በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ልዩ ለሆኑት ስጦታዎችህ አመስጋኝ ሁን

ልዩ ለሆኑት ስጦታዎችህ አመስጋኝ ሁን

ልዩ ለሆኑት ስጦታዎችህ አመስጋኝ ሁን

የሰው አካል ብዙ ነገር ለመሥራት የሚያስችል አስደናቂ ችሎታ አለው። የሰው ልጆች ያሏቸውን ችሎታዎች የሚተካከል ችሎታ ያለው አንድም እንስሳ የለም። የተለያዩ ነገሮችን የመሥራት ችሎታ እንዲኖረን አስተዋጽኦ ካደረጉት ነገሮች አንዱ ቀጥ ብለን የምንቆም መሆናችን ነው፤ ይህ መሆኑ በስፋትና በርቀት ለማየት የሚያስችለን ከመሆኑም በላይ እጃችን ነፃ ስለሚሆን በርካታ ሥራዎችን ማከናወን እንችላለን። በእጅና በእግራችን የምንሄድ ብንሆን ኖሮ መሥራት የምንችላቸው ነገሮች ምንኛ ውስን በሆኑ ነበር!

ሌላው ልዩ ስጦታ ደግሞ እጅግ ውስብስብ የሆኑት የስሜት ሕዋሶቻችን ሲሆኑ ይህ ርዕስ ትኩረት የሚያደርገው በዚህ ነጥብ ላይ ነው። የስሜት ሕዋሶቻችን እጃችንን፣ ጆሯችንን፣ ዓይናችንን እንዲሁም ልዩ የሆነውን አንጎላችንን ያጠቃልላሉ። እስቲ እነዚህን ነገሮች አንድ በአንድ እንመልከታቸው።

የሰው እጅ

እጃችን እያንዳንዱን ተግባር ለማከናወን በሚያስገርም መንገድ እንደተፈለገው መሆን የሚችል ድንቅ መሣሪያ ነው። በእጃችን በመጠቀም በመርፌ ቀዳዳ ውስጥ ክር ማስገባት ወይም በመጥረቢያ መፍለጥ፣ ሥዕል መሣል እንዲሁም ፒያኖ መጫወት እንችላለን። በተጨማሪም እጃችን መልእክት የማስተላለፍ ከፍተኛ ችሎታ አለው። አንድን ነገር ነካ በማድረግ ብቻ እንኳ የነካነው ነገር ፀጉር፣ ወረቀት፣ ቆዳ፣ ብረት፣ ውኃ ወይም እንጨት መሆኑን ለይተን ማወቅ እንችላለን። አዎን፣ እጃችን ነገሮችን ለመያዝና ለማከናወን ብቻ ሳይሆን ከዚህ የበለጡ ሌሎች ተግባሮችንም ለመፈጸም ያስችለናል። እጃችን ስላለንበት ዓለም ለማወቅ ይረዳናል። ከዚህም በተጨማሪ ፍቅርን ለመግለጽ ያስችለናል።

የሰው እጅ ይህን ያህል የላቀ ችሎታ ያለው፣ ብዙ ነገሮችን መሥራት የሚችል፣ ስሜትን ጥሩ አድርጎ የሚገልጽና ትክክለኛ መልእክት የሚያስተላልፍ ሊሆን የቻለው ለምንድን ነው? ብዙ ምክንያቶች አሉ። እስቲ አራቱን እንመልከት፦

1. ሁለቱ እጆቻችን (ከመዳፋችን እስከ ጣታችን ድረስ ባለው ክፍል) በድምሩ ከ50 የሚበልጡ አጥንቶች ያሏቸው ሲሆን ይህም በአጠቃላይ በሰውነታችን ውስጥ ካሉት አጥንቶች ሩብ የሚሆነው የሚገኘው በእጃችን ላይ ነው ማለት ነው። የእጃችን ክፍሎች ማለትም አጥንቶች፣ መገጣጠሚያዎችና ጅማቶች የተዋቀሩበት ውስብስብ መንገድ እጃችን አስገራሚ የሆነ የመተጣጠፍ ችሎታ እንዲኖረው አድርጓል።

