በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

“ከግማሽ የሚበልጡ ሩሲያውያን ‘ችግሮችን ለመፍታት’ ከሁሉ የሚሻለው መንገድ ለባለ ሥልጣናት ጉቦ መስጠት እንደሆነ ያምናሉ።”​—የሮይተርስ ዜና አገልግሎት፣ ሩሲያ

“ለአካለ መጠን ከደረሱ ቻይናውያን መካከል 17.5 በመቶ የሚሆኑት በአእምሮ ሕመም እንደሚሠቃዩ አንድ ጥናት አመልክቷል። . . . ከወንዶች ይበልጥ ሴቶች በስሜት መለዋወጥና በጭንቀት ይሠቃያሉ።”​—ቻይና ዴይሊ፣ ቻይና

“ናሽናል ሴፍቲ ካውንስል የተባለው ድርጅት ያወጣው ግምታዊ አኃዝ እንደሚያሳየው በዩናይትድ ስቴትስ ከሚደርሱት የመኪና አደጋዎች ውስጥ 28 በመቶ ለሚሆኑት ወይም በየዓመቱ ከሚደርሱት ግጭቶች መካከል 1.6 ሚሊዮን ለሚሆኑት መንስኤው አሽከርካሪዎች የሞባይል ስልኮችን መጠቀማቸው ወይም የጽሑፍ መልእክቶችን መለዋወጣቸው ነው።”​—ዩሲ በርክሌ ዌልነስ ሌተር፣ ዩናይትድ ስቴትስ

“አሳፋሪ ታሪክ”

“በልጆች ላይ የሚፈጸመውን በደል ለማጣራት የተቋቋመው ኮሚሽን ያቀረበው ሪፖርት የአየርላንድን አሳፋሪ ታሪክ አጋለጠ” በማለት ዚ አይሪሽ ታይምስ ዘግቧል። ጋዜጣው እንደገለጸው የካቶሊክ ሃይማኖታዊ ተቋማት በልጆች ላይ ለረጅም ጊዜ በተፈጸመ በደል የተበከለ ታሪክ እንዳላቸው ሪፖርቱ አጋልጧል፤ በእነዚህ ተቋማት ውስጥ ከተፈጸሙት በደሎች መካከል “ፀጉራቸው ላይ ቅማል የተገኘባቸውን ልጆች መደብደብ” እንዲሁም ለረጅም ጊዜ የዘለቀ የፆታ ጥቃት ይገኙበታል። ይህ ሁሉ በደል ችላ ተብሎ የታለፈው “ለካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ገደብ የለሽ ሥልጣን” ተገቢ ያልሆነ ታማኝነት በማሳየት እንደሆነ ጋዜጣው ገልጿል። በታይምስ ላይ የወጣ አንድ ርዕሰ አንቀጽ፣ በደል ለተፈጸመባቸው ልጆች ያዘነች አንዲት ሴት የተናገረችውን በመጥቀስ “መንግሥትና ቤተ ክርስቲያን አሳፋሪ ናችሁ” ብሏል።

ጨረቃ ላይ ውኃ ተገኘ

ሮኬት ከጨረቃ ጋር አጋጭተው ያሳረፉ ሳይንቲስቶች በግጭቱ ምክንያት በተነሳው አቧራ ውስጥ ውኃ እንዳገኙ ተናግረዋል። ሳይንቲስቶቹ ስፔክትሮሜትር የተባለ መሣሪያ በመጠቀም አቧራውን መርምረዋል፤ ይህ መሣሪያ ንጥረ ነገሮች የሚያወጡትን ወይም የሚስቡትን የብርሃን ጨረር የሞገድ ርዝመት በመለካት ንጥረ ነገሩ ምን ነገሮች እንደያዘ ይመረምራል። በዋሽንግተን ዲ ሲ የሚገኘው ብሔራዊ የበረራና የሕዋ አስተዳደር (NASA) ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ ዋና የጨረቃ ሳይንቲስት የሆኑት ማይክል ዋርጎ “በቅርብ የምትገኘውን ጎረቤታችንን ብሎም የሥርዓተ ፀሐይን ሚስጥሮች እየፈታን ነው” ብለዋል። በቅርቡ ወደ ጨረቃ የተላከ ሰው አልባ መንኮራኩር በጨረቃ ሰሜናዊ ዋልታ በሚሊዮን የሚቆጠር ቶን የሚመዝን ውኃ መኖሩን አረጋግጧል።

ጥፍጥፍ ወርቅ ከሽያጭ ማሽን

በዓለም ዙሪያ በሚገኙ በርካታ አገሮች ውስጥ ከሽያጭ ማሽኖች ሊገዙ ከሚችሉ በርካታ ሸቀጦች መካከል ጥፍጥፍ ወርቅም ሊካተት ችሏል። ለምሳሌ በአቡ ዳቢ፣ ዩናይትድ አረብ ኢሚሬትስ የሚገኝ አንድ ሆቴል እስከ 10 ግራም የሚመዝን ጥፍጥፍ ወርቅና የወርቅ ሳንቲሞችን ጨምሮ 320 ሸቀጦችን የሚሸጥ ማሽን ተክሏል። የወርቁ ዋጋ በኮምፒውተር አማካኝነት በዓለም አቀፉ ገበያ መሠረት በየአሥር ደቂቃው ይስተካከላል። መጀመሪያ ላይ ማሽኑ ይቀበል የነበረው የአገሩን ገንዘብ ብቻ ቢሆንም የክሬዲት ካርድ ክፍያ አማራጭ እንዲኖረው ለማድረግ እየታሰበ ነው። ጥፍጥፍ ወርቅ ለመሸጥ ይህ ቦታ የተመረጠው “በአካባቢው ከፍተኛ የሆነ የወርቅ ፍላጎት በመኖሩ ነው” ይላል የሮይተርስ ሪፖርት።