በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የዌልስ እረኞች የአንድ ዓመት ሕይወት

የዌልስ እረኞች የአንድ ዓመት ሕይወት

የዌልስ እረኞች የአንድ ዓመት ሕይወት

በመላው ዓለም ያሉ እረኞች ከአንድ ቢሊዮን የሚበልጡ በጎችን ይንከባከባሉ። እያንዳንዱ ወቅት የራሱ የሆኑ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ይዞ ይመጣል። ጀርዊን፣ ዮአንና ህሪያን የበጎቹ ቁጥር ከሕዝቡ በሦስት እጥፍ ገደማ በሚበልጥባቸው በዌልስ ተራሮች ላይ አንድ እረኛ የሚያከናውናቸውን ሥራዎች ይገልጹልናል።

የጸደይ ግልገሎች

ጸደይ ሲመጣ እረኞች ቀን ከሌት እርጉዝ በጎቻቸውን በማዋለድ ሥራ ይጠመዳሉ።

ጀርዊን፦ “በዓመቱ ውስጥ ከምናከናውናቸው ሥራዎች መካከል በጣም አድካሚው በጎቹን ማዋለድ ቢሆንም እጅግ የሚክስ ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ደግሞም በደንብ የሠለጠነ ውሻ የሚሰጠው አገልግሎት በዋጋ ሊተመን አይችልም። አንዲት በግ ምጥ ከጠናባት ውሻዬ በቀስታ ይይዛትና መሬት ላይ እንድትቀመጥ ያደርጋታል። ይህም እሷን ለመርዳት አመቺ ያደርግልኛል።”

ዮአን፦ “በጎችን ብዙ ጊዜ ያዋለድኩ ቢሆንም አዲስ የተወለዱ ግልገሎችን ማየት ሁልጊዜ ልዩ ስሜት ይፈጥርብኛል!”

በበጋ መሸለት

እረኞች በበጋ የሚያከናውኑት ሥራ የበጎችን ፀጉር መሸለት ሲሆን የተሸለተው ፀጉር መጠን እንደየበጎቹ ዝርያ እስከ 10 ኪሎ ግራም ሊመዝን ይችላል። አንድ እረኛ በቀን እስከ 250 የሚደርሱ በጎችን ሊሸልት ይችላል።

ህሪያን፦ “በጎቹ እንዲሸለቱ ለማዘጋጀት በመጀመሪያ በበጎቹ ላት ዙሪያ ያለውን ቆሻሻ ፀጉር አስወግዳለሁ። ችሎታ ያላቸው ሸላቾች በኤሌክትሪክ የሚሠራ መላጫ በመጠቀም በሁለት ደቂቃ ውስጥ የበጉን ፀጉር ሙልጭ አድርገው ሊሸልቱ ይችላሉ። ፀጉሩን በማጽዳቱ ሥራም እርዳታ አበረክታለሁ፤ ከዚያ በኋላ ፀጉሩን በጥንቃቄ ሰብስቤ ጆንያ ውስጥ በመክተት ለሽያጭ አዘጋጀዋለሁ።”

እረኞች በዝቅተኛ ቦታ ካለው ማሳ ላይ ሣር አጭደው ለበጎቻቸው የሚሆን ጥሩ ድርቆሽ ለማዘጋጀት ዝናብ የማይጥልባቸው ሁለት ሳምንታት ቢያገኙ ደስ ይላቸዋል። መንጋው ክረምቱን ሙሉ የሚመገበው ይህን ድርቆሽ ነው። የእረኞቹ የቤተሰብ አባላትና ወዳጆች ተረዳድተው ድርቆሹን ወደሚቀመጥበት ስፍራ ያጓጉዛሉ።

ዮአን፦ “በጣም ደስ ከሚሉኝ ጊዜያት አንዱ አዝመራው ሁሉ ተሰብስቦ ከገባ በኋላ በማግስቱ ጠዋት ማሳው ውስጥ መንሸራሸር ነው።”

