እምነት ልትጥልበት የምትችል መጽሐፍ—ክፍል 7
ሰባተኛው የዓለም ኃያል መንግሥት
ይህ ርዕስ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ የተገለጹትን ሰባት የዓለም ኃያላን መንግሥታት በተመለከተ “ንቁ!” መጽሔት ላይ ከሚወጡት ሰባት ተከታታይ ርዕሶች መካከል የመጨረሻው ነው። ዓላማውም መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበትና በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ መጽሐፍ እንደሆነ እንዲሁም ተስፋ የሚፈነጥቅ መልእክት እንደያዘ ማሳየት ነው፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ተስፋ፣ ጭካኔ የተሞላበት የሰው ልጆች አገዛዝ ያስከተለው መከራና ሥቃይ እንደሚያከትም ይገልጻል።
የምንኖረው በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ከተገለጹት የዓለም ኃያላን መንግሥታት መካከል ሰባተኛው መንግሥት ብቅ በሚልበት ጊዜ በመሆኑ ዘመናችን በጣም ልዩና ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ነው። ከዚህም በላይ እንደሚመጣ አስቀድሞ ከመተንበዩ ውጪ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሌላ ታሪክ ያልተጻፈለት ይህ መንግሥት ብቻ ነው፤ የቀደሙት ስድስት ኃያላን መንግሥታት ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግቦልናል። ሰባቱን የዓለም ኃያላን መንግሥታት ወይም “ነገሥታት” በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው በማለት አስቀድሞ ተናግሮ ነበር፦ “ሰባት ነገሥታት ናቸው፦ አምስቱ ወድቀዋል፤ አንዱ አለ፤ ሌላው ደግሞ ገና አልመጣም፤ በሚመጣበት ጊዜ ግን ለአጭር ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል።” *—ራእይ 17:10
ይህ ትንቢት ከ1,900 ዓመታት በፊት በተጻፈበት ጊዜ ከሰባቱ “ነገሥታት” ወይም ፖለቲካዊ ግዛቶች መካከል አምስቱ ‘ወድቀው’ ነበር። እነዚህ ነገሥታት ግብፅ፣ አሦር፣ ባቢሎን፣ ሜዶ ፋርስና ግሪክ ነበሩ። “አንዱ አለ” የተባለው ሮም ነው። ይሁን እንጂ ሮም ለዘላለም አይገዛም። አንድ ሌላ መንግሥት ይነሳል፤ ትንቢቱ ስለዚህ መንግሥት ሲናገር “ገና አልመጣም” ብሏል። በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ላይ እንደተገለጸው ሰባተኛው ‘ንጉሥ’ በዓለም መድረክ ላይ ብቅ ብሏል! ይህ መንግሥት ማን ነው? ለዘላለም ይገዛ ይሆን? ካልሆነስ ከዓለም መድረክ የሚወገደው እንዴት ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የማያሻማ መልስ ይሰጠናል።
እምነት የሚጣልበት ትንቢት
ሰባተኛው የዓለም ኃያል መንግሥት በዓለም ላይ ብቅ ማለት የጀመረው በሮም መንግሥት ሰሜናዊ ምዕራብ ጫፍ ላይ ትገኝ የነበረችው እንግሊዝ ኃያል እየሆነች ስትመጣ ነበር። በደሴት ላይ ያለችው ይህች አገር በ1760ዎቹ ዓመታት ኃያሏ የብሪታንያ መንግሥት ሆነች። ብሪታንያ ብልጽግናዋ እየጨመረና ይበልጥ ኃያል እየሆነች ስትሄድ በ19ኛው መቶ ዘመን በምድር ላይ በሀብትም ሆነ በኃይል ተወዳዳሪ የሌላት መንግሥት ሆነች። አንድ የማመሳከሪያ ጽሑፍ “የብሪታንያ ግዛት . . . በዓለም ላይ ከታዩት መንግሥታት ሁሉ ይልቅ በጣም ሰፊ ነበር” ብሏል። በብሪታንያ ግዛት ውስጥ “372 ሚሊዮን ነዋሪዎች የነበሩ ሲሆን [ግዛቷ] 28 ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር ይሸፍን ነበር።”
