ጥሩ ምርጫ ታደርግ ይሆን?
ጥሩ ምርጫ ታደርግ ይሆን?
የ17 ዓመቱ ጆርዳን * “ወላጆቼ የሚሰሙት ሙዚቃ በጣም ደባሪ ነው” በማለት ቅሬታውን ገልጿል።
የጆርዳን እናት ዴኒስ ደግሞ “ልጄ የሚሰማው ሙዚቃ ጩኸትና ቁጣ የሞላበት ነው” ስትል አማራለች።
ወላጆችና ልጆች ብዙ ጊዜ በሙዚቃ ምርጫ ረገድ የሚጋጩት ለምንድን ነው? አንደኛው ምክንያት ዕድሜ እየገፋ ሲሄድ የሙዚቃ ምርጫም እየተለወጠ ስለሚሄድ ነው። ሌላው ምክንያት ደግሞ ሙዚቃ ራሱ የሚለወጥ መሆኑ ነው። በመሆኑም ዛሬ ተወዳጅ የሆነ ሙዚቃ ነገ ጊዜ ያለፈበት ይሆናል።
ያም ሆነ ይህ ሙዚቃ በሁላችንም ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ አለ። ሙዚቃ ምን ያህል ስሜትህን እንደሚነካ አስተውለሃል? የጥንቷ እስራኤል ገዢ የነበረው ንጉሥ ሳኦል መንፈሱ በሚረበሽበት ጊዜ ዘና የሚያደርግ ሙዚቃ ሲያዳምጥ ይረጋጋ ነበር። (1 ሳሙኤል 16:23) ሙዚቃ በአንዳንድ መንገዶች ጓደኛ ከምናደርጋቸው ሰዎች ጋር ሊመሳሰል ይችላል። አንዳንዶቹ ሙዚቃዎች እንደ ደስታና ፍቅር ያሉ ጥሩ ስሜቶች በውስጣችን እንዲፈጠሩ ያደርጋሉ። ሌሎቹ ደግሞ እንደ ቁጣና ጥላቻ ያሉትን መጥፎ ባሕርያት እንድናንጸባርቅ ያደርጉናል።—ምሳሌ 13:20
ሙዚቃ ይህን ያህል ከባድ ተጽዕኖ የሚያሳድርብን በመሆኑ ወላጆችም ሆኑ ልጆች የሚያዳምጡትን ሙዚቃ በጥንቃቄ ቢመርጡ ጥሩ ይሆናል። ወላጅ ከሆንክ ልጆችህ የሚያዳምጡትን ሙዚቃ በንቃት ትከታተላለህ? የሚያዳምጡትን ሙዚቃ የሚመርጡበትን መስፈርትስ ታወጣላቸዋለህ?
እንዲህ ሲባል አንዳንድ አልበሞችን ወይም የሙዚቃ ዓይነቶችን እንዳይሰሙ መከልከል ማለት ብቻ አይደለም። ልጆችህ ተቀባይነት ያላቸውን ሙዚቃዎች እንዲመርጡ መርዳትም ይኖርብሃል። ኦን ቢካሚንግ ቲንዋይዝ የተባለው መጽሐፍ “አንድን ሰው በጣም የሚወደውን ነገር ቀምተኸው እንዲሁ ባዶውን ልትተወው አትችልም። በምትኩ ሌላ አዲስ ነገር ሊኖረው ይገባል፤ ካልሆነ ግን ወደነበረበት መመለሱ አይቀርም” ይላል።
ሌላም ግምት ውስጥ መግባት የሚኖርበት ጉዳይ አለ፦ ልጆችህ ሙዚቃ በማዳመጥ ምን ያህል ጊዜ ያሳልፋሉ? የቤት ሥራ ለመሥራት፣ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ለመካፈል፣ በቤት ውስጥ ያሉባቸውን ኃላፊነቶች ለመወጣትና ለመሳሰሉት ይበልጥ አስፈላጊ ለሆኑ ጉዳዮች የሚያውሉትን ጊዜ እየተሻማባቸው ነው? መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “ለሁሉም ነገር ጊዜ አለው።”—መክብብ 3:1
