በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የመኪና አደጋ እንዳይደርስ መከላከል የሚቻለው እንዴት ነው?

የመኪና አደጋ እንዳይደርስ መከላከል የሚቻለው እንዴት ነው?

የመኪና አደጋ እንዳይደርስ መከላከል የሚቻለው እንዴት ነው?

ሲጢጥ የሚል የጎማ ድምፅ፣ የብረት መንኳኳት፣ የመስተዋት መሰባበር፣ የሰዎች ጩኸት . . . ። እነዚህ ድምፆች የመኪና አደጋ ደርሶበት ለሚያውቅ ማንኛውም ሰው አዲስ አይሆኑም። ፖፑሌሽን ሬፈረንስ ቢሮ የተባለው ድርጅት “በመላው ዓለም በግምት 1.2 ሚሊዮን የሚያክሉ ሰዎች በየዓመቱ ጎዳና ላይ በሚደርስ ግጭት ምክንያት እንደሚሞቱና እስከ 50 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች ደግሞ ጉዳት እንደሚደርስባቸው” ሪፖርት አድርጓል።

ይሁን እንጂ አንዳንድ የጥንቃቄ እርምጃዎችን በመውሰድና የማመዛዘን ችሎታችንን በመጠቀም አብዛኞቹን አደጋዎች መቀነስ ይቻላል። ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

የፍጥነት ገደብ፣ የደኅንነት ቀበቶና የጽሑፍ መልእክት

በአንዳንድ መንገዶች ላይ የተደረገው የፍጥነት ገደብ ያላግባብ ዝግ ብለን እንድናሽከረክር የሚያስገድድ መስሎ ሊታይ ይችላል። ይሁን እንጂ የፈለግክበት ቦታ ቶሎ ለመድረስ ከተወሰነው ፍጥነት በላይ ብትነዳ የምታተርፈው ጊዜ ያን ያህል ብዙ ለውጥ የሚያመጣ አይደለም። ለምሳሌ 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ለመሸፈን በሰዓት 104 ኪሎ ሜትር ከመጓዝ ይልቅ ፍጥነትህን ጨምረህ በሰዓት 129 ኪሎ ሜትር ብትጓዝ የምታተርፈው ጊዜ ከዘጠኝ ደቂቃ አይበልጥም። ይህችን ትንሽ ጊዜ ለማትረፍ ብለህ ራስህን ለአደጋ ማጋለጥ ተገቢ ይሆናል?

የደኅንነት ቀበቶዎች የተሠሩት ከአደጋ ለመከላከል ነው። በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኝ አንድ መንግሥታዊ ድርጅት ከ2005 እስከ 2009 ባለው ጊዜ ውስጥ የደኅንነት ቀበቶዎች በዚያች አገር ብቻ 72,000 የሚያክሉ ሰዎችን ነፍስ እንዳዳኑ ገልጿል። ኤይር ባግ ለደኅንነት ቀበቶ ምትክ ሊሆን ይችላል? አይችልም። ኤይር ባግ ከአደጋ ለመከላከል የሚረዳው ከደኅንነት ቀበቶ ጋር ሲሆን ነው። የደኅንነት ቀበቶ ካላሰርክ ኤይር ባጉ ያን ይህል ውጤታማ አይሆንም፤ እንዲያውም አደገኛ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ የደኅንነት ቀበቶ የማሰር ልማድ ይኑርህ፤ አብረውህ የተሳፈሩ ሰዎችም የደኅንነት ቀበቶ እንዲያስሩ አድርግ። ሌላው የጥንቃቄ እርምጃ፦ እያሽከረከርክ የጽሑፍ መልእክት ለማንበብም ሆነ ለመላክ ፈጽሞ አትሞክር።

የመንገድ ሁኔታዎችና ጥገና

እርጥብ በሆኑ ወይም በአቧራ፣ በአሸዋ ወይም በጠጠር በተሸፈኑ መንገዶች ላይ የተሽከርካሪዎች ጎማ መንገድ የመቆንጠጥ ኃይሉ ይቀንሳል። እንደነዚህ ባሉት መንገዶች ላይ በዝግታ የምታሽከረክር ከሆነ ፍሬን በምትይዝበት ጊዜ ተሽከርካሪህ ብዙ አይንሸራተትም። በበረዶ በተሸፈኑ መንገዶች ላይ በብዛት የምታሽከረክር ከሆነ ለክረምቱ ወራት የሚሆኑ የበረዶ ጎማዎች ለመግዛት ብታስብ ጥሩ ይሆናል። እነዚህ ጎማዎች ትላልቅ ጥርሶች ስላሏቸው መንገዱን ጥሩ አድርገው ይቆነጥጣሉ።