ይሁን እንጂ አንደኛው የዓለም ጦርነት (ከ1914 እስከ 1918) ብሪታንያ፣ የቀድሞ ቅኝ ግዛቷ ከነበረችው ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ልዩ የሆነ ጥምረት እንድትመሠርት አነሳሳት። ታዲያ ውጤቱ ምን ሆነ? ኃያሉ የብሪታንያ መንግሥት፣ በብዙ መንገዶች ኅብረት ያላቸውን ሁለት እንግሊዝኛ “ትኩረት የሚስብ ኅብረት” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።
ተናጋሪ አገራት ያቀፈ የዓለም ኃያል መንግሥት ለሆነውና እስከ ዛሬ ድረስ ለዘለቀው የአንግሎ አሜሪካ ኅብረት ቦታውን ለቀቀ።—በራእይ 17:10 ላይ የሚገኘው ትንቢት በዳንኤል መጽሐፍ ውስጥ የሚገኝን ሌላ ትንቢት ለመረዳት የሚያስችል መረጃ ይሰጠናል። አምላክ ለባቢሎኑ ንጉሥ ለናቡከደነፆር በራእይ ስላሳየው “ታላቅ ምስል” ዳንኤል ጽፏል። (ዳንኤል 2:28, 31-43) ዳንኤል፣ የምስሉ የተለያዩ የአካል ክፍሎች በጊዜው ከነበረው የዓለም ኃያል መንግሥት ማለትም ከባቢሎን ጀምሮ በየተራ የሚነሱ ፖለቲካዊ ኃይላትን እንደሚያመለክቱ ለዚህ ንጉሥ ነግሮታል። (ከዚያ በፊት የነበሩት ኃያላን መንግሥታት ይኸውም ግብፅና አሦር አልፈዋል።) ታሪክ ከዚህ በታች ያለውን ሐሳብ እውነተኝነት አረጋግጧል።
ከወርቅ የተሠራው ራስ የባቢሎንን መንግሥት ያመለክታል።
ከብር የተሠሩት ደረቱና ክንዶቹ ሜዶ ፋርስን ያመለክታሉ።
ከነሐስ የተሠሩት ሆዱና ጭኖቹ የጥንቷን ግሪክ ያመለክታሉ።
ከብረት የተሠሩት ቅልጥሞቹ የሮምን መንግሥት ያመለክታሉ።
ከብረትና ከሸክላ የተሠሩት እግሮቹ የአንግሎ አሜሪካ ጥምር ኃያል መንግሥት በሚኖርበት ዘመን የሚታየውን አንድነት የሌለው ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ ያመለክታሉ።
በራእይ 17:10 መሠረት ሰባተኛው የዓለም ኃያል መንግሥት “ለአጭር ጊዜ ሊቆይ ይገባዋል።” ይህ አጭር ጊዜ ምን ያህል ርዝመት ይኖረዋል? ይህ መንግሥት ከዓለም መድረክ የሚወገደው እንዴት ነው? ከዚያ በኋላስ ምን ይሆናል? ዳንኤል ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጠናል።
እምነት ልትጥልበት የምትችል ተስፋ
ዳንኤል ከላይ የተጠቀሰውን ምስል ፍቺ ካብራራ በኋላ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “አንድ ድንጋይ የሰው እጅ ሳይነካው [ከተራራ] ተፈንቅሎ ወረደ፤ ከብረትና ከሸክላ የተሠሩትን የምስሉን እግሮች መታቸው፤ አደቀቃቸውም። (ዳንኤል 2:34) ይህ አስደናቂ ክንውን ምን ትርጉም ይኖረዋል?
ዳንኤል በመቀጠል እንዲህ ብሏል፦ “በነዚያ [በመጨረሻዎቹ] ነገሥታት ዘመን፣ የሰማይ አምላክ ፈጽሞ የማይፈርስና ለሌላም ሕዝብ የማይሰጥ መንግሥት ይመሠርታል፤ እነዚያን [ሰብዓዊ] መንግሥታት ሁሉ ያደቃል፤ እስከ መጨረሻውም ያጠፋቸዋል፤ ይህ መንግሥት ራሱ ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።” * (ዳንኤል 2:44, 45) እስቲ የሚከተሉትን አስፈላጊ ነጥቦች ልብ በል፦
-
በትልቅ ድንጋይ የተመሰለውን ድል አድራጊ መንግሥት ‘የሚመሠርተው’ “የሰው እጅ” ሳይሆን አምላክ ነው። በመሆኑም ይህ መንግሥት የአምላክ መንግሥት መባሉ ተገቢ ነው።
-
የአምላክ መንግሥት፣ ሰባተኛውን የዓለም ኃያል መንግሥት ጨምሮ ሁሉንም ሰብዓዊ መንግሥታት “ያደቃል።” ለምን? ሁሉም ሥልጣናቸውን ለማስረከብ እምቢተኛ ከመሆናቸውም ሌላ በመጨረሻው ታላቅ ጦርነት ላይ ሐር ማጌዶን ወይም አርማጌዶን በሚባል ምሳሌያዊ ቦታ ከአምላክ ጋር ውጊያ ይገጥማሉ። በዚህ ጦርነት ላይ ‘የዓለም ነገሥታት ራእይ 16:13, 14, 16
