በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

የታታር ሕዝቦች—የቀድሞ፣ የአሁንና የወደፊት ሕይወታቸው

የታታር ሕዝቦች—የቀድሞ፣ የአሁንና የወደፊት ሕይወታቸው

የታታር ሕዝቦች—የቀድሞ፣ የአሁንና የወደፊት ሕይወታቸው

ከልጅነቴ ጀምሮ “አንድ ሩሲያዊ ቢፋቅ ውስጡ ታታር ነው” እየተባለ ሲነገር እሰማ ነበር። እኔም ሩሲያዊ እንደሆንኩ አስብ ነበር፤ ነገር ግን አያቴ የታታር ተወላጅ እንደነበረ ዘመዶቼ በቅርቡ ነገሩኝ። * ይህን ለጓደኞቼ ስነግራቸው ከእነሱ አንዳንዶቹ እንደ እኔ የታታር ዝርያ እንዳላቸው አጫወቱኝ።

ዝነኛ ስለነበሩ የታታር ሰዎች እንዲሁም በኪነ ጥበብ፣ በስፖርትና በሌሎችም መስኮች ስላገኙት ከፍተኛ ስኬት ሳውቅ ገረመኝ። ለምሳሌ ያህል፣ የተዋጣለት የባሌ ዳንስ ተዋዛዋዥ የነበረውና በመስኩ ላይ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣው ሩዶልፍ ነሪየቭ የተወለደው ሩሲያ ውስጥ ሲሆን ቤተሰቦቹ የታታር ሰዎች ነበሩ። የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ክፍል በነበሩ አገሮች ውስጥ ሰባት ሚሊዮን የሚያህሉ የታታር ሕዝቦች ይኖራሉ። እስቲ ስለ ታታር ሕዝቦች አንዳንድ ነገሮችን ላውጋችሁ።

የቀድሞ ታሪካቸው

የታታር ሕዝብ ለብዙ መቶ ዘመናት ይጠቀስ የነበረው ከሞንጎላውያንና ከቱርካውያን ጋር ተያይዞ ነበር። የታታር ሕዝቦች በ13ኛው መቶ ዘመን የሞንጎላውያን መሪ በነበረው በጀንጊስ ካን አዝማችነት በተካሄደ ወታደራዊ ዘመቻ ተካፍለዋል። * እጅግ ሰፊ የነበረው የጀንጊስ ካን ግዛት የቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት ከነበራት ስፋት ጋር ይተካከል ነበር። በ1236 ወደ 150,000 የሚጠጉ ወታደሮቹ ከኡራል ተራሮች በስተ ምዕራብ አንስቶ ወደሚገኘው የአውሮፓ ግዛት አመሩ። እዚያም ሲደርሱ በመጀመሪያ በሩሲያ ከተሞች ላይ ጥቃት ሰነዘሩ።

ሞንጎላውያን ሩሲያን ድል ካደረጉ በኋላ ብዙም ሳይቆይ የሞንጎላውያንና የቱርክ ሕዝቦች የሚኖሩበት ግዛት መሠረቱ፤ አንዳንዶች የዚህን ግዛት ምዕራባዊ ክፍል ወርቃማው ሠራዊት ብለው ጠርተውታል። የዚህ ግዛት ዋና ከተማ የሆነችው ሳራይ ባቱ በታችኛው የቮልጋ ወንዝ አካባቢ ትገኝ ነበር። ይህ ግዛት የሳይቤሪያን የተወሰነ ክፍልና በዚያ የሚገኙትን የኡራል ተራሮች እንዲሁም በዩክሬንና በጆርጂያ ያሉትን የካርፓቲያና የካውካሰስ የተራራ ሰንሰለቶች ይጨምር ነበር። በመሳፍንት የሚተዳደሩ የሩሲያ ግዛቶች ለዚህ ግዛት ግብር እንዲከፍሉ ተደርገው ነበር። በ15ኛው መቶ ዘመን ግዛቱ ተከፋፍሎ እንደ ክሪሚያ፣ አስትራካን እና ካዛን ያሉት መንግሥታት ተቋቋሙ።

