በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሐዘን ለተደቆሱ ሰዎች የሚሆን ምክር

በሐዘን ለተደቆሱ ሰዎች የሚሆን ምክር

በሐዘን ለተደቆሱ ሰዎች የሚሆን ምክር

“እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው።”​—መዝሙር 34:18

የምትወደው ሰው ከሞተ በኋላ የድንጋጤ፣ የመደንዘዝና የሐዘን ስሜት ሌላው ቀርቶ የጥፋተኝነት ስሜትና ንዴት ይፈራረቅብህ ይሆናል። ባለፈው ርዕስ ላይ እንደተጠቀሰው ሁሉም ሰው ሐዘኑን የሚገልጸው በተመሳሳይ መንገድ አይደለም። በመሆኑም ከላይ የተዘረዘሩት ስሜቶች በሙሉ ላይሰሙህ አልፎ ተርፎም ሐዘንህን ከሌሎች በተለየ መንገድ ልትገልጽ ትችላለህ። ይሁን እንጂ እንደሚያስፈልግህ በተሰማህ ጊዜ ሁሉ ሐዘንህን ብትገልጽ ምንም ስህተት የለውም።

‘ሐዘንህን ግለጽ!’

ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ኤሎኢዘ የተባለችው ዶክተር እናቷ ከሞተች በኋላ ስሜቷን አምቃ ለመያዝ ሞክራ ነበር። እንዲህ ብላለች፦ “መጀመሪያ ላይ አለቀስኩ፤ ነገር ግን አንድ ሕመምተኛ ሲሞትብኝ እንደማደርገው ሁሉ ወዲያውኑ ስሜቴን ማፈን ጀመርኩ። ጤንነቴ በእጅጉ የተቃወሰው በዚሁ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም። የሚወዱትን ሰው በሞት ለተነጠቁ ሰዎች የምሰጠው ምክር ቢኖር ‘ሐዘናችሁን ግለጹ! እስኪወጣላችሁ ድረስ አልቅሱ። ከዚያ በኋላ ቀለል ይላችኋል’ የሚል ነው።”

ቀናት ብሎም ሳምንታት እያለፉ ሲሄዱ ግን ባሏን በካንሰር እንዳጣችው እንደ ሴሲሊያ ይሰማችሁ ይሆናል። እንዲህ ትላለች፦ “አንዳንዶች እስከ አሁን ድረስ መጽናናት አለባት ብለው ያስባሉ፤ እነሱ እንደጠበቁት ሳልሆን መቅረቴ ግን ያበሳጨኛል።”

አንተም እንደዚህ የሚሰማህ ከሆነ ሐዘንን ለመግለጽ “ትክክለኛ” የሚባል መንገድ እንደሌለ አስታውስ። በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ አንዳንዶች ብዙም ሳይቸገሩ ከሐዘናቸው ይጽናናሉ። ሌሎች ግን ቶሎ መጽናናት ያቅታቸዋል። አንተም ቶሎ መጽናናት ካቃተህ ይህን ሂደት ማፋጠን እንደማትችል አምነህ መቀበል ይገባሃል፤ በመሆኑም ‘በዚህ ጊዜ ውስጥ መጽናናት ይገባኛል’ ብለህ በማሰብ ባስቀመጥከው “ቀነ ገደብ” ውስጥ ለመጽናናት ራስህን አታስገድድ። *

ይሁን እንጂ ሐዘንህ ማብቂያ የሌለው ቢሆንና በተስፋ መቁረጥ ስሜት ብትዋጥ ምን ማድረግ ትችላለህ? ምናልባት የደረሰብህ ሁኔታ ከጻድቁ ከያዕቆብ ጋር የሚመሳሰል ሊሆን ይችላል፤ ያዕቆብ ልጁ ዮሴፍ እንደሞተ በተነገረው ጊዜ ‘ሊጽናና አልቻለም’ ነበር። (ዘፍጥረት 37:35) አንተም ያለህበት ሁኔታ እንደዚህ ከሆነ በሐዘን ተደቁሰህ እንዳትቀር ተግባራዊ ሊሆኑ የሚችሉ ምን እርምጃዎችን መውሰድ ትችላለህ?

