ማስረጃውን መርምር
ማስረጃውን መርምር
ማንም ሰው በማይኖርበት ርቆ የሚገኝ ደሴት ላይ ነህ እንበል። በባሕሩ ዳርቻ ላይ እየተንሸራሸርህ ሳለ “John 1800” የሚል ጽሑፍ የተቀረጸበት ዐለት ታያለህ። ደሴቱ ሰው የማይኖርበትና በጣም ርቆ የሚገኝ በመሆኑ እዚያ ቦታ ላይ ይህ ጽሑፍ ሊኖር የቻለው ዐለቱን ውኃ ስለሸረሸረው ወይም በነፋስ ምክንያት ነው ብለህ ትደመድማለህ? እንደዚህ እንደማትል የታወቀ ነው! ይህን ጽሑፍ አንድ ሰው ቀርጾታል ብለህ እንደምታስብ ጥርጥር የለውም፤ ደግሞም ትክክል ነህ። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? አንደኛ ነገር፣ በማታውቀው ቋንቋ ቢሆንም እንኳ በግልጽ የሰፈሩ ፊደላትና ቁጥሮች እንደ ነፋስና ውኃ ባሉት ተፈጥሯዊ ነገሮች ሊጻፉ እንደማይችሉ ግልጽ ነው። ሁለተኛ፣ ጽሑፉ ትርጉም ያለው መረጃ የያዘ መሆኑ የማሰብ ችሎታ ባለው አካል እንደተጻፈ የሚጠቁም ነው።
በዕለት ተዕለት ሕይወታችን በተለያዩ መንገዶች የሚቀርቡ መረጃዎች ያጋጥሙናል፤ ከእነዚህ መካከል የብሬይል ወይም የጽሑፍ ፊደላት፣ ሥዕላዊ መግለጫዎች፣ የሙዚቃ ኖታዎች፣ ንግግር፣ የእጅ ምልክቶች፣ የሬዲዮ መልእክቶች እንዲሁም ዜሮና አንድ ቁጥርን በመጠቀም የተጻፉ የኮምፒውተር ፕሮግራሞች ይገኙበታል። መረጃ የሚተላለፍበት መንገድ የተለያየ ነው፤ ለምሳሌ የብርሃን ወይም የሬዲዮ ሞገድ አለዚያም ወረቀትና ቀለም ሊሆን ይችላል። የሚተላለፍበት መንገድ ምንም ይሁን ምን ሰዎች ማንኛውም ትርጉም ያለው መረጃ ማሰብ ከሚችል አእምሮ የመነጨ እንደሆነ ይቀበላሉ፤ በሌላ በኩል ግን መረጃው ሕያው በሆነ ሴል ውስጥ የሚገኝ ሲሆን ከዚህ የተለየ አቋም ይይዛሉ። የዝግመተ ለውጥ አራማጆች እንዲህ ያለው መረጃ እንዲሁ በአጋጣሚ የተገኘ ወይም ራሱን በራሱ የጻፈ እንደሆነ ይገልጻሉ። ይህ ሊሆን ይችላል? እስቲ ማስረጃውን እንመርምር።
ውስብስብ የሆነ መረጃ ራሱን በራሱ ሊጽፍ ይችላል?
