አምላክ ያስብልናል?
አምላክ ያስብልናል?
ኅዳር 1, 1755 ጠዋት የፖርቱጋል ዋና ከተማ የሆነችው ሊዝበን በርዕደ መሬት ተመታች። ይህን ተከትሎ የተከሰተው ሱናሚና የእሳት ቃጠሎ የከተማዋን አብዛኛውን ክፍል ያወደመ ከመሆኑም በላይ በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ለሞት ዳረገ።
በ2010 በሄይቲ ርዕደ መሬት ከተከሰተ በኋላ በካናዳ የሚታተመው ናሽናል ፖስት ጋዜጣ በርዕሰ አንቀጹ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር፦ “በጣም አሳዛኝ የሆኑ ነገሮች በሚከሰቱበት ጊዜ ሁሉ የሰው ልጆች በፈጣሪ ላይ ያላቸው እምነት ይፈተናል። ያም ሆኖ በሄይቲ እንደደረሰው ያሉ በዚህ ዘመን የሚከሰቱ ርዕደ መሬቶች በሊዝበን እንደተከሰተው [እጅግ አሳዛኝ አደጋ] ሁሉ ከሌሎች መከራዎች የበለጠ የሰውን ልጅ እምነት ፈተና ላይ ይጥላሉ።” ርዕሰ አንቀጹ ሲደመድም “አምላክ ሄይቲን የተዋት ይመስላል” ብሏል።
ይሖዋ ‘ሁሉን ቻይ አምላክ’ እንደመሆኑ መጠን መከራን ማስወገድ ጨምሮ ማንኛውንም ነገር ለማድረግ የሚያስችል ገደብ የለሽ ኃይል አለው። (መዝሙር 91:1) ከዚህ በተጨማሪ አምላክ እንደሚያስብልን እርግጠኛ መሆን እንችላለን። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው?
ስለ አምላክ ምን የምናውቀው ነገር አለ?
አምላክ በመከራ ውስጥ ለሚገኙ ሰዎች ያዝናል። በግብፅ በባርነት ሥር የነበሩት እስራኤላውያን ግፍ በሚፈጸምባቸው ጊዜ አምላክ ሙሴን እንዲህ አለው፦ “በግብፅ አገር የሚኖሩትን የሕዝቤን መከራ አይቻለሁ፤ ከአሠሪዎቻቸው ጭካኔ የተነሣ የሚያሰሙትንም ጩኸት ሰምቻለሁ፤ ሥቃያቸውንም ተረድቼአለሁ።” (ዘፀአት 3:7) ይህ ምን ያሳያል? አምላክ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰውን መከራ በቸልታ አይመለከትም። እንዲያውም ከብዙ ዘመናት በኋላ ነቢዩ ኢሳይያስ እስራኤላውያንን አስመልክቶ “በጭንቃቸው ሁሉ ተጨነቀ” በማለት ጽፎ ነበር።—ኢሳይያስ 63:9
‘መንገዶቹ ሁሉ ፍትሕ ናቸው።’ (ዘዳግም 32:4 NW) አምላክ የሚያደርገው ነገር በሙሉ ፍትሐዊና አድሎ የሌለበት ነው። አምላክ ‘የታማኞቹን አካሄድ ያጸናል’፤ በሌላ በኩል ደግሞ በጻድቃን ላይ ‘መከራን ለሚያመጡ በአጸፋው መከራን ይከፍላቸዋል።’ (ምሳሌ 2:8፤ 2 ተሰሎንቄ 1:6, 7) “ሁሉም የእጁ ሥራ ስለ ሆኑ፣ እርሱ ለገዦች አያደላም፤ ባለጠጋውንም ከድኻው አብልጦ አይመለከትም።” (ኢዮብ 34:19) ከዚህም ሌላ አምላክ በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰውን መከራ ማስወገድ የሚችልበትን ከሁሉ የተሻለ መንገድ ያውቃል። በአንጻሩ ግን ሰዎች የሚያመጧቸው መፍትሔዎች በጥይት ተመትቶ የቆሰለን ሰው ፕላስተር ብቻ ተጠቅሞ ከማከም ተለይቶ አይታይም። ፕላስተሩ ቁስሉን ሊሸፍንለት ቢችልም ችግሩን ከሥረ መሠረቱ ሊያስወግድም ሆነ የተጎዳው ሰው እየደረሰበት ያለውን ሥቃይ ሊያስቆም አይችልም።
‘አምላክ መሐሪና ሩኅሩኅ እንዲሁም ፍቅራዊ ደግነቱ እጅግ የበዛ ነው።’ (ዘፀአት 34:6 NW) ‘ምሕረት’ የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ፣ አንድ ሰው የተቸገረን ሰው ለመርዳት እንዲነሳሳ የሚያደርገውን ከልብ የመነጨ የርኅራኄና የሐዘኔታ ስሜት ለማመልከት ተሠርቶበታል። “ሩኅሩኅ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ደግሞ “አንድ ሰው ችግር ላይ የወደቀን ግለሰብ ለመርዳት ሲል ከልቡ ተነሳስቶ የሚወስደውን እርምጃ” ያመለክታል። ቲኦሎጂካል ዲክሽነሪ ኦቭ ዚ ኦልድ ቴስታመንት የተባለው መጽሐፍ እንደሚገልጸው ‘ፍቅራዊ ደግነት’ ተብሎ የተተረጎመው ቃል “አሳዛኝ ወይም አስጨናቂ ሁኔታ ያጋጠመውን ሰው ለመርዳት ጣልቃ መግባት” የሚል ፍቺ አለው። ይሖዋ አምላክ ሰዎች መከራ ሲደርስባቸው ከማዘን ያለፈ ነገር ያደርጋል፤ መሐሪ፣ ሩኅሩኅና ፍቅራዊ ደግነት ያለው መሆኑ እነሱን ለመርዳት ይገፋፋዋል። በመሆኑም መከራን ያስወግዳል ብለን በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን።
