በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ከየትኛውም ሥራ የበለጠ ውድ ነገር

ከየትኛውም ሥራ የበለጠ ውድ ነገር

ከየትኛውም ሥራ የበለጠ ውድ ነገር

ሙራት ኢቤቱሊን እንደተናገረው

በ1987 የሩሲያ ጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በአፍሪካ ወደምትገኘው ኡጋንዳ ላከኝ። በዚያም የሕክምና ዶክተር ሆኜ ለመሥራት ለአራት ዓመት ኮንትራት ገባሁ። በመሠረቱ ወደ ሩሲያ የመመለስ ፍላጎት አልነበረኝም፤ ቢያንስ እንደ አሜሪካ፣ አውስትራሊያ ወይም ካናዳ ባሉ አገሮች ውስጥ ለመሥራት የሚያስችለኝ የሥራ ልምድ አገኛለሁ የሚል ተስፋ ነበረኝ። ይሁን እንጂ በ1991 ሐሳቤን ቀይሬ ወደ ሩሲያ ተመለስኩ። እስቲ ምክንያቴን ልንገራችሁ።

የተወለድኩት በ1953 በማዕከላዊ ሩሲያ የታታርስታን ሪፑብሊክ ዋና ከተማ በሆነችው በካዛን ነበር። ወላጆቼ ታታር ሲሆኑ አብዛኛው የታታር ሕዝብ ደግሞ ሙስሊም ነው። ልጅ ሳለሁ አያቶቼ ለአላህ ሲሰግዱ ትዝ ይለኛል። ወላጆቼን ጨምሮ አጎቶቼና አክስቶቼ፣ አያቶቻችንን እንዳንረብሻቸው ከሚሰግዱበት ክፍል እንድንወጣ ይነግሩን ነበር። ወላጆቼ ኮሚኒዝምን ስለተቀበሉና በወቅቱ በአምላክ እንደማያምኑ ይናገሩ ስለነበር ወላጆቻቸው ሃይማኖተኞች በመሆናቸው ያፍሩ ነበር።

የአራት ዓመት ልጅ ሳለሁ በሶቪየት ኅብረት ውስጥ በፖሊዮ በሽታ ተያዝኩ። በመሆኑም የልጅነት ጊዜዬን ሳስታውስ የሚታየኝ ነገር ቢኖር ለሕክምና ወደ ሆስፒታል ስመላለስ ነው። እንዲያውም አያቴ ከበሽታዬ እንድድን ሲጸልይልኝ ትዝ ይለኛል። እንደ ሌሎቹ ልጆች ጤነኛ ሆኜ መታየት ስለምፈልግ አንዱ እግሬ ጉዳት ቢደርስበትም እግር ኳስ፣ ሆኪና ሌሎች ስፖርቶችን እጫወት ነበር።

እያደግሁ ስሄድ ሐኪም የመሆን ፍላጎት አደረብኝ። ሃይማኖተኛ ባልሆንም አምላክ የለም ብዬም አላምንም ነበር። ስለ አምላክ ግን አስቤ አላውቅም። በወቅቱ የኮሚኒስቱን ርዕዮተ ዓለም በጣም እተችና ብዙ ጊዜም ከአባቴና ከአጎቴ ጋር እከራከር ነበር። አጎቴ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ የፍልስፍና አስተማሪ የነበረ ሲሆን አባቴ ደግሞ ኬጂቢ እየተባለ በሚጠራው የሶቪየት ኅብረት የደኅንነት ኮሚቴ ውስጥ ይሠራ ነበር። የሕክምና ትምህርቴን ስጨርስ ጥሩ የነርቭ ቀዶ ሕክምና ባለሙያ ለመሆንና ወደ ሌላ አገር ሄጄ የመሥራት ግብ ነበረኝ።

