅዱስን የማወቅ ፍላጎት ነበራቸው።
ዘዳግም 6:4) ብዙ ሰዎች መጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን በደስታ ይቀበሉ የነበረ ሲሆን ፍላጎት ካሳዩት መካከል አንዳንዶቹ ከጊዜ በኋላ ጥሩ መንፈሳዊ እድገት አድርገዋል። በባታክ ቋንቋ በተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ይሖዋ የሚለው ስም ስለሚገኝ አብዛኞቹ ክርስቲያን ነን የሚሉ በቶባ ሐይቅ ዳር የሚኖሩ የባታክ ሕዝቦች የአምላክን ስም ያውቃሉ። (መዝሙር 83:18 NW) ሆኖም ስለ አምላክና ለሰው ዘር ስላለው ዓላማ ይበልጥ ግልጽ የሆነ እውቀት ማግኘት ያስፈልጋቸው ነበር። አብዛኞቹ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀብለው ቀናተኛ ወንጌላውያን ሆነዋል።
በፓዳንግ አካባቢ የሚኖሩ ሙስሊሞች የሚበዙባቸው ሚኔንክባው የሚባሉት ሕዝቦች፣ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት እንደሚያስተምሩት አምላክ ሥላሴ ሳይሆን አንድ አምላክ መሆኑን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ስናሳያቸው ይደነቁና ይደሰቱ ነበር። (በጃቫ ለሰዎች ተስፋውን መስበክ
በ1973 እኔና ጆሴፍ ከ80 ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎች በነበሩበትና የታላቋ ብሪታንያ ግማሽ በሚያህለው በጃቫ ደሴት ተመደብን። * በዚያም ለጃቫናውያን፣ ለሳንዳናውያንና የቻይና ዝርያ ላላቸው ጎሳዎች ምሥራቹን ሰብከናል።
በቻይና-ኢንዶኔዥያ ባሕል ውስጥ ያደግሁ እንደመሆኔ መጠን ጃቫኔን፣ ሳንዳኔን፣ ኢንዶኔዥያንና እንግሊዝኛን ጨምሮ በርካታ ቋንቋዎችን እናገር ነበር። በዚህም ምክንያት ከበርካታ ሰዎች ጋር በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው አስደሳች የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ውይይቶችን ማድረግ ችያለሁ።
በጃቫ በምትገኘው የኢንዶኔዥያ ዋና ከተማ በጃካርታ አንዲት የተከፋች የምትመስል የ19 ዓመት ወጣት ያገኘሁ ሲሆን ለእሷም ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ እንዳለ ነገርኳት። ልጅቷ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጥቅስ ሳነብላት እንባዋ መፍሰስ ጀመረ። የፍቅርና የአክብሮት አጠራር በመጠቀም “አክስቴ፣ ይህን ነገር ስለነገርሽኝ አመሰግንሻለሁ” አለችኝ። አክላም እንዲህ አለች፦ “ነገ ለዩኒቨርሲቲ ተጨማሪ 1.5 ሚሊዮን ሩፒ [160 የአሜሪካ ዶላር] መክፈል ይኖርብኛል፤ ይህን ገንዘብ ለማግኘት ስል ድንግልናዬን ለመሸጥ እያሰብኩ ነበር። አንቺን ከማግኘቴ በፊት መመሪያ ለማግኘት ወደ አምላክ እየጸለይኩ ነበር። አሁን መልሱን አግኝቻለሁ። ትምህርቴን ለሌላ ጊዜ ለማስተላለፍና የሥነ ምግባር ንጽሕናዬን ጠብቄ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ አድርጌያለሁ።” ይህች ወጣት ተጨማሪ መንፈሳዊ እርዳታ ለማግኘት ፈቃደኛ ነበረች።
ከዚያን ጊዜ ወዲህ ሳንዳናውያንንና ቻይናውያንን ጨምሮ በርካታ ጃቫናውያን በሕይወታቸው ውስጥ ለውጥ አድርገው በአምላክ ቃል ውስጥ የተገለጹትን ጠቃሚ መመሪያዎች መከተል ጀምረዋል። ይህ ደግሞ አምላክ በገባው ቃል መሠረት እውነተኛ የሆነ ውስጣዊ ሰላምና ደስታ አስገኝቶላቸዋል።—ኢሳይያስ 48:17, 18