ሌላው ችግር ደግሞ ራስን ማግለል ሊሆን ይችላል። እርግጥ ነው፣ ሁላችንም የአስተሳሰብ ብስለት እንዲኖረን ከፈለግን ብቻችንን ሆነን የምናሰላስልበት ጊዜ ሊኖረን ይገባል። (መዝሙር 1:2, 3) ይሁን እንጂ አንድ ሰው ብዙ ጊዜ ብቻውን መሆን የሚመርጥ ከሆነ ራስ ወዳድና ስለ ራሱ ብቻ የሚያስብ ሊሆን ይችላል። (ምሳሌ 18:1) የ20 ዓመቱ ፌሊፔ ‘ለራሱ የሚሆን ጊዜ’ እንዳገኘ የሚሰማው ሙዚቃ በሚያዳምጥበት ጊዜ ነው። “እናቴ ግን ራሴን እያገለልኩ እንደሆነ ስለሚሰማት ትጨነቃለች” በማለት ተናግሯል።
እንደ ፌሊፔ ያሉትን ወጣቶችና ወላጆቻቸውን እንዲጨቃጨቁ ሊያደርጋቸው የሚችለውን ነገር ወደ ጋራ መድረክነት መለወጥ የሚቻለው እንዴት ነው? ሁላችንም በሙዚቃ ረገድ ጥሩ ምርጫ ልናደርግ የምንችለው እንዴት ነው? ብዙዎች የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች በዚህ ረገድ ጥሩ እገዛ እንደሚያደርጉ ተገንዝበዋል። ለምን የሚከተሉትን ሦስት ጥያቄዎች ከልጆቻችሁ ጋር አትወያዩባቸውም?
● ሙዚቃው ምን መልእክት ያስተላልፋል? “ዝሙትና ማንኛውም ዓይነት ርኩሰት ወይም ስግብግብነት በመካከላችሁ ከቶ አይነሳ።” (ኤፌሶን 5:3) መጥፎ መልእክት የማያስተላልፉ ግጥሞች ያሏቸው ብዙ ዘፈኖች አሉ። በዚያው መጠን ደግሞ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተዘረዘሩት ያሉትን ጤናማ እሴቶች የሚጻረር መልእክት የሚያስተላልፉ ዘፈኖች ብዙ ናቸው። እንዲያውም በወራዳነታቸው እንዲሁም ጥላቻንና ዓመፅን የሚያስፋፉ በመሆናቸው ተለይተው የሚታወቁ አንዳንድ የሙዚቃ ስልቶች አሉ። ካረን ስተርንሃይመር የተባሉ ደራሲ “የራፕ ግጥሞች አልፎ አልፎ አስደንጋጭ፣ አንዳንድ ጊዜ ጭካኔ የሞላባቸው፣ ሴቶችን የሚያጥላሉና ጸያፍ አነጋገርን የሚያስፋፉ ናቸው” ብለዋል። የሄቪ ሜታል ግጥሞች ብዙውን ጊዜ ዓመፅንና መናፍስታዊ ድርጊቶችን ይቀላቅላሉ። ሰፊ ተቀባይነት ያገኙ ሙዚቃዎችም እንኳ ሳይቀሩ አጠያያቂ ባሕርያትን ሊያስፋፉ ይችላሉ። ስለዚህ ሙዚቃ በምትመርጡበት ጊዜ “የማሰብ ችሎታችሁን” ተጠቀሙ። (ሮም 12:1) ዜማው ስለጣማችሁ ወይም ተወዳጅ ስለሆነ ብቻ በጭፍን አትወሰዱ።
● ሙዚቃው ምን ዓይነት ስሜት ይፈጥርብኛል? “ልብህን ጠብቅ፤ የሕይወት ምንጭ ነውና።” (ምሳሌ 4:23) የሙዚቃ ምርጫህ በልብህና በአእምሮህ ውስጥ ያለውን ውስጣዊ ማንነትህን በማሳየት ብቻ ተወስኖ የሚቀር አይደለም። በአእምሮህና በልብህ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። ቀደም ሲል የተጠቀሰው ጆርዳን “አንዳንድ የሙዚቃ ዓይነቶችን ማዳመጥ ግልፍተኛና ጠበኛ እንድሆን ያደርገኝ ነበር” ብሏል። ራስህን እንደሚከተለው ብለህ ጠይቅ፦ ‘የማዳምጠው ሙዚቃ በአስተሳሰቤና በስሜቴ ላይ ምን ለውጥ ያመጣል? ዘና እንድልና መንፈሴ እንዲታደስ ያደርጋል ወይስ ውጥረት ውስጥ እንድገባና እንድበሳጭ ያደርገኛል? ተገቢ ያልሆኑ ሐሳቦችን ይቀሰቅስብኛል?’ (ቆላስይስ 3:5) አንድ ሙዚቃ የማትፈልገውን ስሜት ካሳደረብህ ወይም በውስጥህ ተገቢ ያልሆነ ነገር እንዲቀሰቀስ ካደረገ ብታስወግደው የተሻለ ይሆናል። (ማቴዎስ 5:28, 29) የ17 ዓመቷ ሃና “መጥፎ ሙዚቃ የሚያስከትለው ጉዳት ስለሚታየኝ ምንም ዓይነት ንክኪ እንዲኖረኝ አልፈልግም” ብላለች።
