በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“ፖስታ ቤት ደረስ ብዬ ለመምጣት ወጣ ማለቴ ነበር”

“ፖስታ ቤት ደረስ ብዬ ለመምጣት ወጣ ማለቴ ነበር”

“ፖስታ ቤት ደረስ ብዬ ለመምጣት ወጣ ማለቴ ነበር”

“ያንን ቀን ፈጽሞ አልረሳውም” በማለት የደቡብ አፍሪካ ተወላጅ የሆነውና በናሚቢያ የሚኖረው አንድሬ ይናገራል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ዕለቱ ሰኞ ሲሆን ማለዳ ላይ ፖስታ ቤት ሄጄ ነበር። ቦታውም በሕዝብ ተጨናንቋል። ፖስታ ቤቱ ውስጥ አንድ ቦርሳ አየሁ፤ በአቅራቢያው ማንም አልነበረም። እኔም ፖስታ መጥቶልኝ እንደሆነ ከጠየቅሁ በኋላ ወጥቼ ሄድኩ። መኪናዬ ውስጥ ገብቼ ጉዞ ከጀመርኩ ሦስት ደቂቃ እንኳ ሳይሞላ ኃይለኛ ፍንዳታ ሰማሁ። ፖስታ ቤቱ ውስጥ ከቆምኩበት ቦታ ጥቂት እርምጃዎች እልፍ ብሎ ቦምብ ፈንድቶ ነበር።

“ፖስታ ቤት ደረስ ብዬ ለመምጣት ወጣ ማለቴ ነበር። በዚያች ቅጽበት እዚያ የነበሩት ንጹሐን ሰዎች በፍንዳታው እንደሞቱ ሳውቅ በጣም ደነገጥኩ፤ አብዛኞቹን አውቃቸው ነበር። ይህ ከሆነ 25 ዓመታት ቢያልፉም እስከ አሁን ድረስ ያንን ቀን ሳስበው ዝግንን ይለኛል። አንዳንድ ጊዜ በፍንዳታው የሞቱትና የተጎዱት ሰዎች ምስል ወደ አእምሮዬ ይመጣል፤ ያን ዕለት ከሞት ያመለጥኩት ለጥቂት ነበር።”

ዓለም አቀፍ ችግር

ምናልባት አንተ እንዲህ ባለ ሁኔታ ውስጥ አላለፍክ ይሆናል፤ ሆኖም በዓለም ዙሪያ ተመሳሳይ ሁኔታዎች ብዙጊዜ እንደሚያጋጥሙ ሰምተህ ይሆናል። እያደር ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ሰዎች ዓላማቸውን ለማሳካት የዓመፅ ድርጊት ወደ መፈጸም እያዘነበሉ ነው፤ እንዲህ ያለው ድርጊት ብዙውን ጊዜ ሽብርተኝነት እየተባለ ይጠራል።​—“አሸባሪዎች እነማን ናቸው?” የሚለውን በሚቀጥለው ገጽ ላይ የሚገኘውን ሣጥን ተመልከት።

በምርመራ ጋዜጠኝነት ሙያ ላይ የተሰማሩ አንድ ግለሰብ፣ በ1997 “በተደጋጋሚ ጊዜ የአጥፍቶ ጠፊዎች ጥቃት የተሰነዘረባቸው አገሮች አራት ብቻ” እንደነበሩ ገልጸዋል። ይሁን እንጂ እኚሁ ሰው በ2008 እንደጻፉት “ከአውስትራሊያና ከአንታርክቲካ በስተቀር በሁሉም አህጉራት የሚገኙ ከ30 በላይ አገሮች በአጥፍቶ ጠፊዎች አውዳሚ ጥቃት ተሰንዝሮባቸዋል።” እኚህ ጋዜጠኛ ሐሳባቸውን ሲደመድሙ እንዲህ ብለዋል፦ “እንዲህ ያለውን ጥቃት . . . የሚሰነዝሩት ድርጅቶች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ ሲሆን የጥቃቱ ሰለባ የሚሆኑት ሰዎች ቁጥርም በየዓመቱ እየጨመረ ነው።”​—ዘ ግሎባላይዜሽን ኦቭ ማርተርደም

