2ኛው ቁልፍ—የሰውነትህን መሠረታዊ ፍላጎቶች አሟላ
2ኛው ቁልፍ—የሰውነትህን መሠረታዊ ፍላጎቶች አሟላ
“የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ማንም የለም፤ ይመግበዋል፤ ይንከባከበዋል።” (ኤፌሶን 5:29 አ.መ.ት.) ራስህን ለመንከባከብ መሠረታዊ እርምጃዎችን መውሰድህ በጤንነትህ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል።
◯ በቂ እረፍት አግኝ። “በድካምና ነፋስን በመከተል ከሚገኝ ሁለት ዕፍኝ ይልቅ፣ በርጋታ የሚገኝ አንድ ዕፍኝ ይሻላል።” (መክብብ 4:6) ዘመናዊ አኗኗር ያመጣቸው ግዴታዎችና ጊዜ ማሳለፊያዎች ሰዎች በእንቅልፍ ሊያሳልፉት የሚገባውን ጊዜ ሸራርፎባቸዋል። ይሁን እንጂ እንቅልፍ ለጥሩ ጤንነት ወሳኝ ነገር ነው። በእንቅልፍ ሰዓት ሰውነታችንና አንጎላችን ራሳቸውን እንደሚያድሱ ጥናቶች ያመለክታሉ፤ ይህ ደግሞ የማስታወስ ችሎታን የሚያሻሽል ከመሆኑም በላይ ግለሰቡ ጥሩ ስሜት እንዲሰማው ያደርጋል።
እንቅልፍ የሰውነትን በሽታ የመከላከል አቅም በማጠናከር ለተላላፊ በሽታዎች፣ ለስኳር ሕመም፣ በአንጎል ውስጥ ደም ለመፍሰስ፣ ለልብ ሕመም፣ ለካንሰር፣ ከመጠን ላለፈ ውፍረት፣ ለመንፈስ ጭንቀት አልፎ ተርፎም አልዛይመር ለሚባለው የመርሳት በሽታ የመጋለጥን አጋጣሚ ይቀንሳል። ተፈጥሯዊው “አደጋ መከላከያችን” እንድንተኛ ሲጠይቀን ጥያቄውን ችላ ብለን ሰውነታችንን በጣፋጭ፣ በካፌን ወይም በሌላ ዓይነት ማነቃቂያ ከመደለል ይልቅ ጥሪውን መቀበልና መተኛት ይኖርብናል። አዋቂዎች አብዛኛውን ጊዜ ውበታቸውና ስሜታቸው እንዲጠበቅ እንዲሁም ሥራቸውን በጥሩ ሁኔታ እንዲያከናውኑ በየቀኑ ከሰባት እስከ ስምንት ሰዓት መተኛት ያስፈልጋቸዋል። ወጣቶች ደግሞ ከዚያ በላይ እንቅልፍ ያስፈልጋቸዋል። በአሥራዎቹ ዕድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶች እንቅልፍ ማጣታቸው ለሥነ ልቦና ችግር ሊያጋልጣቸው የሚችል ከመሆኑም በላይ መኪና ሲያሽከረክሩ ሊተኙ ይችላሉ።
በተለይ ስንታመም እንቅልፍ ያስፈልገናል። ከወትሮው የበለጠ በመተኛትና በብዛት ፈሳሽ በመጠጣት ብቻ እንደ ጉንፋን ያሉ አንዳንድ በሽታዎችን መቋቋም ይቻላል።
◯ ለጥርስህ እንክብካቤ አድርግ። ምግብ ከበላህ በኋላ በተለይም ከመተኛትህ በፊት ጥርስህን መቦረሽህና በጥርሶችህ መሃል የገባውን ምግብ ማውጣትህ ጥርስህ እንዳይበሰብስ ብሎም ለድድ በሽታና ለጥርስ መነቀል እንዳትጋለጥ ሊረዳህ ይችላል። ጥርሶችህ ካለቁ ከምትበላው ምግብ ሙሉ ጥቅም ማግኘት አትችልም። ዘገባዎች እንደሚገልጹት ዝሆኖች በአብዛኛው የሚሞቱት በእርጅና ሳይሆን ጥርሶቻቸው ረግፈው ካለቁ በኋላ በአግባቡ ማኘክ አቅቷቸው ለረሃብ ስለሚጋለጡ ነው። ልጆች ከበሉ በኋላ ጥርሳቸውን እንዲቦርሹና በጥርሶቻቸው መካከል የገባውን ምግብ እንዲያወጡ ትምህርት ከተሰጣቸው በወጣትነታቸውም ሆነ በቀሪው ሕይወታቸው ጥሩ ጤንነት ይኖራቸዋል።
◯ ሐኪም ቤት ሂድ። አንዳንድ በሽታዎች የሕክምና ባለሞያ ክትትል ያስፈልጋቸዋል። አንድ ዓይነት በሽታ እንዳለብህ ቀደም ብሎ መታወቁ ቶሎ ለመዳን የሚረዳህ ከመሆኑም በላይ ወጪ ይቀንስልሃል። ስለዚህ ጤንነት ካልተሰማህ ማስታገሻ ከመውሰድ ይልቅ መንስኤውን ለማወቅና ችግሩን ለማስወገድ ወደ ሐኪም ቤት ሂድ።
እርጉዝ ሴቶች የሕክምና ክትትል እንደሚያደርጉት ሁሉ አንድ ሰው በተወሰነ ጊዜ ወደ ሕክምና ባለሞያ ሄዶ ምርመራ ማድረጉ ለከባድ የጤና ችግር እንዳይጋለጥ ይረዳዋል። * ይሁንና ሐኪሞች ተአምር መፈጸም እንደማይችሉ አስታውስ። ለበሽታዎቻችን ሁሉ የተሟላ ፈውስ የምናገኘው አምላክ ‘ሁሉንም ነገር አዲስ ሲያደርግ’ ነው።—ራእይ 21:4, 5
[የግርጌ ማስታወሻ]
^ አን.8 በኅዳር 2009 ንቁ! መጽሔት ላይ የወጣውን “ጤናማ እናቶች፣ ጤናማ ሕፃናት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።