2. የኮርቻ ቅርጽ ባለው መገጣጠሚያ ላይ ያረፈው የእጃችን አውራ ጣት የሌሎቹን አራት ጣቶች ጫፍ ፊት ለፊት መንካት ይችላል። በ90 ዲግሪ በተቀመጡና የኮርቻ ዓይነት ቅርጽ ባላቸው ሁለት ነገሮች አስደናቂ በሆነ መንገድ የተዋቀረው ይህ መገጣጠሚያ፣ አብረውት ከሚሠሩት ሌሎች ጡንቻዎችና ሕብረ ሕዋሳት ጋር በመሆን አውራ ጣታችን አስገራሚ የመተጣጠፍ ችሎታና ጥንካሬ እንዲኖረው ያደርጋል።

3. ከመዳፋችን እስከ ጣታችን ያለውን የእጃችንን ክፍል የሚቆጣጠሩት በሦስት ቡድን የተከፈሉ ጡንቻዎች ናቸው። ከእነዚህ መካከል በጣም ጠንካራ የሆኑት ሁለቱ ቡድኖች ዘርጊዎችና አጣፊዎች የሚባሉት ሲሆኑ እነሱም የሚገኙት በታችኛው ክንዳችን ላይ ነው፤ እነዚህ ጡንቻዎች በጅማቶች አማካኝነት ጣቶቻችንን ያንቀሳቅሳሉ። እነዚህ ጡንቻዎች የሚገኙት በመዳፋችን ላይ ቢሆን ኖሮ እጃችን በጣም ትልቅና ለማንቀሳቀስ የማይመች ይሆን ነበር! ሦስተኛውና መጠኑ በጣም አነስተኛ የሆነው የጡንቻዎች ቡድን የሚገኘው በመዳፋችን ላይ ሲሆን ይህም በጣቶቻችን መሥራት የፈለግነውን ነገር ሁሉ በትክክል ማከናወን እንድንችል ይረዳናል።

4. ጣቶችህ እንደ እንቅስቃሴ ወይም ሙቀት አሊያም ብርሃን ያሉ ነገሮች መኖራቸውን ለማወቅ እንደሚያገለግሉ መሣሪያዎች ናቸው ማለት ይቻላል፤ የጣቶችህ ጫፎች የአንድ ካሬ ሴንቲ ሜትር አንድ ስድስተኛ በሚሆን ቦታ ላይ ብቻ እንኳ 2,500 መልእክት ተቀባዮች አሏቸው። እነዚህ መልእክት ተቀባዮች ዓይነታቸው የተለያየ ነው፤ እያንዳንዳቸው የየራሳቸው ሥራ ያላቸው ሲሆን አንድ ነገር ለስላሳ ይሁን ሸካራ፣ ሞቃት ይሁን ቀዝቃዛ፣ እርጥብ ይሁን ደረቅ ለማወቅ እንዲሁም ንዝረትንና ግፊትን ለመለየት ያስችላሉ፤ በተጨማሪም ሕመም የሚያስከትል ነገር ሲያጋጥመን ይህን የሚያሳውቅ መልእክት ያስተላልፋሉ። በዚህም የተነሳ ጣታችን የሰው ልጅ ከሠራቸው የአንድን ነገር ምንነት ለማወቅ የሚያስችሉ መሣሪያዎች ሁሉ የላቀ ነው።

የሰው ጆሮ

አንዳንድ እንስሳት የሰው ልጆች ሊሰሙት የማይችሉትን የድምፅ ሞገድ እርግብግቢት መስማት ይችላሉ፤ ሆኖም የሰው ልጆች ጆሮና አእምሮ አንድ ላይ ሲቀናጁ በጣም አስገራሚ ነገር እንደሚያከናውኑ ባለሙያዎች ይናገራሉ። የመስማት ችሎታችን የድምፅን ከፍታ፣ ቅጥነትና ውፍረት እንዲሁም ቃና ለመለየትና ድምፁ የመጣበትን አቅጣጫና ርቀቱን ለመገመት ያስችለናል። ጤናማ የሆነ የሰው ጆሮ መስማት የሚችለው ድምፅ፣ በሴኮንድ ከ20 እስከ 20,000 ኸርዝ ወይም ሞገድ ነው። የሰው ጆሮ ይበልጥ የሚለየው ከ1,000 እስከ 5,000 ኸርዝ ያሉ ድምፆችን ነው፤ በተጨማሪም በዚህ ክልል ውስጥ የአንድ ኸርዝ ልዩነትን እንኳ (ለምሳሌ በ440 እና በ441 ኸርዝ መካከል ያለውን ልዩነት) መለየት እንችላለን።

