በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከንፈሮችህ “ብርቅ ጌጦች” ናቸው?

ከንፈሮችህ “ብርቅ ጌጦች” ናቸው?

ከንፈሮችህ “ብርቅ ጌጦች” ናቸው?

● “ወርቁም አለ፤ ቀዩም ዕንቍ ተትረፍርፎአል፤ ዕውቀት የሚናገሩ ከንፈሮች ግን ብርቅ ጌጦች ናቸው” በማለት በጥንት ዘመን የኖረው ንጉሥ ሰለሞን ጽፏል። (ምሳሌ 20:15) ወርቅ ምንጊዜም ቢሆን ከፍተኛ ዋጋ ያለው ነገር ነው፤ በሰለሞን ዘመን ደግሞ ቀይ እንቁዎችም በጣም ተፈላጊ ነበሩ። ሆኖም ከንፈራችን ከወርቅና ከእንቁም የበለጠ ውድ ሊሆን ይችላል። እንዴት? ይህ የሚሆነው በውበቱ ሳይሆን በሚያፈልቃቸው ቃላት ነው።

ብርቅ ወይም ውድ የሆኑ ከንፈሮች ጥሩነት፣ ደግነትና ፍቅር የሚንጸባረቅባቸው ቃላትን ያፈልቃሉ። ደግሞም እነዚህ ከንፈሮች “ዕውቀት የሚናገሩ” እንደመሆናቸው መጠን መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተገለጸው መሠረት ስለ አምላክ እውነቱን ይናገራሉ። ይህ ጥንታዊ መጽሐፍ በጥበብ፣ ስለ ፈጣሪያችን በሚገልጽ እውነትና ለሕይወት በሚጠቅም ግሩም ምክር የተሞላ ነው።​—ዮሐንስ 17:17

የሚያሳዝነው ብዙ ሰዎች ስለ አምላክ እውነት ያልሆኑ ነገሮችን በመናገር ከንፈሮቻቸውን አላግባብ ይጠቀማሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በአብዛኛው በዓለማችን ላይ ለሚታየው የፍትሕ መዛባትና መከራ መንስኤው የሰው ልጆች ሆነው ሳለ አንዳንዶች አምላክን ይወቅሳሉ። ምሳሌ 19:3 እንዲህ ስላሉት ሰዎች ሲናገር “ሰው በራሱ ተላላነት ሕይወቱን ያበላሻል፤ በልቡ ግን እግዚአብሔርን ያማርራል” ይላል።

ሌሎች ደግሞ የሽንገላ ቃላት በመናገር ወይም ሐሜት በመንዛት ሌላው ቀርቶ የሰዎችን ስም በማጥፋት የከንፈራቸውን ዋጋማነት ያራክሱታል። ምሳሌ 26:23 “ክፋትን በልብ ቋጥሮ ለስላሳ ቃል የሚናገር ከንፈር፣ በብር ፈሳሽ እንደ ተለበጠ የሸክላ ዕቃ ነው” በማለት በጣም ገላጭ የሆነ ምሳሌያዊ አነጋገር ተጠቅሟል። አንድን የሸክላ ዕቃ በብር ፈሳሽ በመለበጥ ሸክላነቱ እንዳይታይ ማድረግ እንደሚቻል ሁሉ አንድ ሰው ከልቡ እንደሆነ አልፎ ተርፎም በቅንነት እየተናገረ እንደሆነ በማስመሰል በሌላ አባባል ‘ለስላሳ ቃል በሚናገር ከንፈሩ’ በመጠቀም ‘ልቡ ክፋት የቋጠረ’ መሆኑ እንዳይታወቅበት ሊያደርግ ይችላል።​—ምሳሌ 26:24-26

እርግጥ ነው፣ እንዲህ ዓይነቱ ክፋት ከአምላክ የተሰወረ አይደለም። አምላክ የእኛን እውነተኛ ማንነት ያውቃል! ኢየሱስ ክርስቶስ “በመጀመሪያ ጽዋውንና ሳህኑን ከውስጥ በኩል አጽዳ፤ ከዚያ በኋላ ከውጭ በኩልም ንጹሕ ይሆናል” በማለት የተናገረው ለዚህ ነው። (ማቴዎስ 23:26) የኢየሱስ ቃላት ምንኛ እውነት ናቸው! ከዚህም በላይ ውስጣችን ንጹሕና ከክፋት የጸዳ ከሆነ ብሎም ልባችን በመንፈሳዊ እውነት ከተሞላ አነጋገራችን ይህንኑ የሚያንጸባርቅ ይሆናል። ታዲያ ይህ ምን ውጤት ያስገኛል? ከንፈሮቻችን በተለይ በአምላክ ዓይን ሲታዩ “ብርቅ ጌጦች” ይሆናሉ።

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጠቢብ ከንፈሮች “ብርቅ ጌጦች” ናቸው