በሰውነትህ ውስጥ ባሉት በአብዛኞቹ ሕያው ሴሎች ኒውክሊየስ ውስጥ ዲኦክሲራይቦኑክሊክ አሲድ ይገኛል፤ ይህ አስደናቂ የሆነ የመረጃ ኮድ በአጭሩ ዲ ኤን ኤ ተብሎ ይጠራል። ዲ ኤን ኤ የሚገኘው የተጠማዘዘ መሰላል በሚመስል ረጅም ሞለኪውል ውስጥ ነው። ዲ ኤን ኤ በትሪሊዮን የሚቆጠሩት የሰውነትህ ሴሎች የሚፈጠሩበትን፣ የሚያድጉበትን፣ የሚታደሱበትንና የሚራቡበትን ሥርዓት የሚመራ መጽሐፍ ወይም የኮምፒውተር ፕሮግራም ነው ሊባል ይችላል። ዲ ኤን ኤ የተዋቀረባቸው መሠረታዊ ነገሮች ኒክሊዮታይድ ይባላሉ። ኒክሊዮታይዶች በውስጣቸው በያዟቸው ኬሚካሎች መሠረት ኤ፣ ሲ፣ ጂ እና ቲ ተብለው ይጠራሉ። * እነዚህ አራት ነገሮች እንደ ፊደላት በተለያየ መልኩ ተቀናጅተው “ዓረፍተ ነገሮችን” ይሠራሉ፤ ይኸውም በሴሎች ውስጥ ዲ ኤን ኤ የሚገለበጥበትን ሂደትና ሌሎች ሥራዎችን የሚያዝዙ መመሪያዎች ያስገኛሉ።
በዲ ኤን ኤ ውስጥ የሚቀመጠው መረጃ በጥቅሉ ጂኖም ተብሎ ይጠራል። በሴሎችህ ውስጥ የዲ ኤን ኤ ፊደላት ከሚቀመጡበት ቅደም ተከተል መካከል አንዳንዱ በአንተ ውስጥ ብቻ የሚገኝ ነው፤ ምክንያቱም ዲ ኤን ኤ የዓይንህን ቀለም፣ የቆዳህን
ቀለም፣ የአፍንጫህን ቅርጽና የመሳሰሉትን በዘር የሚተላለፉ መረጃዎች ይይዛል። በቀላል አነጋገር የአንተ ጂኖም እያንዳንዱ የሰውነትህ ክፍል እንዴት እንደተሠራ የሚገልጽ መረጃ በያዘ ትልቅ ቤተ መጻሕፍት ሊመሰል ይችላል፤ አንተ የተገኘኸው እነዚህ መረጃዎች አንድ ላይ በመቀናጀታቸው ነው።ይህ “ቤተ መጻሕፍት” ምን ያህል ትልቅ ነው? ሦስት ቢሊዮን “ፊደላት” ወይም ኒክሊዮታይዶች ይዟል። ይህን የሚያህል መረጃ ወረቀት ላይ ቢሰፍር እያንዳንዳቸው 1,000 ገጽ ባላቸው 200 ጥራዞች የተዘጋጀ የስልክ ማውጫ እንደሚወጣው ሂውማን ጂኖም ፕሮጀክት በተባለው ምርምር ላይ የተሳተፉ የሳይንስ ሊቃውንት ገልጸዋል።
ይህ ሐቅ ከ3,000 ዓመታት በፊት የተመዘገበን አንድ አስደናቂ ጸሎት ያስታውሰናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መዝሙር 139:16 ላይ የሚገኘው ይህ ጸሎት “ዐይኖችህ ገና ያልተበጀውን አካሌን አዩ፤ ለእኔ የተወሰኑልኝም ዘመናት፣ . . . በመጽሐፍ ተመዘገቡ” ይላል። እርግጥ ነው፣ ጸሐፊው ይህን ያለው ስለ ሳይንስ ለመናገር ፈልጎ አይደለም፤ ሆኖም የአምላክን አስደናቂ ጥበብና ኃይል ቀላል በሆነ መንገድ በትክክል ገልጾታል። መጽሐፍ ቅዱስ በተረቶችና በአጉል እምነቶች ከተሞሉት ሌሎች ጥንታዊ የሃይማኖት ጽሑፎች ምንኛ የተለየ ነው!
“ቤተ መጻሕፍቱን” ያደራጀው ማን ነው?
