በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ሰዎች የኢየሱስን ተከታዮች የሚጠሏቸው ለምንድን ነው?

ሰዎች የኢየሱስን ተከታዮች የሚጠሏቸው ለምንድን ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

ሰዎች የኢየሱስን ተከታዮች የሚጠሏቸው ለምንድን ነው?

“ሰዎች ለመከራ አሳልፈው ይሰጧችኋል፣ ይገድሏችኋል እንዲሁም በስሜ ምክንያት በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።” ​—ማቴዎስ 24:9

ኢየሱስ እነዚህን ቃላት የተናገረው በጭካኔ ከመገደሉ ከጥቂት ቀናት በፊት ነበር። ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ለታማኝ ሐዋርያቱ “እኔን ስደት አድርሰውብኝ ከሆነ እናንተንም ስደት ያደርሱባችኋል” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 15:20, 21) ይሁን እንጂ ኢየሱስን የሚታዘዙና እሱን ለመምሰል የሚጥሩ ሰዎች በሌሎች ዘንድ የሚጠሉት ለምንድን ነው? ኢየሱስ ድሆችን ለማጽናናትና ለተጨቆኑት ተስፋ ለመስጠት ሲል ራሱን ሳይቆጥብ ሰዎችን ይረዳ ነበር። ታዲያ የእሱን ተከታዮች መጥላት ለምን አስፈለገ?

መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥላቻ ምክንያት የሆኑትን ነገሮች ለይቶ ይገልጻል። እነዚህን ምክንያቶች ስንመረምር በዛሬው ጊዜ የክርስቶስን ዱካ የሚከተሉ ሰዎች በአብዛኛው ልክ እሱ የደረሰበት ዓይነት ተቃውሞ የሚገጥማቸው ለምን እንደሆነ እንመለከታለን።

አንዳንዶች የሚቃወሙት ባለማወቅ ሊሆን ይችላል

ኢየሱስ ለተከታዮቹ “እናንተን የሚገድል ሁሉ ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት እንዳቀረበ አድርጎ የሚያስብበት ሰዓት እየመጣ ነው። ሆኖም እነዚህን ነገሮች የሚያደርጉት አብንም ሆነ እኔን ስላላወቁ ነው” ብሏቸዋል። (ዮሐንስ 16:2, 3) ብዙ አሳዳጆች ኢየሱስ ያገለገለውን አምላክ እንደሚያገለግሉ ቢናገሩም በሐሰት ላይ የተመሠረቱ ሃይማኖታዊ እምነቶችና ወጎች ተጽዕኖ እንዳሳደሩባቸው እሙን ነው። በእርግጥም “በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ አይሁን እንጂ ለአምላክ ቅንዓት [አላቸው]።” (ሮም 10:2) እንደነዚህ ከመሰሉት ተቃዋሚዎች መካከል ጳውሎስ ተብሎ የሚጠራውና በኋላ ላይ ክርስቲያን ሐዋርያ የሆነው የጠርሴሱ ሳኦል ይገኝበታል።

ሳኦል ከፈሪሳውያን ወገን ነበር፤ ፖለቲካዊ ሥልጣንና ከፍተኛ ተሰሚነት የነበራቸው ፈሪሳውያን ደግሞ ክርስትናን ይቃወሙ ነበር። ጳውሎስ “ቀደም ሲል ተሳዳቢ፣ አሳዳጅና እብሪተኛ ነበርኩ” በማለት ተናግሯል። በተጨማሪም “ባለማወቅና ባለማመን [አደረግኩት]” ብሏል። (1 ጢሞቴዎስ 1:12, 13) ይሁን እንጂ ስለ አምላክና ስለ ልጁ እውነቱን ሲያውቅ ወዲያውኑ አካሄዱን አስተካከለ።

በዛሬው ጊዜም ቀደም ሲል አሳዳጆች የነበሩ ተመሳሳይ ለውጥ አድርገዋል። ከዚህም በላይ ከእነዚህ ሰዎች መካከል አንዳንዶቹ እንደ ሳኦል እነሱ ራሳቸው የስደት ዒላማዎች ሆነዋል። ይሁን እንጂ ክፉን በክፉ አልመለሱም፤ ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ “ለጠላቶቻችሁ ፍቅር ማሳየታችሁን እንዲሁም ስደት ለሚያደርሱባችሁ መጸለያችሁን ቀጥሉ” በማለት የሰጣቸውን ምክር ተከትለዋል። (ማቴዎስ 5:44) የይሖዋ ምሥክሮች፣ ቢያንስ የተወሰኑ ተቃዋሚዎች እንደ ሳኦል ልባቸው ይለወጥ ይሆናል ብለው ተስፋ በማድረግ የኢየሱስን ምክር ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ያደርጋሉ።

አንዳንዶች የሚቃወሙት ስለሚቀኑ ነው

ብዙዎች ኢየሱስን የተቃወሙት ቅናት ስላደረባቸው ነው። ሮማዊው ገዥ ጳንጥዮስ ጲላጦስም “የካህናት አለቆች [ኢየሱስ እንዲገደል] አሳልፈው የሰጡት በቅናት ተነሳስተው እንደሆነ ያውቅ” ነበር። (ማርቆስ 15:9, 10) የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች በኢየሱስ ላይ ቅናት ያደረባቸው ለምን ነበር? አንዱ ምክንያት የሃይማኖት መሪዎቹ የሚንቁት ተራው ሕዝብ ኢየሱስን ይወደው ስለነበር ነው። ፈሪሳውያን “ዓለሙ ሁሉ ግልብጥ ብሎ ተከትሎታል” በማለት በምሬት ተናግረዋል። (ዮሐንስ 12:19) ከጊዜ በኋላ ብዙ ሰዎች የኢየሱስ ተከታዮች ላከናወኑት ስብከት አዎንታዊ ምላሽ በሰጡ ጊዜም ሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎቹ እንደገና “በቅናት ተሞልተው” በእነዚህ ወንጌላውያን ላይ ተቃውሞና ስደት አስነስተውባቸዋል።​—የሐዋርያት ሥራ 13:45, 50