የተሻለ ሕይወት ፍለጋ

በ1984 የአንጎል ዕጢ ምርመራን አስመልክቶ ያዘጋጀሁትን የዶክተርነት መመረቂያ ጽሑፍ አቀረብኩ። ከዚያም በ1987 ኡጋንዳ ውስጥ ወደሚገኘው የሙላጎ ሆስፒታል ተላክሁ። ወደዚህ ውብ አገር የሄድኩት ባለቤቴን ዲልባርን እንዲሁም በወቅቱ የሰባትና የአራት ዓመት ዕድሜ የነበራቸውን ሩስቴምና አሊሳ የተባሉትን ልጆቻችንን ይዤ ነበር። በክሊኒኩ መሥራት ከባድ የነበረ ሲሆን በኤች አይ ቪ ቫይረስ ለተያዙ ሕሙማን ቀዶ ሕክምና ማድረግን ይጨምር ነበር። በዚያን ጊዜ በኡጋንዳ የነበርነው የነርቭ ቀዶ ሕክምና ባለሙያዎች ሁለት ብቻ ስለሆንን ብዙውን ጊዜ በመላው አገሪቱ ወደሚገኙት ክሊኒኮች እሄድ ነበር።

አንድ ቀን እኔና ዲልባር ሰዎች መጽሐፍ ዘርግተው በሚሸጡበት ቦታ ላይ በሩሲያኛ ቋንቋ የተተረጎመ መጽሐፍ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ አየን። በወቅቱ በሩሲያ መጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት በጣም አስቸጋሪ ስለነበር በሶቪየት ኅብረት ላሉ ጓደኞቻችን ለመላክ ብዙ መጽሐፍ ቅዱሶች ገዛን። ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተወሰኑ ምዕራፎችን ለማንበብ ብንሞክርም ለመረዳት አዳጋች ስለሆነብን ብዙም ሳንቆይ ማንበቡን ተውነው።

ያም ሆኖ የአካባቢው ሰዎች ምን እንደሚያምኑና የያዙትን እምነት እንዲቀበሉ ያነሳሳቸው ምን እንደሆነ ለመረዳት በኡጋንዳ ወዳሉ የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ለሦስት ዓመታት ሄድን። በተጨማሪም ቁርዓንን መጀመሪያ በተጻፈበት ቋንቋ ለማጥናት ወሰንኩ። እንዲያውም እኔና ሩስቴም አረብኛ መማር ጀመርን። ከጥቂት ወራት በኋላ ለመግባቢያ ያህል አረብኛ ችለን ነበር።

በዚያው ጊዜ ላይ ሃይንትስ እና ማሪያነ ከተባሉ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያስተምሩ ጀርመናዊና ኦስትሪያዊ ሚስዮናውያን ጋር ተገናኘን። መጀመሪያ ላይ ከእነዚህ ባልና ሚስት ጋር ሃይማኖት ስለሚባል ነገር አላወራንም ነበር። አውሮፓውያን በአፍሪካ ሲገናኙ ከሚያነሷቸው ነገሮች የተለየ ነገር አልተወያየንም። ወደ ኡጋንዳ ለምን እንደመጡ ስንጠይቃቸው የይሖዋ ምሥክሮች ሚስዮናውያን እንደሆኑና ወደዚህች አገር የመጡት ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ ለመርዳት እንደሆነ ነገሩን።

በዚህ ጊዜ በሩሲያ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት እየተከታተልኩ ሳለ በፍልስፍና ክፍለ ጊዜ ላይ የይሖዋ ምሥክሮች መናፍቃን እንደሆኑና ልጆቻቸውን መሥዋዕት በማድረግ ደማቸውን እንደሚጠጡ የተነገረንን አስታወስኩ። ሃይንትስና ማሪያነ እንዲህ ያለውን ነገር ያደርጋሉ ብሎ ማመን ስለከበደኝ ጉዳዩን አነሳሁላቸው። ለእኔና ለዲልባር በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተሰኘውን መጽሐፍ አንድ አንድ ቅጂ የሰጡን ሲሆን በጥቂት ሰዓታት ውስጥ አብዛኛውን ክፍል በጉጉት አነበብነው። ንባቤን አቁሜ ባለቤቴን ምን እንደተሰማት ስጠይቃት እጅግ ደስ እንዳላትና ስሜቷ በጥልቅ እንደተነካ ነገረችኝ! እኔም እንደ እሷ እንደተሰማኝ ነገርኳት።

ከዚያ በኋላ ከሃይንትስና ከማሪያነ ጋር ተገናኝተን ለመነጋገር ጉጉት አደረብን። ከእነሱ ጋር ስንገናኝ በብዙ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ተወያየን። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የተማርነው ነገር የበለጠ ልባችንን ነካው። የተማርነውን ለወዳጆቻችንና ለሥራ ባልደረቦቻችን ለማካፈል ተገፋፋን። ካነጋገርናቸው ሰዎች መካከል የሩሲያው አምባሳደር እንዲሁም የሩሲያና የሌሎች አገሮች ቆንሲላዎች ብሎም የቫቲካን ተወካይ ይገኙበታል። የቫቲካን ተወካዩ ብሉይ ኪዳን “ተረት ብቻ” እንደሆነ ሲናገር በጣም ገረመን።

