በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

“እውቀት በመቅሰም ረገድ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ማሽን”

“እውቀት በመቅሰም ረገድ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ማሽን”

“እውቀት በመቅሰም ረገድ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ማሽን”

የሕፃን ልጅ አእምሮ “እውቀት በመቅሰም ረገድ በአጽናፈ ዓለም ውስጥ ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ማሽን” ተብሎ የሚጠራ ሲሆን እንዲህ የተባለውም ያለ በቂ ምክንያት አይደለም። አንድ ሕፃን ሲወለድ በአካባቢው ያሉትን ነገሮች በማየት፣ በመስማትና በመዳሰስ የሚያገኛቸውን መረጃዎች እንደ ስፖንጅ ለመምጠጥ አእምሮው ዝግጁ ነው። *

ከሁሉ በላይ ደግሞ አንድ ሕፃን የሰዎችን ፊት ሲያይ፣ ድምፃቸውን ሲሰማና ሲደባብሱት ትኩረቱ ይሳባል። በፐነሎፒ ሊች የተጻፈው ሕፃንነት (እንግሊዝኛ) የተሰኘው መጽሐፍ እንዲህ ይላል፦ “ከምንም ነገር በላይ የአንድን ሕፃን ዓይን የሚማርኩትን ነገሮች፣ ትኩረቱን የሚስቡትን ድምፆች እንዲሁም እንዲደጋገሙለት የሚፈልጋቸውን ስሜቱን የሚኮረኩሩ ድርጊቶች በተመለከተ በርካታ ጥናቶች ተካሂደዋል። ሕፃኑ እነዚህን ሁሉ ነገሮች ከሚንከባከበው ሰው በማንኛውም ጊዜ በቀላሉ ማግኘት ይችላል።” በእርግጥም ወላጆች ከልጃቸው እድገት ጋር በተያያዘ ወሳኝ ሚና የሚጫወቱ መሆናቸው ምንም አያስገርምም!

‘እንደ ሕፃን እናገር ነበር’

አንድ ሕፃን በመስማት ብቻ ቋንቋን መማር መቻሉ ወላጆችንም ሆነ የሕፃናት ሐኪሞችን በጣም ያስገርማቸዋል። ተመራማሪዎች በጥናት እንደደረሱበት አንድ ሕፃን በተወለደ በጥቂት ቀናት ውስጥ የእናቱን ድምፅ የሚለይ ከመሆኑም በላይ ከሌላ ሰው ድምፅ ይልቅ የእናቱን ድምፅ መስማት ያስደስተዋል፤ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ የወላጆቹን ቋንቋ ከሌሎች ቋንቋዎች መለየት ይችላል፤ በጥቂት ወራት ውስጥ ደግሞ ሰዎች በሚናገሩበት ወቅት ቃላትን እየነጣጠሉ እንደሚጠሩ ስለሚያስተውል በንግግርና ትርጉም በማይሰጡ ድምፆች መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ ይችላል።

ክርስቲያኑ ሐዋርያው ጳውሎስ “ሕፃን በነበርኩበት ጊዜ እንደ ሕፃን እናገር . . . ነበር” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮንቶስ 13:11) አንድ ሕፃን የሚናገረው እንዴት ነው? ብዙውን ጊዜ ለመረዳት የሚያስቸግር ውል የሌለው ድምፅ በማውጣት ነው። ታዲያ ይህ ትርጉም የሌለው ድምፅ ምንም ጥቅም የለውም ማለት ነው? በፍጹም! ዶክተር ሌዝ ኢሊየት በአእምሯቸው ውስጥ ምን እየተከናወነ ነው?—በመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት የሕፃናት አንጎልና አእምሮ የሚዳብርበት መንገድ (እንግሊዝኛ) በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ እንደገለጹት መናገር “ከንፈርን፣ ምላስን፣ ላንቃንና ማንቁርትን የሚቆጣጠሩትን በርካታ ጡንቻዎች በፍጥነት ማቀናጀትን የሚጠይቅ ውስብስብ ሥራ” ነው። እኚህ ሴት አክለውም እንዲህ ብለዋል፦ “ሕፃናት ድምፅ የሚያሰሙት እንዲያው ትኩረት ለማግኘት ብቻ ሊመስል ቢችልም እንዲህ ማድረጋቸው ውስብስብ የሆነውንና ጡንቻዎችን ማቀናጀትን የሚጠይቀውን የንግግር ችሎታ ለመለማመድም ይረዳቸዋል።”

