ከመናፍስታዊ ነገሮች በስተጀርባ ያለው ኃይል ማነው?
ከመናፍስታዊ ነገሮች በስተጀርባ ያለው ኃይል ማነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፈጣሪያችን ሲናገር “አምላክ ብርሃን ነው፤ በእሱ ዘንድም ፈጽሞ ጨለማ የለም” ይላል። (1 ዮሐንስ 1:5) ይህ በተለይ በመንፈሳዊ ሁኔታ እውነት ነው። ታዲያ ከመናፍስታዊ ነገሮች በስተጀርባ ያለው ኃይል እውነተኛው አምላክ ሊሆን ይችላል? ወይስ ሌላ ክፉ ኃይል ይኖራል?
ከመናፍስታዊ ድርጊቶች መካከል ሟርት፣ ጥንቆላ፣ ኮከብ ቆጠራ፣ ዐውደ ነገሥት መግለጥ፣ የእጅ መዳፍ ማንበብ፣ መተት፣ አስማት እንዲሁም “ከሙታን” ጋር መነጋገርና ድግምት በዋነኝነት ይጠቀሳሉ። እነዚህ ድርጊቶች የረጅም ዘመን ታሪክ ያላቸው ሲሆኑ አብዛኞቹ የመነጩት ዛሬ ፍርስራሿ በኢራቅ ከሚገኘው ከጥንቷ ባቢሎን ነው። (ኢሳይያስ 47:1, 12, 13) መናፍስታዊ ነገሮች ከባቢሎን ተነስተው በጥንቱ ዓለም በሙሉ የተሠራጩ ሲሆን በበርካታ ባሕሎችና ማኅበረሰቦች ውስጥ ሥር ሰደዋል።
በጥንቷ መቄዶንያ ትገኝ በነበረችው በፊልጵስዩስ ከተማ የተፈጸመውን ሁኔታ እንመልከት። በዚያች ከተማ ሐዋርያው ጳውሎስንና ሐኪሙን ሉቃስን ጨምሮ የተወሰኑ ክርስቲያኖች መናፍስታዊ ኃይል ካላት አንዲት ሴት ጋር ተገናኙ። የዚህች ሴት ኃይል ከየት የተገኘ እንደሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የሆነው ሉቃስ እንዴት እንደገለጸው ልብ በል። እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “የጥንቆላ ጋኔን የሐዋርያት ሥራ 16:16-18
ያደረባት አንዲት አገልጋይ አገኘችን። እሷም በጥንቆላ ሥራዋ ለጌቶቿ ከፍተኛ ገቢ ታስገኝላቸው ነበር።”—አዎን፣ የዚህች ሴት ኃይል ምንጭ እውነተኛው አምላክ ይሖዋ ሳይሆን ጋኔን ማለትም ክፉ መንፈስ ነበር። ስለሆነም ጳውሎስና ባልደረቦቹ ይህችን ሴት ሊሰሟት አልፈለጉም። ታዲያ ‘አጋንንት እነማን ናቸው? የመጡትስ ከየት ነው?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። አሁንም መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መልስ ልብ በል።
አጋንንት እነማን ናቸው?
ይሖዋ የሰው ልጆችን ከመፍጠሩ ከረጅም ጊዜ በፊት የማሰብ ችሎታ ያላቸውን መንፈሳዊ ፍጡራን ማለትም ‘መላእክትን’ በሰማይ ፈጥሮ ነበር። (ኢዮብ 38:4, 7) እጅግ ብዙ የሆኑት እነዚህ መንፈሳዊ ፍጡራን እንደ ሰው ልጆች ነፃ ምርጫ ያላቸው ሲሆኑ ለረጅም ጊዜ ያህል ሁሉም ለአምላክ ታማኝ ነበሩ። ይሁን እንጂ ይህን የመሰለውን አስደሳች ሁኔታ በድንገት የሚያደፈርስ ነገር ተፈጠረ። እንዴት?