“John 1800” የሚለው ጽሑፍ በዐለት ላይ ተቀርጾ ሊገኝ የቻለው የማሰብ ችሎታ ያለው አካል ስለጻፈው እንደሆነ ካመንን ከዚህ ይበልጥ እጅግ ውስብስብ የሆነውንና ጥልቅ ትርጉም ያዘለውን በዲ ኤን ኤ ውስጥ የሚገኘውን መረጃ በተመለከተስ ተመሳሳይ ድምዳሜ ላይ ልንደርስ አይገባም? ደግሞም በዲ ኤን ኤ ውስጥ ትርጉም ያለው መረጃ እንደሚገኝ ማንም ሊክድ አይችልም። የኬሚስትሪ፣ የኮምፒውተርና የመረጃ ሳይንስ ምሁር የሆኑት ዳኖልድ ጆንሰን እንደገለጹት በዲ ኤን ኤ ውስጥ የሚገኘው ውስብስብ መረጃ የተመዘገበበትም ሆነ ጥቅም ላይ የሚውልበት ኬሚካላዊ ሂደት እንዲያው በአጋጣሚ የተገኘ ሊሆን እንደማይችል የኬሚስትሪና የፊዚክስ ሕግጋት ያሳያሉ። አንድ መረጃ የተጠናቀረበት መንገድ ይበልጥ ውስብስብ በሆነ መጠን ይህንን መረጃ ለመጻፍ የሚያስፈልገው እውቀትና ችሎታ የላቀ እንደሚሆን ግልጽ ነው። አንድ ሕፃን “John 1800” ብሎ ሊጽፍ ይችላል። የሕይወትን ኮድ ግን ሊጽፍ የሚችል ከሰው የላቀ የማሰብ ችሎታ ያለው አካል ብቻ ነው። ከዚህም በላይ ኔቸር የተባለው መጽሔት እንደሚለው እያንዳንዱ አዲስ ግኝት “የሥነ ሕይወት ምሥጢር እጅግ ውስብስብ” መሆኑን እያሳየ ነው።
በዲ ኤን ኤ ውስጥ የሚገኘውን ውስብስብ መረጃ የያዘ ቤተ መጻሕፍት ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት እንዲሁ በአጋጣሚ የተገኘ ነው ብሎ ማመን ምክንያታዊ ካለመሆኑም ሌላ በተሞክሮ ከምናውቀው ነገር ጋር ይጋጫል። * እንዲህ ያለው አስተሳሰብ ከጭፍን እምነት አይለይም።
የዝግመተ ለውጥ አማኞች፣ አምላክ እንደሌለ ለማሳመን ሲሉ የተናገሯቸው አንዳንድ ነገሮች ስህተት እንደሆኑ ከጊዜ በኋላ ተረጋግጧል። ለምሳሌ ያህል፣ ከሰው ልጆች ጂኖም ውስጥ 98 በመቶ የሚሆነው “አሰስ ገሰስ” (ጀንክ ዲ ኤን ኤ) ይኸውም በቢሊዮን የሚቆጠሩ እርባና ቢስ ቃላትን የያዙ
መጻሕፍት የሚገኙበት ቤተ መጻሕፍት እንደሆነ ተናግረዋል፤ እስቲ ይህን ጉዳይ እንመርምር።እውነት “አሰስ ገሰስ” ነው?
የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች ዲ ኤን ኤ ፕሮቲኖች እንዲመረቱ የሚያስፈልገውን መመሪያ ከመያዝ ውጪ ሌላ ጥቅም የለውም የሚል መደምደሚያ ላይ ከደረሱ ረጅም ጊዜ ሆኗቸዋል። ይሁንና ለፕሮቲኖች መመረት አስፈላጊ የሆነውን ኮድ የያዘው ክፍል ከጠቅላላው ጂኖም 2 በመቶ ገደማ ብቻ እንደሆነ ከጊዜ በኋላ ታወቀ። ታዲያ የቀረው 98 በመቶ የሚሆን ጂኖም ዓላማው ምንድን ነው? በብሪስበን፣ አውስትራሊያ የኩዊንስላንድ ዩኒቨርስቲ የሞለኪውላር ባዮሎጂ ፕሮፌሰር የሆኑት ጆን ማቲክ እንደተናገሩት ሊቃውንቱ እንቆቅልሽ የሆነባቸውን ይህን የዲ ኤን ኤ ክፍል “ከዝግመተ ለውጥ የተረፈ አሰስ ገሰስ” እንደሆነ ገልጸዋል።
“‘አሰስ ገሰስ’ ዲ ኤን ኤ” (ጀንክ ዲ ኤን ኤ) የሚለውን መጠሪያ እንደፈጠሩ የሚነገርላቸው የዝግመተ ለውጥ አራማጅ የሆኑት ሱሱሙ ኦኖ ናቸው። እኚህ ሰው “ሶ ማች ‘ጀንክ’ ዲ ኤን ኤ ኢን አወር ጂኖም” በተባለው ጥናታዊ ጽሑፋቸው ላይ 98 በመቶ የሚሆነውን የዲ ኤን ኤ ክፍል በተመለከተ እንዲህ ብለዋል፦ “ውጤታማ ያልሆኑ የተፈጥሮ ሙከራዎች ናቸው። ምድራችን ዝርያቸው በጠፋ ፍጥረታት ቅሪተ አካል ተሞልታለች፤ ታዲያ የእኛም ጂኖም በጠፉ ጂኖች ቅሪተ አካል የተሞላ መሆኑ ምን ያስደንቃል?”
