በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ገንዘብ መቆጠብ ያለብኝ ለምንድን ነው?

ገንዘብ መቆጠብ ያለብኝ ለምንድን ነው?

ገንዘብ መቆጠብ ያለብኝ ለምንድን ነው?

ብዙዎች እንዲህ ይላሉ፦ “ገንዘብ መቆጠብ አሰልቺ ነው። ልብሶችን፣ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችንና እነዚህን የመሳሰሉ ነገሮችን መግዛት ግን በጣም ያስደስታል።”

በዓለም ላይ የደረሰው የኢኮኖሚ ውድቀት በአንተ ሕይወት ላይ ተጽዕኖ አሳድሮብህ ቢሆንም ባይሆንም ገንዘብህን መቆጠብ እንዲሁም በአግባቡ መጠቀም ስለምትችልበት መንገድ ማወቅህ ይጠቅምሃል። ባለፉት መቶ ዘመናት፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ላጋጠሟቸው ችግሮች መፍትሔ መስጠት የቻለ አንድ አስተማማኝ መጽሐፍ የያዘውን ምክር እንመልከት።

ጥበብ የተንጸባረቀባቸው ሦስት ጥንታዊ ምሳሌዎች

የናዝሬቱ ኢየሱስ ከተናገራቸው ምሳሌዎች በአንዱ ላይ ገንዘብን በሚመለከት በጣም አስፈላጊ የሆነ መመሪያ ጠቁሟል። በዚህ ምሳሌ ላይ አንድ ጌታ አገልጋዩን “ገንዘቤን በባንክ ማስቀመጥ ነበረብህ፤ እኔም በመጣሁ ጊዜ ገንዘቤን ከነወለዱ እወስድ ነበር” የሚል ተግሣጽ እንደሰጠው ተገልጿል። (ማቴዎስ 25:27 የ1980 ትርጉም) ኢየሱስ በዚያ ዘመን የተናገረው ነገር በአሁኑ ጊዜ ለምንኖረውም ጠቃሚ ምክር ይዟል። እንዲህ የምንለው ለምን እንደሆነ እስቲ እንመልከት።

ከጥቂት ዓመታት በፊት በአንዳንድ አገሮች ሰዎች በባንክ ያስቀመጡት ገንዘብ በአሥር ዓመት ውስጥ የሚያስገኘው ወለድ መጀመሪያ ላይ ከተቀመጠው ገንዘብ ይበልጣል። በአሁኑ ጊዜ ግን እንዲህ ዓይነት ጠቀም ያለ ወለድ የሚከፍሉ ባንኮች ብዙ አይደሉም፤ አክሲዮን በመግዛት የሚገኘው ጥቅምም ብዙውን ጊዜ ባለአክስዮኖቹ ያሰቡትን ያህል ላይሆን ይችላል። ያም ሆኖ ለመጠባበቂያ የሚሆን ገንዘብ ማስቀመጥ ጥበብ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ገንዘብ ማስቀመጥ ያለውን ጥቅም ጎላ አድርጎ ሲገልጽ “ገንዘብ ጥላ ከለላ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ጥበብም ጥላ ከለላ ነው” ይላል። (መክብብ 7:12) ሆኖም ገንዘብህን ካልቆጠብክ ጥላ ከለላ ሊሆንልህ አይችልም! መጽሐፍ ቅዱስ “ከእናንተ እያንዳንዱ . . . እንደ ገቢው ሁኔታ የተወሰነ መጠን በቤቱ ያስቀምጥ” የሚል ማበረታቻ ይሰጣል።​—1 ቆሮንቶስ 16:2

ገንዘብ መቆጠብ የምትችለው እንዴት ነው?