ሁሉ’ እንደሚካፈሉ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።— -
ሰባተኛውን የዓለም ኃያል መንግሥት ጨምሮ ሰብዓዊ መንግሥታት በሙሉ አላፊ ናቸው፤ ከዚህ በተቃራኒ ግን የአምላክ መንግሥት “ፈጽሞ የማይፈርስ” መስተዳድር ነው። በተጨማሪም የአምላክ መንግሥት መላውን ምድር ይገዛል።—ዳንኤል 2:35, 44
በዚህ አምድ ሥር በሚወጡት ተከታታይ ርዕሶች መጀመሪያ ላይ የተጠቀሰው በዘፍጥረት 3:15 ላይ የሚገኘው ትንቢት፣ የአምላክ ተቃዋሚዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሲጠፉ አስደናቂ ፍጻሜውን ያገኛል። የሴቲቱ ዘር ማለትም ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌያዊውን እባብ ይኸውም ሰይጣንን እንዲሁም ዘሩን ያደቅቃቸዋል። (ገላትያ 3:16) የሰይጣን ዘር፣ የእሱን የክፋት መንገዶች የተቀበሉትን እንዲሁም ለአምላክና ለክርስቶስ ከመገዛት ይልቅ የሰው ልጆች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደራቸውን የሚደግፉትን ሰዎች በሙሉ ያጠቃልላል።—መዝሙር 2:7-12
ይህ ደግሞ በጣም አስፈላጊ ወደሆነ አንድ ጥያቄ ይመራናል፦ ይህ የመጨረሻ ጥፋት የሚመጣው መቼ ነው? ‘ድንጋዩ’ ይኸውም የአምላክ መንግሥት ሰብዓዊ መንግሥታትን ከነርዝራዣቸው የሚያስወግደው መቼ ነው? መጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻውን ቀን ለማወቅ ስለሚረዳን “ምልክት” የሚናገረው ሐሳብ ለዚህ ጥያቄ መልስ ይሰጠናል።—ማቴዎስ 24:3
‘ምልክቱን’ አስተውል!
ከመጨረሻው ቀን ምልክቶች መካከል ዓለም አቀፍ ጦርነት፣ “ታላላቅ የምድር ነውጦች፣” “ቸነፈር” እንዲሁም ከባድ “የምግብ እጥረት” ይገኙበታል። (ሉቃስ 21:10, 11፤ ማቴዎስ 24:7, 8፤ ማርቆስ 13:8) በተጨማሪም “በመጨረሻዎቹ ቀኖች” በኅብረተሰቡ ውስጥ ከባድ የሆነ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ውድቀት ይታያል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) ታዲያ “እነዚህ ነገሮች ሁሉ” ተፈጽመዋል? (ማቴዎስ 24:8) አዎን፣ እንዲያውም የእነዚህ ትንቢቶች ፍጻሜ ብዙ ሰዎች ስለወደፊቱ ጊዜ ስጋት እንዲያድርባቸው አድርጓል። ዘ ግሎብ ኤንድ ሜይል የተባለው ጋዜጣ እንዲህ ብሏል፦ “ከፍተኛ ተደማጭነት ካላቸው የሳይንስና የማኅበረሰብ ሊቃውንት መካከል አንዳንዶቹ የሰው ልጅ ወደ ፍጻሜው በመቃረብ ላይ እንዳለ የሚገልጽ አስፈሪ ትንቢት በመናገር ላይ ናቸው።”
ይሁን እንጂ ይህ ትንበያቸው ትልቅ ቦታ ከሚሰጠው አንድ ነጥብ አንጻር የተሳሳተ ነው፤ የሰው ዘር በአጠቃላይ ከሕልውና ውጪ አይሆንም። የአምላክ መንግሥት ጣልቃ በመግባት የሚወስደው እርምጃ የሰው ዘር ሙሉ በሙሉ እንደማይጠፋ ዋስትና ይሆናል! ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ መጨረሻው ቀን ምልክት ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለሕዝቦች ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።” (ማቴዎስ 24:14) ይህ ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው እንዴት ነው?