ታታርስታንና ዋና ከተማዋ ካዛን

በዛሬው ጊዜ የአውሮፓ ክፍል በሆነችው በሩሲያ ምሥራቃዊ ክፍል የምትገኘውና የበርካታ ብሔር ብሔረሰቦች መኖሪያ የሆነችው የታታርስታን ሪፑብሊክ አራት ሚሊዮን የሚያህሉ ሕዝቦች ይገኙባታል። የግዛት ክልሏ 68,000 ካሬ ኪሎ ሜትር ያህል ሲሆን “በሩሲያ ፌዴሬሽን ውስጥ በኢኮኖሚ እጅግ የበለጸጉ ዜጎች” ከሚገኙባቸው ክልሎች አንዷ በመሆኗ ትታወቃለች። ታታርስታን ሩሲያ ውስጥ በዘይትና በጋዝ አምራችነት በዋነኝነት የምትጠቀስ ናት። በአገሪቱ የሚገኙት የኢንዱስትሪ ተቋማት አውሮፕላኖችና አውቶሞቢሎች የሚያመርቱ ሲሆን ሪፑብሊኳ በርካታ አውሮፕላን ማረፊያዎችም አሏት።

ካዛን፣ የቮልጋና የካዛንካ ወንዞች የሚገናኙባት አንድ ሚሊዮን ነዋሪዎች ያሏት ዘመናዊ ከተማ ናት። የሚያማምሩ የመሬት ውስጥ የባቡር መሥመሮችን ከገነቡ በርካታ የሩሲያ ከተሞች መካከል አንዷ ናት። * እያንዳንዱ ባቡር ጣቢያ ለሕዝቡ የሚተላለፍ መልእክት የያዘ ሥዕል አለው። አንዳንዶቹ አሠራራቸው ዘመናዊ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ የምሥራቁን ዓለም ወይም የመካከለኛውን መቶ ዘመን የግንባታ ንድፍ ያንጸባርቃሉ። በካዛን የሚገኝ አንድ ባቡር ጣቢያ በታታር ሕዝቦች ባሕላዊ ተረት ውስጥ የሚጠቀሱ ምናባዊ ፍጥረታትን በሚያሳዩ ግድግዳ ላይ በጠጠር በተሳሉ 22 ሥዕሎች ያጌጠ ነው።

የካዛን ፌዴራል ዩኒቨርሲቲ በ1804 ቀዳማዊ አሌክሳንደር በሚባለው የሩሲያ ዛር የተቋቋመ ሲሆን በሩሲያ ካሉት ግዙፍ ቤተ መጻሕፍት አንዱ በዚያ ይገኛል። ዩኒቨርሲቲው በማስተማር ሂደትና ባሕልን በማስፋፋት ረገድ ጉልህ ድርሻ ያበረከተ ከመሆኑም ሌላ በታታርስታን ለሚገኙ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም ፈር ቀዳጅ ሆኗል። ቤተ መጻሕፍቱ ካሉት 5,000,000 ጽሑፎች መካከል 30,000 የሚሆኑት ጥንታዊ የእጅ ጽሑፎች ሲሆኑ ከእነሱም መካከል አንዳንዶቹ በዘጠነኛው መቶ ዘመን ዓ.ም. የተጻፉ ናቸው።

በከተማዋ መካከል በሚገኘው በባውማን ጎዳና ላይ በእግር መንሸራሸር መንፈስን ያድሳል። በአካባቢው የሚያማምሩ ሱቆችና ሻይ ቤቶች በብዛት ይገኛሉ። እኔና ባለቤቴ በቅርቡ ወደዚህ ቦታ ሄደን በነበረበት ጊዜ ከተማዋን ከጎበኘን በኋላ በቮልጋ ወንዝ ላይ በጀልባ በመንሸራሸር ተዝናንተናል።

በካዛን ጉልህ ስፍራ ከሚሰጣቸው ነገሮች አንዱ ዝነኛው የክሬምሊን ግንብ ነው። የተለያዩ ሕንፃዎችን አቅፎ የያዘው ይህ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ግንብ በ16ኛው መቶ ዘመን የተሠራ ሲሆን በሩሲያ እስከዚህ ዘመን ድረስ የዘለቀ ብቸኛው የታታር ግንብ ነው። በካዛን በሚገኙት የክሬምሊን ግንቦች ውስጥ የሲዩዩምቢኬ ማማ፣ የታታርስታን መንግሥት ሕንፃዎች፣ አንድ መስጊድና አንድ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ይገኛሉ።

በ2000 በካዛን የሚገኘው የክሬምሊን ግንብ የዓለም ቅርስ ሆኖ በዩኔስኮ ተመዝግቧል። በክሬምሊን የሚገኙት ሕንፃዎች ንድፍ በተለይ በማታ ሲታይ በጣም ያምራል። ይህ ሊሆን የቻለው ወንዙ ላይ በሚያንጸባርቁት መብራቶች የተነሳ ነው።