አምላክ የሰው ልጆችን ከፈጠረ በኋላ አንድ መንፈሳዊ ፍጡር የማይገባውን ነገር ይኸውም አምልኮ ለማግኘት መመኘት ጀመረ። ይህ ክፉ መልአክ አንድ እባብ የተናገረ አስመስሎ የመጀመሪያዋ ሴት የነበረችውን ሔዋንን በማሳሳት የፈጣሪዋን ትእዛዝ እንድትጥስ አደረገ። (ዘፍጥረት 3:1-6) መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ዓመፀኛ መልአክ “ዲያብሎስና ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው የመጀመሪያው እባብ” ይለዋል። (ራእይ 12:9) ኢየሱስም “ነፍሰ ገዳይ” ብሎ የጠራው ሲሆን አክሎም “በእውነት ውስጥ ጸንቶ አልቆመም። ውሸታምና የውሸት አባት ስለሆነ ውሸት ሲናገር ከራሱ አመንጭቶ ይናገራል” ብሏል።—ዮሐንስ 8:44
ከጊዜ በኋላ ሌሎች መንፈሳዊ “የእግዚአብሔር ወንዶች ልጆች” ከሰይጣን ጋር በዓመፁ ተባበሩ። (ዘፍጥረት 6:1, 2) እነዚህ የአምላክ ልጆች ‘ኃጢአት የሠሩት መላእክት’ እንዲሁም ‘መጀመሪያ የነበራቸውን ቦታ ያልጠበቁትና ትክክለኛ መኖሪያቸውን [በሰማይ የነበራቸውን ቦታ] የተዉት መላእክት’ ተብለዋል። (2 ጴጥሮስ 2:4፤ ይሁዳ 6) በኋላም እነዚህ መላእክት አጋንንት ተብለው ተጠሩ። (ያዕቆብ 2:19) አጋንንት በጥንት ጊዜ ብዙ እስራኤላውያን ከእውነተኛው አምልኮ እንዲርቁ እንዳደረጉ ሁሉ ዛሬም የተቻላቸውን ያህል ብዙ ሰዎችን ከአምላክ ለማራቅ ቆርጠው ተነስተዋል። (ዘዳግም 32:16, 17) ዛሬም እንደ ጥንቱ ሰይጣንና አጋንንቱ ሰዎችን ለማሳት በሃይማኖታዊ ውሸት ይጠቀማሉ።—2 ቆሮንቶስ 11:14, 15
ራስህን ጠብቅ!
ክፉ መናፍስት ከሰው የበለጠ ኃይል ያላቸው ይሁኑ እንጂ በአምላክ እርዳታ ‘ልንቃወማቸውና’ ልናሸንፋቸው እንችላለን። (1 ጴጥሮስ 5:9) ይሁን እንጂ የአምላክን እርዳታ ለማግኘት እሱ የሚፈልግብንን ነገሮች ማወቅና ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። ሐዋርያው ጳውሎስ በዘመኑ ስለነበሩት ክርስቲያኖች ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፦ “ከጥበብና ከመንፈሳዊ ግንዛቤ ሁሉ ጋር በፈቃዱ ትክክለኛ እውቀት ትሞሉ ዘንድ ስለ እናንተ መጸለያችንንና መለመናችንን አላቋረጥንም፤ ይህም . . . ይሖዋን ሙሉ በሙሉ በማስደሰት ለእሱ በሚገባ ሁኔታ እንድትመላለሱ [ነው]።”—ቆላስይስ 1:9, 10
እንዲህ ያለውን “ትክክለኛ እውቀት” ካገኙት ሰዎች መካከል የአስማት ሥራዎችን ይሠሩ የነበሩ በኤፌሶን ከተማ የሚኖሩ በርካታ ሰዎች ይገኙ ነበር። እውነቱን ማወቃቸው ምን እርምጃ እንዲወስዱ እንዳነሳሳቸው ልብ በል። መጽሐፍ ቅዱስ “አስማት ይሠሩ ከነበሩት መካከል ብዙዎች መጽሐፎቻቸውን አንድ ላይ ሰብስበው በማምጣት በሁሉ ሰው ፊት አቃጠሉ” ይላል። የሚገርመው ነገር የሐዋርያት ሥራ 19:17-19) ድፍረት ስለሚጠይቀው ስለዚህ እርምጃ የሚገልጸው ዘገባ ተመዝግቦ የቆየው ለእኛ ጥቅም ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:16