ራስህን ተንከባከብ። ሴሲሊያ “አንዳንድ ጊዜ በጣም ይደክመኛል፤ በዚህ ጊዜ ሐዘኑን እንዳበዛሁት እገነዘባለሁ” በማለት ተናግራለች። ሴሲሊያ ከተናገረችው ሐሳብ መረዳት እንደሚቻለው ሐዘን በአካልም ሆነ በስሜት ላይ ከባድ ሥቃይ ሊያስከትል ይችላል። ስለዚህ ለጤንነትህ ለየት ያለ ትኩረት መስጠትህ አስፈላጊ ነው። ተገቢ እረፍት አድርግ፤ እንዲሁም ተመጣጣኝ ምግቦችን ተመገብ።

እርግጥ ነው፣ በዚህ ጊዜ የምግብ ፍላጎትህ ሊቀንስ አልፎ ተርፎም ገበያ ወጥቶ አንዳንድ ነገሮችን መግዛትና ማብሰል ይበልጥ ከባድ ሊሆንብህ ይችላል። ይሁን እንጂ ተመጣጣኝ ምግቦችን አለመመገብህ በቀላሉ ለበሽታ እንድትጋለጥ የሚያደርግህ ሲሆን ይህ ደግሞ ጭንቀትህን ከማባባስ በቀር የሚፈይደው ነገር የለም። ጥሩ ጤንነት እንዲኖርህ በትንሹም ቢሆን ለመብላት ጥረት ማድረግ አለብህ። *

የምትችል ከሆነ አካላዊ እንቅስቃሴ አድርግ፤ በዚህ ረገድ የእግር ጉዞ ማድረግ ብቻ እንኳ በቂ ሊሆን ይችላል። አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግህ ከቤት ወጣ እንድትል ሰበብ ሊሆንልህ ይችላል። ከዚህም በላይ መጠነኛ የሆነ አካላዊ እንቅስቃሴ፣ ጥሩ ስሜት እንዲሰማህ የሚያደርገውን ኢንዶርፊን የተባለውን ኬሚካላዊ ንጥረ ነገር አንጎልህ እንዲያመነጭ ያደርጋል።

ሌሎች የሚሰጡህን እርዳታ ተቀበል። በተለይ የትዳር ጓደኛ ሲሞት ሌሎች የሚሰጡትን እርዳታ መቀበል በጣም አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ምናልባትም የሞተው ግለሰብ ያከናውናቸው የነበሩ በርካታ ሥራዎች ይኖሩ ይሆናል፤ አሁን ግን እነዚህን ሥራዎች የሚያከናውን ሰው የለም። ለምሳሌ ያህል፣ ገንዘብ ነክ ጉዳዮችን ወይም የቤት ውስጥ ሥራዎችን መከታተል የአንተ ሥራ ካልነበረ እነዚህን ጉዳዮች ማከናወን መጀመሪያ ላይ አስቸጋሪ ሊሆንብህ ይችላል። እንዲህ ባሉት ሁኔታዎች ሥር አስተዋይ የሆኑ ወዳጆች የሚሰጡትን ምክር መቀበል በእጅጉ ሊረዳህ ይችላል።—ምሳሌ 25:11

መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ ወዳጅ ‘ለክፉ ቀን እንደተወለደ’ ወንድም እንደሆነ ይናገራል። (ምሳሌ 17:17) ስለዚህ በሌሎች ላይ ሸክም እሆናለሁ ብለህ ራስህን አታግልል። በተቃራኒው ከሌሎች ጋር መሆን ይህን አስቸጋሪ ጊዜ ለመወጣት መሸጋገሪያ ድልድይ ሊሆንልህ ይችላል። ሳሊ የተባለች አንዲት ወጣት እናቷ ከሞተች በኋላ ከሌሎች ጋር መሆኗ መንፈሷን በእጅጉ እንዳደሰላት ተገንዝባለች። ሳሊ እንዲህ ብላለች፦ “አብዛኞቹ ጓደኞቼ አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን ሲያደርጉ እኔንም ይጋብዙኛል። ይህም የሚሰማኝን ኃይለኛ የሆነ የብቸኝነት ስሜት እንድቋቋም ረድቶኛል። ሰዎች ‘እንዴት ነው? ከእናትሽ ሞት እየተጽናናሽ ነው?’ እንደሚለው ያሉ ቀላል ጥያቄዎችን ሲጠይቁኝ ደስ ይለኝ ነበር። ስለ እናቴ ማውራት ከሐዘኔ እንድጽናና እንደረዳኝ ተገንዝቤያለሁ።”

ለማስታወስ ሞክር። ከምትወደው ሰው ጋር ያሳለፍካቸውን አስደሳች ትዝታዎች (ምናልባትም ፎቶዎችን በመመልከት ሊሆን ይችላል) ለማስታወስ ሞክር። እውነት ነው፣ እነዚያን ጊዜያት ማስታወስ መጀመሪያ ላይ ሐዘንህን ይቀሰቅስብህ ይሆናል። ከጊዜ በኋላ ግን እነዚህ ትዝታዎች ሐዘንህን ከማባባስ ይልቅ እንድትጽናና ሊረዱህ ይችላሉ።