ሕዝቡና መግባቢያ ቋንቋው

በሩሲያ ካሉት የቱርክ ዝርያ ያላቸው ሕዝቦች ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የታታር ሕዝቦች ሲሆኑ ቁጥራቸው 5,500,000 እንደሚደርስ ይገመታል። ይሁን እንጂ እጅግ ሰፊ በሆነው በሩሲያ የሚኖሩት የታታር ሕዝቦች ምን ያህል እንደሆኑ አይታወቅም።

የታታር ሕዝቦች ቋንቋ ከቱርክ ቋንቋዎች ግንድ የተገኘ ነው። ይህ የቋንቋ ግንድ አዘርባጃኒ፣ ባሽኪር፣ ካዛክ፣ ኪርጊዝ፣ ኖጋይ፣ ተርኪሽ፣ ቱርኮማን፣ ቱቪኒየን፣ ኡዝቤክና ያኩት የሚባሉትን ቋንቋዎች ያጠቃልላል። ከእነዚህ ቋንቋዎች ውስጥ አንዳንዶቹ ከመመሳሰላቸው የተነሳ በተወሰነ ደረጃም ቢሆን የአንዱ ቋንቋ ተናጋሪ በሌላው ቋንቋ የሚነገረውን ነገር መረዳት ይችላል።

በዓለም ላይ፣ መሠረታቸው ቱርክኛ የሆኑ ቋንቋዎችን የሚናገሩ ሰዎች በብዙ ሚሊዮን ይቆጠራሉ። በመላው የታታርስታን ከተሞች ውስጥ ሰዎች የታታርና የሩሲያኛ ቋንቋዎችን የሚናገሩ ሲሆን በጋዜጦችና በመጻሕፍት ላይ እንዲሁም በሬዲዮና በቴሊቪዥን በሚተላለፉ ፕሮግራሞች ላይ እነዚሁ ቋንቋዎች ይሠራባቸዋል። ታታርስታን ውስጥ በታታር ቋንቋ የሚቀርቡ ቲያትሮች በሕዝቡ ታሪክ፣ ባሕልና የዕለት ተዕለት ሕይወት ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው።

በካዛንም ሆነ በሌሎች ከተሞች በሚገኙ ሱቆችና ጎዳናዎች ላይ ምልክቶች የሚጻፉት በሩሲያኛና በታታር ቋንቋ ነው። ሩሲያኛ፣ ከታታር ቋንቋ የተወሰዱ ብዙ ቃላት አሉት። ሶቪየት ኅብረት ውስጥ በ1928 የታታር ቋንቋ የሚጻፍበት ፊደል ከአረብኛ ወደ ላቲንኛ እንዲለወጥ ተደርጎ ነበር። ከ1939 ወዲህ ደግሞ የታታር ቋንቋ ከሩሲያው ሲሪሊክ ጋር በሚመሳሰል የሲሪሊክ ፊደል ሲጻፍ ቆይቷል።

የሕዝቡ ባሕል

የታታር ሕዝቦች በአንድ ወቅት አዳኞችና ከብት አርቢዎች ነበሩ። በዛሬው ጊዜም ባሕላዊ ምግቦቻቸው በብዛት ከሥጋ የሚዘጋጁ ናቸው። ከእነዚህ አንዱ ቤሌሽ የሚባለው ብዙዎቹ የታታር ቤተሰቦች የሚወዱት ምግብ ነው። ይህ ምግብ የሚዘጋጀው በተዳመጠ ሊጥ ውስጥ ድንች፣ ሥጋ፣ ሽንኩርትና የተለያዩ ቅመሞች በመክተት፣ ከዚያም መጋገሪያ ውስጥ ለሁለት ሰዓት ያህል በማብሰል ነው። በሚገባ በስሎ በትኩሱ የቀረበው ምግብ ገበታ በቀረቡት ሰዎች ሁሉ ፊት ይቆራረጣል።

የታታር ሕዝቦች ከሚያከብሯቸው በዓላት መካከል ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረውና እጅግ ተወዳጅ የሆነው ሳባንቱኢ የሚባለው ሳይሆን አይቀርም። ይህ በዓል በአረማዊ ልማድ ላይ የተመሠረተ ሲሆን ሰዎች አንድ ላይ ሆነው የሚጸልዩበት እንዲሁም ለፀሐይ አምላክና ለቀድሞ አባቶች መንፈስ መሥዋዕት የሚያቀርቡበት ነው። በዓሉን የሚያከብሩት ሰዎች እንደዚህ ያሉት መሥዋዕቶች የዘር ሐረጋቸው ቀጣይ እንዲሆን፣ እንስሶቻቸው እንዲራቡና ምድራቸው ፍሬያማ እንዲሆን ያደርጋሉ ብለው ያምናሉ።