በእርግጥም ጤናማ ጆሮ ድምፅን በቀላሉ የሚለይ በመሆኑ ወደ ጆሮ ታምቡር የሚደርሰው የአየር እርግብግቢት ከአንድ አተም ዳያሜትር ያነሰ ቢሆን እንኳ ጆሯችን ሊለየው ይችላል! የመስማት ችሎታን በተመለከተ በተሰጠ አንድ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት መሠረት “የሰው የመስማት ችሎታ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ መድረስ ወደሚቻልበት የመጨረሻ ደረጃ የቀረበ ነው። . . . ከዚህ በላይ የመስማት ችሎታ ቢኖረን ምንም አይጠቅመንም፤ ምክንያቱም የምንሰማው ነገር ቢኖር [በአየር ውስጥ የሚገኙት አተሞችና ሞለኪውሎች ሲንቀሳቀሱ የሚፈጥሩትን] ‘ስስስ’ የሚል ድምፅ ብቻ ይሆናል።”

የጆሮ ታምቡር ሲርገበገብ የድምፁ ሞገድ ይጎላና ኦሲክል በሚባሉ ትንንሽ አጥንቶች አማካኝነት ወደ ውስጠኛው የጆሮ ክፍል ይተላለፋል፤ ኦሲክል የሚባሉት በጆሮ ውስጥ የሚገኙ መደወያ (ሃመር)፣ መስፍ (አንቭል) እና እርካብ (ስቴፒዝ) የተባሉ አጥንቶች ናቸው። ይሁን እንጂ ጆሮ የሚያደነቁር ኃይለኛ ድምፅ በድንገት ቢያንባርቅብህስ? እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥም ጆሯችን በጡንቻዎች አማካኝነት ኦሲክሎቹን በማስተካከል የድምፁን ኃይል ለመቀነስ እንዲችሉ የሚያደርግበት መንገድ አለ። ይሁን እንጂ ጆሯችን ረዘም ላለ ጊዜ የሚቀጥል ኃይለኛ ድምፅን መቋቋም አይችልም። እንዲህ ላለው ኃይለኛ ድምፅ መጋለጥ የመስማት ችሎታችንን ለዘለቄታው ይጎዳዋል። እንግዲያው ከፈጣሪህ ላገኘኸው ለዚህ “ግሩምና ድንቅ” ሆኖ የተሠራ ስጦታ ጥንቃቄ አድርግለት።—መዝሙር 139:14

የመስማት ችሎታህ አንድ ድምፅ ከየት እንደመጣ ለይተህ እንድታውቅም ይረዳሃል። እንዲህ ለማድረግ እንድትችል አስተዋጽኦ የሚያደርጉ በርካታ ነገሮች አሉ፤ ከእነዚህም መካከል የዛጎል ቅርጽ ያለው የጆሮ ውጨኛ ክፍል፣ ስርጉዶቹ፣ ሁለቱ ጆሮዎች ተለያይተው መቀመጣቸው እንዲሁም አንጎል መረጃዎችን የሚያስተናግድበት አስደናቂ መንገድ ይገኙበታል። በመሆኑም ወደ አንድ ጆሮህ የገባው የድምፅ መጠን በሌላኛው ከምትሰማው በትንሹ ካነሰ አሊያም ደግሞ ድምፁ ወደ አንደኛው ጆሮህ የደረሰው ወደ ሁለተኛው ጆሮ ከመድረሱ ከአንድ ሴኮንድ 30 ሚሊዮንኛ ጊዜ ቀደም ብሎ ከሆነ አእምሮህ ወዲያውኑ ዓይኖችህን ድምፁ ወደመጣበት አቅጣጫ እንድታዞር ያዝዝሃል።

አእምሮህ የሚያከናውናቸውን ስሌት የሚጠይቁ ነገሮች ራስህ አስበህ መሥራት ቢኖርብህ ኖሮ ምን ሊሆን እንደሚችል እስቲ አስበው! እጅግ የመጠቀ የሒሳብ ስሌትን በብርሃን ፍጥነት መሥራት እንደሚኖርብህ ጥርጥር የለውም! አንድ መሐንዲስ ፈጣሪህ ከሰጠህ ጆሮ ጋር በጣም በጥቂቱ እንኳ የሚቀራረብ “የመስሚያ” መሣሪያ ቢሠራ ኖሮ ከፍተኛ ክብር ይዥጎደጎድለት ነበር። ይሁንና አምላክ ለሠራቸው አስደናቂ ነገሮች ሰዎች ምን ያህል ክብር ይሰጡታል?—ሮም 1:20