ካለማንታን—የዴያክ ሕዝቦች መኖሪያ
እኔና ጆሴፍ ከጃቫ ተዛውረን ከግሪንላንድና ከኒው ጊኒ ቀጥሎ በዓለም ሦስተኛ ትልቅ ደሴት ወደሆነችው ቦርኔዮ ወደምትባለው
የኢንዶኔዥያ ግዛት ሄድን። ጥቅጥቅ ያሉ ደኖች፣ አቀበትና ቁልቁለት የበዛባቸው ተራሮችና የታላላቅ ወንዞች ባለቤት የሆነችው ቦርኔዮ የቻይናውያን፣ የማሌይ ሙስሊሞችና በአብዛኛው በወንዝ ዳር የሚኖሩ የአገሬው ተወላጅ የሆኑት የዴያክ ሕዝቦች መኖሪያ ናት፤ እነዚህ ሕዝቦች በጭካኔ አንገት እየቀሉ የራስ ቅል የማከማቸት ባሕል ነበራቸው።ርቀው ወደሚኖሩት የዴያክ ማኅበረሰቦች ለመድረስ ምንም ባልተነኩ ጥቅጥቅ ባሉ ደኖች ውስጥ አቆራርጠው በሚያልፉ ወንዞች ላይ በጀልባ ወይም በታንኳ እንጓዝ ነበር። በመንገዳችን ላይ ግዙፍ የሆኑ ዓዞዎች በወንዝ ዳርቻዎች ላይ ተሰጥተው ፀሐይ ሲሞቁ፣ ዝንጀሮዎች ዛፍ ላይ ሆነው ቁልቁል ሲመለከቱ በቀለማት ያሸበረቁ ወፎች ከወዲያ ወዲህ ብር ብር ሲሉ ማየት የተለመደ ነበር። አዎን፣ በዚያ አካባቢ ሚስዮናዊ ሆኖ ማገልገል ከፍተኛ ድፍረት የሚጠይቅ ነበር!
አብዛኞቹ የዳያክ ቤተሰቦች ከደን ውስጥ የተገኙ ቁሳቁሶችን በመጠቀም እንደ ቆጥ በተሠሩ ቤቶች ውስጥ ይኖሩ ነበር። አንዳንዶቹ ቤቶች ትንንሾች ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ በርካታ ቤተሰቦችን መያዝ የሚችሉ ሰቀላ ቤቶች ነበሩ። ብዙ ሰዎች አውሮፓዊ አይተው ስለማያውቁ ጆሴፍን ለማየት ይፈልጉ ነበር። ልጆች በመንደሮች ውስጥ እየሮጡ “ፓስተር! ፓስተር!” እያሉ ይጮሁ ነበር። በዚያን ጊዜ ብዙ ሰዎች ነጩ አገልጋይ የሚናገረውን ለመስማት ይጎርፉ ነበር። ጆሴፍ የሚናገረውን ሐሳብ የአካባቢው ተወላጅ የሆኑ ወንድሞች የሚያስተረጉሙለት ሲሆን ፍላጎት ላሳዩ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመምራት ዝግጅት ይደረግ ነበር።
ፓፑዋ ኒው ጊኒ ተመደብን
ሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎች የሚያደርሱት ጫና እየጨመረ በመሄዱ የኢንዶኔዥያ መንግሥት ታኅሣሥ 1976 በይሖዋ ምሥክሮች ሥራ ላይ እገዳ ጣለ። በዚህም የተነሳ እኔና ጆሴፍ ፓፑዋ ኒው ጊኒ ተመደብን።
የደሴቲቱ ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ፖርት ሞረዝቢ ከደረስን በኋላ ሂሪ ሞቱ የሚባለውን የመገበያያ ቋንቋ ለመማር የሁለት ወር ኮርስ ወሰድን። ከዚያም በምዕራባዊው የአገሪቱ ክፍል ርቃ ወደምትገኘው ዳሩ ወደምትባል አንዲት ትንሽ ደሴት ተዛወርን። እዚያም ዩነስ ከምትባል አንዲት ግዙፍ፣ ጠንካራና ደስ የምትል ሴት ጋር ተዋወቅን፤ ይህች ሴት ለረጅም ዓመታት ቢተል ነት በማኘኳ የተነሳ ጥርሷ በልዟል። ዩነስ አምላክ አገልጋዮቹ በአካላዊ፣ በሥነ ምግባራዊና በመንፈሳዊ ንጹሕ እንዲሆኑ እንደሚፈልግ ስትማር ሱሷን አሸንፋ ታማኝ ክርስቲያን ሆነች። (2 ቆሮንቶስ 7:1) እንዲህ ያሉ ትሑት ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በሥራ ላይ ሲያውሉ ስናይ “ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቅመሱ፣ እዩም” ለሚሉት የመዝሙር 34:8 [NW] ቃላት ያለን አድናቆት ይበልጥ እየጨመረ መጣ።