የታታር ሕዝቦች ፈረስ ይወዳሉ። ፈረሶች በባሕላቸው ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጣቸው ሲሆን ይህም ከቀድሞ የዘላንነት ሕይወታቸው ጋር የተያያዘ ነገር ነው። ካዛን በዓለም ላይ ካሉ የፈረስ እሽቅድምድም ከሚካሄድባቸው በጣም ግሩም የሆኑ የመወዳደሪያ ቦታዎች አንዱ የሚገኝባት ከተማ ናት፤ የመወዳደሪያ ስፍራው 12 የፈረስ ጋጣዎችና አንድ የእንስሳት ሕክምና ክሊኒክ ያቀፈ ነው። ለፈረሶቹ የመዋኛ ገንዳም ሳይቀር ተዘጋጅቶላቸዋል!

የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዟል?

ቁርዓን “ከተውራት በኋላ በመዝሙር መጽሐፍ ውስጥ ‘ጻድቃን አገልጋዮቼ በእርግጥ ምድርን ይወርሳሉ’ ብለን ጽፈንላችኋል” ይላል። (ሱራ 21፣ አል አንቢያ [ነቢያቶች]፣ ቁጥር 105) ይህ ጥቅስ የተወሰደው ከቁርዓን በፊት ከ1,500 ዓመታት አስቀድሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጻፈው ከዳዊት መዝሙር እንደሆነ በግልጽ ማየት ይቻላል። መዝሙር 37:29 “ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፤ በእርሷም ለዘላለም ይኖራሉ” ይላል።

ይህ ደስተኛና ጻድቅ ሕዝብ የተውጣጣው ከየትኛው ብሔርና ጎሣ ነው? ኢንጂል ውስጥ (ከአዲስ ኪዳን የተወሰዱ ጽሑፎች ናቸው) “ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች የተውጣጡ አንድም ሰው ሊቆጥራቸው የማይችል እጅግ ብዙ ሕዝብ” እንደሚኖር የሚናገር ትንቢት ይገኛል። (ራእይ 7:9) ወደፊት ምድርን የሚሞላ ከብዙ ብሔርና የቆዳ ቀለም የተውጣጣ የወንድማማች ማኅበር ክፍል ሆኖ መኖር ምንኛ አስደሳች ይሆን! *

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.2 የታታር ሕዝቦች በአብዛኛው በሩሲያ የሚኖሩ ትልቅ የቱርክ ጎሣ ናቸው።

^ አን.5 በግንቦት 2008 የንቁ! እትም ላይ የወጣውን “ታላቅ ግዛት ያቋቋሙት የእስያ ዘላኖች” የሚል ርዕስ ተመልከት።

^ አን.9 የመሬት ውስጥ የባቡር መሥመር ካላቸው ሌሎቹ የሩሲያ ከተሞች መካከል የካተሪንበርግ፣ ሞስኮ፣ ኒዥኒ ኖቭጎሮድ፣ ኖቮሲቢሪስክ፣ ሴንት ፒተርስበርግ እና ሳማራ ይገኛሉ።

^ አን.25 የይሖዋ ምሥክሮች በሚያዘጋጁት ዘ ጋይዳንስ ኦቭ ጎድ​አወር ዌይ ቱ ፓራዳይዝ በተሰኘው ብሮሹር ላይ ስለ አምላክ ዓላማ ተጨማሪ መረጃ ማግኘት ይቻላል።

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የአምላክ ስም በታታር ቋንቋ

ዲነር ታሪክስብ (የዓለም ሃይማኖቶች) የተሰኘው ኤም. ከዣዪቭ በሚባሉ የታታር ደራሲ የተጻፈ መጽሐፍ አዳም የተፈጠረው በያኽቬ አላህ ወይም በይሖዋ አምላክ እንደሆነ ይናገራል። በተጨማሪም በታታር ቋንቋ በተዘጋጁት የኦሪት መጻሕፍት ውስጥ (በዘመናዊ መጽሐፍ ቅዱሶች መጀመሪያ ላይ የሚገኙት አምስት መጻሕፍት ማለት ነው) በ⁠ዘፍጥረት 2:4 ላይ የሚገኘው የግርጌ ማስታወሻ የአምላክን ስም አስመልክቶ ሲናገር “የጥንቶቹ ዕብራውያን ይህን ስም ይጠሩ የነበረው ያህቬ ብለው ሊሆን ይችላል” ይላል።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