የሰው ዓይን

ጥሩ የማየት ችሎታ ያላቸው ሰዎች በዙሪያቸው ስላሉት ነገሮች ከሚሰበስቡት መረጃ 80 በመቶ ገደማ የሚሆነውን የሚያገኙት በዓይናቸው አማካኝነት እንደሆነ አንዳንድ ተመራማሪዎች ይገምታሉ። ዓይናችን ከአንጎላችን ጋር በመቀናጀት ሁሉንም ቀለማት ለመለየት፣ የሚንቀሳቀሱ ነገሮችንና ምስሎችን ያለ አንዳች ችግር በዓይናችን ለመከታተል፣ ንድፎችንና ቅርጾችን ለይተን ለማወቅ እንዲሁም የነገሮችን ወርድ፣ ቁመትና ጥልቀት ለመመልከት ያስችለናል። ከዚህም በላይ የተለያየ የብርሃን መጠን ባለበት ሁኔታ ማየት እንችላለን።

የተለያየ የብርሃን መጠን ባለበት ሁኔታ የማየት ችሎታ እንዲኖረን በርከት ያሉ የዓይን ክፍሎች አንድ ላይ ተቀናጅተው ይሠራሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የዓይን ብሌን ዳያሜትር ከ1.5 ሚሊ ሜትር እስከ 8 ሚሊ ሜትር ድረስ መስፋት የሚችል ሲሆን ይህም ወደ ዓይን የሚገባው የብርሃን መጠን በ30 እጥፍ እንዲጨምር ሊያደርግ ይችላል። ከዚያም ብርሃኑ በዓይን ሌንስ በኩል አልፎ ሬቲና ላይ ያርፋል፤ ሬቲና የብርሃኑን ኃይል 100,000 ጊዜ ያህል ይጨምረዋል። ፀሐይን ፈጽሞ በቀጥታ መመልከት የሌለብህ ለዚህ ነው!

ሬቲና ሁለት ዓይነት ብርሃን ተቀባይ ሴሎች (ፎቶሪሰፕተር) አሉት፤ እነሱም ቀለማትንና ጥርት ያለ ምስል ማየት እንድንችል የሚረዱን ኮን የተባሉ ሴሎች (በግምት 6 ሚሊዮን ይሆናሉ) እና ኮን ከተባሉት ሴሎች ይበልጥ ምስልን ማየት የሚችሉትና ደብዘዝ ባለ ብርሃን ለማየት የሚያስችሉን ሮድ (120-140 ሚሊዮን ይሆናሉ) የተባሉ ሴሎች ናቸው።

እይታችንን ከሁኔታዎች ጋር እንድናስማማ የሚረዳን ሌላው መንገድ ደግሞ ኮን እና ሮድ ከተባሉት ሴሎች ጋር የተያያዙት የሬቲና የነርቭ ሴሎች ናቸው። የአሜሪካው የዓይን ምርምር ማኅበር እንደገለጸው እነዚህ የነርቭ ሴሎች “በሴኮንዶች ጊዜ ውስጥ” እይታችንን ማስማማት እንዲሁም “በምሽት የማየት ችሎታን በ10 እጥፍ ወይም ከዚያ በላይ ማሻሻል” ይችላሉ።

ብዙውን ጊዜ መሐንዲሶች ካሜራዎችን፣ ስካነሮችን እና ኮምፒውተሮችን ሲሠሩ ከእነዚህ መሣሪያዎች ጋር የሚስማማ ፕሮግራም አብረው ያዘጋጃሉ። ይሁን እንጂ እነዚህ መሣሪያዎች ከፕሮግራሙ ጋር ተቀናጅተው የሚሠሩበት ደረጃና ውስብስብነታቸው ከስሜት ሕዋሶቻችን ጋር ሲወዳደሩ ልዩነታቸው የሰማይና የምድር ያህል ነው። ታዲያ ‘የዝግመተ ለውጥ አማኞች እንደሚሉት እጅግ የላቁት የስሜት ሕዋሶቻችን በአጋጣሚ የተገኙ እንደሆኑ ማመን ምክንያታዊ ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ስለ ሰው አካል ዛሬ እኛ ከምናውቀው አንጻር በጥንት ዘመን የኖረው ኢዮብ የተባለ የአምላክ አገልጋይ የሚያውቀው ነገር በጣም ትንሽ ነበር። ያም ሆኖ ኢዮብ ለአምላክ “እጅህ አበጀችኝ” ብሎ ለመናገር ተነሳስቷል።—ኢዮብ 10:8

