“ለዚህ ዓምድ አመሰግናችኋለሁ!”
“ለዚህ ዓምድ አመሰግናችኋለሁ!”
● በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች፣ በንቁ! መጽሔት ገጽ 30 እና 31 ላይ የሚወጣውን “ቤተሰብ የሚወያይበት” የሚለውን ዓምድ አስመልክተው አድናቆታቸውን ገልጸዋል። ውይይትና ምርምር ለማድረግ የሚያስችሉት ሥዕሎችና ጥያቄዎች፣ ከመጽሔቱ ላይ ተቆርጠው የሚወጡት የመጽሐፍ ቅዱስ ካርዶች፣ ለልጆች የቀረበው የሥዕል ጥያቄ እንዲሁም ቤተሰብን የሚያሳትፈው ክፍል ለመላው ቤተሰብ ትምህርት ሰጪና አስደሳች ናቸው። ከዚህ በታች የቀረቡትን አንዳንድ አስተያየቶች ተመልከት፦
“የ12 ዓመት ዕድሜ ያላቸውን ሁለት የልጅ ልጆቼን በደብዳቤ አማካኝነት መጽሐፍ ቅዱስ አስጠናቸዋለሁ። ‘ቤተሰብ የሚወያይበት’ በሚለው ዓምድ ላይ ለሚወጡት ጥያቄዎች መልሳቸውን እንዲልኩልኝ አደርጋለሁ። የልጅ ልጆቼ ጥናቱን በጣም ወደውታል፤ እኔም በዓምዱ ላይ ከተጠቀሱት ሐሳቦች ጋር የሚዛመዱ ተጨማሪ ነጥቦችን መልሼ እጽፍላቸዋለሁ። ለዚህ ዓምድ አመሰግናችኋለሁ!”
ቪ. ኬ.፣ ዩናይትድ ስቴትስ
“በቅርቡ፣ የአምስት ዓመት ልጄ ከመተኛቱ በፊት ‘በዚህ ሥዕል ላይ ምን ስህተቶች ይታዩሃል?’ የሚለውን ዓምድ ከሠራን በኋላ ሌላም እንድንደግም ጠየቀኝ። እኔም ሌላ መጽሔት አመጣሁና በሥዕሉ ላይ መነጋገር ጀመርን። ዘገባውን ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ሳነብ ልጄ በጥሞና ያዳምጠኝ ነበር። አሁን አሁን፣ ልጄ በእያንዳንዱ ምሽት ማለት ይቻላል መጽሐፍ ቅዱስን አብረን እንድናነብ ይፈልጋል። ልጆቻችን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ አስደሳች እንዲሆንላቸው ስለረዳችሁን እኔና ቤተሰቤ ከልብ እናመሰግናችኋለን።”
ኤም. ኤፍ.፣ ፈረንሳይ
“በአውቶቡስ ፌርማታ ላይ የ12 ዓመት ልጅ ከሆነው ከዴቪድና የ6 ዓመት ልጅ ከሆነችው ከጄኒፈር ጋር ተገናኘሁ። የልጆቹ አባት ለተሳፋሪዎች ንቁ! መጽሔት ሳበረክት ሲያየኝ ልጆቹ ወደ እኔ መጥተው ምን እንደማደርግ እንዲመለከቱ ልኳቸው ነበር። አባትየውና ወንዱ ልጅ መጽሔቶቹን ሲያነቡ እኔና ጄኒፈር በመጽሔቱ ላይ ያሉትን የሚያማምሩ የአእዋፍና የእንስሳት ሥዕሎች እንዲሁም ፎቶግራፎች መመልከት ጀመርን። በተጨማሪም ይሖዋ አምላክ እንድንደሰትባቸው ስለፈጠራቸው በርካታ ውብ ነገሮች አወራን። ገጽ 31 ላይ ስንደርስ ‘ለልጆች የቀረበ የሥዕል ጥያቄ’ የሚለውን ክፍል ለመሥራት ሞከርን። እኔ የመጀመሪያውን ሥዕል ለማግኘት ስፈልግ ጄኒፈር በቅጽበት ገጾቹን ገልጣ ሥዕሉን አገኘችው። ሁለተኛውንና ሦስተኛውን ሥዕሎችም ከእኔ ቀድማ አገኘቻቸው። እንዲያውም ጄኒፈር ይህን ክፍል መሥራታችንን እንድንቀጥል ስለፈለገች በሌሎች አሥር እትሞች ላይ የሚገኙትን የሥዕል ጥያቄዎች አብረን ሠራን! በመጨረሻም ጄኒፈር ለአባቷና ለወንድሟ የምትወስዳቸው ሁለት መጽሔቶችን እንድሰጣት ጠየቀችኝ። ስንሰነባበት ሦስቱም ለዚህ ግሩም መጽሔት ያላቸውን አድናቆት ገለጹልኝ።”
ኤም. ኬ.፣ ኢኳዶር