በዚህ ርዕስ መጀመሪያ ላይ የተጠቀሰውን ጥቃት መለስ ብለን እንመልከት። ለፍንዳታው ኃላፊነቱን የወሰደው ቡድን አባላት ራሳቸውን የነፃነት ተዋጊ እንደሆኑ አድርገው ይቆጥራሉ። እነዚህ ሰዎች በዚያን ጊዜ አገራቸውን ነፃ ለማውጣት እየታገሉ ነበር። ይሁን እንጂ ሰዎች ዓላማቸውን ለማሳካት ሲሉ እንዲህ ያለ ድርጊት እንዲፈጽሙ የሚያነሳሳቸው ምንድን ነው? የሃፌኒን ተሞክሮ እንደ ምሳሌ እንመልከት።

ሃፌኒ የተወለደው በዛምቢያ ሲሆን በአጎራባች አገሮች በሚገኙ የስደተኞች መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ አደገ። ሃፌኒ “በቤተሰቦቼና በሌሎች ሰዎች ላይ የሚፈጸመው ጭካኔ የተሞላበት ድርጊትና ግፍ በጣም ያበሳጨኝ ነበር” ይላል። በመሆኑም ወላጆቹ የነበሩበት የታጣቂዎች ቡድን አባል ሆነ።

ሃፌኒ ያለፈውን ሕይወቱን መለስ ብሎ ሲያስታውስ እንዲህ ይላል፦ “ከስደት ኑሮ ጋር በተያያዘ በጣም የሚያሳዝነው ነገር ይህ ዓይነቱ ሕይወት የሚያስከትለው የስሜት ጠባሳ ነው። ልጆች ከእናቶቻቸውና ከአባቶቻቸው እንዲሁም ከወንድሞቻቸውና ከእህቶቻቸው ይነጠሉ ነበር። በዕድሜ ከፍ ያሉት ወደ ጦር ሜዳ የሚሄዱ ሲሆን ከእነዚህም አብዛኞቹ ወደ ቤተሰቦቻቸው አይመለሱም። አባቴን በፎቶግራፍ እንኳ አይቼው አላውቅም። የማውቀው ነገር ቢኖር በውጊያ ላይ እንደሞተ ብቻ ነው። ይህ ሁኔታ ያስከተለብኝ የስሜት ጠባሳ ዛሬም ድረስ አለ።”

በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ጉዳዩ ውስብስብ ነው። ስለዚህ ጉዳይ የተሻለ ግንዛቤ ማግኘትህ እንዲህ ያለው የዓመፅ ድርጊት እንዲያበቃ ለማድረግ ምን እንደሚያስፈልግ ለመረዳት ያስችልሃል።

[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

አሸባሪዎች እነማን ናቸው?

በዚህ መስክ ጥናት ያካሄዱት ማርክ ጀርገንስማየር እንዲህ ብለዋል፦ “አንድ ሰው የዓመፅ ድርጊቶችን ለመግለጽ ‘አሸባሪ’ የሚለውን ቃል መጠቀም አለመጠቀሙ የሚመካው እነዚህን ድርጊቶች ተገቢ እንደሆኑ አድርጎ ይመለከታቸዋል ወይስ አይመለከታቸውም በሚለው ነጥብ ላይ ነው። አንድ ግለሰብ በዚህ ቃል መጠቀሙ በአመዛኙ የተመካው ለዓለም ባለው አመለካከት ላይ ነው፦ ዓለም ሰላም የሰፈነበት ቦታ እንደሆነ የሚያስብ ከሆነ የዓመፅ ድርጊቶች ሽብርተኝነት እንደሆኑ ይሰማዋል። ዓለም በጦርነት ላይ እንዳለ አድርጎ የሚያስብ ከሆነ ግን የዓመፅ ድርጊቶችን ተገቢ እንደሆኑ አድርጎ ይቆጥራቸዋል።”

ስለዚህ “አሸባሪ” የሚለው ቃል ጥቅም ላይ የሚውልበት መንገድ ብዙውን ጊዜ ፖለቲካዊ አንድምታ አለው። ብዙዎቹ ቡድኖች፣ አሸባሪዎች እንደሆኑ ሳይሆን የነፃነት ተዋጊዎች እንደሆኑ ያስባሉ። አንዲት ጸሐፊ እንደገለጹት ከሆነ ሽብርተኝነት የሚለው ቃል (1) በሲቪሉ ኅብረተሰብ ላይ የተነጣጠሩ የጥቃት ድርጊቶችንና (2) በሰዎች ላይ ፍርሃት ለመልቀቅ ሲባል በዓመፅ ድርጊት መጠቀምን ያመለክታል። በመሆኑም ዓማፂያንም ሆኑ የመንግሥት አካላት የሚደግፏቸው ታጣቂዎች ብዙውን ጊዜ የሽብርተኝነት ስልቶችን ወይም ዘዴዎችን ሊጠቀሙ ይችላሉ።