ወደ ትውልድ አገራችን መመለስ

እኔና ዲልባር በ1991 ወደ ሩሲያ ከመመለሳችን ከአንድ ወር በፊት የይሖዋ ምሥክር ለመሆን ወሰንን። ወደ ካዛን ስንመለስ ወዲያውኑ በስብሰባዎች ላይ መገኘታችንን የምንቀጥል መስሎን ነበር። የሚያሳዝነው ግን ለሦስት ወራት ጥረት ብናደርግም የመንግሥት አዳራሽ ይቅርና አንድ የይሖዋ ምሥክር እንኳ ማግኘት አልቻልንም! ስለዚህ ብቻችንን ብንሆንም በዓለም ዙሪያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች እንደሚያደርጉት ከቤት ወደ ቤት መሄድ ጀመርን። በዚህም ምክንያት ጥቂት ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት የጀመርን ሲሆን ከመካከላቸው አንዷ ከጊዜ በኋላ የይሖዋ ምሥክር ሆናለች።

በዚህ ሁኔታ ላይ እንዳለን አድራሻችንን በኡጋንዳ ካሉት የይሖዋ ምሥክሮች የተቀበለ አንድ አረጋዊ የይሖዋ ምሥክር ወደ ቤታችን መጣ። ከዚያም ከ15 ሰዎች ጋር ሆነን ባለ አንድ ክፍል አፓርታማ ውስጥ መሰብሰብ ጀመርን። ሃይንትስና ማሪያነ ከእኛ ጋር የነበራቸውን ግንኙነት አላቋረጡም፤ እንዲያውም እኛን ለመጠየቅ ካዛን ድረስ መጥተው ነበር። ከኡጋንዳ በኋላ ቀጣዩ ምድባቸው በሆነችው በቡልጋሪያ አሁንም ድረስ እያገለገሉ ነው፤ እኛም እነሱን ለመጠየቅ ቡልጋሪያ ሄደን ነበር።

በትውልድ አገሬ ጥሩ ፍሬ ተገኘ

ሩሲያ ውስጥ በምሠራባቸው ሆስፒታሎች ውስጥ ለማገኛቸው የሥራ ባልደረቦቼ ባገኘሁት አጋጣሚ ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት አካፍላለሁ። ብዙዎቹ በጊዜ ሂደት ጥሩ ምላሽ በመስጠት የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል፤ ከእነሱም መካከል በርካታ የሕክምና ባለሙያዎች ይገኙበታል። በ1992 ማለትም ወደ ሩሲያ ከተመለስን ከአንድ ዓመት በኋላ በካዛን ያለው የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር 45 የደረሰ ከመሆኑም ሌላ በቀጣዩ ዓመት ከ100 በላይ ሆነ። በዛሬው ጊዜ በካዛን ሰባት ጉባኤዎች የሚገኙ ሲሆን አምስቱ በሩሲያኛ ቋንቋ፣ አንዱ በታታር ቋንቋ እንዲሁም ሌላው በምልክት ቋንቋ የሚመሩ ናቸው። የአርመንኛና የእንግሊዝኛ ቋንቋ ቡድኖችም አሉ።

በ1993 በኒው ዮርክ ሲቲ በተደረገ የሕክምና ጉባኤ ላይ ለመካፈል በሄድኩበት ወቅት በብሩክሊን የሚገኘውን የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ለመጎብኘት አጋጣሚ አግኝቼ ነበር። በዚህ ጊዜ በመላው ዓለም የሚካሄደውን የይሖዋ ምሥክሮች የስብከት እንቅስቃሴ ከሚያስተባብረው ከሎይድ ባሪ ጋር ተገናኘሁ። ወንድም ሎይድ ሥራ የሚበዛበት ቢሆንም ጊዜ ወስዶ አነጋገረኝ።

