በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ታሪክን የቀየረ የአየር ሁኔታ

ታሪክን የቀየረ የአየር ሁኔታ

ታሪክን የቀየረ የአየር ሁኔታ

የታሪክ መዛግብት እንደሚያሳዩት የአየር ሁኔታ በአንዳንድ ክንውኖች ረገድ ከፍተኛ ሚና የተጫወተባቸው አስገራሚ አጋጣሚዎች አሉ። እስቲ ከእነዚህ አጋጣሚዎች መካከል ሁለቱን እንደ ምሳሌ እንመልከት።

አውሎ ነፋስ ሲነሳ

በ1588 የስፔኑ ንጉሥ ፊሊፕ፣ እንግሊዝን ለመውረር ስፓኒሽ አርማዳ በመባል የሚታወቁትን የጦር መርከቦች ላከ። ይሁን እንጂ የአየሩ ሁኔታ ነገሮች እንዲመሰቃቀሉ በማድረጉ ዕቅዱ አልተሳካም።

የስፔን የጦር መርከቦች ኢንግሊሽ ቻነል ወደሚባለው የባሕሩ ክፍል ሲገቡ ከእንግሊዝ የጦር መርከቦች ጋር ተገናኙ። በቀላሉ ለማንቀሳቀስ የሚመቹት የእንግሊዝ መርከቦች ከስፔን መርከቦች ጋር ውጊያ የገጠሙ ቢሆንም እምብዛም ጉዳት አላደረሱባቸውም። ከዚያም የስፔን የጦር መርከቦች፣ እንግሊዝን ለመውረር የሚረዳቸውን ሠራዊት እንዲያሳፍሩ በተሰጣቸው ትእዛዝ መሠረት ካሌ በተባለችው ወደብ አጠገብ መልሕቃቸውን ጣሉ።

ይህ በዚህ እንዳለ እንግሊዛውያን ጨለማን ተገን በማድረግ ከራሳቸው መርከቦች ውስጥ ብዙዎቹን በእሳት ለኩሰው ወደ ስፔን መርከቦች አቅጣጫ ሰደዷቸው። ሰው የሌለባቸው እነዚህ መርከቦች በነፋስና በባሕሩ ሞገድ እየተነዱ፣ መልሕቃቸውን ወደጣሉት የስፔን መርከቦች ቀጥ ብለው ሄዱ። ብዙ የስፔን መርከቦች፣ እንግሊዞች የላኳቸው በእሳት የተያያዙ መርከቦች እንዳያቃጥሏቸው ሲሉ መልሕቃቸውን ቆርጠው ሸሹ። ስፔናውያኑ የወሰዱት ይህ እርምጃ ግን የኋላ ኋላ ጉዳት አስከትሎባቸዋል።

በካሌ ከደረሰው ከዚህ ሁኔታ በኋላ የሁለቱም አገሮች የጦር መርከቦች ከኋላቸው በሚነፍሰው ነፋስ እየታገዙ ወደ ሰሜናዊው ባሕር አመሩ። በዚህ ጊዜ የእንግሊዝ መርከቦች ባሩድ እያለቀባቸው ስለነበር ወደ እንግሊዝ የባሕር ዳርቻ አፈገፈጉ። የስፔን የጦር መርከቦች ግን ነፋሱ ወደማይፈልጉት አቅጣጫ ይገፋቸው የነበረ ከመሆኑም ሌላ እንግሊዛውያኑ በእነሱና በስፔን መካከል ስለነበሩ ወደ አገራቸው ለመመለስ በስተሰሜን በስኮትላንድ በኩል ከዞሩ በኋላ በአየርላንድ አድርገው ለመጓዝ ተገደዱ።

በዚህ ጊዜ በስፔን የጦር መርከቦች ላይ ከፍተኛ የምግብና የውኃ እጥረት አጋጥሞ ነበር፤ ከዚህም ሌላ ጉዳት የደረሰባቸው መርከቦች ብዙ ቁስለኛ መርከበኞችንና ስከርቪ በሚባለው ከቪታሚን ሲ እጥረት በሚመጣ በሽታ የተጠቁ ሰዎችን ይዘው ነበር። በመርከቡ ላይ ለነበሩት ሰዎች በሙሉ ምግብና ውኃ የሚታደለው በቁጠባ ሲሆን ይህም ሰዎቹ ይበልጥ እንዲዳከሙ አደረጋቸው።

መርከቦቹ በስኮትላንድ በኩል ከዞሩ በኋላ ደግሞ ኃይለኛ የአትላንቲክ ማዕበል ተነስቶ ብዙዎቹን መርከቦች ወደ አየርላንድ የባሕር ዳርቻ ወሰዳቸው። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥም የተለመደው የመከላከያ ዘዴ የመርከቦቹን መልሕቆች ጥሎ ተስማሚ ነፋስ እስኪነፍስ መጠበቅ ነበር። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል የስፔን መርከቦች፣ በእሳት የተያያዙት የእንግሊዝ መርከቦች ሲመጡባቸው ለመሸሽ ሲሉ መልሕቆቻቸውን ቆርጠው ጥለዋቸው ስለነበር 26 መርከቦች ከአየርላንድ የባሕር ዳርቻ ጋር ተጋጭተው ተሰባበሩ፤ በዚህ ወቅት ከ5,000 እስከ 6,000 የሚያህሉ ሰዎች ሞቱ።

