በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

አንድን ዘፈን ተወዳጅ የሚያደርገው ምንድን ነው?

አንድን ዘፈን ተወዳጅ የሚያደርገው ምንድን ነው?

አንድን ዘፈን ተወዳጅ የሚያደርገው ምንድን ነው?

የሙዚቃው ኢንዱስትሪ እጅግ በጣም ፈጣን እድገት የሚታይበት፣ ተለዋዋጭና ከፍተኛ ፉክክር ያለበት ነው። የሙዚቃ ምርጫ ይለዋወጣል፤ ዛሬ ተወዳጅ የሆነ ሙዚቃ ወዲያው ይሰለቻል፤ አሮጌ ቴክኖሎጂዎች በአዲስ ይተካሉ፤ የቆዩ ስልቶችም በአዲስ መልክ ይቀርባሉ። የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያ የሆኑት ኬሊ ኤስ. በርንስ የሙዚቃ ሥራ አስተዋዋቂዎች “ሁልጊዜ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት የሚችል አዲስ ሙዚቃ ይፈልጋሉ” ሲሉ ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ያንን “ሙዚቃ” ተወዳጅ እንዲሆንና በብዛት እንዲሸጥ ማድረግ ቀላል ሥራ አይደለም። ስለ ሙዚቃ ኢንዱስትሪ የሚናገር አንድ መጽሐፍ “በጣም ብዙ ወጣቶች ኮከብ ሙዚቀኞች የመሆን ሕልም አላቸው፤ . . . ይሁን እንጂ ሙዚቃ በማስቀረጽ ይህን ሕልማቸውን እውን ማድረግ ብዙ ውጣ ውረድ የሚጠይቅ ነገር ነው” ብሏል።​—በገጽ 6 ላይ የሚገኘውን “በሙዚቃው ኢንዱስትሪ የተደረጉ ለውጦች” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

ግጥምን ከሙዚቃ ጋር ማዋሃድ

የግጥምና የዜማ ደራሲዎች (1) የሰዎችን ስሜት የሚኮረኩሩ ማለትም በተስፋቸው፣ በሚያልሙት ነገርና በውስጣዊ ስሜታቸው ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ስንኞችን ለመጻፍ ይጥራሉ። ለመሆኑ ብዙ የሚጻፍለት ርዕሰ ጉዳይ የትኛው ይመስልሃል? ትክክል ገምተሃል፤ ፍቅር ነው። በተጨማሪም እነዚህ ደራሲዎች የአድማጮችን ቀልብ የሚስብና ከተሰማ በኋላም ከአእምሮ የማይጠፋ ዜማ ለመድረስ ይሞክራሉ።

ከዚያም ደራሲው የዘፈኑን የሙከራ ወይም የናሙና ቅጂ ያዘጋጃል። የሙዚቃ አሳታሚው ኩባንያ ኃላፊዎች ዘፈኑ ገበያ ያገኛል ብለው ካመኑበት የቀረጻ ኮንትራት (2) ይዋዋላሉ። በዘፋኙ ላይ ትንሽ ቅር የሚላቸው ነገር ካለ ግን (ምናልባትም ያን ያህል ታዋቂ ዘፋኝ ካልሆነ ወይም ካልሆነች) ዘፈኑን ገዝተው የተሻለ እውቅና ያለው ዘፋኝ እንዲዘፍነው ሊያደርጉ ይችላሉ።

ስቱዲዮ ውስጥ

የሙዚቃ ቀረጻ ኩባንያዎች የቀረጻውን ሂደት (3) የሚቆጣጠርላቸው ልምድ ያለው ፕሮዲዩሰር ይቀጥራሉ። ፕሮዲዩሰሩ ዘፈኑንና የአዘፋፈን ስልቱን አይቶ ጥሩ መሆን አለመሆኑን ይወስናል። በተጨማሪም የሙዚቃ አቀናባሪዎችን፣ ኖታ ገልባጮችን፣ የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾችን፣ አጃቢ ድምፃውያንንና የቀረጻ ቴክኒሽያኖችን ይቀጥራል፤ ከዚህም ሌላ ቀረጻው የሚደረግበትን ስቱዲዮ እንዲሁም ጥራቱን የጠበቀና ጥሩ ገበያ የሚያስገኝ ሥራ ለመሥራት የሚያስችሉ ሌሎች አስፈላጊ የቀረጻ መሣሪያዎችን ይከራያል።

አብዛኞቹ ቀረጻዎች የሚካሄዱት ደረጃ በደረጃ ሲሆን ብዙውን ጊዜ ከበሮ፣ ጊታር፣ ቤዝ ጊታርና ኪቦርድ መጀመሪያ ላይ ይቀረጻሉ። በኋላ ላይ የዋናው ዘፋኝና የአጃቢዎቹ ድምፅ፣ በተናጠል ጎልተው የሚወጡ የሙዚቃ መሣሪያዎች እንዲሁም ለየት ያሉ የድምፅ ቅንብሮች ይታከሉበትና ማስተር ቅጂው (4) ይዘጋጃል።