● ሙዚቃ በሥነ ምግባር እሴቶቼ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል? አሞጽ 5:15 “ክፉውን ጥሉ፤ መልካሙንም ውደዱ” ይላል። በዛሬው ጊዜ ይህን ማድረግ በጣም አስቸጋሪ ነገር ሆኗል፤ ምክንያቱም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንደሚለው ዛሬ ሰዎች “ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች፣ ተሳዳቢዎች፣ ለወላጆች የማይታዘዙ፣ የማያመሰግኑ፣ ታማኝ ያልሆኑ፣ ተፈጥሯዊ ፍቅር የሌላቸው፣ ለመስማማት ፈቃደኞች ያልሆኑ፣ ስም አጥፊዎች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ ጥሩ ነገር የማይወዱ፣ . . . አምላክን ከመውደድ ይልቅ ሥጋዊ ደስታን የሚወዱ” የሆኑበት ጊዜ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-4) በመሆኑም ቁጥር 5 “ከእነዚህ ደግሞ ራቅ” ይላል።
ኤፌሶን 4:25, 29, 31) ታዲያ ይህን ማድረግህ የሙዚቃ ምርጫህን በእጅጉ ያጠብብሃል? በፍጹም!
እንደነዚህ ካሉት ሰዎች የምትርቀው እንዴት ነው? በአካል ከእነሱ ከመራቅ የበለጠ ነገር ማድረግን እንደሚጨምር ግልጽ ነው። ከአምላክ የራቁ መሆናቸውን ከሚያንጸባርቁ ሸቀጦቻቸውም መራቅ ይኖርብሃል። (ምርጫህን አስፋ
በብዙ ቤተሰቦች ውስጥ ወላጆችና ልጆች አንዳቸው ሌላው የሚያዳምጠውን ሙዚቃ ማወቅ ያስደስታቸዋል። ሊና እንዲህ ትላለች፦ “የ13 ዓመት ልጄ የምትወደውን ሙዚቃ አሰማችኝ፤ አሁን እኔም ደስ ብሎኝ አዳምጠዋለሁ።” የ16 ዓመቷ ሄዘርና ወላጆቿ አንዳቸው የሌላውን ሙዚቃ ያዳምጣሉ፤ አዘውትረውም ሲዲዎችን ይዋዋሳሉ።
በመላው ዓለም በሁሉም የዕድሜ ክልሎችና ባሕሎች የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የይሖዋ ምሥክሮች ለይሖዋ ዘምሩ * በተባለው የመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ የሚገኙትን በመንፈሳዊ የሚያበለጽጉ ሙዚቃዎች ጨምሮ የተለያየ ይዘት ያላቸውን በርካታ የሙዚቃ ስልቶች ያዳምጣሉ። ሆኖም በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ያሉት ዜማዎች በአንዳንድ ባሕሎች ከተለመደው ስልት ለየት ያሉ ናቸው።
