ከዓለም አካባቢ
ከዓለም አካባቢ
በካናዳና በዩናይትድ ስቴትስ፣ በአካባቢ ላይ ጉዳት የማያስከትሉ በተባሉ 5,296 ምርቶች ላይ በተደረገ ጥናት 95 በመቶ የሚሆኑት “አካባቢን የማይበክሉ መሆናቸው ገና እንዳልተረጋገጠ ተደርሶበታል።”—ታይም፣ ዩናይትድ ስቴትስ
በባንኮክ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ የሚሠሩት የደኅንነት ሠራተኞች የአንዲትን ሴት ሻንጣዎች በኤክስሬይ ሲመረምሩ በውስጡ “አንድ እንግዳ ነገር እንዳለ ጠረጠሩ።” ሠራተኞቹ አንዱን ሻንጣ ሲከፍቱት ማደንዘዣ የተወጋ በሕይወት ያለ የታይገር ግልገል አገኙ።—ወርልድ ዋይልድላይፍ ፈንድ፣ ታይላንድ
ብዝሃ ሕይወት በአማዞን አካባቢ
የአማዞን ወንዝ ተፋሰስ አካባቢ፣ ብዛት ያላቸው ሕያዋን ፍጥረታት መርመስመሻ በመሆናቸው በዓለም ላይ ከሚታወቁት አካባቢዎች አንዱ ነው። ባለፈው አሥር ዓመት ውስጥ ከ1,200 በላይ ዕፅዋትና እንስሳት ይኸውም ዓሦች፣ በውኃ ውስጥም ሆነ በየብስ ላይ የሚኖሩ እንስሳት፣ በደረታቸው የሚሳቡ እንስሳት፣ ወፎችና አጥቢ እንስሳት እንደተገኙና እንደየወገናቸው እንደተለዩ ወርልድ ዋይልድላይፍ ፈንድ ያወጣው ዘገባ ይጠቁማል። ይህ ማለት በአማዞን ወንዝ ተፋሰስ አካባቢ በአማካይ በየሦስት ቀኑ አንድ ዝርያ ይገኛል ማለት ነው። በብራዚል የሚገኘው የወርልድ ዋይልድላይፍ ፈንድ አስተባባሪ የሆኑት ሣራ ኸቸሰን እንዲህ ብለዋል፦ “[በየጊዜው] የሚገኙት አዳዲስ ዝርያዎች ብዛት በጣም አስገራሚ ነው፤ ይህ ቁጥር ደግሞ የተገኙትን በርካታ ነፍሳት አይጨምርም።”
በሥራ ቦታ የሚያጋጥም ውጥረት
አንድ አምስተኛ የሚሆኑት ፊንላንዳውያን ትኩረት ማድረግና ማስታወስ አለመቻላቸው ሥራቸውን በብቃት ማከናወን እንዳይችሉ እንዳደረጋቸው ይሰማቸዋል። ከሥራ ጋር ስለተያያዘ ጤንነት የሚያጠና በፊንላንድ የሚገኝ አንድ ተቋም ባወጣው ዘገባ መሠረት እንዲህ ዓይነቶቹ ችግሮች ከ35 ዓመት በታች ያሉ ሰዎችን ይበልጥ እያጠቁ ነው፤ በዚህ ዕድሜ ያሉ ሰዎች አእምሮ፣ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ከፍተኛ ብቃት ሊኖረው ይገባ ነበር። ለዚህ ችግር መንስኤ እንደሆኑ ከሚጠቀሱት ነገሮች መካከል የመረጃ መዥጎድጎድና በኮምፒውተር አሠራር ላይ በየጊዜው የሚደረጉ ለውጦች ይገኙበታል። “ብዙዎች ለሥራቸው አስፈላጊ የሆነውን መረጃ መርጠው ለማውጣት አስቸጋሪ እስኪሆንባቸው ድረስ ብዛት ያለው መረጃ እንደሚጎርፍባቸው ይሰማቸዋል” በማለት ፕሮፌሰር ኪቲ መለር ይናገራሉ። ሄልሲንኪ ታይምስ ደግሞ እንዲህ ይላል፦ “ውጥረቱ ለረጅም ጊዜ ከዘለቀ አንጎላችን ይለምደውና በጠና እስክንታመም ድረስ ከልክ ያለፈ ውጥረት እንደገጠመው ምልክት መስጠቱን ሊያቆም ይችላል።”
ዓመፅ ስለሚንጸባረቅባቸው ጨዋታዎች ማሰብ ብስጩ ያደርጋል?
አንድ ሰው ዓመፅ ያለበት የቪዲዮ ጨዋታ ከተጫወተ በኋላ ብስጩ የሚሆነው ለምን ያህል ጊዜ ነው? ተመራማሪዎች የተወሰኑ ወንድና ሴት ተማሪዎችን መርጠው ለ20 ደቂቃ ያህል ዓመፅ የሚንጸባረቅባቸውን ወይም ዓመፅ የሌለባቸውን የቪዲዮ ጨዋታዎች እንዲጫወቱ አደረጉ። ከዚያም ከእያንዳንዱ ቡድን አባላት መካከል ግማሾቹ ስለተጫወቱት ጨዋታ እንዲያስቡ ተጠየቁ። ዘገባው እንዲህ ይላል፦ “በቀጣዩ ቀን እነዚህ ተማሪዎች ከአንድ ሰው ጋር እንደሚፎካከሩ በማሰብ የሚሠሩት ሥራ ተሰጣቸው፤ በውድድሩ ያሸነፈው ግለሰብ በጆሮ ማዳመጫ በኩል የሚያደነቁር ድምፅ በማሰማት ተሸናፊውን ይቀጣዋል።” በውጤቱም ዓመፅ ስለሚንጸባረቅበት ጨዋታ እንዲያስቡ የተነገራቸው ወንዶች ይበልጥ ብስጩ እንደሆኑ ታይቷል። ሶሻል ሳይኮሎጂካል ኤንድ ፐርሰናሊቲ ሳይንስ የተሰኘው መጽሔት ጥናቱን ያቀረቡት ሰዎች እንደሚከተለው እንዳሉ ዘግቧል፦ “ዓመፅ ያለባቸውን ጨዋታዎች የሚጫወቱ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ የሚጫወቱት ከ20 ደቂቃ ለሚበልጥ ጊዜ ሲሆን ምናልባትም ስለ ጨዋታው የማሰብ ልማድ ይኖራቸዋል።” ሴቶቹ ተማሪዎች ግን ያን ያህል የጎላ የባሕርይ ለውጥ አልታየባቸውም፤ በጥቅሉ ሲታይ ሴቶች ዓመፅ የሚንጸባረቅባቸውን የቪዲዮ ጨዋታዎች መጫወት አይወዱም።