ወላጆችም ልክ እንደ ሕፃኑ በመናገር ልጃቸው ለሚያሰማው ድምፅ ምላሽ የሚሰጡ ሲሆን ይህም ጠቃሚ ነው። እንዲህ ዓይነት አነጋገር ሕፃኑም ምላሽ እንዲሰጥ ያነሳሳዋል። በወላጆችና በልጆች መካከል የሚደረገው እንዲህ ያለው ምልልስ ለሕፃኑ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ የሚቻልበትን መንገድ የሚያስተምረው ሲሆን ይህም ሕይወቱን በሙሉ የሚጠቀምበት ችሎታ ነው።

ሚናቸው ሲለወጥ

አራስ ልጅ ያላቸው ወላጆች የሕፃኑን የዕለት ተዕለት ፍላጎት ለማሟላት ስለሚጥሩ በጣም ሥራ ይበዛባቸዋል። ልክ ሕፃኑ ሲያለቅስ ይመግቡታል ወይም የሽንት ጨርቁን ይቀይሩለታል አሊያም ያቅፉታል። እንዲህ ዓይነቱ እንክብካቤ ተገቢና አስፈላጊ ነው። ወላጆች ሕፃኑን የመንከባከብ ኃላፊነታቸውን የሚወጡበት ዋነኛው መንገድ ይህ ነው።​—1 ተሰሎንቄ 2:7

ከላይ ከተገለጸው ሐሳብ አንጻር፣ አንድ ሕፃን ከማንም በላይ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሰው እሱ እንደሆነና አዋቂዎች በተለይም ደግሞ ወላጆቹ ዋነኛ ሥራቸው የእሱን ትእዛዝ መፈጸም እንደሆነ አድርጎ ቢያስብ ምንም አያስገርምም። ይህ አመለካከቱ የተሳሳተ ቢሆንም እንዲህ የሚሰማው ለምን እንደሆነ መረዳት አያዳግትም። ከአንድ ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ሕፃኑ በየዕለቱ የዚህ ዓይነት እንክብካቤ ሲያገኝ እንደቆየ መዘንጋት የለብንም። ሕፃኑ ራሱን የሚመለከተው እሱን ለማገልገል ብቻ የተቀመጡ ትልልቅ ሰዎች በሚኖሩበት ዓለም ላይ እንደሚገዛ ንጉሥ አድርጎ ነው። የቤተሰብ አማካሪ የሆኑት ጆን ሮዝመንድ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ ‘ሕፃኑ እንዲህ ያለውን ከእውነታው የራቀ አመለካከት ለማዳበር ሁለት ዓመት እንኳ አይፈጅበትም፤ ይህን አመለካከት ለማስተካከል ግን ቢያንስ ቢያንስ አሥራ ስድስት ዓመታት ያስፈልጋሉ! ይህን እርስ በርሱ የሚጋጭ የሚመስል ተግባር ማከናወን የወላጆች ኃላፊነት ነው፤ ልጃቸው ከእውነታው የራቀ አመለካከት እንዲያዳብር ካደረጉ በኋላ መልሰው ደግሞ ሐቁን እንዲገነዘብ በደግነት ይረዱታል።’

ልጁ ሁለት ዓመት ገደማ ሲሆነው የወላጆች ሚና ከተንከባካቢነት ወደ አስተማሪነት እየተቀየረ ይሄዳል፤ በዚህ ጊዜ ልጁ ሐቁን መገንዘብ ይጀምራል። ሕፃኑ፣ ወላጆቹን የሚመራቸው እሱ እንዳልሆነ ከዚህ ይልቅ የእነሱን መመሪያ መከተል እንደሚጠበቅበት ይገነዘባል። ልጁ እንደ ንጉሥ መግዛቱ አብቅቶለታል፤ ይህ ለውጥ ግን ላያስደስተው ይችላል። ሕፃኑ በዚህ በመበሳጨት ሥልጣኑን ላለመልቀቅ ያንገራግራል። ይህን የሚያደርገው እንዴት ነው?