ቀደም ባለው ርዕስ ላይ በዛሬው ጊዜ በሰው ልጆች ላይ እየደረሰ ላለው መከራ በአብዛኛው መንስኤ የሆኑትን ሦስት ነገሮች ተመልክተናል፤ ለእነዚህ ነገሮች ደግሞ አምላክ ተጠያቂ ሊሆን አይችልም። እስቲ ከእነዚህ ነገሮች በስተጀርባ ያለውን ምክንያት እንመልከት።
ሰዎች የሚያደርጉት ምርጫ
አዳም በመጀመሪያ በአምላክ አገዛዝ ሥር ነበር። ይሁን እንጂ ምርጫ በቀረበለት ጊዜ በመለኮታዊው አገዛዝ ላይ ለማመፅና ከአምላክ መራቁ የሚያስከትልበትን ማንኛውንም ነገር ለመቀበል ወሰነ። በዘፍጥረት 2:17 ላይ የሚገኘውን “በእርግጥ ትሞታለህ” የሚለውን የይሖዋን ማስጠንቀቂያ ችላ አለ። አዳም ፍጹም የሆነውን የአምላክን አገዛዝ ለመቀበል አሻፈረኝ ማለቱ ኃጢአትና አለፍጽምና አስከትሏል። መጽሐፍ ቅዱስ “በአንድ ሰው አማካኝነት ኃጢአት ወደ ዓለም ገባ፤ በኃጢአትም ምክንያት ሞት መጣ፤ ሁሉም ኃጢአት ስለሠሩም ሞት ለሰው ሁሉ ተዳረሰ” ይላል። (ሮም 5:12) ያም ሆኖ አምላክ ኃጢአት ያስከተለውን መዘዝ ያስወግዳል።
ያልተጠበቁ ክስተቶች
ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው የመጀመሪያው ሰው አዳም፣ ከተፈጥሮ አደጋዎች ጭምር ሊጠብቀን የሚችለውን ለሰው ልጆች ደኅንነት አስፈላጊ የሆነውን መለኮታዊ መመሪያ ለመቀበል ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። አዳም ያደረገው ውሳኔ ችሎታና ልምድ ያለው ሐኪም የሚሰጠውን ሕክምና ለመቀበል ፈቃደኛ ካልሆነ ሕመምተኛ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ዶክተሩ፣ በሽታው በሕመምተኛው ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋና የጤና ቀውስ ጠንቅቆ የሚያውቅ ቢሆንም ግለሰቡ የሚነገረውን ነገር ለመስማት ፈቃደኛ ካልሆነ ለመከራ ሊዳረግ ይችላል። በተመሳሳይም ብዙውን ጊዜ ከተፈጥሮ አደጋዎች ጋር በተያያዘ ለሚፈጠረው ችግር ዋነኛ መንስኤ የሆነው ነገር አስተማማኝ ያልሆኑ ሕንፃዎችን መገንባትንና የምድር የተፈጥሮ ኃይሎች የሚሰጡትን የማስጠንቀቂያ ምልክት ቸል ማለትን ጨምሮ ሰዎች ምድርን ማበላሸታቸው ነው። ይሁንና አምላክ ይህ ሁኔታ ባለበት እንዲቀጥል አይፈቅድም።
“የዚህ ዓለም ገዥ”
አምላክ፣ ሰይጣን ካመፀ በኋላ ዓለምን እንዲገዛ የፈቀደለት ለምንድን ነው? አንድ ምንጭ እንደገለጸው ከሆነ “የትኛውም ዓይነት አዲስ መስተዳድር በሥልጣን ዘመኑ መጀመሪያ አካባቢ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ያሉትን ችግሮች በቀድሞው መንግሥት ላይ ማላከኩ አይቀርም።” ይሖዋ ሰይጣንን ወዲያውኑ ቢያጠፋው ኖሮ “የዚህ ዓለም ገዥ” ድክመቱን በቀድሞው ገዥ ይኸውም በአምላክ ላይ ሊያላክክ ይችል ነበር። (ዮሐንስ 12:31) ይሁንና ሰይጣን በዓለም ላይ ያለውን ሥልጣን ሙሉ በሙሉ እንዲጠቀምበት በቂ ጊዜ መሰጠቱ አገዛዙ ስኬታማ እንዳልሆነ አሳይቷል። ያም ሆኖ ‘ወደፊት መከራ እንደሚወገድ እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን?’ የሚለው ጥያቄ መልስ ያሻዋል።