በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የወጣቶች ጥያቄ

ሰዎች መጀመሪያ ሲያገኙኝ ለእኔ ጥሩ ግምት እንዲኖራቸው ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?

ሰዎች መጀመሪያ ሲያገኙኝ ለእኔ ጥሩ ግምት እንዲኖራቸው ማድረግ የምችለው እንዴት ነው?

“ይህ ቃለ መጠይቅ አሪፍ የሚሆን ይመስለኛል! የወደፊቱን አለቃዬን ቢሮው ከገባሁ ጀምሮ አንተ እያልኩ ስላነጋገርኩት ዘና ያልኩ ሰው እንደሆንኩ ሳይገነዘብ አይቀርም። እንደሚቀጥረኝ ምንም አልጠራጠርም!”

“ያንን የመሰለ ሲቪ አስገብቶ የነበረው ወጣት ይሄ ነው? ይህንንስ በጭራሽ አልቀጥረውም! ገና ሳይቀጠር እንዲህ የሆነ ሲቀጠርማ እንዴት ሊሆን ነው?”

ፎቶግራፉን ተመልከትና ከላይ የሚገኘውን ሐሳብ አንብብ። አመልካቹ ካደረጋቸው ነገሮች መካከል ቀጣሪው ለእሱ ጥሩ ግምት እንዳይኖረው ያደረጉትን ሦስት ነገሮች መጥቀስ ትችላለህ?

  1. ․․․․

  2. ․․․․․

  3. ․․․․․

 

1. የወጣቱ አለባበስ የሥራ ቃለ መጠይቅ ለማድረግ የሚመጥን አይደለም። 2. አነጋገሩ (ቀጣሪውን አንተ እያለ ማነጋገሩ) ተገቢ አይደለም። 3. የተጠቀመባቸው አካላዊ መግለጫዎች አክብሮት እንደጎደለው ያመለክታሉ።

ከዚህ በፊት በልተህ የማታውቀው ምግብ ቀርቦልሃል እንበል። ምግቡን ትወደው እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ ምን ያህል መጉረስ ያስፈልግሃል? አንዴ ብቻ በመጉረስ ምግቡን ሌላ ጊዜ መብላት ትፈልግ እንደሆነና እንዳልሆነ ሌላው ቀርቶ ከፊትህ የቀረበውን ትጨርሰው እንደሆነና እንዳልሆነ መወሰን ትችላለህ።

ከአንድ ሰው ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ስትገናኝ የሚፈጠረው ሁኔታም ተመሳሳይ ነው። በዚያው ቅጽበት ስለ ሰውየው የሆነ ግምት ያድርብሃል። እሱም በዚያው ቅጽበት ስለ አንተ የሆነ ግምት እንደሚኖረው መዘንጋት አይኖርብህም።

ሥራ፣ ጓደኛ ወይም የትዳር አጋር እየፈለግህ ነው? በዚህ ረገድ ስኬታማ መሆንህ የተመካው ሰዎች መጀመሪያ ሲያገኙህ ስለ አንተ በሚያድርባቸው ግምት ላይ ነው። ሌሎች ስለ አንተ ጥሩ ግምት እንዲኖራቸው በማድረግ ረገድ ስኬታማ ለመሆን ከሰዎች ጋር ካለህ ግንኙነት ጋር በተያያዘ ማሻሻያ ልታደርግባቸው የሚገቡ ሦስት ነገሮችን እንመልከት።

1. አለባበስህ

ተገቢ ይሁንም አይሁን፣ ሰዎች ለመጀመሪያ ጊዜ ሲያዩህ ስለ አንተ የሆነ ግምት የሚወስዱት ከላይ በሚያዩት ነገር ማለትም በውጫዊ ገጽታህ ላይ ተመሥርተው ሊሆን ይችላል። ይሁንና ብዙዎች፣ በሌሎች ዘንድ ጥሩ ግምት ለማግኘት ለሚረዳው ለዚህ ነገር ተገቢውን ትኩረት አይሰጡም። ክላሪሳ * የምትባል አንዲት ወጣት እንዲህ ትላለች፦ “አሁን አሁን ወደ ምግብ ቤት ስትሄዱ እዚያ የምታገኟቸው ሰዎች የለበሱት ልብስ ቀሚስ ይሁን ፒጃማ መለየት ይቸግራል!”