እልኸኝነትን ማሸነፍ

ብዙ ሕፃናት ሁለት ዓመት ገደማ ሲሆናቸው ከፍተኛ የባሕርይ ለውጥ የሚታይባቸው ሲሆን ብዙውን ጊዜ ብስጩና እልኸኛ ይሆናሉ። ይህ ዕድሜ ለወላጆች በጣም ፈታኝ ጊዜ ነው። ድክ ድክ የሚለው ሕፃን ልጃቸው የሚቀናው ነገር “እምቢ!” ወይም “አልፈልግም!” ማለት ይሆናል። እርስ በርስ የሚጋጩ ስሜቶቹን ለማስተናገድ ስለሚጥር በራሱም ሆነ በወላጆቹ ሊበሳጭ ይችላል። በአንድ በኩል ከወላጆቹ መራቅ የሚፈልግ ሲሆን በሌላ በኩል ደግም አጠገባቸው መሆን ይሻል። በዚህ ግራ የተጋቡት ወላጆች የልጃቸው ጠባይ አልጨበጥ ይላቸዋል፤ አልፎ ተርፎም ችግሩን ለመፍታት የሚያደርጉት ጥረት ሁሉ ፍሬ ቢስ እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል። ልጁ ምን ሆኖ ይሆን?

እስቲ በሕፃኑ ሕይወት ውስጥ የተከናወኑትን ከፍተኛ ለውጦች እንመልከት። እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ሕፃኑ ባለቀሰ ቁጥር ትልልቅ ሰዎች ፈጥነው ይደርሱለት ነበር። አሁን ግን “ንግሥናው” ጊዜያዊ እንደነበረና ከዚህ በኋላ ቢያንስ ቢያንስ አንዳንድ ነገሮችን ራሱ ማከናወን እንዳለበት መገንዘብ ይጀምራል። የእሱ ሚና መገዛት እንደሆነ እያደር ይገባዋል፤ መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ሁኔታ ጠቅለል አድርጎ ሲገልጸው “ልጆች ሆይ፣ . . በሁሉም ነገር ለወላጆቻችሁ ታዘዙ” ይላል።​—ቆላስይስ 3:20

በዚህ አስቸጋሪ ዕድሜ ላይ ወላጆች ሥልጣናቸውን ማስከበር ይኖርባቸዋል። ጠንከር ባለ ሆኖም ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ይህን ካደረጉ ልጁ አዲሱን የሥራ ድርሻውን ይለምደዋል። ይህም ለቀጣዮቹ የእድገት ደረጃዎች ሁኔታው ምቹ እንዲሆን ያደርጋል።

ሥነ ምግባራዊ አቋም

እንስሳት፣ ሌላው ቀርቶ ማሽኖች እንኳ ቃላትን መለየትና የሰዎችን ንግግር አስመስሎ መናገር ይችላሉ። ቆም ብሎ ራሱን መመርመር የሚችለው ግን የሰው ልጅ ብቻ ነው። በመሆኑም አንድ ሕፃን በሁለት ወይም በሦስት ዓመት ዕድሜው የኩራት ባሕርይ ሊታይበት እንዲሁም የኀፍረት፣ የጥፋተኝነትና የመሸማቀቅ ስሜት ሊኖረው ይችላል። ሕፃኑ አሁን እንደነዚህ ያሉት ስሜቶችን ማዳበሩ ወደፊት ጥሩ የሥነ ምግባር አቋም ያለው ሰው እንዲሆን ይኸውም ሌሎች የተሳሳተ ነገር በሚያደርጉበት ጊዜም እንኳ እሱ ትክክል ለሆነው ነገር አቋም የሚወስድ ሰው እንዲሆን ይረዱታል።