“የአሰስ ገሰስ” ዲ ኤን ኤ ጽንሰ ሐሳብ በጄኔቲክስ መስክ በሚደረገው ጥናት ላይ ምን ተጽዕኖ አሳድሯል? ቮኢቼክ ማካሎቭስኪ የተባሉት የሞለኪውላር ባዮሎጂ ምሁር እንዲህ ያለው አስተሳሰብ “ታዋቂ የሆኑት ተመራማሪዎች ፕሮቲን ለመሥራት የሚያስችል መረጃ ባልያዘው የዲ ኤን ኤ ክፍል [አሰስ ገሰስ ዲ ኤን ኤ] ላይ ጥናት ከማካሄድ ወደኋላ እንዲሉ አድርጓቸዋል” ብለዋል። ሆኖም የተወሰኑ የሳይንስ ሊቃውንት “ለፌዝ ሊዳርጋቸው የሚችል ቢሆንም በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ ባልሆነው በዚህ ጉዳይ ላይ ምርምር አድርገዋል። በእነዚህ ሊቃውንት ምክንያት ስለ አሰስ ገሰስ ዲ ኤን ኤ ያለው ግንዛቤ . . . በ1990ዎቹ ዓመታት መባቻ አካባቢ መለወጥ ጀመረ።” ቮኢቼክ ማካሎቭስኪ አክለው እንደገለጹት ብዙዎች አሰስ ገሰስ ዲ ኤን ኤ ብለው ይጠሩት የነበረውን ነገር በአሁኑ ጊዜ የሥነ ሕይወት ተመራማሪዎች “የጂኖም ሀብት” እንደሆነ አድርገው መመልከት ጀምረዋል።
ጆን ማቲክ እንዳሉት ከሆነ የአሰስ ገሰስ ዲ ኤን ኤ ንድፈ ሐሳብ፣ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘው ሳይንሳዊ አስተሳሰብ ‘እውነታውን ሊያዛባ’ እንደሚችል የሚያሳይ ዓይነተኛ ምሳሌ ነው። አክለውም “ይህ የሚኖረውን አንድምታ አለመገንዘብ . . . በሞለኪውላር ባዮሎጂ ታሪክ ውስጥ በጣም ትልቅ ከሚባሉት ስህተቶች አንዱ ሳይሆን አይቀርም” ብለዋል። ሳይንሳዊ እውነቶች የሚወሰኑት በድምጽ ብልጫ ሳይሆን በማስረጃ መሆን እንዳለበት ግልጽ ነው። ታዲያ በቅርብ ጊዜ የተገኙ መረጃዎች ስለ “አሰስ ገሰስ” ዲ ኤን ኤ የሥራ ድርሻ ምን ያሳያሉ?