የምትለብሰው ልብስ ለሁኔታው የሚስማማ መሆን እንዳለበት የታወቀ ነው። ለምሳሌ ለሥራ ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ስትሄድ፣ ስትዝናና የምትለብሰውን ልብስ ለብሰህ አትሄድም። ይሁንና ምን ዓይነት ልብስ መልበስ እንደሚገባህ እርግጠኛ ባትሆንስ? በዚህ ጊዜ ወደ ሁለቱም ጽንፎች ባለማዘንበል አስተዋይ መሆንህን ማሳየትህ ጠቃሚ ነው። ተገቢ የሚሆነው አለባበስ የትኛው እንደሆነ እርግጠኛ ካልሆንክ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያለውን አለባበስ መከተልህ ጥሩ ነው።

ይህን ልብ በል፦ አለባበስህና የፀጉር አያያዝህ ልክ እንደ ራጅ ውስጣዊ ማንነትህን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።

“በግብዣ ቦታ ላይ ወጣ ያለ ልብስ የለበሱ ሰዎች ሳይ በተቻለኝ መጠን ከእነሱ ጋር ላለመገናኘት ጥረት አደርጋለሁ። በዚያ ሰዓት ማየት የቻልኩት አለባበሳቸውን ብቻ ቢሆንም አለባበሳቸው ስለ እነሱ መጥፎ ግምት እንዲኖረኝ ያደርጋል።”​ዳያን

መጽሐፍ ቅዱስ ‘ልከኝነትና ማስተዋል’ እንዳለህ የሚያሳይ ‘ሥርዓታማ ልብስ’ እንድትለብስ ይመክራል።​—1 ጢሞቴዎስ 2:9

ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘አለባበሴ ሥርዓታማ ነው ወይስ የተዝረከረከ? ወደፊት ሥራ ሊቀጥረኝ፣ ጓደኛ ሊያደርገኝ ወይም የትዳር አጋር ሊሆነኝ የሚችል ሰው አለባበሴን በማየት “ልከኝነትና ማስተዋል” እንደሚጎድለኝ ያስብ ይሆን?’

የመፍትሔ ሐሳብ፦ ጥሩ አለባበስ እንዳለው የምታስበውን ሰው ምክር ጠይቅ።

2. አነጋገርህ

አነጋገርህ ትሑት ወይም ትዕቢተኛ አሊያም የተረጋጋህ ወይም ቀዥቃዣ መሆን አለመሆንህን ይጠቁማል። ተቃራኒ ፆታ ካላቸው ወጣቶች ጋር ስትሆን የምትናገረው ነገር ስለ አንተ ጥሩ ግምት እንዲያድርባቸው በማድረግ ረገድ የሚጫወተው ሚና እንዳለ አትዘንጋ። ቫለሪ የተባለች አንዲት ወጣት “ከአንድ ወጣት ጋር ሳወራ የሚናገረው ስለ ራሱ ብቻ ከሆነ ያናድደኛል” በማለት ተናግራለች። አክላም እንዲህ ብላለች፦ “በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ ወንዶች ወዲያውኑ ስለ አንተ ሁሉንም ነገር ማወቅ ይፈልጋሉ። እንዲህ ያለው ሁኔታ አንዲትን ወጣት በጣም ስለሚያናድዳት እንዲህ ካለ ሰው ትርቃለች።”

ይህን ልብ በል፦ የምትናገራቸው ቃላት እውነተኛ ማንነትህን እንደሚያሳይ መስኮት ስለሆኑ ሌሎች ደስ የሚል ነገር እንዲያዩ ለማድረግ ጥረት አድርግ።

“ከአንድ ወጣት ጋር ስተዋወቅ ራሱን ሆኖ ሲቀርበኝ ያስደስተኛል። መጀመሪያ ስንገናኝ የሚያወራው ነገር ወሳኝ ነው። ልጁ ስለሚናገረው ነገር ብዙ የሚጨነቅ ከሆነ ስለ ራሱ ትክክል ያልሆነ ነገር የመናገር አጋጣሚው ሰፊ ነው።”​ሰሌነ

መጽሐፍ ቅዱስ “ብዙ የምታወራ ከሆነ የተሳሳተ ነገር መናገርህ አይቀርም፤ ስለዚህ አስተዋይ በመሆን ስለምትናገረው ነገር ተጠንቀቅ” ይላል።​—ምሳሌ 10:19 ኮንቴምፖራሪ ኢንግሊሽ ቨርሽን

ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘በጣም ብዙ እንዳላወራ ወይም ደግሞ በጣም ዝምተኛ እንዳልሆን ሚዛኔን መጠበቅ የምችለው እንዴት ነው? የምናገርበት መንገድ ሌሎችን ሊያስደነግጥ ወይም ሊያስቆጣ ይችል ይሆን?’