ወላጅም ሆንክ ልጅ አንድን የሙዚቃ አልበም ለመግዛት ወይም ከኢንተርኔት ዳውንሎድ ለማድረግ ስታስብ ለምን ራስህን የሚከተሉትን ጥያቄዎች አትጠይቅም፦ ‘ሙዚቃ ሰምቶ የመደሰትን ችሎታ የሰጠኝ ማነው? ፈጣሪዬ ይሖዋ አምላክ አይደለም? ታዲያ ለስጦታዎቹ አድናቆት እንዳለኝ ማሳየት የምችለው እንዴት ነው? ትክክልና ስህተት እንዲሁም ጥበብ ወይም ሞኝነት ስለሆኑ ምርጫዎች ላወጣው መስፈርት ከፍተኛ ግምት በመስጠት አይደለም?’ እንደነዚህ ባሉት ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰልህ የምታዳምጠውን ሙዚቃ በጥበብ እንድትመርጥና ይህንንም በማድረግ የገዛ ራስህንም ሆነ የፈጣሪህን ልብ ደስ እንድታሰኝ ያስችልሃል።—ምሳሌ 27:11
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.2 አንዳንዶቹ ስሞች ተቀይረዋል።
^ አን.17 www.pr418.com ከተባለው ድረ ገጽ ላይ ዳውንሎድ ማድረግ ይቻላል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
አንዳንድ የሙዚቃ ስልቶች በወራዳነታቸው የታወቁ ናቸው
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
አዳምጠህ የምትደሰትባቸው ብዙ ዓይነት ሙዚቃዎች አሉ
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ለውጥ ያደረግኩት ለምንድን ነው?
የ24 ዓመቱ አሽሊ “የጉርምስና ዕድሜዬ በአልኮል መጠጥ፣ በዕፅና በጠበኝነት የተሞላ ነበር” ይላል፤ “ለዚህ ሁሉ የዳረገኝ ደግሞ ሄቪ ሜታልና ራፕ ሙዚቃ ማዳመጤ ነበር። በብልግናና በጥላቻ ቃላት የተሞሉት ግጥሞችና ስሜት ቀስቃሽ የሆኑት ምቶቹ ጉልበተኛ እንደሆንኩ እንዲሰማኝ ያደርጉ ነበር። በተጨማሪም ሙዚቃው የዕፅ ሱሰኛ ከሆኑት ጓደኞቼ ጋር ይበልጥ አስተሳሰረኝ። እኔም ሆንኩ ጓደኞቼ የራፕ አቀንቃኞችንና የሄቪ ሜታል ባንዶችን እንደ ጣዖት እንመለከታቸው ነበር።
“ይሁን እንጂ ብዙም ሳይቆይ መላ ሕይወቴ ከቁጥጥር ውጭ በሆነ አቅጣጫ ማምራት ጀመረ። የ17 ዓመት ወጣት ሳለሁ ከመጠን ያለፈ ዕፅ በመውሰዴ ሞት አፋፍ ደርሼ ነበር። ልክ ስነቃ አምላክ እንዲረዳኝ ጸለይኩ። በአንድ ወቅት አንድ ልጅ የአምላክ ስም ይሖዋ እንደሆነ ነግሮኝ ነበር፤ እኔም ስለዚህ ስም ሳስብ የይሖዋ ምሥክሮች ወደ አእምሮዬ መጡ። በመሆኑም የስልክ ማውጫውን አንስቼ ለይሖዋ ምሥክሮች ደወልኩ፤ ከዚያም ከእነሱ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀመርኩ።
“መጥፎ ልማዶቼን ተውኩ እንዲሁም ሙዚቃዎቼን በሙሉ አውጥቼ ጣልኩ። ሲዲዎቼን ቆሻሻ መጣያ ውስጥ ከጣልኳቸው በኋላ እነሱን እያየሁ ፍዝዝ ብዬ ቀረሁ። ልቤ ለሁለት ተከፍሎ ነበር። ይሁንና ሙዚቃውም ሆነ መጥፎ ልማዶቼ ሊያጠፉኝ እንደነበር አሰብኩ። በመሆኑም ዞር ብዬ መሄድ ጀመርኩ።
“ይህ ከሆነ ዓመታት ያለፉ ቢሆንም ዛሬም ሄቪ ሜታልና ራፕ ሙዚቃዎች ቀልቤን መሳባቸው አልቀረም። በመሆኑም ሱስ እንደሚያስይዙ ዕፆች በመቁጠር እሸሻቸዋለሁ። አሁን እንደ ክላሲካል፣ ባላድና ኢዚ ሮክ የመሳሰሉትን ለስለስ ያሉ ሙዚቃዎች መስማት ያስደስተኛል። በጣም ደስ የሚለው ነገር አሁን ሙዚቃ ሕይወቴን አይቆጣጠረውም።”