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በታታር ቋንቋ ማዘጋጀት አስፈላጊ እንደሆነ ከወንድም ሎይድ ጋር ተነጋገርን። ከጥቂት ዓመታት በኋላ በሩሲያ ውስጥ የታታር ቋንቋ የትርጉም ቡድን በመቋቋሙ በራሳችን ቋንቋ ጽሑፎች ማግኘት ጀመርን። ከጊዜ በኋላ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ታስቦ የሚዘጋጀውን የመጠበቂያ ግንብ መጽሔት በቋሚነት ማግኘት ስንጀምር የተሰማንን ደስታ መግለጽ ያቅተኛል! ከዚያ ብዙም ሳይቆይ የመጀመሪያው የታታር ቋንቋ ጉባኤ ተቋቋመ።

ደም እንዳይባክን በሚያደርጉ የሕክምና ዘዴዎች መጠቀም

የአምላክ አገልጋዮች “ከደም እንዲርቁ” የሚያዝዘውን በ⁠ሐዋርያት ሥራ 15:20 ላይ የሚገኘውን ትእዛዝ ጨምሮ ለሁሉም የአምላክ የሥነ ምግባር ሕጎች ከፍ ያለ ቦታ እሰጣለሁ። ቁጥር 29 የአምላክ አገልጋዮች “ለጣዖት ከተሠዉ ነገሮች፣ ከደም፣ ታንቆ ከሞተ እንስሳ ሥጋና ከዝሙት [መራቅ]” እንዳለባቸው አክሎ ይናገራል።

በመሆኑም የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ሕክምና ቦታዎች ሲሄዱ ፍላጎታቸው ያለ ደም የሚሰጥ ሕክምና ማግኘት መሆኑን በመግለጽ ዶክተሮቹ ይህን አቋማቸውን እንዲያከብሩላቸው ይጠይቃሉ። በካዛን ካለው የይሖዋ ምሥክሮች የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ ጋር ለተወሰነ ጊዜ ሠርቼ ነበር። * በ1997 በኖቮሲቢርስክ ከተማ የምትኖር አንዲት የይሖዋ ምሥክር፣ ፓቬል የሚባል የአንድ ዓመት ልጇ አፋጣኝ ቀዶ ሕክምና ባስፈለገው ጊዜ እንድንረዳት ጠየቀችን። በዚያን ጊዜ በሩሲያ የነበሩት ያለ ደም ቀዶ ሕክምና ለማድረግ ፈቃደኞች የሆኑ ልምድ ያካበቱ ዶክተሮች በጣም ጥቂት ነበሩ። በመሆኑም ያለ ደም የሚሰጥ አማራጭ ሕክምና ለመጠቀም ፈቃደኛ የሆነ ሐኪም ማፈላለግ ጀመርን።

ብዙም ሳይቆይ በካዛን በሚገኝ አንድ የልብ ቀዶ ሕክምና ክሊኒክ ውስጥ ሕፃኑን ፓቬልን ቀዶ ሕክምና ለማድረግ የተስማሙ ዶክተሮች አገኘን። መጋቢት 31, 1997 ቴትራሎጂ ኦቭ ፋሎት በመባል የሚታወቀውን ከባድ የልብ ችግር ለማስተካከል ዶክተሮቹ ያለ ደም ቀዶ ሕክምና ያከናወኑ ሲሆን ቀዶ ሕክምናውም የተሳካ ነበር። ሚያዝያ 3 ላይ ቨቼርንያየ ካዛን የተሰኘው ጋዜጣ እንደሚከተለው በማለት ዘገበ፦ “ሕፃኑ በጣም ደህና ስለሆነ ከእንግዲህ የልብ መድኃኒት መውሰድ አያስፈልገውም። . . . የፓቭሊክ [የፓቬል የቁልምጫ አጠራር ነው] እናት ከአሥራ አንድ ወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከጭንቀቷ እፎይ አለች።” ፓቬል በአጭር ጊዜ ውስጥ ከቀዶ ሕክምናው ያገገመ ሲሆን ድክ ድክ ማለት የጀመረው በሆስፒታሉ ኮሪደር ላይ ነበር።

