በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“መጽሐፉን ማስቀመጥ አልቻልኩም!”

“መጽሐፉን ማስቀመጥ አልቻልኩም!”

“መጽሐፉን ማስቀመጥ አልቻልኩም!”

ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2 * የተሰኘውን መጽሐፍ ያነበቡ በዓለም ዙሪያ የሚኖሩ ወጣቶች ለመጽሐፉ ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል። እስቲ ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት።

“መጽሐፉ ከወላጆቻችን ጋር ውይይት እንድናደርግ የሚያበረታታ በመሆኑ ወድጄዋለሁ። የተሰጡትን ምክሮች በተግባር ላይ ለማዋል ጥረት አድርጌያለሁ፤ አሁን በእኔና በወላጆቼ መካከል ያለው የሐሳብ ልውውጥ ተሻሽሏል ማለት እችላለሁ።”​—ሮቤርቶ፣ ሜክሲኮ

“አንዴ ማንበብ ከጀመርኩ በኋላ መጽሐፉን ማስቀመጥ አልቻልኩም! በእያንዳንዱ ምዕራፍ መጨረሻ ላይ የሚገኘውን ‘ላደርጋቸው ያሰብኳቸው ነገሮች’ የሚለውን ሣጥንና በእያንዳንዱ ክፍል መጨረሻ ላይ ያለውን ‘የግል ማስታወሻ’ የሚለውን ገጽ እወዳቸዋለሁ። ይህ መጽሐፍ በትምህርት ቤት ለእምነቴ ጥብቅና እንድቆም ረድቶኛል።”​—ጆኤላ፣ ዩናይትድ ስቴትስ

“ባነበብኩት ቁጥር ይበልጥ ለተግባር እነሳሳለሁ። በመጽሐፉ ላይ የተጠቀሱት ብዙ ወጣቶች የሰጧቸውን አስተያየቶች እንዲሁም ‘ይህን ታውቅ ነበር?’ እና ‘ጠቃሚ ምክር’ የሚሉትን ሣጥኖች ሳነብ በጣም ተገርሜያለሁ። ይህ መጽሐፍ፣ የይሖዋ ምሥክሮች የበላይ አካል የወጣቶች ጉዳይ እንደሚያሳስበው ግልጽ አድርጎልኛል!”​—ሕዊወን፣ ደቡብ ኮሪያ

“የይሖዋ ምሥክሮች ካዘጋጇቸው መጻሕፍት ሁሉ በጣም ያስደሰተኝ ይህ መጽሐፍ ነው። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ በሚገኙ ወጣቶች አእምሮ ውስጥ የሚጉላላውን ሐሳብ እንዲሁም በቤተሰብና በትምህርት ቤት የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ብሎም ጓደኞቻቸው የሚያደርሱባቸውን ተጽዕኖ በደንብ ታውቃላችሁ።”​—ሻነ፣ ካናዳ

“ወላጆቼ በተጨቃጨቁ ቁጥር ወደ ክፍሌ ሄጄ አለቅስ ነበር። ‘ወላጆቼ የሚጨቃጨቁ ከሆነ ምን ማድረግ ይኖርብኛል?’ የሚል ርዕስ ያለውን ምዕራፍ 24⁠ን ካነበብኩ በኋላ ግን ስለ ጉዳዩ ከእናቴና ከአባቴ ጋር መነጋገር ቻልኩ። የእነሱ ጭቅጭቅ ምን ያህል እየጎዳኝ መሆኑን ሲገነዘቡ ተገረሙ። እነሱም ምዕራፉን አነበቡት። አሁን ከበፊቱ በተሻለ ስሜቴን የሚረዱልኝ ሲሆን ያን ያህል አይጨቃጨቁም።”​—ማርያና፣ ቼክ ሪፑብሊክ

“‘አርዓያ የሚሆኑ ሰዎች’ የሚል ርዕስ ያላቸው ገጾች በጥልቅ ስለነኩኝ ደካማ ጎኖቼን እንዳሻሽል ረድተውኛል። ለምሳሌ ያህል፣ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እምብዛም የማላውቃቸውን ሰዎች መቅረብ ይከብደኛል። በገጽ 97 ላይ የሚገኘው ክፍል ግን ሊዲያ ለጳውሎስና ለጓደኞቹ የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ በማሳየት ከበፊቱ ይበልጥ እንዴት ልታውቃቸው እንደቻለች ይናገራል። አሁን የእሷን ምሳሌ ለመከተል እሞክራለሁ።”​—ሞኒካ፣ ሃንጋሪ

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

“ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ስህተት የሆነው ለምንድን ነው?”

በዩናይትድ ስቴትስ የምትኖር ካትሪና የተባለች የ16 ዓመት ወጣት የንግግር ችሎታን ለማዳበር በሚሰጠው የትምህርት ክፍለ ጊዜ የፈለገችውን ርዕስ መርጣ ንግግር እንድታቀርብ የቤት ሥራ ተሰጥቷት ነበር። ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መሆን የሚችሉ መልሶች፣ ጥራዝ 2⁠ን ተጠቅማ “ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ስህተት የሆነው ለምንድን ነው?” በሚል ጭብጥ ንግግር ለማቅረብ ወሰነች። ወላጆቿ እንደሚከተለው በማለት ተናግረዋል፦ “ካትሪና ንግግሯን ስታቀርብ ‘መታቀብ’ የሚለውን ቃል ትርጉም ከገለጸች በኋላ ከጋብቻ በፊት የፆታ ግንኙነት መፈጸም ያሉትን አደጋዎች ያብራራች ሲሆን የአምላክን የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መጣስ የሚያስከትላቸውን ጎጂ መዘዞች ዘረዘረች። በተጨማሪም ካትሪና አንዳንድ ወጣቶች የአምላክን መሥፈርቶች ከጣሱ በኋላ ምን እንደተሰማቸው የተናገሩትን ሐሳብ በቀጥታ ከመጽሐፉ ላይ አነበበች። ከዚያም አድማጮቿ ጥያቄ እንዲጠይቁ የጋበዘች ሲሆን ለቀረቡላት ጥያቄዎችም በሙሉ መልስ ሰጥታለች። ንግግሯን ከጨረሰች በኋላ አስተማሪዋ ማስታወሻ ጽፋ ሰጠቻት፤ ማስታወሻው በከፊል እንዲህ ይላል፦ ‘እውነትን ስለተናገርሽና በጨለማው ዓለም ላይ ብርሃን ስለፈነጠቅሽ አመሰግንሻለሁ። በእምነትሽ ጸንተሽ ኑሪ።’”