የሰው አንጎል

አንጎል፣ በነርቮች በኩል ከስሜት ሕዋሳት የሚጎርፉለትን ምልክቶች አስገራሚ በሆነ ፍጥነት ይተረጉማቸዋል። ከዚህም በላይ እነዚህን ምልክቶች በመዝገቡ ውስጥ ካከማቻቸው ዝርዝር መረጃዎች ጋር ያዛምዳቸዋል። በመሆኑም የሆነ ነገር ሲሸተን፣ ለረጅም ጊዜ ረስተነው የነበረ አንድ ክንውን ወይም ሁኔታ ወዲያውኑ ወደ አእምሯችን ሊመጣ ይችላል። በተጨማሪም አንድ የምታውቀውን ነገር በጨረፍታ ብቻ እንኳ ብትመለከት ለምሳሌ የድመትህን ጅራት ጫፍ ብታይ አእምሮህ ያላየሃቸውን ዝርዝር መረጃዎች አሟልቶ ስለሚያቀርብልህ ድመትህ በአቅራቢያህ መኖሯን ታውቃለህ።

እርግጥ ነው፣ አእምሮህ የድመትን ምስል፣ የጽጌረዳን መዓዛ፣ ውኃ ሲፈስስ የሚያሰማውን ድምፅ ወይም ፀጉራማ የሆነን ነገር ስትዳስስ የሚሰማህን ስሜት መለየት የቻለው ልክ በኮምፒውተር ላይ መረጃ እንደሚጫነው እነዚህ ነገሮች አስቀድመው ስለተጫኑለት አይደለም። አእምሮህ እነዚህን ነገሮች ማገናዘብ የቻለው በጊዜ ሂደት ስለተማረው ነው። ይህ እውነታ ይበልጥ ግልጽ የሚሆንልን ዓይነ ስውር ሆነው የተወለዱ ሰዎች፣ ምናልባትም በቀዶ ሕክምና አማካኝነት የማየት ችሎታቸው ሲመለስላቸው የሚፈጠረውን ሁኔታ ስንመለከት ነው። የእነዚህ ሰዎች አእምሮ በዓይናቸው በኩል የሚጎርፉለትን ምልክቶች እንዴት እንደሚተረጉም መማር ያስፈልገዋል። ታዲያ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች እንዴት ይሆናሉ?

እነዚህ ሰዎች ብዙም ሳይቆዩ ቀለምን፣ እንቅስቃሴንና ያልተወሳሰቡ ነገሮችን የመለየት ችሎታ ያዳብራሉ። ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ የሚኖራቸው መሻሻል ይለያያል። ልጆች፣ በተለይ በጣም ትንንሾች ከሆኑ በደንብ መማራቸውን ይቀጥላሉ። በትልልቅ ሰዎች ረገድ ግን ሁኔታው እንዲህ አይደለም። የሰዎችን ፊት አስታውሰው የመለየት ችሎታቸው እንኳ በጣም ደካማ ነው። በካሊፎርኒያ የቴክኖሎጂ ተቋም ውስጥ የሚገኘው የኮች ላቦራቶሪ እንደገለጸው “እይታቸው የተመለሰላቸው” አዋቂዎች ብዙውን ጊዜ “መጀመሪያ ላይ ከፍተኛ ደስታ ቢሰማቸውም የጠበቁት ሳይሆን በመቅረቱ ብስጭት ስለሚያድርባቸውና በማየት ችሎታቸው ግራ ስለሚጋቡ አብዛኛውን ጊዜ በከባድ የመንፈስ ጭንቀት ይዋጣሉ።”

