በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

ከዓለም አካባቢ

“ድሃ በሆኑ አገሮች የሚኖሩ ሴቶች በእርግዝና ወይም በወሊድ ወቅት የመሞት አጋጣሚያቸው በሀብታም አገሮች ከሚኖሩት ሴቶች 300 ጊዜ ይበልጣል።”​—ቢዝነስወርልድ፣ ፊሊፒንስ

በጀርመን የተደረገ አንድ ጥናት እንዳሳየው በዚያ አገር ከሚኖሩት ከ11 እስከ 15 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ልጆች መካከል 40 በመቶ የሚሆኑት ፀሐይ በምሥራቅ እንደምትወጣ አያውቁም፤ 60 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ ሙሉ ጨረቃ የምትታየው በየአራት ሳምንቱ እንደሆነ አያውቁም።​—ቬልት ኦንላይን፣ ጀርመን

የአርኪኦሎጂ ባለሙያዎች፣ በጥንቷ ጌት አንድ የፍልስጥኤማውያን ቤተ መቅደስ አግኝተዋል። ቤተ መቅደሱን መሃል ላይ ደግፈው የያዙት ሁለት ምሰሶዎች ቆመው የሚታዩ ሲሆን ይህም ስለ ሳምሶን የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ያስታውሰናል፤ ሳምሶን እነዚህን ሁለት ምሰሶዎች በመግፋት ቤተ መቅደሱን አፍርሶታል።​—ዘ ጀሩሳሌም ፖስት፣ እስራኤል

እስያውያን ሙሽሮችን ማስመጣት

ቢዝነስወርልድ የተባለ ኢንተርኔት ላይ የሚወጣ አንድ የፊሊፒንስ ጋዜጣ “ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ እንደ ጃፓንና ደቡብ ኮሪያ ባሉ የበለጸጉ አገሮች የሚኖሩ ወንዶች፣ እንደ ቬትናምና ፊሊፒንስ ካሉት ድሃ [የእስያ አገሮች] ሚስት ለማግባት እየሞከሩ ነው” በማለት ዘግቧል። ከ1995 እስከ 2006 ባሉት ዓመታት የውጭ አገር ሴቶችን ያገቡ ጃፓናውያን ወንዶች ቁጥር በ73 በመቶ ጨምሯል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? “በገንዘብ ረገድ ራሳቸውን ችለው የሚኖሩ የአገሬው ሴቶች መራጭ” እንደሚሆኑ ሪፖርቱ ገልጿል፤ እነዚህ ሴቶች ትዳር ለመመሥረት ያን ያህል ፈቃደኞች አይሆኑም። በአንጻሩ ግን የድሃ አገር ሴቶች፣ በበለጸጉ አገሮች የሚኖሩ አነስተኛ ገቢ ያላቸውን ወንዶች እንኳ ቢያገቡ “የተሻለ ሕይወት የማግኘት ተስፋ” እንደሚኖራቸው ስለሚሰማቸው ከእነዚህ ወንዶች ጋር ትዳር ለመመሥረት ፈቃደኛ ይሆናሉ።

ውስልትናን “ማሻሻል?”

ወንዶችንና ሴቶችን የሚያገናኝና በአምስት አገሮች አገልግሎት የሚሰጥ የኢንተርኔት ድረ ገጽ አገልግሎቱን የሚያስተዋውቀው “ሕይወት አጭር ነው፤ በአንድ አትወሰን” በሚል መፈክር ነው። አወዛጋቢ የሆነው የዚህ ድረ ገጽ መሥራች፣ ድረ ገጹ ሰዎች በፍቅረኛቸው ላይ እንዲወሰልቱ እንደማያነሳሳቸው ገልጿል፤ ይህን ያለበትን ምክንያት ሲያብራራ በዚህ ድረ ገጽ የሚጠቀሙ ሰዎች “ቀድሞውንም ቢሆን ይህን ለማድረግ ወስነዋል” ብሏል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “በፍቅረኛቸው ላይ የሚወሰልቱ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ችግር የሚያጋጥማቸው ጉዳዩ ሲታወቅባቸው ነው። መማገጥ የሚፈልጉ ሰዎች ይህን በድብቅ ማድረግ እንዲችሉ እንረዳቸዋለን።” በተጨማሪም “ውስልትናን እኛ አልፈጠርነውም፤ አሻሻልነው እንጂ” ሲል ተናግሯል። በአሁኑ ጊዜ 6.4 ሚሊዮን የሚሆኑ ሰዎች የዚህ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ናቸው።

የመደነስ ፍላጎት አብሮን የሚፈጠር ነገር ነው?

በእንግሊዝ የሚገኘው የዮርክ ዩኒቨርሲቲ እና በፊንላንድ የሚገኘው የይዌቫስክዌላ ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎች በጋራ ባወጡት ሪፖርት ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “የሰው ልጆች የሰውነታቸውን እንቅስቃሴ ከሚሰሙት ድምፅ ጋር የማቀናጀት፣ ለምሳሌ የሙዚቃን ምት በመከተል እግራቸውን የማንቀሳቀስ ወይም የመደነስ ልዩ ችሎታ አላቸው።” ተመራማሪዎቹ፣ ሕፃናት አፍ ከመፍታታቸው በፊት እንኳ የሙዚቃ ምቶችን በመከተል ከሙዚቃው እኩል ሰውነታቸውን ለማንቀሳቀስ እንደሚሞክሩ ተገንዝበዋል። ምቱን እየተከተሉ ለመንቀሳቀስ የሚያደርጉት ሙከራ በተሳካላቸው መጠን የዚያኑ ያህል ይደሰታሉ። ይህም የሙዚቃ ምቶችን የመረዳትና ከሙዚቃው ጋር የተቀናጀ እንቅስቃሴ የማድረግ ፍላጎት እያደር የምንማረው ነገር ሳይሆን በተፈጥሮ ያገኘነው ነገር እንደሆነ ያሳያል።