በመጀመሪያ፣ አንድ ውድ ነገር ከመግዛትህ በፊት ‘በእርግጥ ይህ ነገር ያስፈልገኛል?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ።

ሁለተኛ፣ አንድ ነገር መግዛት ሲያስፈልግህ በቅናሽ የሚሸጡ ዕቃዎችን ወይም በጥሩ ሁኔታ ላይ የሚገኙ ያገለገሉ ዕቃዎችን ፈልግ። በኖርዌይ የሚኖሩ ኢስፔን እና ያኒ የሚባሉ ባልና ሚስት ዳንየል ለተባለው ሕፃን ልጃቸው ጋሪ ለመግዛት ፈለጉ። ከዚያም አዲስ ጋሪ ከሚሸጥበት በግማሽ በሚያንስ ዋጋ በጥሩ ይዞታ ላይ ያለ ያገለገለ ጋሪ ገዙ። ኢስፔን “ዳንየል ሲያድግ መልሰን በጥሩ ዋጋ ልንሸጠው እንደምንችል እርግጠኛ ነኝ” ብሏል። ይሁን እንጂ “ጥራት ያለው ዕቃ በጥሩ ዋጋ ለመግዛት ጊዜ ወስዶ መፈለግ ይጠይቃል” በማለት ተናግሯል። *

ሦስተኛ፣ ችኩል አትሁን፤ አንድን ነገር ከመግዛትህ በፊት በደንብ አስብበት። በነገሩ ካሰብክበት በኋላም ዕቃው እንደሚያስፈልግህ ከተሰማህ ዕቃውን ቅናሽ ከተደረገበት ወይም ያገለገሉ ዕቃዎች ከሚሸጡበት ሱቅ ለመግዛት ሞክር። በተጨማሪም ታዋቂ የሆኑ የንግድ ምልክቶች ያሉባቸውን ዕቃዎች ባለመግዛት ገንዘብህን መቆጠብ ትችላለህ። ከዚህም ሌላ ፋሽን የሆኑ የሕፃናት ልብሶችን ውድ ልብሶች ከሚሸጡባቸው ሱቆች ከመግዛት ይልቅ የወዳጅ ዘመዶችህ ልጆች ሕፃን ሳሉ ይለብሷቸው የነበሩትን ልብሶች ወስደህ መጠቀም ትችል ይሆናል።

በተመሳሳይም አንዲት እናት ሊታጠቡ የሚችሉ የሽንት ጨርቆችን መጠቀም ልትመርጥ ትችላለች። ዴኒዝ ቻምበርስ በጀቲንግ፣ ፐርሰናል ስፔንዲንግ ኤንድ መኒ ማኔጅመንት ኤ ኪ ቱ ዌዘሪንግ ዘ ስቶርም በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንደሚከተለው ብለዋል፦ “ካገለገሉ በኋላ የሚጣሉ የሕፃናት የንጽሕና መጠበቂያዎች (ዳይፐር) በ2 ዓመት ጊዜ ውስጥ 2,000 ወይም ከዚያ በላይ ዶላር (33,600 ብር) የሚያስወጡ ሲሆን . . . ከጨርቅ የሚዘጋጁ የንጽሕና መጠበቂያዎች ግን በተመሳሳይ ጊዜ ውስጥ ከ300 ዶላር (5,040 ብር) እስከ 500 ዶላር (8,400 ብር) ያስወጣሉ።” አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “ከጨርቅ የሚዘጋጁ የንጽሕና መጠበቂያዎች ለአጠቃቀም ምቹ ከመሆናቸውም በላይ አካባቢን አይበክሉም!”