ፓቬል በአሁኑ ጊዜ በጥሩ ጤንነት ላይ የሚገኝ ሲሆን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴውን ያለ ምንም ችግር ያከናውናል። መዋኘት፣ በረዶ ላይ መንሸራተትና እግር ኳስ መጫወት ይወዳል። በትምህርቱም ስምንተኛ ክፍል የደረሰ ከመሆኑም በላይ በኖቮሲቢርስክ ከተማ ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ አባል በመሆን ከእናቱ ጋር አምልኮውን ያከናውናል። ለፓቬል ሕክምና ከተደረገለት በኋላ በክሊኒኩ የሚሠሩት ዶክተሮች፣ የይሖዋ ምሥክሮች ለሆኑ በርካታ የልብ ሕሙማን ያለ ደም የተሳካ ቀዶ ሕክምና አድርገዋል። በታታርስታን የሕክምናው መስክ ጥሩ እድገት እየታየበት ከመሆኑም ባሻገር ያለ ደም ቀዶ ሕክምና ማድረግም የተለመደ ሆኗል።

በአሁኑ ጊዜ የምሠራው ሥራ

እኔና ባለቤቴ እንዲሁም ሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች የነርቭና የልብ ችግሮች ላሉባቸው ሕሙማን የረቀቀ ቴክኖሎጂ በመጠቀም ሕክምና በሚሰጥበት አንድ ክሊኒክ ውስጥ እንሠራለን። በዚህ ክሊኒክ ውስጥ የተለያዩ ቀዶ ሕክምናዎችን የምናከናውን ሲሆን በተለይም ይህን የምናደርገው ደም እንዳይባክን የሚረዱ ዘዴዎችን መጠቀም ለሚፈልጉ ሕሙማን ነው። በአሁኑ ጊዜ የምሠራው በጨረር አማካኝነት የነርቭ ሕክምና መስጠት ሲሆን ለወደፊቱም ሰውነትን ሳይቀዱ ያለ ደም በሚሰጥ የነርቭ ሕክምና ረገድ ተጨማሪ ምርምር አደርጋለሁ። በካዛን የመንግሥት የሕክምና ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የነርቭ ጥናትና ቀዶ ሕክምና ዲፓርትመንት ፕሮፌሰር እንደ መሆኔ መጠን ለሕክምና ተማሪዎችና ለሐኪሞች ትምህርት በምሰጥበት ጊዜ ያለ ደም የሚሰጥ ሕክምና ያለውን ጥቅም እንዲገነዘቡ ለመርዳት እጥራለሁ። *

ባለቤቴ በክሊኒኩ ውስጥ የአልትራሳውንድ ስፔሻሊስት በመሆን አብራኝ ትሠራለች። ሰዎችን ለመርዳት ስለሚያስችለን ሥራችንን እንወደዋለን። ከሁሉ የላቀ እርካታ የሚያስገኝልን ግን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ለሰዎች መንፈሳዊ ፈውስ ሲያመጣላቸው ማየት ነው። አምላክ “‘ታምሜአለሁ’ የሚል አይኖርም” በማለት የሰጠው ተስፋ በቅርቡ እንደሚፈጸም ለሰዎች መንገር ልባችን በደስታ እንዲሞላ ያደርጋል።​—ኢሳይያስ 33:24

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.23 የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ፣ ያለ ደም ሕክምና ማግኘት አስቸጋሪ በሚሆንበት ጊዜ በሆስፒታልና በሕሙማን መካከል የትብብር መንፈስ እንዲሰፍን ለመርዳት የተቋቋመ የይሖዋ ምሥክሮችን ያቀፈ ቡድን ነው።

^ አን.27 ያለ ደም ሕክምና መስጠት ሲባል ደም በመስጠት ፋንታ አማራጭ የሕክምና ዘዴዎችን ተጠቅሞ ማከም ማለት ነው። ደም ከመውሰድ ጋር ተያይዘው የሚመጡ ብዙ አደጋዎች በመኖራቸው ያለ ደም የሚሰጥ ሕክምናና ቀዶ ጥገና በመላው ዓለም ተቀባይነት እያገኘ ነው። ደም መውሰድ ለኤች አይ ቪና ለሌሎች ተላላፊ በሽታዎች እንዲሁም ለአለርጂ ያጋልጣል።

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በአፍሪካ የሕክምና ዶክተር ሆኜ ስሠራ

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

እኔና ባለቤቴ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት በጀመርንበት ጊዜ፣ 1990

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ብሩክሊን ኒው ዮርክ በሄድኩበት ጊዜ ከወንድም ሎይድ ባሪ ጋር፣ 1993

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በዛሬው ጊዜ ፓቬልና እናቱ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከባለቤቴ ከዲልባር ጋር በአገልግሎት ላይ ሆነን