የሚሰማህን ነገር በማስታወሻ ላይ ለማስፈር ሞክር። በማስታወሻህ ላይ አስደሳች ስለሆኑት ትዝታዎችህ ልትጽፍ እንዲያውም የምትወደው ሰው በሕይወት ቢኖር ኖሮ ልትነግረው የምትፈልገውን ነገር ጭምር ልታሰፍር ትችላለህ። የጻፍከውን ነገር ስታነበው የሚሰማህን ስሜት በትክክል ለመረዳት ይበልጥ ቀላል ይሆንልሃል። የሚሰማህን በጽሑፍ ማስፈርህ ተንፈስ እንድትል ሊረዳህ ይችላል።

የሟቹን ዕቃዎች ስለ ማስቀመጥስ ምን ማለት ይቻላል? በዚህ ጉዳይ ላይ የሰዎች አመለካከት የተለያየ ነው፤ እያንዳንዱ ሰው ሐዘኑን የሚገልጸው በተለያየ መንገድ ስለሆነ ይህ መሆኑ ምንም አያስደንቅም። አንዳንዶች የሟቹን የግል ዕቃዎች ማስቀመጥ ቶሎ እንዳይጽናኑ እንቅፋት እንደሚሆንባቸው ይሰማቸዋል። ሌሎች ደግሞ ከዚህ ተቃራኒ የሆነ አመለካከት አላቸው። ቀደም ሲል የተጠቀሰችው ሳሊ “የእናቴ የነበሩ ብዙ ነገሮችን አስቀምጫለሁ። ይህ ሐዘንን ለመቋቋም የሚረዳ ጥሩ ዘዴ ነው” ብላለች። *

‘በመጽናናት ሁሉ አምላክ’ ተደገፍ። መጽሐፍ ቅዱስ “የከበደህን ነገር በእግዚአብሔር ላይ ጣል፤ እርሱ ደግፎ ይይዝሃል” በማለት ይናገራል። (መዝሙር 55:22) ጸሎት ጥሩ ስሜት ለማግኘት የሚረዳ ነገር እንደሆነ ብቻ ተደርጎ መታየት የለበትም። ‘በመከራችን ሁሉ ከሚያጽናናን የመጽናናት ሁሉ አምላክ’ ጋር እውነተኛና ጠቃሚ የሆነ ቅርርብ የምንፈጥርበት መንገድ ነው።​—2 ቆሮንቶስ 1:3, 4

ከሁሉም የበለጠውን መጽናኛ የምናገኘው የአምላክ ቃል ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው። ክርስቲያን የሆነው ሐዋርያው ጳውሎስ “ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት እንደሚነሱ በአምላክ ተስፋ አደርጋለሁ” በማለት ተናግሯል። (የሐዋርያት ሥራ 24:15) የሚወደውን ሰው በሞት በመነጠቁ ምክንያት ሐዘን ላይ ያለ ግለሰብ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረተው የትንሣኤ ተስፋ ላይ ማሰላሰሉ ይህ ነው የማይባል መጽናኛ ያስገኝለታል። * በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ወንድሟን በድንገተኛ አደጋ ያጣች ሎረን የምትባል ሴት የትንሣኤ ተስፋ እንዳጽናናት በሕይወቷ ተመልክታለች። እንዲህ ብላለች፦ “ጥሩ ስሜት ባይሰማኝም እንኳ መጽሐፍ ቅዱሴን አንስቼ አንድ ጥቅስም ቢሆን አነባለሁ። በተለይ አጽናኝ ሆነው ያገኘኋቸውን ጥቅሶች አወጣና ደጋግሜ አነባቸዋለሁ። ለምሳሌ ያህል፣ አልዓዛር ከሞተ በኋላ ኢየሱስ ለማርታ የተናገረው ሐሳብ ያጽናናኛል። ‘ወንድምሽ ይነሳል’ ብሏታል።”​—ዮሐንስ 11:23

‘ሐዘኑ እንዲቆጣጠርህ አታድርግ’