አራተኛ፣ አብዛኛውን ጊዜ ውጭ ከመብላት ይልቅ ምግቡን ለማዘጋጀት የሚያገለግሉትን ነገሮች ገዝቶ ቤት ውስጥ ማብሰል ወጪ ይቆጥባል። ልጆቻችሁ ተማሪዎች ከሆኑ ውጪ እንዲበሉ ገንዘብ ከመስጠት ይልቅ ቀለል ያሉ ምግቦችን በማዘጋጀት ይዘው እንዲሄዱ ለምን አታስተምሯቸውም? ውድ የሆኑ የለስላሳ መጠጦችን ከመግዛት ይልቅ ውኃ እንዲጠጡ አድርጉ፤ ይህን ማድረጉ ለጤንነታቸው ጠቃሚ ከመሆኑም ሌላ ኪሳችሁን አይጎዳውም።

ቀደም ባሉት ጊዜያት ብዙ ቤተሰቦች የጓሮ አትክልት ይተክሉ ነበር። አንተስ የጓሮ አትክልቶችን ለማልማት አስበህ ታውቃለህ? በትናንሽ ቤቶችና በአፓርታማዎች የሚኖሩትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች የጓሮ አትክልቶችን ለማልማት የሚያስችል ትንሽ ቦታ አያጡም። በትንሽ መሬት ላይ ምን ያህል አትክልቶችን ማልማት እንደምትችል ስታውቅ መገረምህ አይቀርም!

በተጨማሪም የሚከተለውን ልብ በል፦ ሞባይል ስልክ መያዝ የሚያስፈልግህ ከሆነ ለድንገተኛ ጉዳዮች ብቻ መጠቀም እንዲሁም የቅድሚያ ክፍያ አገልግሎት ተጠቃሚ መሆን ትችላለህ? ወይም የልብስ ማድረቂያ ማሽን ካለህ በአጠቃቀምህ ላይ ገደብ ማድረግ ትችል ይሆን? ምናልባት ካጠብካቸው ልብሶች መካከል አንዳንዶቹን አሊያም ደግሞ ሁሉንም ፀሐይ ላይ ማስጣት ትችላለህ። ይህ ሐሳብ ከፍተኛ ኃይል ለሚጠቀሙ የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎችም ይሠራል። የኤሌክትሮኒክ መሣሪያውን እንደበራ ከመተው ይልቅ ማጥፋት ይኖርብህ ይሆናል። እንዲሁም ሌሎች የኤሌክትሪክ ፍጆታቸውን እንዴት እንደሚቆጥቡ ጠይቅ።

ወለድ የሚያስገኝ የቁጠባ ሂሣብ መክፈትም ጠቃሚ ነው። በተጨማሪም በደቡብ አፍሪካ የበጎ ፈቃድ ሠራተኛ ሆኖ የሚያገለግለው ሂልተን እንደተናገረው “ሁሉንም እንቁላሎችህን በአንድ ቅርጫት ውስጥ ማስቀመጥህ ጥበብ አይደለም።” አክሎም “ባንኮችና የገንዘብ ተቋሞች ከስረው የሚዘጉበት ጊዜ ይኖራል። ይህ ነገር አጋጥሞን ያውቃል” ብሏል። ስለዚህ ባንኩ ቢከስር ያጠራቀምከው ገንዘብ እንዲመለስልህ የመንግሥት ዋስትና ያለው ባንክ ምረጥ።

ከዕዳ መውጣት የሚቻለው እንዴት ነው?

አንደኛ፣ ማንኛውንም ዕዳ ወይም ብድር ስትከፍል በየወሩ መክፈል ከሚጠበቅብህ አነስተኛ መጠን አስበልጠህ ለመክፈል ጥረት አድርግ።

ሁለተኛ፣ መጀመሪያ ላይ ብዙ ወለድ ያለውን ዕዳ ለመክፈል ሞክር።

ሦስተኛ፣ በገንዘብ አወጣጥ ልማድህ ላይ ቁጥጥር አድርግ። በተለይ ይህ በጣም አስፈላጊ ነው።

ቀልብ በሚስብ ማስታወቂያ ላይ ያየኸውን ዕቃ ሁሉ ለማግኘት ትጥራለህ? በስዊድን የሚኖረው ዳኒ የተባለ የቤተሰብ ኃላፊ እንዲህ ያደርግ እንደነበር በግልጽ ተናግሯል። ጥሩ ንግድ የነበረው ቢሆንም ዕዳውን ለመክፈል ሲል ድርጅቱን ለመሸጥ ተገዷል። ከዚህ ጥሩ ትምህርት ስላገኘ ዛሬ በገንዘብ አወጣጥ ረገድ ራሱን መቆጣጠር ችሏል። ዳኒ “ከስግብግብነት ተጠበቁ። እንደ አቅማችሁ በመኖር ለመርካት ጥረት አድርጉ” የሚል ምክር ሰጥቷል።