በመከር መሰብሰብ

እረኞች በጎቹን ጡት ከጣሉት ግልገሎቻቸው ለመለየት፣ መንጎቹን ተሰማርተው ከነበሩበት ከፍ ያለ ቦታ ሰብስበው ያመጧቸዋል።

ዮአን፦ “በአንዳንዶቹ ተራሮች ላይ አጥር ወይም ካብ ባይኖርም እንኳ በጎች የሚጠፉት ወይም ወደ ጎረቤት ይዞታ ገብተው የሚገኙት ከስንት አንዴ ነው። እናት የሆነችው በግ የግጦሽ መስኩን ድንበር ታውቀዋለች። ይህቺ በግ ይህን የምትማረው ከእናቷ ወይም ከእረኛው ነው፤ እሷ ደግሞ በተራዋ ለምትወልዳቸው እንስት ግልገሎች ድንበሩን ታስተምራቸዋለች። ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ፣ ጥቂት በጎች ባዝነው የሚጠፉ ሲሆን እነሱን ለማግኘት ለብዙ ሰዓታት፣ አልፎ ተርፎም ለብዙ ቀናት እንደክማለን።”

በተጨማሪም እረኞቹ ለእንስት በጎቻቸው የሚሆኑ አውራ በጎችን በጥንቃቄ መርጠው ይገዛሉ። ከ25 እስከ 50 ለሚያህሉ እንስት በጎች አንድ አውራ በግ ያስፈልጋል። እነዚህ አውራ በጎች ወደፊት የመንጋው ቁጥር እንዲበራከት ስለሚያደርጉ እንደ መዋዕለ ንዋይ ይታያሉ።

አውራ በጎቹ እንስቶቹን ካጠቋቸው በኋላ ባሉት ከ10 እስከ 12 ሳምንታት ውስጥ እረኛው የአልትራሳውንድ መሣሪያ በመጠቀም የትኞቹ በጎች እንደፀነሱና እያንዳንዳቸው በመጪው ጸደይ ስንት ግልገሎችን እንደሚወልዱ ለማወቅ ጥረት ያደርጋል። መካን የሆኑት እንስት በጎች ይሸጣሉ። አንድ ግልገል ያረገዙት በጎች አንድ ላይ ይደረጋሉ፤ ሁለት ወይም ሦስት ግልገል የፀነሱት ደግሞ ልዩ ትኩረትና ተጨማሪ ምግብ ይሰጣቸዋል።

በክረምት መቀለብ

ቀኑ አጭር በሆነበት የክረምት ወቅት እረኛው አብዛኛውን ጊዜውን የሚያሳልፈው እርጉዝ በጎችን በመመገብ ነው። የአየሩ ሁኔታ ምንም ሆነ ምን እረኛው ምንጊዜም ከበጎቹ አይለይም፤ ይህም አካባቢው በበረዶ በሚሸፈንበት ጊዜ በጎቹ በቂ ምግብ እንዲያገኙ ለማድረግ ያስችለዋል።

ጀርዊን፦ “እንዲህ ባሉት ጊዜያት በጎች የእረኛቸው ክትትል የሚያስፈልጋቸው ሲሆን ምግብ የሚሰጣቸውም ሆነ የሚንከባከባቸው እሱ ነው።”

ህሪያን፦ “በዓመቱ ውስጥ ባሉት ወቅቶች በሙሉ መስክ ላይ መዋልና በእንስሳትም ሆነ በእፅዋት ላይ የሚከሰተውን ለውጥ ማየት መንፈስን ያድሳል፤ ይህም በጣም የምወደው መንጎቼን የመንከባከቡ ሥራ የሚያስገኝልኝ ተጨማሪ ወሮታ ነው።”

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ሰሜናዊ አየርላንድ

አየርላንድ

ስኮትላንድ

ዌልስ

እንግሊዝ

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዮአን አንድን አውራ በግ በጥንቃቄ ሲመረምር

[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ጀርዊን በደንብ ከሠለጠነ በግ ጠባቂ ውሻ ጋር