ሽያጭ

የሙዚቃ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን ለማስተዋወቅ አብዛኛውን ጊዜ የሙዚቃ ክሊፕ (5) ያዘጋጃሉ። እነዚህ ከሦስት እስከ አምስት ደቂቃ የሚደርስ ቆይታ ያላቸው ፊልሞች በቀጥታ ከመድረክ የሚቀርቡ ሙዚቃዎች የሚፈጥሩትን ስሜት በተወሰነ ደረጃ ለማጣጣም የሚረዱ ከመሆናቸውም በላይ አርቲስቶቹ ከሕዝብ ጋር እንዲተዋወቁ ያደርጋሉ። በተጨማሪም ቀላል ነው የማይባል ገቢ ያስገኛሉ።

ዘፋኞች ሥራዎቻቸውን በቀጥታ ከመድረክ በሚያቀርቡባቸው (6) አካባቢዎች የሙዚቃ አልበሞቻቸው ብዙ ይሸጡላቸዋል። በመሆኑም ብዙ ጊዜ ወደተለያዩ ቦታዎች በመጓዝና የሙዚቃ ዝግጅቶችን በማቅረብ አዲስ አልበማቸውን ያስተዋውቃሉ። በተጨማሪም አብዛኞቹ አርቲስቶች የሙዚቃ ናሙናዎችን፣ ፎቶግራፎችን፣ ቪዲዮዎችን፣ ውሏቸውን የሚያሰፍሩበትን ብሎግና ስለሚያቀርቧቸው ኮንሰርቶች የሚናገሩ ዜናዎችን የያዘ የግል ድረ ገጽ (7) ይከፍታሉ፤ ድረ ገጻቸውም ወደ አድናቂዎቻቸው ክበብ የሚመራ ሊንክ ያለው ሲሆን ከሁሉም በላይ ደግሞ ሙዚቃዎቻቸውን በኢንተርኔት አማካኝነት መግዛት ስለሚቻልበት መንገድ ይገልጻል።

አንድ ሙዚቃ ተወዳጅ መሆኑንና አለመሆኑን የሚወስነው ማን ነው? የሙዚቃው አድማጭ ራሱ ነው። ታዲያ የምታዳምጠውን ሙዚቃ የምትመርጥበት መስፈርት ምንድን ነው? እንዲሁ ምቱ ደስ ስላለህ ወይም አርቲስቱ ታዋቂ ስለሆነ ብቻ ነው ወይስ የሥነ ምግባር እሴቶችንም ግምት ውስጥ ታስገባለህ? ሙዚቃ ከፍተኛ ኃይል ስላለውና በስሜታችን ላይ ጥልቅ የሆነ ተጽዕኖ ሊያሳድር ስለሚችል እነዚህን ጥያቄዎች ማንሳት ተገቢ ነው። ይህ ሐቅ ፈጣሪያችን የሰጠንን “ከሁሉም በላይ ልብህን ጠብቅ፤ የሕይወት ምንጭ ነውና” የሚለውን አስፈላጊ የሆነ ምክር እንድናስታውስ ያደርገናል።​—ምሳሌ 4:23

በሙዚቃ ረገድ ይህን ከፍተኛ ጥበብ ያዘለ ምክር ሥራ ላይ ልታውል የምትችለው እንዴት ነው? ወላጅ ከሆንክ ደግሞ ልጆችህን ከመንፈሳዊ፣ ከአእምሯዊና ከስሜታዊ ጉዳት የመጠበቅ ኃላፊነትህን ልትወጣ የምትችለው እንዴት ነው?

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በሙዚቃው ኢንዱስትሪ የተደረጉ ለውጦች

ኢንተርኔት እንዲሁም ሙዚቃን በቀላሉ መቅዳት የሚያስችሉ ብዙ ወጪ የማይጠይቁ መሣሪያዎችና ሶፍትዌሮች መኖራቸው በሙዚቃው ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ ለውጥ አምጥቷል። ዛሬ፣ ዛሬ፣ ሙዚቀኞች ቤታቸው ቁጭ ብለው ከፍተኛ ጥራት ያላቸው ሙዚቃዎችን በመቅረጽ በመላው ዓለም ለሚገኙ አድማጮች ማሰራጨት ይችላሉ። ዚ ኢኮኖሚስት በተባለው መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ሪፖርት እንደሚያሳየው “ከፍተኛ ዝና ያተረፉ በርካታ አርቲስቶች የታወቁ ኩባንያዎችን መጠቀም ሳያስፈልጋቸው ሙዚቃዎቻቸውን ማሰራጨት ችለዋል።”