መስቀለኛ መንገዶች ለማንም አሽከርካሪ አደገኛ ናቸው። አንድ ኤክስፐርት የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል፦ የትራፊክ መብራቱ አረንጓዴ ሲሆን ወዲያው ወደ ማቋረጫው አትግባ። ጥቂት ብትታገሥ ቀይ መብራት ጥሶ በሚመጣ ተሽከርካሪ ከመገጨት ትድናለህ።

መኪናህን በጥሩ ሁኔታ መያዝህ አደጋዎችን ለማስወገድ የሚረዳ መሠረታዊ ነገር ነው። በማሽከርከር ላይ እንዳለህ ፍሬኑ አልይዝ ቢልህ ምን ዓይነት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል አስብ። አንዳንድ የመኪና ባለንብረቶች የቴክኒክ ችግር እንዳያጋጥማቸው በየተወሰነ ጊዜው መኪናቸውን ብቃት ባለው ባለሙያ ያስጠግናሉ። ሌሎች ባለመኪናዎች ደግሞ አንዳንድ ጥገናዎችን ራሳቸው ያደርጋሉ። በዚያም ሆነ በዚህ መኪናህ የሚያስፈልገውን ምርመራና ጥገና በጊዜው ማግኘቱን አረጋግጥ።

ጠጥቶ ማሽከርከር

በሌላ ጊዜ ተጠንቅቀው የሚነዱ አሽከርካሪዎች የአልኮል መጠጥ ጠጥተው ሲያሽከረክሩ ለአደጋ በሚያጋልጥ ሁኔታ ሊያሽከረክሩ ይችላሉ። በ2008 በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከ37,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች በመኪና አደጋ ምክንያት ሕይወታቸውን አጥተዋል። ከእነዚህ መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት የሞቱት ጠጥተው ሲያሽከረክሩ በነበሩ ሰዎች ምክንያት በተፈጠረ ግጭት ነው። ትንሽ የአልኮል መጠጥ መጠጣትህ እንኳ የማሽከርከር ችሎታህን ሊያዛባብህ ይችላል። አንዳንዶች የሚያሽከረክሩ ከሆነ ጭራሽ መጠጥ የሚባል ነገር ላለመጠጣት ይወስናሉ።

የትራፊክ ሕግን ማክበር፣ የደኅንነት ቀበቶ ማሰር፣ መኪናን ጥሩ አድርጎ መያዝና የአልኮል መጠጥ ጠጥቶ አለማሽከርከር ያንተንም ሆነ የሌሎችን ሕይወት ሊያድን ይችላል። እነዚህ ምክሮች ከአደጋ ሊያድኑህ የሚችሉ ቢሆኑም ሊያድኑህ የሚችሉት ተግባራዊ ካደረግካቸው ብቻ ነው።

[በገጽ 11 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

እንቅልፍ እየተጫጫነህ አታሽከርክር

“ሰዎች፣ እንቅልፍ ተጫጭኖት የሚያሽከረክር ሰው ሰክሮ ከሚያሽከረክር ሰው ብዙም እንደማይለይ ማስታወስ አለባቸው።” የዩናይትድ ስቴትስ ናሽናል ስሊፕ ፋውንዴሽን ባለሥልጣን የተናገሩት ይህ ሐሳብ እንቅልፍ ተጫጭኖህ እያለ ማሽከርከር ምን ያህል አደገኛ እንደሆነ ያሳያል። የሚከተሉት ምልክቶች የሚታዩብህ ከሆነ በዚህ ወቅት ማሽከርከርህ አደገኛ ነው ማለት ነው፦ *

ዓይንህ ብዥ ካለብህ፣ ቶሎ ቶሎ ከተርገበገበ ወይም ዓይንህ ከከበደ

ጭንቅላትህን ቀጥ ማድረግ ካስቸገረህ

በተደጋጋሚ ካዛጋህ

ምን ያህል ርቀት እንደነዳህ ማስታወስ ካቃተህ

መገንጠያ መንገዶችን ወይም የትራፊክ ምልክቶችን ከሳትክ

ከመስመርህ ከወጣህ፣ ከፊትህ ወዳለው ተሽከርካሪ በጣም ከተጠጋህ ወይም እያንገጫገጭክ ከነዳህ

እነዚህ ምልክቶች ከታዩብህ ሌላ ሰው እንዲያሽከረክር አድርግ ወይም ደግሞ አመቺ ቦታ ፈልገህ መኪናህን በማቆም ትንሽ አሸልብ። ለራስህም ሆነ ለሌሎች ደኅንነት ስትል ከጉዞህ ትንሽ ብትዘገይ ምንም የሚያስቆጭ አይሆንም።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.16 ከናሽናል ስሊፕ ፋውንዴሽን የተገኘ ዝርዝር።