የይሖዋ ምሥክሮች ከ230 በሚበልጡ አገሮች የአምላክን መንግሥት ምሥራች በማወጅ ላይ ናቸው። እንዲያውም ዋነኛ መጽሔታቸው የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ የሚል ርዕስ አለው፤ ይሖዋ የአምላክ የግል ስም ነው። (ዘፀአት 6:3 የ1879 ትርጉም) የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰጡት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት፣ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ግለሰቦችና ቤተሰቦች መጥፎ የሆነ አኗኗራቸውን ትተው ከአምላክ መሥፈርቶች ጋር የሚስማማ ንጹሕ ሥነ ምግባር የሚንጸባረቅበትና ሰላማዊ የሆነ አኗኗር እንዲከተሉ በመርዳት ላይ ነው። (1 ቆሮንቶስ 6:9-11) በመሆኑም በመላው ምድር የሚኖሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የአምላክ መንግሥት በሰው ልጆች ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ በመግባት እርምጃ በሚወስድበት ጊዜ የአምላክን ጥበቃ እንደሚያገኙ እርግጠኞች ሊሆኑ ችለዋል።
ማቴዎስ 6:10) በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ አምላክን የሚወዱና የሚታዘዙ ሲሆኑ ሕይወት ምን ሊመስል እንደሚችል አስበህ ታውቃለህ? ስለዚያ ጊዜ ሲገለጽ “ምሥራች” መባሉ ተገቢ የሆነው ለምን እንደሆነ ከዚህ በታች ከተዘረዘሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች መረዳት ትችላለህ።
በእርግጥም እነዚህ ሰዎች ብዙውን ጊዜ የጌታ ጸሎት በመባል የሚታወቀው ክርስቶስ የሰጠው የናሙና ጸሎት ፍጻሜውን ሲያገኝ ይመለከታሉ፤ ጸሎቱ በከፊል “መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ በሰማይ እየሆነ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ ይሁን” ይላል። (የአምላክ ፈቃድ በምድር በሚሆንበት ጊዜ . . .
-
አምላክ ጦርነትን በማስወገድ ብቻ ሳይወሰን እውነተኛ ሰላም እንዲሰፍን ያደርጋል። ይሖዋ “ከዳር እስከ ዳር ጦርነትን ከምድር ያስወግዳል፤ ቀስትን ይሰብራል፤ ጦርን ያነክታል፤ ጋሻንም በእሳት ያቃጥላል።” (መዝሙር 46:8, 9) “ገሮች . . . ምድርን ይወርሳሉ፤ በታላቅ ሰላምም ሐሤት ያደርጋሉ።”—መዝሙር 37:11
-
ሁሉም ሰው በቂ ምግብ ያገኛል። “በምድሪቱ ላይ እህል ይትረፍረፍ፤ በተራሮችም ዐናት ላይ ይወዛወዝ።”—መዝሙር 72:16
-
ሁሉም ሰው ፍጹም ጤንነት ይኖረዋል። “‘ታምሜአለሁ’ የሚል አይኖርም።”—ኢሳይያስ 33:24
-
ሁሉም ሰው ምቹ መኖሪያ ይኖረዋል። “ሰዎች ቤት ይሠራሉ፤ በውስጡም ይኖራሉ፤ ወይንን ይተክላሉ፤ ፍሬውንም ይበላሉ። ከእንግዲህ ለሌሎች መኖሪያ ቤት አይሠሩም፤ ወይም ሌላው እንዲበላው አይተክሉም።”—ኢሳይያስ 65:21, 22
-
ማንኛውም ዓይነት መከራና ሥቃይ ይወገዳል። “የአምላክ ድንኳን ከሰዎች ጋር ነው፤ . . . እሱም እንባን ሁሉ ከዓይኖቻቸው ላይ ይጠርጋል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።”—ራእይ 21:3, 4
እነዚህ ተስፋዎች አስደሳች እንደሆኑ ይሰማሃል? ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ይበልጥ እንድትመረምር ያበረታቱሃል። እንዲህ ስታደርግ ጭካኔ የተሞላበት የሰው ልጆች አገዛዝ ሊያበቃ እንደሆነ የሚያሳዩ ተጨማሪ ማስረጃዎችን ትመለከታለህ። ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ እምነት ልትጥልበት የምትችል እንዲሁም በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፈ መጽሐፍ እንደሆነ ትገነዘባለህ።—2 ጢሞቴዎስ 3:16 *
^ አን.4 በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱት መንግሥታት አብዛኛውን ጊዜ በንጉሥ የሚተዳደሩ ነበሩ፤ በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስ እነዚህን መንግሥታት ለማመልከት ብዙውን ጊዜ “ነገሥታት” በሚለው ቃል ይጠቀማል።—ዳንኤል 8:20-22 የ1954 ትርጉም
^ አን.18 በሰማይ ስለሚገኘው የአምላክ መንግሥት የበለጠ መረጃ ለማግኘት በይሖዋ ምሥክሮች የተዘጋጀውን ትክክለኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ምንድን ነው? የተባለውን መጽሐፍ ምዕራፍ 8 እና 9 ተመልከት።
^ አን.35 ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ይበልጥ ለማወቅ ከፈለግህ በአካባቢህ ያሉትን የይሖዋ ምሥክሮች አነጋግራቸው። አሊያም ደግሞ በዚህ መጽሔት ገጽ 5 ላይ ካሉት አድራሻዎች ለአንተ አመቺ ወደሆነው መጻፍ ወይም www.watchtower.org የሚለውን ድረ ገጻችንን መጎብኘት ትችላለህ።