ከጊዜ በኋላ ጆሴፍ እንደገና ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኖ መሥራት የጀመረ ሲሆን 820 ቋንቋዎች በሚነገሩባት በፓፑዋ ኒው ጊኒ ተዘዋውረን ያልጎበኘንበት ቦታ የለም ማለት ይቻላል። ከብዙ ሰዎች ጋር መነጋገር እንድንችል ቶክ ፒሰን የሚባለውን የአካባቢውን የጋራ መግባቢያ ቋንቋ ተማርን። ወደተለያዩ ከተሞችና መንደሮች ለመሄድ በእግር፣ በመኪና፣ በጀልባና በአነስተኛ አውሮፕላኖች እንጓዝ የነበረ ከመሆኑም ሌላ የሚያስጨንቀውን ሙቀት፣ ትንኞችንና ዘወትር የሚያገረሽብንን የወባ በሽታ መቋቋም ነበረብን።
ከዚያም በ1985 ከፓፑዋ ኒው ጊኒ ተቀይረን በስተ ምሥራቅ ወደሚገኙት ወደ ሰለሞን ደሴቶች ሄድን። እዚያም በይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ የሠራን ከመሆኑም በላይ ጉባኤዎችን ለማበረታታትና በትልልቅ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት ወደ ሁሉም አጎራባች ደሴቶች ተጉዘናል። አሁንም እንደገና አንድ አዲስ ቋንቋ ይኸውም በሰለሞን ደሴቶች የሚነገረውን የጋራ መግባቢያ ቋንቋ የመማርን አስቸጋሪ መሰናክል መወጣት ነበረብን። ይሁን እንጂ ለመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅር ካላቸው የሰለሞን ደሴቶች ነዋሪዎች ጋር መግባባት መቻል በጣም የሚያስደስት ነበር!
እጅግ አስቸጋሪ የነበረው ጉዞ
በ2001 በኢንዶኔዥያ ባሉ የይሖዋ ምሥክሮች ላይ የተጣለው እገዳ ሲነሳ እኔና ጆሴፍ ወደ ጃካርታ ተመለስን። ከዚያ በኋላ ብዙም ሳይቆይ ውድ ባለቤቴ በጣም አደገኛ የቆዳ ካንሰር እንዳለበት በምርመራ ተረጋገጠ። ለሕክምና የጆሴፍ የትውልድ አገር ወደሆነችው ወደ ጀርመን ተጓዝን። የሚያሳዝነው ነገር፣ ጆሴፍ በ2005 በ33ኛው የጋብቻ መታሰቢያ ቀናችን ላይ በሞት አንቀላፋ፤ በቅርቡ ትንሣኤ አግኝቶ ገነት በምትሆነው አዲስ ዓለም ውስጥ እንደሚኖር ተስፋ አደርጋለሁ። (ዮሐንስ 11:11-14) ጆሴፍ በሞተበት ወቅት ዕድሜው 62 ዓመት የነበረ ሲሆን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት 40 ዓመታት አሳልፏል።
እኔም ወደ ጃካርታ ተመልሼ ሚስዮናዊ ሆኜ ማገልገሌን ቀጥያለሁ። ባለቤቴ በጣም ይናፍቀኛል። ይሁን እንጂ አገልግሎት ጥልቅ እርካታ ስለሚያስገኝልኝ እንዲሁም ሕይወቴ ዓላማ እንዲኖረው ስለሚያደርግ በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ውድ እውነት ለሌሎች ማስተማሬ ናፍቆቱን እንድቋቋም ረድቶኛል። አዎን፣ ይሖዋ እጅግ ያማረና አስደሳች ሕይወት እንድመራ ረድቶኛል ብዬ ያለጥርጥር መናገር እችላለሁ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.10 በዛሬው ጊዜ የጃቫ ሕዝብ ብዛት ከ120 ሚሊዮን ይበልጣል።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ኢንዶኔዥያ
ጃቫ
ጃካርታ
ቺረቦን
ሱማትራ
ፓዳንግ
ቶባ ሐይቅ
ቦርኔዮ
ፓፑዋ ኒው ጊኒ
ፖርት ሞረዝቢ
ዳሩ
ሰለሞን ደሴቶች
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሄረዋቲ በሰለሞን ደሴቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቿ ጋር
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሆላንድ ውስጥ ከጆሴፍ ጋር፤ በ2005 ከመሞቱ ጥቂት ቀደም ብሎ