1ኛው ቁልፍ—ጥሩ አመጋገብ ይኑርህ
1ኛው ቁልፍ—ጥሩ አመጋገብ ይኑርህ
“ምግብ ብሉ። ብዙ አትብሉ። በአብዛኛው አትክልት ብሉ።” አመጋገብን በተመለከተ ይህን ቀላልና ዘመን የማይሽረው ምክር የሰጡት ደራሲው ማይክል ፖለን ናቸው። ይህን ሲሉ ምን ማለታቸው ነው?
◯ ትኩስ ምግቦችን ተመገብ። በፋብሪካ ከተዘጋጀ ምግብ ይልቅ “እውነተኛ” ማለትም ሰዎች በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ሲመገቧቸው የኖሩትን ያልተፈተጉና ትኩስ ምግቦችን ተመገብ። ለትርፍ ተብለው የሚሠሩ የታሸጉ ምግቦችና በየጎዳናው በፍጥነት የሚዘጋጁ ምግቦች ብዙውን ጊዜ ስኳር፣ ጨውና ቅባት ይበዛባቸዋል፤ እነዚህ ደግሞ አብዛኛውን ጊዜ ለልብ ሕመም፣ በጭንቅላት ውስጥ ደም ለመፍሰስ፣ ለካንሰርና ለሌሎች ከባድ በሽታዎች ሊያጋልጡ ይችላሉ። ምግብ ስታዘጋጅ ከመጥበስ ይልቅ እንደ መጋገር፣ መቀቀልና በእሳት መለብለብ ያሉ ብዙ ቅባት የማይጠይቁ ዘዴዎችን ተጠቀም። የምትጨምረውን የጨው መጠን ለመቀነስ ቅጠላ ቅጠሎችንና ቅመሞችን ለመጠቀም ሞክር። የምትመገበው ሥጋ በደንብ መብሰሉን አረጋግጥ፤ እንዲሁም የተበላሸ ምግብ ፈጽሞ አትመገብ።
◯ ብዙ አትብላ። የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት እንዳደረገው በመላው ዓለም ከመጠን በላይ የወፈሩ ሰዎች ቁጥር በጣም እየጨመረ ነው፤ ብዙውን ጊዜ ለዚህ አደገኛ ሁኔታ መንስኤው ብዙ መብላት ነው። አንድ ጥናት እንዳረጋገጠው አፍሪካ ውስጥ በአንዳንድ አካባቢዎች “በምግብ እጥረት ከሚሠቃዩት ልጆች ይልቅ ከመጠን በላይ የወፈሩ ልጆች ቁጥር ይበዛል።” በጣም ወፍራም የሆኑ ልጆች አሁንም ሆነ ወደፊት የስኳር በሽታን ጨምሮ ለሌሎች የጤና ችግሮች የመጋለጣቸው አጋጣሚ ሰፊ ነው። ወላጆች፣ በልክ በመብላት ለልጆቻችሁ ጥሩ ምሳሌ መሆን ትችላላችሁ።
◯ በአብዛኛው አትክልት ብላ። የምንመገበው ምግብ የተመጣጠነ እንዲሆን ከሥጋና ስታርች ከበዛባቸው ምግቦች ይልቅ ፍራፍሬዎችን፣ አትክልቶችንና ያልተፈተጉ ጥራጥሬዎችን ማዘውተር አለብን። በሳምንት አንድ ወይም ሁለት ጊዜ በሥጋ ምትክ ዓሣ ተመገብ። ነጭ ሩዝ እንዲሁም ከተፈተገ እህል የተዘጋጁ እንደ ፓስታና ነጭ ዳቦ ያሉ ምግቦች ብዙም ገንቢ ንጥረ ነገር ስለሌላቸው እነዚህን ምግቦች ቀንስ። ይሁን እንጂ አደገኛ የሆኑ ተወዳጅ ምግቦችን አስወግድ። ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ጤናማ ምግቦችን እንዲወዱ በመርዳት የልጆቻችሁን ጤንነት ጠብቁ። ለምሳሌ ለመክሰስ ከቺፕስ፣ ከኩኪስ ወይም ከከረሜላ ይልቅ ቆሎ፣ ለውዝ ወይም በሚገባ የታጠቡ ትኩስ ፍራፍሬዎችንና አትክልቶችን ስጧቸው።
◯ ብዙ ፈሳሽ ጠጣ። ትልልቅ ሰዎችና ልጆች በየቀኑ ብዙ ውኃ እንዲሁም ጣፋጭ ያልገባባቸው ፈሳሾችን መጠጣት ያስፈልጋቸዋል። ሞቃት በሆኑ ወቅቶችና ከባድ የጉልበት ሥራ ስትሠራ ወይም አካላዊ እንቅስቃሴ ስታደርግ እነዚህን ፈሳሾች በብዛት ጠጣ። እንዲህ ያሉ ፈሳሾች ለምግብ መፈጨት፣ መርዛማ ነገሮችን ከሰውነት ለማስወገድ፣ ለቆዳ ጥራትና ክብደት ለመቀነስ ይረዳሉ። ጥሩ ስሜት እንዲሰማህ እንዲሁም ውበትህ እንዲጨምር ያደርጋሉ። ብዙ አልኮልና ጣፋጭ የበዛባቸው ፈሳሾች ከመጠጣት ተቆጠብ። በየቀኑ 1 ለስላሳ መጠጥ መጠጣትህ ክብደትህ በዓመት ወደ 6.8 ኪሎ ግራም እንዲጨምር ያደርጋል።
በአንዳንድ አገሮች ንጹሕ የመጠጥ ውኃ ማግኘት አድካሚ ብሎም ውድ ነው። ሆኖም ንጹሕ ውኃ መጠጣት አስፈላጊ ነው። ንጽሕናው የተጓደለ ውኃ ለመጠጥነት ከመዋሉ በፊት መፈላት ወይም በኬሚካል መታከም ይኖርበታል። እንዲህ ያለ ውኃ በመጠጣት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በጦርነት ወይም በምድር መናወጥ ከሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እንደሚበልጥ ይነገራል፤ በቆሸሸ ውኃ ሳቢያ በየቀኑ 4,000 ልጆች እንደሚሞቱ ተዘግቧል። የዓለም ጤና ድርጅት አራስ ልጆች 6 ወር እስኪሆናቸው ድረስ የእናታቸውን ጡት ብቻ እንዲጠቡና ከዚያ በኋላ ቢያንስ 2 ዓመት እስኪሆናቸው ድረስ ከጡት በተጨማሪ ሌሎች ምግቦችን እንዲመገቡ ይመክራል።