በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንዳንዶች የዓመፅ ድርጊት የሚፈጽሙት ለምንድን ነው?

አንዳንዶች የዓመፅ ድርጊት የሚፈጽሙት ለምንድን ነው?

አንዳንዶች የዓመፅ ድርጊት የሚፈጽሙት ለምንድን ነው?

በስፔን የሚኖረው ሆሴባ ወደ ውጊያ የገባው ለምን እንደሆነ ተጠይቆ ነበር። “በወቅቱ ይደርስብን የነበረው ጭቆናና የፍትሕ መዛባት ልንቋቋመው ከምንችለው በላይ ሆኖ ነበር” ይላል። “የምኖረው ቢልባኦ በምትባል ትልቅ ከተማ ውስጥ ሲሆን ፖሊሶች እየመጡ ሰዎችን ይደበድቡ እንዲሁም ያስሩ ነበር።”

ሆሴባ በመቀጠል እንዲህ ብሏል፦ “ይህ ዓይነቱን የፖሊሶች ድርጊት በተመለከተ ሐሳቤን በመግለጼ አንድ ቀን ማለዳ ላይ ተይዤ ታሰርኩ። በጣም ከመበሳጨቴ የተነሳ ሁኔታውን ለማስተካከል አንድ ነገር ማድረግ፣ አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘም የዓመፅ ድርጊት መፈጸም እንዳለብኝ ወሰንኩ።”

ጭቆናን መበቀል

መጽሐፍ ቅዱስ የዓመፅ ድርጊትን ባያበረታታም “ግፍ ጠቢቡን ያሳብደዋል” በማለት ጭቆና፣ ሰዎች ማመዛዘን የጎደለው ድርጊት እንዲፈጽሙ ሊያነሳሳቸው እንደሚችል ይጠቁማል። (መክብብ 7:7 የ1954 ትርጉም) ብዙዎች በዘራቸው፣ በሃይማኖታቸው ወይም በዜግነታቸው ምክንያት ግፍ ሲደርስባቸው በቁጣ ይሞላሉ።

ለምሳሌ ያህል በመጀመሪያው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው ሃፌኒ እንዲህ ብሏል፦ “መሬታችንን ያለ አግባብ ተነጥቀን ነበር። እንስሳትም እንኳ ክልላቸውን ላለማስደፈር ይታገላሉ፤ እኛም ለመሬታችንና ለመብታችን መዋጋታችን ተገቢ እንደሆነ ተሰማን።” አንድ አጥፍቶ ጠፊ ከሞተ በኋላ ይፋ በሆነው ንግግሩ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “ሕዝቤን በቦምብ መደብደባችሁን፣ ማሰራችሁንና ማሠቃየታችሁን እንዲሁም በሕዝቤ ላይ መርዘኛ ጋዝ መርጨታችሁን እስካላቆማችሁ ድረስ እኛም ይህን ውጊያ አናቆምም።”

ሃይማኖታዊ ምክንያቶች

ብዙውን ጊዜ ታጣቂዎች፣ የሽብርተኝነት ድርጊት እንዲፈጽሙ የሚያነሳሷቸው የተለያዩ ምክንያቶች ቢኖሩም በሃይማኖታዊ ምክንያቶች የተነሳ በዓመፅ ድርጊቶች መካፈላቸው እየተለመደ መጥቷል። የአንድ አገር መሪ የሆኑ ሰው፣ ከአንድ የታጣቂዎች ቡድን ቃል አቀባይ የሚከተለው የፋክስ መልእክት ደርሷቸው ነበር፦ “እኛ እብዶች ወይም የሥልጣን ጥመኞች አይደለንም። አምላክን እያገለገልን ሲሆን በአቋማችን እንድንጸና ያደረገንም ይህ ነው።”