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ለወላጆች የሚጠቅሙ ሐሳቦች
የልጃችሁ የሙዚቃ ምርጫ ያሳስባችኋል? በእናንተና በልጃችሁ መካከል ግጭት ሳይፈጠር ልጃችሁን መርዳት የምትችሉት እንዴት ነው? የሚከተሉትን ነጥቦች ልብ በሉ፦
በቂ መረጃ ይኑራችሁ ከመናገራችሁ በፊት በቂ መረጃ ይኑራችሁ። ሙዚቃውን አዳምጡ፣ ግጥሞቹን ልብ በሉ እንዲሁም የሲዲውን ሽፋን በደንብ ተመልከቱ። ‘በእርግጥ ሊያሳስበኝ የሚገባ ነገር አለ ወይስ ከልክ በላይ ጥብቅ ሆኜ ነው?’ በማለት ራሳችሁን ጠይቁ። መጽሐፍ ቅዱስ “አስተዋይ ሰዎች ከመናገራቸው በፊት ቆም ብለው ያስባሉ፤ ከዚያ በኋላ የሚናገሩት ነገር ይበልጥ አሳማኝ ይሆናል” ይላል።—ምሳሌ 16:23 ቱዴይስ ኢንግሊሽ ቨርሽን
አስተዋይ ሁኑ ሙዚቃ በልጃችሁ ልብ ውስጥ ያለውን ነገር የሚያሳይ መስኮት ሊሆን ይችላል። ቀስ ብላችሁ ስሜቱን አውጥቶ እንዲናገር አድርጉት። “ይህን ሙዚቃ የምትወደው ለምንድን ነው? ስሜትህን ስለሚገልጽልህ ነው?” ብላችሁ ጠይቁት። ከዚያም የሚሰጠውን መልስ በጥንቃቄ አዳምጡ። ምሳሌ 20:5 “የሰው ሐሳብ በጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ እንዳለ ውሃ ነው፤ ይሁን እንጂ ማስተዋል ያለው ሰው ይቀዳዋል” ይላል።—የታረመው የ1980 ትርጉም
ገንቢ ሁኑ ግባችሁ ልጁ መጥፎ የሆነውን ሲዲ አውጥቶ እንዲጥል ማድረግ ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ‘ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መለየት እንዲችል የማስተዋል ችሎታውን’ በማሠልጠን የራሱን ትክክለኛ ውሳኔ እንዲያደርግ መርዳት መሆን አለበት። (ዕብራውያን 5:14) ስለዚህ ለልጃችሁ ለዘለቄታው የሚጠቅመው ቅርስ ስጡት፦ ምርምር እንዲያደርግና የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች መሠረት አድርጎ እንዲያገናዝብ አሠልጥኑት። በዚህ መንገድ የማመዛዘን ችሎታና አምላካዊ ጥበብ እንዲያዳብር ትረዱታላችሁ፤ ይህ ደግሞ በዓለም ላይ ካለው ወርቅ ሁሉ የበለጠ ትልቅ ዋጋ አለው!—ምሳሌ 2:10-14፤ 3:13, 14
የማትወላውሉ፣ አዛኝና ደግ ሁኑ “ከአንጀት የመነጨ ርኅራኄን፣ ደግነትን፣ ትሕትናን፣ ገርነትንና ትዕግሥትን ልበሱ።” (ቆላስይስ 3:12) ከወጣት ልጃችሁ ጋር በምትነጋገሩበት ጊዜ ግትር ወይም ተጨቃጫቂ አትሁኑ። እናንተም በአንድ ወቅት ወጣት እንደነበራችሁ አትዘንጉ።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የምታዳምጠውን ሙዚቃ ለመምረጥ የላቀ መስፈርት ይኑርህ