አጥቢ የሆኑ የባሕር እንስሳት ስብ
ንድፍ አውጪ አለው?
አጥቢ የሆኑ የባሕር እንስሳት ስብ
● ዶልፊኖች በሰዓት 40 ኪሎ ሜትር በሚደርስ ፍጥነት ሊዋኙ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ የሳይንስ ሊቃውንት ለበርካታ ዓመታት ግራ ተጋብተው ነበር። ሊቃውንቱ፣ እነዚህ እንስሳት በዚህ ፍጥነት ለመዋኘት የሚያስችል በቂ ጡንቻ የላቸውም ብለው ያስቡ ነበር። ይሁንና ዶልፊኖች ይህን ለማድረግ የሚያስችላቸው ሚስጥር አላቸው፤ በፍጥነት ለመዋኘት ከሚያስችሏቸው ነገሮች አንዱ ከቆዳቸው ሥር የሚገኘው ውስብስብ አሠራር ያለው ስብ ነው። ዓሣ ነባሪዎች፣ ፖርፐስ የተባለው አነስተኛ ዓሣ ነባሪ እንዲሁም ሌሎች የባሕር እንስሳት እንዲህ ያለ ስብ አላቸው።
እስቲ የሚከተለውን አስብ፦ አጥቢ የሆኑ የባሕር እንስሳት ስብ፣ የሰውነት ክፍሎችን እርስ በርስ የሚያያይዙ በጣም የተደራጁ ሕብረ ሕዋሳት ንብርብር ሲሆን ይህ ንብርብር ደግሞ ወፍራምና ጥቅጥቅ ያለ ነው። ይህ ስብ የባሕር እንስሳቱን ሙሉ አካል ይሸፍናል ማለት ይቻላል፤ ኒው ዎርልድ ኢንሳይክሎፒዲያ እንደሚገልጸው “ይህ ስብ በጣም በተደራጁና እንደ መረብ ያለ ቅርጽ ባላቸው ጅማቶች አማካኝነት ከእንስሳቱ ጡንቻና አጥንቶች ጋር ተያይዟል።” እነዚህ ጅማቶች ደግሞ በተለጣጭ ጭረቶችና ኮለጅን በተባለ ፕሮቲን የተዋቀሩ ናቸው፤ ኮለጅን የተባለው ፕሮቲን በቆዳና በአጥንት ውስጥም ይገኛል። የባሕር እንስሳት ስብ፣ ቅዝቃዜ እንዳይገባ የሚከላከል ነገር ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ እጅግ የተወሳሰበ የተለያዩ ሕያዋን ሕብረ ሕዋሳት ጥምረት ነው።
ይሁንና ይህ ስብ፣ ዶልፊኖች እንዲሁም ፖርፐስ የተባሉት ዓሣ ነባሪዎች በከፍተኛ ፍጥነት እንዲዋኙ (ለምሳሌ፣ ዶል ፖርፐስ በሰዓት እስከ 56 ኪሎ ሜትር በሚደርስ ፍጥነት መዋኘት ይችላል) የሚያስችላቸው እንዴት ነው? አንደኛ ነገር የባሕር እንስሳት ስብ፣ እንስሳቱ በፍጥነትና ጉልበት ሳያባክኑ ለመዋኘት የሚያስችል ቅርጽ እንዲኖራቸው ያደርጋል። በሌላ በኩል ደግሞ ጀርባቸው ላይ ባለው ወጣ ብሎ የሚታይ ክፍል እና በጅራታቸው መካከል ያለው ስብ ከፍተኛ መጠን ያለው ኮለጅንና ተለጣጭ ጭረት የያዘ ነው፤ ኮለጅኑና ተለጣጩ ጭረት የተቀመጡት እርስ በርስ ተጠላልፈው ነው። ይህ መሆኑ ደግሞ የእንስሳቱ ጅራት የሚለጠጥ እንዲሆንና ኃይልን አምቆ የመያዝ ችሎታ እንዲኖረው ያደርጋል። በመሆኑም በአንዳንድ የባሕር እንስሳት ስብ ውስጥ የሚገኙት ሕብረ ሕዋሳት፣ እንስሳቱ ብዙም ጉልበት ሳያባክኑ መዋኘት እንዲችሉ ይረዷቸዋል።
በተጨማሪም የባሕር እንስሳት ስብ፣ እንስሳቱ መንሳፈፍና ሙቀታቸውን መጠበቅ እንዲችሉ ይረዳቸዋል። በሰውነታቸው ውስጥ የተጠራቀመው ስብ ለችግር ጊዜ የሚያገለግል ኃይል እንዲኖራቸው ያደርጋል። በእርግጥም በርካታ አገልግሎቶች ያሉት የባሕር እንስሳት ስብ፣ መርከቦች ብዙም ጉልበት ሳያባክኑ በፍጥነት የመጓዝና የመስፈንጠር ችሎታቸው የተሻለ እንዲሆን ለማድረግ የሚጥሩ ሊቃውንትን ትኩረት መሳቡ የሚያስደንቅ አይደለም።
ታዲያ ምን ይመስልሃል? በርካታ አስደናቂ ባሕርያት ያሉት የባሕር እንስሳት ስብ እንዲሁ በአጋጣሚ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የመሰላል ቅርጽ ያላቸው ጭረቶች
እርስ በርስ ተጠላልፈው የተቀመጡት ኮለጅንና ተለጣጭ ጭረት ከጎን ሲታዩ