የመፍትሔ ሐሳብ፦ ጥሩ ጭውውት የማድረግ ችሎታ ያላቸውን ሰዎች ልብ ብለህ ተመልከት። ጭውውቱ እንዲቀጥል ለማድረግ የሚጠቀሙበት ዘዴ ምንድን ነው? አንተም ተመሳሳይ ዘዴ መጠቀም ትችል ይሆን?

3. ድርጊትህ

ከቃላት ይልቅ ተግባር የጎላ ድምፅ አለው የሚል አንድ አባባል አለ። ለምሳሌ ያህል፣ ሥርዓታማ ከሆንክ ድርጊትህ ለሌሎች አክብሮት እንዳለህ “ይናገራል።” ትዳር ለመመሥረት ዝግጁ በምትሆንበት ጊዜ ልታስታውሰው የሚገባህ ሌላው ጠቃሚ ምክር ይህ ነው። ካሪ የተባለች አንዲት ወጣት “በር ከፍቶ እንደ ማስገባት ያሉ ጥቃቅን የሚመስሉ ነገሮችን ማድረግ አክብሮት እንዳለህ ያሳያል። እንዲህ ያሉ ነገሮችን ማድረግ የተለመደ ባሕርይ ነው” በማለት ተናግራለች።

ይህን ልብ በል፦ ድርጊትህ ውስጣዊ ባሕርይህን እንደሚያሳይ ፖስተር ነው። (ምሳሌ 20:11) ታዲያ ድርጊትህ ስለ አንተ ምን ነገር “ያሳያል?”

“ጥሩ አድማጭ መሆን አስፈላጊ እንደሆነ ይሰማኛል። ደግሞም አስፈላጊ ሆኖ ካልተገኘ በቀር ሌላ ሰው ሲናገር ጣልቃ አለመግባት ጥሩ ምግባር እንዳለን የሚያመለክት ነው።”​ነታሊየ

መጽሐፍ ቅዱስ “ሰዎች እንዲያደርጉላችሁ እንደምትፈልጉት ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው” ይላል።​—ሉቃስ 6:31

ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ሥርዓታማ ነኝ? ለሌሎች ልባዊ አሳቢነት አሳያለሁ? እምነት የሚጣልብኝ ነኝ? ቀጠሮ አክባሪ ነኝ?’

የመፍትሔ ሐሳብ፦ በቀጠሮህ ቦታ ቢያንስ ከአሥር ደቂቃ በፊት ለመድረስ እቅድ ካወጣህ ያልተጠበቁ ሁኔታዎች አጋጥመውህ ብትዘገይ እንኳ በሰዓቱ መድረስ ትችላለህ። በመጀመሪያው የቀጠሯችሁ ቀን አርፋጅ የሚል ስም እንዳታተርፍ ጥንቃቄ አድርግ!

ጥንቃቄ ልታደርግበት የሚገባ ነገር፦ ሰዎች ስለ አንተ ጥሩ ግምት እንዲኖራቸው ማድረግ አለብህ ሲባል ማንነትህን ትደብቃለህ ማለት አይደለም፤ እንዲህ ማድረግ ከማታለል ተለይቶ አይታይም። (መዝሙር 26:4 NW) በሰዎች ዘንድ በየትኞቹ ባሕርያት ተለይተህ መታወቅ እንደምትፈልግ ከወሰንክ በኋላ እነዚህን ባሕርያት ለማዳበርና ከልብ ለማንጸባረቅ ጥረት አድርግ። (ቆላስይስ 3:9, 10) በሌሎች ዘንድ ጥሩ ስም እንዲኖርህ ማድረግ የምትችለው አንተው ራስህ እንደሆንክ አትዘንጋ። ለአለባበስህ፣ ለአነጋገርህና ለድርጊትህ አስፈላጊውን ትኩረት በመስጠት ሰዎች መጀመሪያ ሲያገኙህ ስለ አንተ ጥሩ ግምት እንዲኖራቸው ማድረግ ትችላለህ!

 

^ አን.15 በዚህ ርዕስ ውስጥ የተጠቀሱት አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።