በታታርስታን የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች

በሩሲያ ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ለሰዎች ስለ አምላክ መንግሥት የሚገልጸውን ምሥራች ለመናገር ከፍተኛ ፍላጎት ስላላቸው የታታርን ቋንቋ ለማስተማር ዝግጅት አድርገዋል። በታታርስታን የምትኖር አንዲት ሴት “በአፍ መፍቻ ቋንቋዬ ስለ አምላክ ያገኘሁት እውቀት ልቤን በጥልቅ ስለነካው አለቀስኩ” በማለት ተናግራለች።

በ1973 የታታር ተወላጆች የሆኑ የይሖዋ ምሥክሮችን ያቀፈ አንድ ትንሽ ቡድን በታታር ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት መሰብሰብ ጀመረ። በ1990ዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች በታታር ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማዘጋጀት ጀመሩ። * ከዚያም በ2003 በታታርስታን ሪፑብሊክ ውስጥ በናቤሬዥንዬ ቼልኒ በታታር ቋንቋ የሚካሄድ የመጀመሪያው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ተቋቋመ። በዛሬው ጊዜ ሩሲያ ውስጥ በታታር ቋንቋ የሚካሄዱ 8 ጉባኤዎችና 20 ቡድኖች አሉ።

በ2008 ከአስትራካን፣ ከቮልጋ አካባቢ፣ ከኡራል ተራሮች፣ ከምዕራብ ሳይቤሪያና ርቆ ከሚገኘው ሰሜናዊ ክፍል የመጡ ልዑካን በታታር ቋንቋ በተዘጋጀ የአውራጃ ስብሰባ ላይ ተገኝተዋል። አሁን በታታርስታን ግዛት በሩሲያኛ፣ በታታር ቋንቋና በሩሲያኛ የምልክት ቋንቋ የሚካሄዱ 36 ጉባኤዎችና ቡድኖች ያሉ ሲሆን ከ2,300 የሚበልጡ የምሥራቹ ሰባኪዎች በዚያ የሚኖሩትን ሰዎች ስለ አምላክ እውነቱን በማስተማሩ ሥራ በንቃት እየተካፈሉ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.37 የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ከ560 በሚበልጡ ቋንቋዎች መጽሐፍ ቅዱሶችንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን አዘጋጅቷል።

[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን/​ሥዕል]

አንድ አትሌት እረኛ ሆነ

ፒዮትር ማርከቭ የተወለደው በ1948 በታታርስታን በምትገኝ አንዲት መንደር ውስጥ ነበር። ለ30 ዓመታት ያህል በነፃ ትግልና ክብደት በማንሳት ችሎታው በአካባቢው የታወቀ ሰው ለመሆን በቅቶ ነበር። በአንድ ወቅት 32 ኪሎ ግራም ክብደት ያለው ብረት 130 ጊዜ አንስቷል። አሁን የይሖዋ ምሥክር ከሆነ ወዲህ የሚታወቀው ለሰዎች በታታርና በሩሲያኛ ቋንቋዎች ስለ አምላክ በመናገርና በሕይወታቸው ውስጥ የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች መቋቋም የሚያስችላቸውን እርዳታ በመስጠት ነው።

ፒዮትር አሳቢ የሆነውን የፈጣሪውን ባሕርይ ለማንጸባረቅ እየጣረ ይገኛል፤ ኢሳይያስ 40:11 ስለ አምላክ ሲናገር “መንጋውን እንደ እረኛ ያሰማራል፤ ጠቦቶቹን በክንዱ ይሰበስባል፤ በዕቅፉም ይይዛቸዋል፤ የሚያጠቡትንም በጥንቃቄ ይመራል” ይላል።

[ሥዕል]

ፒዮትር አሁን መንፈሳዊ እረኛ ሆኖ ያገለግላል

[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

ሩሲያ

ኡራል ተራሮች

ሞስኮ

ሴንት ፒተርስበርግ

የታታርስታን ሪፑብሊክ

ካዛን

ቮልጋ ወንዝ

[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በካዛንካ ወንዝ አካባቢ የሚገኘው የካዛኑ የክሬምሊን ግንብ

[የሥዕሉ ምንጭ]

© Michel Setboun/CORBIS

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

“ቤሌሽ” አብዛኞቹ የታታር ቤተሰቦች የሚወዱት ምግብ ነው