ተፈታታኝ ሊሆንብህ ቢችልም ከሐዘንህ ለመጽናናት ጥረት ማድረግህ ወደወትሮው እንቅስቃሴህ እንድትመለስ ይረዳሃል። ወደወትሮው እንቅስቃሴህ በመመለስህ የምትወደውን ሰው እንደከዳኸው ወይም እንደረሳኸው ሊሰማህም ሆነ በጥፋተኝነት ስሜት ልትዋጥ አይገባም። የማይሻር አንድ ሐቅ አለ፦ የምትወደውን ሰው ፈጽሞ ልትረሳው አትችልም። ያሳለፋችኋቸው ትዝታዎች አንድ በአንድ ወደ አእምሮህ የሚመጡበት ጊዜ ቢኖርም ሐዘኑ ግን እየቀነሰልህ ይሄዳል።

በተጨማሪም ደስታና ሐዘን የተቀላቀለበት ስሜት የሚፈጥሩ ትዝታዎች ይኖሩህ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ ባለፈው ርዕስ ላይ የተጠቀሰችው አሽሊ እንዲህ ብላለች፦ “እናቴ ከመሞቷ በፊት የነበረውን ቀን አስታውሰዋለሁ። የዚያን ቀን የተሻላት ትመስል ነበር፤ እንዲያውም ከብዙ ቀናት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከአልጋ ወርዳ ነበር። እህቴ ፀጉሯን እያበጠረችላት ሳለ አንድ ነገር ሦስታችንንም አሳቀን፤ በእናቴ ፊት ላይ እንዲህ ዓይነት ፈገግታ ካየሁ ረጅም ጊዜ ሆኖኝ ነበር። እናቴ ከእኛ ከልጆቿ ጋር በመሆኗ ብቻ በጣም ተደስታ ነበር።”

እናንተም የምትወዱት ሰው በሕይወት እያለ ከእሱ በቀሰማችሁት ጠቃሚ ትምህርት ላይ ማሰላሰል ትችላላችሁ። ለምሳሌ ያህል ሳሊ እንዲህ ብላለች፦ “እናቴ በጣም ግሩም አስተማሪ ነበረች። እየመከረች እንዳለች ሳታስታውቅ ግሩም ምክር መስጠት ትችልበታለች፤ እንዲሁም እሷ ወይም አባቴ ስለነገሩኝ ሳይሆን በራሴ ጥሩ ውሳኔ እንዴት ማድረግ እንደምችል አስተምራኛለች።”

ከምትወደው ሰው ጋር ያሳለፋችሁት ትዝታ ወደወትሮው እንቅስቃሴህ እንድትመለስ የሚረዳህ ጠቃሚ መሣሪያ ሊሆን ይችላል። አሌክስ የሚባል አንድ ወጣት ይህን ተገንዝቧል። እንዲህ ብሏል፦ “አባቴ ከሞተ በኋላ እሱ እንዳስተማረኝ ሆኜ ለመኖር ይኸውም ሕይወትን ማጣጣም እንዳለብኝ ፈጽሞ ላለመርሳት ቁርጥ ውሳኔ አደረግሁ። ወላጅ ለሞተባቸው ሰዎች የምላቸው ነገር ቢኖር ይህ ነው፦ የወላጃችሁ ሞት ያስከተለባችሁን ሐዘን ሙሉ በሙሉ ልትረሱት አትችሉም፤ ይሁን እንጂ ሐዘኑ እንዲቆጣጠራችሁ ማድረግ የለባችሁም። ማልቀስና ማዘን ይኖርባችኋል፤ ነገር ግን የወደፊት ሕይወታችሁን በተቻለ መጠን በጥሩ መንገድ ልትጠቀሙበት እንደሚገባችሁ አትርሱ።”

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.7 ቤት መቀየርን ወይም ትዳር ለመመሥረት አስበህ ከአንድ ሰው ጋር መቀራረብን የመሳሰሉ ውሳኔዎችን በችኮላ ከማድረግ መቆጠብ ይኖርብሃል። እንዲህ ያሉ ውሳኔዎችን ማድረግ ያለብህ በሕይወትህ ውስጥ ካጋጠመህ አዲስ ሁኔታ ጋር ለመላመድ በቂ ጊዜ ካገኘህ በኋላ መሆን ይኖርበታል።

^ አን.10 የአልኮል መጠጥ ሐዘኑ ያስከተለብህን የስሜት ሥቃይ ለማደንዘዝ ሊረዳህ ቢችልም ውጤቱ ጊዜያዊ ነው። የአልኮል መጠጥ ለዘለቄታው ሐዘንህን እንድትቋቋም የማይረዳህ ከመሆኑም በላይ ሱስ ሊሆንብህ ይችላል።

^ አን.16 እያንዳንዱ ሰው ሐዘኑን የሚገልጸው በተለያየ መንገድ ስለሆነ ወዳጅ ዘመዶች ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የእነሱን የግል አመለካከት እንዲቀበል ሐዘንተኛውን መጫን የለባቸውም።​—ገላትያ 6:2, 5