በዚህ ዕድሜ አካባቢ ወላጆች ሌላም የሚያስደንቅ ነገር ያጋጥማቸዋል። ልጃቸው የሌሎችን ስሜት መረዳት ይጀምራል። በሁለት ዓመት ዕድሜው ሌሎች አጠገቡ እያሉ ብቻውን ይጫወት የነበረው ልጅ አሁን ግን ከእነሱ ጋር መጫወት ሊጀምር ይችላል። በተጨማሪም ወላጆቹ መደሰታቸውን ማወቅ ስለሚችል እነሱን ለማስደሰት ይሞክር ይሆናል። ይህም ትምህርት ለመቀበል ይበልጥ ዝግጁ እንዲሆን ሊረዳው ይችላል።

አንድ ልጅ በሦስት ዓመቱ፣ ትክክል ወይም ስህተት እንዲሁም ጥሩ ወይም መጥፎ ስለሆኑት ነገሮች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ማወቅ ይጀምራል። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ይህ ዕድሜ ወላጆች፣ ልጆቻቸው ኃላፊነት የሚሰማቸው ሰዎች እንዲሆኑ ለመርዳት ሥልጠና የሚሰጡበት ጊዜ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

^ አን.2 ለአጻጻፍ እንዲያመች ሲባል በዚህ መጽሔት ውስጥ ስለ ሕፃናት ስንናገር በወንድ ፆታ የተጠቀምን ቢሆንም የቀረቡት ነጥቦች ለሁለቱም ፆታዎች ይሠራሉ።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አንድ ሕፃን በተወለደ በጥቂት ቀናት ውስጥ የእናቱን ድምፅ የሚለይ ከመሆኑም በላይ ከሌላ ሰው ድምፅ ይልቅ የእናቱን ድምፅ መስማት ያስደስተዋል

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አንድ ልጅ በሦስት ዓመቱ፣ ትክክል ወይም ስህተት እንዲሁም ጥሩ ወይም መጥፎ ስለሆኑት ነገሮች ይበልጥ ማወቅ ይጀምራል

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

እልኸኝነት የሚባባስበት ምክንያት

“አንዳንድ ወላጆች፣ ልጆቻቸው እልኸኛ የሚሆኑት የሚፈልጉትን ነገር ስላልተሟሉላቸው እንደሆነ አድርገው ያስባሉ” በማለት ጆን ሮዝመንድ የተባሉት ሰው ወላጆች ሥልጣናቸውን መልሰው ሲያገኙ (እንግሊዝኛ) በተሰኘ ጽሑፋቸው ላይ ገልጸዋል። “ወላጆች፣ ልጁ እልኸኛ እንዲሆን ያደረጉት እነሱ ከሆኑ በተቻለ ፍጥነት ችግሩን ለመቅረፍ ሌላ ነገር ማድረግ እንዳለባቸው ይሰማቸዋል። በመሆኑም ልጃቸው የጠየቀውን ነገር እምቢ ካሉት በኋላ ተመልሰው እሺ ይሉታል። ወይም ደግሞ ልጃቸውን ከገረፉት በኋላ የጥፋተኝነት ስሜት እንዳይሰማቸው ሲሉ ልጁ መጀመሪያ ከጠየቀው የበለጠ ነገር ይሰጡታል። እንዲህ ዓይነቱ እርምጃ ሁለቱንም ወገኖች ያስደስታቸዋል። ወላጆች የልጁ እልህ ሲበርድ እፎይታ ያገኛሉ፤ ልጁ ደግሞ በእልህ የፈለገውን ማግኘት እንደሚችል ስለሚገነዘብ ይህ ባሕርይው እየባሰበት ይሄዳል።”