አስፈላጊ የሆነ ብድር

አንድን ቤት ወይም አፓርታማ ሙሉውን ዋጋ ከፍለው መግዛት የሚችሉት ሁሉም ሰዎች አይደሉም። በመሆኑም ብዙ ሰዎች ከባንክ ይበደራሉ። ለተሰጣቸው ብድር በየወሩ የሚከፍሉት ገንዘብ እንደ ቤት ኪራይ ሊቆጠር ይችላል። ሆኖም በተወሰነ ጊዜ ውስጥ ዕዳቸውን ከፍለው ሲጨርሱ ቤቱ የራሳቸው ይሆናል።

በተጨማሪም ብዙ ሰዎች ነዳጅ ቆጣቢ የሆነ ተሽከርካሪ በብድር መግዛታቸው ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል። ዕዳቸውን ቶሎ ብለው ከከፈሉ መኪናው ዋጋ የሚያወጣ ንብረት ይሆንላቸዋል፤ ይህ ደግሞ ሌላው የቁጠባ ዘዴ ነው። * አንዳንዶች በጥሩ ይዞታ ላይ የሚገኝ ያገለገለ መኪናን መግዛት ጥሩ ሆኖ አግኝተውታል። ሌሎች ደግሞ በሕዝብ ማመላለሻ ወይም በብስክሌት በመጠቀም ገንዘብ ይቆጥባሉ።

ሁኔታው ምንም ይሁን ምን ስለምትገዛው ነገር ሚዛናዊና እውነታውን ያገናዘበ አመለካከት በመያዝ በጥንቃቄ ውሳኔ አድርግ። ገንዘብህን በግድየለሽነት የምታባክን ከሆነ ይህ ድርጊት ሱስ ሊሆንብህና ውሎ አድሮ ለከፍተኛ ጉዳት ሊዳርግህ ይችላል። ስለዚህ በገንዘብ አጠቃቀምህ ረገድ ብልህና ጠንቃቃ በመሆን ዘላቂ ደስታ ማግኘት ትችላለህ።

በተጨማሪም ቆጣቢ ለመሆን ከፈለግህ ገንዘብህን በአግባቡ መጠቀም የምትችለው እንዴት እንደሆነ ማወቅ ይኖርብሃል። የሚቀጥለው ርዕስ ይህን ጉዳይ ያብራራል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.10 የተሰረቀ ዕቃ እንዳትገዛ የሻጩ ስምና አድራሻ የተጻፈበት ደረሰኝ መቀበልህ ጥበብ ነው።

^ አን.24 የገቢ ምንጭ አጥተህ ዕዳህን መክፈል ቢያቅትህ እስከዚያን ጊዜ ድረስ የከፈልከውን ገንዘብ ጨምሮ ቤትህን ወይም መኪናህን ልታጣ እንደምትችል ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርብሃል።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ገንዘብ መቆጠብ የሚቻልባቸው መንገዶች

የዋጋ ቅናሽ የተደረገባቸውን ዕቃዎች ፈልግ

ልብሶችን ቅናሽ ከተደረገባቸው ወይም ያገለገሉ ልብሶች ከሚሸጡባቸው ሱቆች ግዛ

ልጆችህን ምግብ ማዘጋጀት አስተምራቸው

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጓሮ አትክልት በመትከል የምግብ ወጪህን ቀንስ። የታጠቡ ልብሶችን ውጪ በማስጣት ገንዘብ ቆጥብ