^ አን.18 ሙታን ስላሉበት ሁኔታና ስለ ትንሣኤ ተስፋ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች ከተዘጋጀው ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? ከተባለው መጽሐፍ ላይ ምዕራፍ 6⁠ን እና 7⁠ን ተመልከት።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ጥሩ ስሜት ባይሰማኝም እንኳ መጽሐፍ ቅዱሴን አንስቼ አንድ ጥቅስም ቢሆን አነባለሁ”​—ሎረን

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

የጥፋተኝነትን ስሜት መቋቋም

ምናልባት የምትወዱትን ሰው ለሞት ያደረሰው የእናንተ ቸልተኝነት እንደሆነ ይሰማችሁ ይሆናል። ይህ ዓይነቱ ትክክለኛም ሆነ ግምታዊ የጥፋተኛነት ስሜት የሐዘን ስሜት ከሚገለጥባቸው ጤናማ መንገዶች አንዱ እንደሆነ መገንዘባችሁ ራሱ ሊረዳችሁ ይችላል። እንዲህ ያለውንም ስሜት ቢሆን ለራሳችሁ ብቻ አምቃችሁ መያዝ አይኖርባችሁም። ምን ያህል የበደለኛነት ስሜት እንደሚሰማችሁ መናገራችሁ ስሜታችሁ እንዲወጣላችሁ ያስችላል።

ይሁን እንጂ አንድን ሰው ምንም ያህል ብንወደው ሕይወቱን ልንቆጣጠርለት እንደማንችል ወይም ‘ጊዜና አጋጣሚ’ እንዳያገኘው መከልከል እንደማንችል መገንዘብ ይኖርብናል። (መክብብ 9:11) ከዚህም ሌላ ለመጉዳት ብላችሁ ያደረጋችሁት ነገር እንዳልሆነ ጥርጥር የለውም። ለምሳሌ ያህል የምትወዱትን ሰው ቀደም ብላችሁ ሐኪም ቤት ያልወሰዳችሁት ታሞ እንዲሞት ፈልጋችሁ ነው? በፍጹም አይደለም! ታዲያ ለዚህ ሰው መሞት ምክንያት ሆናችኋል ለማለት ይቻላል? በጭራሽ አይቻልም።

አንዲት እናት ሴት ልጅዋ በመኪና አደጋ ከሞተች በኋላ የተሰማትን የበደለኛነት ስሜት እንዴት ለመቋቋም እንደቻለች እንደሚከተለው በማለት ገልጻለች፦ “የላክኋት እኔ ስለነበርኩ የጥፋተኛነት ስሜት ተሰምቶኝ ነበር። ይሁን እንጂ ይህ አስተሳሰቤ ምክንያታዊ እንዳልሆነ መገንዘብ ቻልኩ። ከአባቷ ጋር መልእክት እንድታደርስልኝ መላኬ ምንም ዓይነት ስህተት የለውም። ድንገት የተፈጠረ አደጋ ነው።”

ይሁን እንጂ ‘እንዲህ ብዬ ወይም እንዲህ አድርጌ ቢሆን ኖሮ’ ብላችሁ ታስቡ ይሆናል። ግን ከመካከላችን ፍጹም አባት ወይም ፍጹም እናት ወይም ፍጹም ልጅ የሆነ ማን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ “ሁላችን በብዙ ነገር እንሰናከላለንና፤ በቃል የማይሰናከል ማንም ቢኖር እርሱ . . . ፍጹም ሰው ነው” በማለት ያሳስበናል። (ያዕቆብ 3:2፤ ሮሜ 5:12) ስለዚህ ፍጹም አለመሆናችሁን አትርሱ። “እንዲህ ቢሆን ኖሮ” እያሉ ሺህ ምክንያቶችን መደርደር ከሐዘናችሁ ቶሎ እንዳትጽናኑ ከማድረጉ በስተቀር አንዳች የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም። *

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.36 እዚህ ሣጥን ውስጥ የሚገኘው ሐሳብ የተወሰደው የምትወዱት ሰው ሲሞት ከተሰኘው በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀ ብሮሹር ነው።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሐዘን ላይ ያለ አረጋዊ ወላጅ ጎልማሳ ልጁን ማጽናናት ያለበት ጊዜ ይኖራል

[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የሚወዱትን ሰው በሞት የተነጠቁ ሰዎች ማስታወሻ በመጻፍ፣ ፎቶዎችን በመመልከትና ሌሎች የሚሰጧቸውን እርዳታ በመቀበል ሐዘናቸውን መቋቋም ይችላሉ