የስፔን የጦር መርከቦች ስፔን በደረሱበት ወቅት ወደ 20,000 የሚጠጉ ሰዎች ሕይወት ጠፍቶ ነበር። ይህን ያህል ብዙ ሕይወት እንዲጠፋና መርከቦቹ እንዲወድሙ ያደረገው አንዱ ወሳኝ ምክንያት የአየሩ ሁኔታ ነበር። ከሁኔታው መረዳት እንደሚቻለው የእንግሊዞች አጋር የነበሩት ደቾች ለዚያ ጥፋት መንስኤው የአየሩ ሁኔታ እንደሆነ ተሰምቷቸው ነበር። ቆየት ብሎ የስፔን የጦር መርከቦች ድል የተደረጉበት ወቅት በተከበረበት ጊዜ፣ ደቾች ለተፈጥሮ አደጋዎች ተጠያቂው አምላክ ነው የሚለውን የብዙኃኑን አመለካከት ያስተጋቡ ከመሆኑም ሌላ በወቅቱ በተዘጋጀው ሜዳልያ ላይ “ይሖዋ ነፋስ አመጣባቸው፤ እነሱም ተበተኑ” የሚል ሐሳብ እንዲቀረጽ አድርገው ነበር።

በዝናብ ምክንያት ድል መነሳት

የአየር ሁኔታ ከባድ ተጽዕኖ ያሳደረበት ሌላው ዓለምን የለወጠ ክስተት ደግሞ በ1815 የተደረገው የዋተርሉ ጦርነት ነው። ከብራስልስ፣ ቤልጅየም በስተደቡብ 21 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ በሚገኘው በዋተርሉ በተካሄደው ጦርነት ላይ በጥቂት ሰዓታት ውስጥ ከ70,000 በላይ ሰዎች እንደተገደሉ ወይም እንደቆሰሉ የታሪክ መዛግብት ያሳያሉ። ብሪታንያዊው የዌሊንግተን መስፍን ይህን የጦር ሜዳ የመረጠ ከመሆኑም ሌላ ከፍ ያለውን ቦታ ይዞ ነበር። በናፖሊዮን የሚመራው የፈረንሳይ ሠራዊት ከዌሊንግተን ሠራዊት በቁጥር ይበልጥ የነበረ ቢሆንም ዌሊንግተን በዚያን ዕለት ሌሊት ከፕራሽን ተጨማሪ ሠራዊት ይመጣለት ስለነበር ናፖሊዮን ከመምሸቱ በፊት ጠላቱን ድል ማድረግ ያስፈልገው ነበር። ይሁን እንጂ በዚህ ጊዜም የአየሩ ሁኔታ ወሳኝ ሚና ተጫውቷል።

ከውጊያው በፊት በነበረው ሌሊት ዶፍ ዝናብ ጥሎ ነበር። አብዛኞቹ ወታደሮች ያ ሌሊት በሕይወታቸው ውስጥ እጅግ አስከፊ እንደነበር ያስታውሳሉ። አንዳንድ ወታደሮች ትንንሽ ድንኳኖችን መትከል የቻሉ ቢሆንም በድንኳኑ ውስጥ ያዘጋጇቸው መኝታዎች ሐይቅ ውስጥ ያሉ ያህል በውኃ ርሰው እንደነበር አንዱ ወታደር በምሬት ተናግሯል። መሬቱ በዝናብ ከመራሱ የተነሳ ረግረግ ሆኖ ነበር። ናፖሊዮን ከመምሸቱ በፊት ዌሊንግተንን ድል ለማድረግ ሲል ጎሕ እንደቀደደ ጥቃቱን መሰንዘር ፈልጎ ነበር። ይሁን እንጂ ጥቃቱን ለመሰንዘር ለተወሰኑ ሰዓታት መጠበቅ ነበረበት።

ውጊያው በታሰበበት ሰዓት እንዳይጀምር ያደረገው ዋነኛ ምክንያት ሌሊት የጣለው ዝናብ ነበር፤ ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት መሬቱ ጠፈፍ ማለት ነበረበት። በተጨማሪም ናፖሊዮን በመድፍ መዋጋትን ቢመርጥም ጭቃው በመድፎቹ ውጤታማነት ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ ነበር። አንደኛ ነገር፣ በጭቃው የተነሳ ወታደሮቹ ከባድ የሆኑትን መድፎች ማንቀሳቀስ አስቸጋሪ ስለሆነባቸው ረጅም ርቀት መተኮስ አልቻሉም። ሁለተኛ ደግሞ የመድፉ ጥይት መሬት ላይ ነጥሮ በመስፈንጠር በዌሊንግተን ሠራዊት ላይ ተጨማሪ ጉዳት እንዲያደርስ ታስቦ ነበር። ይሁን እንጂ እርጥብ የሆነው መሬት የጥይቱ ኃይል እንዲቀንስ ስላደረገ ያሰቡት ሳይሳካ ቀረ። ይህ በናፖሊዮንና በሠራዊቱ ላይ ከባድ ኪሳራ አስከተለ። በመሆኑም በመጥፎ የአየር ሁኔታ የተነሳ የናፖሊዮን ሠራዊት ድል የተደረገ ሲሆን እሱም ተማርኮ በግዞት ተወሰደ።

ከላይ በተገለጹት በሁለቱም አጋጣሚዎች የአየሩ ሁኔታ፣ በዓለም ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ በነበራቸው ክንውኖች ላይ ወሳኝ ሚና እንደተጫወተ በግልጽ ማየት ይቻላል። እነዚህ ክንውኖች ደግሞ ብሪታንያ ኃያል መንግሥት እንድትሆን ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል።

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የስፔን የጦር መርከቦች

[የሥዕሉ ምንጭ]

© 19th era/Alamy

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የዋተርሉ ጦርነት

[የሥዕሉ ምንጭ]

© Bettmann/CORBIS