የመጽሐፎቹ ዋጋ “ሃምሳ ሺህ የብር ሳንቲሞች” ሲሆን ይህም ትንሽ የሚባል ገንዘብ አልነበረም! (ከጉዳት የሚጠብቁን መመሪያዎች
ራሳችንን ከአጋንንት ለመጠበቅ ልናደርጋቸው የሚገቡ ሌሎች ነገሮችም አሉ። የሚከተሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ልብ በል።
“በመንፈስ የተነገረን ቃል ሁሉ አትመኑ፤ ከዚህ ይልቅ በመንፈስ የተነገሩት ቃላት ከአምላክ የመነጩ መሆን አለመሆናቸውን መርምሩ።” (1 ዮሐንስ 4:1) ኮከብ ቆጣሪዎች፣ ከሰው በላይ የሆነ ኃይል አላቸው የሚባሉ ግለሰቦች፣ መናፍስት ጠሪዎችና ጠንቋዮች ከሚናገሯቸው ነገሮች አንዳንዶቹ እውነት ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ በፊልጵስዩስ የነበረችው ጋኔን ያደረባት ሴት “የመዳንን መንገድ የሚነግሯችሁ እነዚህ ሰዎች የልዑሉ አምላክ ባሪያዎች ናቸው” በማለት ስለ ጳውሎስና ስለ ባልደረቦቹ የተናገረችው እውነት ነበር። (የሐዋርያት ሥራ 16:17) ይሁን እንጂ ጳውሎስና ባልደረቦቹ ከእነሱ ጋር እንድትሆን አልፈቀዱላትም። ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ ክፉውን መንፈስ ከእሷ እንዲወጣ አዝዞታል። ሃይማኖታዊ ትምህርቶችን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በማወዳደር ትክክለኛነታቸውን መርምር።—የሐዋርያት ሥራ 17:11
“ራሳችሁን ለአምላክ አስገዙ፤ ዲያብሎስን ግን ተቃወሙት፤ እሱም ከእናንተ ይሸሻል።” (ያዕቆብ 4:7) አጋንንት የአምላክም ሆነ የአንተ ጠላቶች ናቸው። ሚስጥራዊ ስለሆኑት ሥራዎቻቸው የማወቅ ጉጉት እንኳ አይደርብህ። ከዚህ ይልቅ ፍቅር የሚንጸባረቅባቸውን የአምላክ ትእዛዛት በመፈጸም ራስህን ለእሱ አስገዛ፤ የአምላክ ትእዛዛት ደግሞ ከባዶች አይደሉም። (1 ዮሐንስ 5:3) ለምሳሌ አምላክ ለጥንቱ የእስራኤል ብሔር እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ሟርተኛ፣ ወይም መተተኛ፣ ሞራ ገ[ላ]ጭ፣ ጠንቋይ ወይም በድግምት የሚጠነቍል፤ መናፍስት ጠሪ ወይም ሙት አነጋጋሪ በመካከልህ ከቶ አይገኝ። እነዚህን የሚያደርግ ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ አስጸያፊ ነውና።” (ዘዳግም 18:10-12) የአምላክ አመለካከት ዛሬም አልተለወጠም።—ገላትያ 5:19, 20