እነዚህ እውነታዎች፣ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት የፈጸማቸው ፈውሶች ምን ነገሮችን እንደሚጨምሩ ሙሉ በሙሉ ለመረዳት ያስችሉናል። ማየትና መስማት የተሳናቸው ሰዎች ማየትና መስማት ከመቻላቸውም በላይ በዙሪያቸው የሚያዩአቸውን ነገሮችና የሚሰሟቸውን ድምፆች ለይተው ማወቅ ይችሉ ነበር። በተመሳሳይም ዲዳዎች እንደ ማንኛውም ሰው መናገር ችለው ነበር፤ በተለይ ደግሞ ሲወለዱ ጀምሮ ዲዳ የነበሩ ሰዎች ይህን ማድረግ መቻላቸው በጣም አስደናቂ ነገር ነው። (ማቴዎስ 15:30፤ ማርቆስ 8:22-25፤ ሉቃስ 7:21, 22) ደግሞም ኢየሱስ ከፈወሳቸው ዓይነ ስውራን መካከል አንዱም ቢሆን በመንፈስ ጭንቀት እንዳልተዋጠ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እንዲያውም ኢየሱስ ከፈወሳቸው ሰዎች አንዱ ኢየሱስን ይጠሉት ለነበሩት ሃይማኖታዊ መሪዎች እንደሚከተለው ብሎ በመናገር በድፍረት ለኢየሱስ ተከራክሮለታል፦ “ዓይነ ስውር ሆኖ የተወለደን ሰው ዓይኖች የከፈተ አለ ሲባል ከጥንት ዘመን ጀምሮ ተሰምቶ አይታወቅም። ይህ ሰው ከአምላክ ባይሆን ኖሮ ምንም ነገር ሊያደርግ አይችልም ነበር።”—ዮሐንስ 9:1-38

በሚቀጥለው ርዕስ ላይ እንደ ድፍረትና ፍቅር ስላሉት የሰው ልጆች የሚያንጸባርቋቸው ባሕርያት እንመረምራለን። እንዲህ ያሉትን ባሕርያት ከእንስሳት በላቀ ደረጃ ሰዎች ማንጸባረቅ የሚችሉት ለምን እንደሆነ አስበህ ታውቃለህ? እንደዚህ ያሉት የሰው ልጆች የሚያሳዩአቸው ልዩ ባሕርያት፣ ሰዎች በዝግመተ ለውጥ አማካኝነት እየተሻሻሉ የመጡ እንስሳት እንደሆኑ ሊያረጋግጡ ለሚፈልጉ ግለሰቦች ትልቅ መሰናክል እንደፈጠሩባቸው ምንም ጥርጥር የለውም።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

አስደናቂ የሆነው አንጎልህ

አንጎልህ እንደ መዳሰስ፣ መስማት፣ ማየትና ማሽተት ያሉት የስሜት ሕዋሶቻችን የሚልኳቸውን መልእክቶች የሚመዘግበው እንዴት ነው? ይህ ለሳይንስ ሊቃውንት እንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል። ጄራልድ ሽሮደር የተባሉ የሳይንስ ተመራማሪ “አሁን የምታነባቸውን ቃላት እንዴት ልታያቸው እንደቻልክ የሚጠቁም ፍንጭ በአንጎልህ ውስጥ አይታይም” ብለዋል።

አክለውም “አንጎላችን ሥራውን ስለሚያከናውንበት አስደናቂ መንገድ ያገኘነው እውቀት ከዚህ በፊት ጨርሶ ያላሰብነው ሲሆን ይህም ሕይወት እንዲሁ በአጋጣሚ በዝግመተ ለውጥ እንደመጣ የሚገልጸውን ጽንሰ ሐሳብ አጠያያቂ አድርጎታል” በማለት ጽፈዋል። በመቀጠልም “ዳርዊን ሕይወት ባላቸው ነገሮች ላይ ስለሚታየው ጥበብ አውቆ ቢሆን ኖሮ ከዚህ ፍጹም የተለየ ጽንሰ ሐሳብ ያመነጭ እንደነበር እተማመናለሁ” ብለዋል።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ/​ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

እጃችንን የሚቆጣጠሩ ጡንቻዎች

የኮርቻ ቅርጽ ያለው መገጣጠሚያ

አስደናቂ አወቃቀር ያላቸው አጥንቶች

ፈጣን መልእክት አስተላላፊ የሆነው የጣት ጫፍ

[ሥዕል]

እጆቻችን ብዙ ነገር መሥራት የሚችሉ የሆኑት ለምንድን ነው?

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አእምሮህ በስሜት ሕዋሳት በኩል የሚጎርፉለትን ምልክቶች የሚተረጉም ከመሆኑም ሌላ እነዚህን ምልክቶች በመዝገቡ ውስጥ ካከማቻቸው ዝርዝር መረጃዎች ጋር ያዛምዳቸዋል