ሌሎች ተቃዋሚዎች ደግሞ የአምላክ አገልጋዮች ባላቸው ጥሩ ምግባር ይናደዳሉ። ሐዋርያው ጴጥሮስ የእምነት አጋሮቹ ለሆኑት ክርስቲያኖች “ይህን በመሰለው ያዘቀጠ ወራዳ ሕይወት ከእነሱ ጋር መሮጣችሁን ስለማትቀጥሉ ይደነቃሉ እንዲሁም ይሰድቧችኋል” ብሏቸዋል። (1 ጴጥሮስ 4:4) እንዲህ ያለው አሉታዊ አስተሳሰብ በዛሬው ጊዜም ሊታይ ይችላል። እርግጥ ነው፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች መጥፎ ምግባር ከመፈጸም ቢቆጠቡም ራሳቸውን በማመጻደቅ ከሌሎች የበለጡ እንደሆኑ ለማሳየት አይሞክሩም። ደግሞም ራስን ማመጻደቅ ክርስቲያናዊ ባሕርይ አይደለም፤ ምክንያቱም ሁሉም ሰው ኃጢአተኛ ስለሆነ የአምላክ ምሕረት ያስፈልገዋል።​—ሮም 3:23

‘የዓለም ክፍል ባለመሆናቸው’ ይጠላሉ

መጽሐፍ ቅዱስ “ዓለምንም ሆነ በዓለም ውስጥ ያሉትን ነገሮች አትውደዱ” ይላል። (1 ዮሐንስ 2:15) ሐዋርያው ዮሐንስ የጠቀሰው የትኛውን ዓለም ነው? ከአምላክ የራቀውንና በሰይጣን የሚገዛውን የሰው ዘር ዓለም ነው። ሰይጣን “የዚህ ዓለም አምላክ” ነው።​—2 ቆሮንቶስ 4:4 አዲሱ መደበኛ ትርጉም፤ 1 ዮሐንስ 5:19

የሚያሳዝነው ነገር፣ ዓለምንና የዓለምን መጥፎ መንገዶች የሚወዱ አንዳንድ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት መሠረት ሕይወታቸውን ለመምራት የሚጥሩ ሰዎችን ይቃወማሉ። በመሆኑም ኢየሱስ ለሐዋርያቱ “የዓለም ክፍል ብትሆኑ ኖሮ ዓለም የራሱ የሆነውን በወደደ ነበር። አሁን ግን እኔ ከዓለም መረጥኳችሁ እንጂ የዓለም ክፍል ስላልሆናችሁ ከዚህ የተነሳ ዓለም ይጠላችኋል” ብሏቸዋል።​—ዮሐንስ 15:19

ሰዎች የይሖዋ አገልጋዮችን የሚጠሏቸው ሙስና፣ የፍትሕ መዛባትና ዓመፅ ከነገሠበት በሰይጣን ከሚገዛው ዓለም ጋር ባለመተባበራቸው ምክንያት መሆኑ ምንኛ የሚያሳዝን ነው! ብዙ ቅን ሰዎች በዓለም ላይ ያለውን ሁኔታ ለማሻሻል ልባዊ ፍላጎት ቢኖራቸውም በዓይን የማይታየው የዚህ ዓለም ገዥ የሚያሳድረውን ተጽዕኖ ማስወገድ አይችሉም። ሰይጣንን ማስወገድ የሚችለው ይሖዋ አምላክ ብቻ ሲሆን ወደፊት በእሳት የማቃጠል ያህል መሉ በሙሉ ይደመስሰዋል!​—ራእይ 20:10, 14

ይህ አስደናቂ ተስፋ የይሖዋ ምሥክሮች በመላው ዓለም የሚሰብኩት ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው የአምላክ ‘መንግሥት ምሥራች’ አቢይ ክፍል ነው። (ማቴዎስ 24:14) አዎን፣ የይሖዋ ምሥክሮች በምድር ላይ ዘላቂ ሰላምና ደስታ የሚያመጣው በክርስቶስ የሚተዳደረው የአምላክ መንግሥት ብቻ እንደሆነ በጥብቅ ያምናሉ። (ማቴዎስ 6:9, 10) በመሆኑም ከሰው ይልቅ የአምላክን ሞገስ ማግኘት ትልቅ ዋጋ እንደሚሰጠው ስለሚያምኑ የመንግሥቱን ምሥራች ማወጃቸውን ይቀጥላሉ።

ይህን አስተውለኸዋል?

● የጠርሴሱ ሳኦል የክርስቶስን ተከታዮች ይቃወም የነበረው ለምንድን ነው?​—1 ጢሞቴዎስ 1:12, 13

● ከኢየሱስ ጠላቶች መካከል አንዳንዶቹ ተቃዋሚ እንዲሆኑ ያነሳሳቸው የትኛው መጥፎ ዝንባሌ ነበር?​—ማርቆስ 15:9, 10

● እውነተኛ ክርስቲያኖች ዓለምን የሚመለከቱት እንዴት ነው?​—1 ዮሐንስ 2:15

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች የአምላክን መንግሥት ምሥራች በመስበካቸው ምክንያት በ1945 በኩዊቤክ፣ ካናዳ የሕዝብ ዓመፅ አጋጥሟቸዋል

[የሥዕሉ ምንጭ]

Courtesy Canada Wide