“[በይሖዋ አገልጋዮች]ላይ የሚሠራ አስማት አይኖርም።” (ዘኍልቍ 23:23) አምላክን ለማስደሰት የሚፈልጉ ሁሉ አጋንንትን መፍራት አያስፈልጋቸውም። በእርግጥም እነዚህ ክፉ መናፍስት አምላክ ታላቅ ኃይል እንዳለው ስለሚያውቁ በእሱ ፊት “ይንቀጠቀጣሉ”፤ ወደፊት አምላክ ይህን ኃይሉን እነሱን ለማጥፋት ይጠቀምበታል። (ያዕቆብ 2:19) አምላክ “በፍጹም ልባቸው የሚታመኑበትን [ያበረታል]”፤ እንዲሁም “የጻድቁንም መናወጥ ከቶ አይፈቅድም።”—2 ዜና መዋዕል 16:9፤ መዝሙር 55:22
“ሕያዋን እንደሚሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን ምንም አያውቁም።” (መክብብ 9:5) የአምላክ ቃል ሙታን በድን እንደሆኑ ያስተምራል። በማንም ላይ ጉዳት ሊያደርሱ ስለማይችሉ ልንፈራቸው አይገባም። (ኢሳይያስ 26:14) አጋንንት ሰዎችን ለማሳት ሲሉ የሞቱ ሰዎች መንፈስ እንደሆኑ መስለው ይቀርባሉ፤ አንዳንድ ጊዜ ሰዎች፣ በሕይወት እያለ ደግ የነበረው ሰው ከሞተ በኋላ “መንፈሱ” ሲያናግራቸው ባሕርይው ድሮ ከሚያውቁት የተለየ እንደሆነ የሚሰማቸው በዚህ ምክንያት ሊሆን ይችላል።
“‘ከይሖዋ ማዕድ’ እና ከአጋንንት ማዕድ መካፈል አትችሉም።” (1 ቆሮንቶስ 10:21, 22) ይሖዋን በእውነት የሚወዱ ሁሉ በመናፍስታዊ ነገሮች ላይ ተመሥርተው ከሚዘጋጁ ወይም መናፍስታዊ ተግባራትንና እምነቶችን ከሚያስፋፉ መጻሕፍት፣ ፊልሞችና የኮምፒውተር ጨዋታዎች ይርቃሉ። * መዝሙር 101:3 “በዐይኔ ፊት፣ ክፉ ነገር አላኖርም” ይላል። አብዛኛውን ጊዜ ከመናፍስታዊ ነገሮች ጋር የተያያዙ መዝናኛዎች ‘እግዚአብሔርን የሚወዱ’ ሰዎች ሊጠሏቸው የሚገቡትን ዓመፅንና ብልግናን እንደ ጥሩ ነገር አድርገው ያቀርባሉ።—መዝሙር 97:10
አጋንንት ምንጊዜም እውነተኛ ማንነታቸውን ከሰው ልጆች ሲሸሽጉ ኖረዋል። ይሁን እንጂ ሙሉ በሙሉ አልተሳካላቸውም። ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት የአጋንንትን እውነተኛ ማንነት ይኸውም በክፋት ተነሳስተው ውሸት እንደሚናገሩና የሰው ልጅ ጨካኝ ጠላቶች እንደሆኑ አጋልጧል። ከፈጣሪያችን ከይሖዋ አምላክ ምንኛ የተለዩ ናቸው! ቀጣዩ ርዕስ እንደሚያሳየው ይሖዋ ይወደናል፣ ሁልጊዜም እውነቱን ይነግረናል እንዲሁም ለዘላለም በደስታ እንድንኖር ይፈልጋል።—ዮሐንስ 3:16፤ 17:17
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.19 የሰዎች ሕሊና እንደ ሃይማኖታቸውና እንደ መንፈሳዊ ጉልምስናቸው ይለያያል። ትልቅ ቦታ ሊሰጠው የሚገባው ነገር በአምላክ ፊት ንጹሕ ሕሊና ይዞ መገኘት እንዲሁም የቤተሰብ አባላትን ጨምሮ የሌሎችን ሕሊና የሚጎዳ ነገር አለማድረግ ነው። ሮም 14:10, 12 “ሁላችንም በአምላክ የፍርድ ወንበር ፊት እንቆማለን” ይላል።