በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

በሳምንት አንድ ቅዱስ ቀን መመደብ ያስፈልጋል?

በሳምንት አንድ ቅዱስ ቀን መመደብ ያስፈልጋል?

መጽሐፍ ቅዱስ ምን ይላል?

በሳምንት አንድ ቅዱስ ቀን መመደብ ያስፈልጋል?

በምድር ዙሪያ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ሙስሊሞች፣ አይሁዶችና ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች በየሳምንቱ ለተለያዩ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች የሚሆን አንድ ቀን መድበዋል። ይህን የሚያደርጉት ለምንድን ነው? ለምሳሌ ያህል፣ ለስግደትና ስብከት ለማዳመጥ በየሳምንቱ ዓርብ ወደ መስጊድ የሚሄድ ኢብራሂም የሚባል አንድ ቀናተኛ ሙስሊም “ወደ አምላክ ለመቅረብ እንዲሁም የአእምሮ ሰላም ለማግኘት እፈልጋለሁ” በማለት ተናግሯል።

ታዲያ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ በሳምንት ውስጥ አንዱን ቀን ቅዱስ አድርገን መመደብ እንዳለብን ይናገራል? በአንድ የተወሰነ ቀን ብቻ አምልኮን ማከናወን እውነተኛ መንፈሳዊ እረፍት ያስገኛል?

ለተወሰነ ጊዜ ብቻ የሚቆይ ዝግጅት

ከ3,500 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት አምላክ በነቢዩ ሙሴ አማካኝነት በርካታ ሕግጋትን ሰጥቶ ነበር። የሙሴ ሕግ ለአምልኮ የተመደቡ የእረፍት ቀናትን ወይም ሰንበታትን ያካትት ነበር። በተደጋጋሚ ይከበር የነበረው የእረፍት ቀን ሳምንታዊው ሰንበት ነበር። ሳምንታዊው ሰንበት ዓርብ ጀምበር ስትጠልቅ ጀምሮ ቅዳሜ ጀምበር ስትጠልቅ ያበቃ ነበር።​—ዘፀአት 20:8-10

ሁሉም ብሔራት ሳምንታዊውን የሰንበት ቀን እንዲያከብሩ ይጠበቅባቸው ነበር? በፍጹም። የሙሴ ሕግ የተሰጠው ለእስራኤላውያንና የእነሱን እምነት ለተቀበሉ ሰዎች ነበር። አምላክ፣ ‘እስራኤላውያን ሰንበትን እንዲጠብቁ’ ለሙሴ ነግሮት የነበረ ሲሆን አክሎም “[ሰንበት] በእኔና በእስራኤላውያን መካከል ለዘላለም ምልክት ይሆናል” ብሎታል። *​—ዘፀአት 31:16, 17

መጽሐፍ ቅዱስ የሙሴ ሕግ “ለሚመጡት ነገሮች ጥላ” እንደነበረ ይናገራል። (ቆላስይስ 2:17) በመሆኑም ሰንበት ወደፊት የሚመጣውን የላቀ ትርጉም ያለው ነገር ከሚያመለክቱትና ለተወሰነ ጊዜ ብቻ ከሚቆዩት ዝግጅቶች መካከል አንዱ ነበር። (ዕብራውያን 10:1) ሳምንታዊውን የሰንበት ቀን እንዲያከብሩ የሚጠይቀውን ሕግ ጨምሮ ለእስራኤል የተሰጡት ሕግጋት በሙሉ ኢየሱስ ሲሞት ከአምላክ አመለካከት አንጻር ወደ ፍጻሜ እንደመጡ መጽሐፍ ቅዱስ ያመለክታል። (ሮም 10:4) ታዲያ ሕጉ የተተካው በምን ነበር?

አዲስ ዓይነት አምልኮ

መጽሐፍ ቅዱስ፣ የሙሴ ሕግ ዓላማውን ካከናወነ በኋላ በምትኩ የሚቋቋመው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው አምልኮ የትኛው እንደሆነ በማያሻማ መንገድ ይገልጻል። ታዲያ ይህ አምልኮ በሳምንት ውስጥ አንድን ቀን ለአምልኮ መመደብን ይጨምራል?

ለእስራኤል ብሔር የተሰጡት አንዳንድ ትእዛዛት በክርስቲያን ጉባኤ አባላት ላይም እንደሚሠሩ ቅዱሳን መጻሕፍት ያመለክታሉ። እነዚህም ከጣዖት አምልኮ፣ ከዝሙትና ደምን ከመብላት መራቅን አስመልክቶ የተሰጡትን ትእዛዛት ይጨምራሉ። (የሐዋርያት ሥራ 15:28, 29) እዚህ ላይ፣ ክርስቲያኖች እንዲጠብቁ ከተሰጧቸው ትእዛዛት መካከል ሳምንታዊውን ሰንበት ስለማክበር የሚናገረው ሕግ እንዳልተካተተ ልብ ሊባል ይገባዋል።​—ሮም 14:5

መጽሐፍ ቅዱስ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች አምልኳቸውን ያከናውኑ ስለነበረበት መንገድ ምን የሚነግረን ተጨማሪ ነገር አለ? ክርስቲያኖች ለመጸለይ፣ ቅዱሳን መጻሕፍትን ለማንበብ፣ ንግግሮችን ለማዳመጥና በመዝሙር አምላክን ለማወደስ አዘውትረው ይሰበሰቡ እንደነበር ይነግረናል። (የሐዋርያት ሥራ 12:12፤ ቆላስይስ 3:16) እንዲህ ባሉት ስብሰባዎች ላይ መገኘታቸው እምነታቸውን ያጠናክርላቸው የነበረ ከመሆኑም ሌላ በስብሰባዎቹ ላይ መመሪያ ይቀበሉና እርስ በርስ ይበረታቱ ነበር።​—ዕብራውያን 10:24, 25

ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ስብሰባዎችን እሑድ ዕለት ወይም በሳምንቱ ውስጥ በአንድ የተወሰነ ቀን ያደርጉ እንደነበረ አይናገርም። ታዲያ ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙ ሰዎች እሑድን እንደ ቅዱስ ቀን አድርገው የሚመለከቱት ለምንድን ነው? በእሑድ ዕለት አምልኮን የማከናወን ልማድ ብቅ ያለው መጽሐፍ ቅዱስ ተጽፎ ከተጠናቀቀና ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረት የሌላቸው የተለያዩ እምነቶችና ልማዶች መታየት ከጀመሩ በኋላ ነበር።

ታዲያ አምላክ ከጊዜ በኋላ በሳምንቱ ውስጥ ሰዎች በኅብረት ሆነው አምልኮ የሚያቀርቡበት አንድ ቀን እንዲኖራቸው ወስኖ ነበር ማለት ነው? በፍጹም። መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛው አምልኮ እንዴት መካሄድ እንዳለበት በዝርዝር ይገልጻል። ቅዱሳን መጻሕፍት ተጽፈው ከተጠናቀቁ በኋላ በመንፈስ መሪነት የተጻፉ ሌሎች ተጨማሪ ጽሑፎች የሉም። ሐዋርያው ጳውሎስ “ከእኛ መካከል አንዱ ወይም ከሰማይ የወረደ መልአክ፣ ከሰበክንላችሁ ምሥራች የተለየ ሌላ ምሥራች ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን” በማለት በመንፈስ መሪነት ጽፏል።​—ገላትያ 1:8

አምላክን የሚያስደስትና እረፍት የሚሰጥ አምልኮ

በኢየሱስ ዘመን የነበሩት የሃይማኖት መሪዎች በሳምንት ውስጥ አንዱን ቀን ቅዱስ አድርገው ያከብሩ ነበር፤ ሆኖም ልባቸው ክፉ ስለነበረ አምልኳቸው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አልነበረውም። እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ገንዘብን የሚወዱና ትሑት የሆነውን ተራ ሕዝብ የሚንቁ ነበሩ። የክብር ቦታ እንዲሰጣቸው ይፈልጉ የነበረ ሲሆን በሙስና እና በዘመኑ በነበረው ፖለቲካዊ ሽኩቻ ውስጥ ተዘፍቀው ነበር። (ማቴዎስ 23:6, 7, 29-33፤ ሉቃስ 16:14፤ ዮሐንስ 11:46-48) አምላክን እንደሚወክሉ ይናገሩ የነበረ ቢሆንም አምላክ ለሰዎች እረፍት እንዲያስገኝ ብሎ የሰጠውን የሰንበትን ሕግ ጨቋኝ በሆኑ ሰው ሠራሽ ደንቦች ለወጡት።​—ማቴዎስ 12:9-14

ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው አንድን ቀን ቅዱስ አድርጎ ማክበር በአምልኳችን እርካታ ለማግኘት ወሳኝ ነገር አይደለም። ታዲያ ወሳኝ የሆነው ነገር ምንድን ነው? ኢየሱስ እንዲህ ያለ ግሩም ግብዣ አቅርቧል፦ “እናንተ የደከማችሁና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ።” (ማቴዎስ 11:28) በእርግጥም ኢየሱስ ባስተማራቸው ትምህርቶች ላይ የተመሠረተ አምልኮ እረፍት ያስገኛል። እንዲህ ያለው አምልኮ ከግብዝነትና ሸክም ከሆኑ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች የጸዳ ነው።

በዓለም ዙሪያ የሚገኙት የይሖዋ ምሥክሮች የጥንቶቹ የኢየሱስ ተከታዮች ያካሂዱ የነበረውን የአምልኮ ሥርዓት በጥብቅ ይከተላሉ። የይሖዋ ምሥክሮች የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት የሚማሩባቸው በየሳምንቱ የሚያካሄዱ ስብሰባዎች አሏቸው። ስብሰባዎቻቸውን የሚያደርጉባቸውን ቀናት የሚወስኑት በአካባቢያቸው ባሉ ሁኔታዎች ላይ ተመሥርተው እንጂ ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆኑ ልማዶች አይደለም። አንተም በአካባቢህ በሚደረገው እንዲህ ባለው ስብሰባ ላይ በመገኘት እረፍት በሚያስገኘው በዚህ አምልኮ መካፈል ትችላለህ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.7 በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ “ዘላለም” የሚለው ቃል የተሠራበት ፍጻሜ የሌለውን ዘመን ለማመልከት ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ መጨረሻው ያልተወሰነ ረጅም ጊዜን ሊያመለክት ይችላል።

ይህን አስተውለኸዋል?

● አምላክን በሳምንቱ ውስጥ አንድ የተወሰነ ቀን መድበህ ማምለክ ይኖርብሃል?​—ሮም 10:4፤ 14:5

● ለአምልኮ አንድ ላይ መሰብሰብ ያለብን ለምንድን ነው?​—ዕብራውያን 10:24, 25

● አምልኳችን እርካታ እንዲያስገኝልን ወሳኝ የሆነው ነገር ምንድን ነው?​—ማቴዎስ 11:28

[በገጽ 10 እና 11 ላይ የሚገኝ ቻርት/​ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ማክሰኞ

ረቡዕ

1 ሐሙስ

2 ዓርብ

3 ቅዳሜ

4 እሑድ