ዳንኤል ቤንጃሚን እና ስቲቨን ሳይመን፣ በሃይማኖታዊ ምክንያት የሽብር ድርጊት መፈጸምን በተመለከተ ባዘጋጁት ዚ ኤጅ ኦቭ ሴክረድ ቴረር በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ የሚከተለውን ጽፈዋል፦ “እያደር ይበልጥ ሃይማኖተኛ እየሆነ በመጣው ዓለም ውስጥ የታላላቆቹ ሃይማኖቶችም ሆነ በፍጥነት እየተባዙ ያሉት አዳዲስ ኑፋቄዎች በርካታ ተከታዮች፣ የዓመፅ ድርጊትን የአምልኮታቸው ክፍል እያደረጉት ነው።” በዚህ ጉዳይ ላይ ጥናት ያካሄዱ ሌላ ሰው ደግሞ “በዓለም ዙሪያ የተፈጸሙ ጉድ የሚያሰኙ የሽብርተኝነት ድርጊቶች” ብለው የጠሯቸውን በርካታ ክስተቶች ከዘገቡ በኋላ እንዲህ ብለዋል፦ “ድርጊቱን የሚፈጽሙ ሰዎችን ሁሉ አንድ የሚያደርጋቸው ነገር፣ ተግባራቸው መለኮታዊ ድጋፍ እንዳለው እንዲያውም አምላክ ይህን ለማድረግ ሥልጣን እንደሰጣቸው የሚሰማቸው መሆኑ ነው።”

ያም ሆኖ ግን ሃይማኖተኛ የሆኑ ብዙ ታጣቂ ቡድኖች፣ ሃይማኖታቸው ከሚያስተምራቸው ነገሮችም ሆነ ከሥነ ምግባራዊ እሴቶቹ ጋር የማይስማማ ጽንፈኛ አመለካከት አላቸው።

ሥር የሰደደ ጥላቻ

ቀደም ሲል የተጠቀሰው ሆሴባ በታሰረበት ወቅት ከፍተኛ በደል ደርሶበት ነበር። እንዲህ ብሏል፦ “ጭካኔያቸው እነሱን መጥላቴ ትክክል እንደሆነ ይበልጥ አሳመነኝ። ለውጥ ለማምጣት ስል ብሞት እንኳ አይቆጨኝም ነበር።”

ብዙውን ጊዜ በዓማፂያን ቡድን ውስጥ የሚሰጠው ትምህርት አባላቱ በዓመፅ ድርጊት እንዲካፈሉ ይበልጥ ያነሳሳቸዋል። ሃፌኒ እንዲህ ብሏል፦ “በስደተኞች መጠለያ ጣቢያ ውስጥ በነበርንበት ወቅት በሚደረጉት ስብሰባዎች ላይ ነጮች ጥቁሮችን ለመቆጣጠር ሁልጊዜ ዘዴ እንደሚፈጥሩ እንማር ነበር።” ታዲያ ይህ ምን አስከተለ?

ሃፌኒ “ለነጮች ያለኝ ጥላቻ እየጨመረ እንደሆነ ይታወቀኝ ነበር” ብሏል። “ነጮችን በሙሉ አላምናቸውም ነበር። እያደር ትዕግሥቴ እየተሟጠጠ ስለሄደ የእኛ ትውልድ አንድ ነገር ማድረግ አለበት ብዬ አሰብሁ።”

የሚገርመው ነገር፣ ሆሴባም ሆነ ሃፌኒ እንዲህ ዓይነት ጠንካራ አቋም የነበራቸው ቢሆንም በልባቸው የነበረውን ሥር የሰደደ የጥላቻና ሌሎችን አለማመን ስሜት ማስወገድ ችለዋል። አእምሯቸውና ልባቸው እንዲለወጥ ያደረገው ምንድን ነው? የሚቀጥለው ርዕስ ይህን ያብራራል።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ጭካኔያቸው እነሱን መጥላቴ ትክክል እንደሆነ ይበልጥ አሳመነኝ። ለውጥ ለማምጣት ስል ብሞት እንኳ አይቆጨኝም ነበር።”​—ሆሴባ