“የአሰስ ገሰስ” ዲ ኤን ኤ የሥራ ድርሻ
መኪና የሚያመርት ፋብሪካን እንደ ምሳሌ ብንወስድ ፋብሪካው የተለያዩ የመኪና ክፍሎችን የሚያመርቱ ማሽኖች ይኖሩታል። የመኪኖቹን ክፍሎች በአንድ ሴል ውስጥ ከሚኖሩት ፕሮቲኖች ጋር እናመሳስላቸው። ፋብሪካው እነዚህን የመኪና ክፍሎች ደረጃ በደረጃ የሚገጣጥሙ ማሽኖች እንዲሁም በዚህ ሂደት ላይ ማሽኖቹን የሚቆጣጠሩ ሌሎች መሣሪያዎች ያስፈልጉታል። በሴል ውስጥ የሚካሄደው እንቅስቃሴም ተመሳሳይ ነው። “አሰስ ገሰስ” ተብሎ የሚጠራው የዲ ኤን ኤ ክፍል የሚያስፈልገው እዚህ ላይ እንደሆነ ተመራማሪዎች ይናገራሉ። “አሰስ ገሰስ” ከሚባለው የዲ ኤን ኤ ክፍል አብዛኛው ሬጉሌተሪ አር ኤን ኤ (ራይቦኑክሊክ አሲድ) የሚባሉት ውስብስብ ሞለኪውሎች የሚሠሩበትን መመሪያ የያዘ ነው፤ እነዚህ ሞለኪውሎች ሴሎች በሚያድጉበትና ሥራቸውን በሚያከናውኑበት መንገድ ረገድ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ። * የማቲማቲካል ባዮሎጂ ባለሞያ የሆኑት ጆሽዋ ፕሎትከን ኔቸር በተባለው መጽሔት ላይ እንዲህ ብለዋል፦ “ሬጉሌተሪ አር ኤን ኤ የተባሉት ሞለኪውሎች መኖር በራሱ እጅግ መሠረታዊ ስለሆኑ ነገሮች ያለን ግንዛቤ . . . ለማመን በሚያዳግት ደረጃ ጠባብ እንደሆነ ይጠቁማል።”
ሥራውን በጥሩ ሁኔታ የሚያከናውን ፋብሪካ ውጤታማ የሆነ የመገናኛ አውታር ያስፈልገዋል። ከሴል ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በኦንታርዮ የቶሮንቶ ዩኒቨርስቲ የሴል ባዮሎጂ ባለሙያ የሆኑት ቶኒ ፖሰን “በሴሎች ውስጥ የመልእክት ልውውጥ የሚካሄደው ውስብስብ በሆኑ የመገናኛ አውታሮች አማካኝነት እንጂ ራሱን በቻለ አንድ ወጥ መስመር አይደለም” ይላሉ። ይህም መላውን ሂደት ከዚህ ቀደም ይታሰብ ከነበረው “ይበልጥ እጅግ ውስብስብ” ያደርገዋል። በእርግጥም አንድ የፕሪንስተን ዩኒቨርስቲ የጄኔቲክስ ተመራማሪ እንዳሉት “በሴሎች ውስጥ የሚከናወነውን ተግባርና ሴሎች አብረው የሚሠሩበትን መንገድ የሚቆጣጠሩት ብዙዎቹ ሥርዓቶችና መመሪያዎች አሁንም ድረስ ሚስጥር ናቸው።”
ስለ ሴል አዳዲስ ነገሮችን ባወቅን ቁጥር በውስጡ ላቅ ያለ ሥርዓትና ውስብስብነት እንደሚንጸባረቅ እንገነዘባለን። ይህ ከሆነ ታዲያ ብዙ ሰዎች፣ ሕይወትም ሆነ የሰው ልጅ እስከ ዛሬ ከደረሰበት ሁሉ ይበልጥ እጅግ ውስብስብ የሆነው የመረጃ ሥርዓት እንዲሁ በአጋጣሚ በዝግመተ ለውጥ ሂደት የመጣ ነው የሚለውን አስተሳሰብ የሙጥኝ ያሉት ለምንድን ነው?
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
^ አን.5 እያንዳንዱ ኒክሊዮታይድ (ኤ) አደኒን፣ (ሲ) ሳይተሲን፣ (ጂ) ጉዋኒን እና (ቲ) ታይሚን ከሚባሉት አራት መሠረታዊ ኬሚካሎች አንዱን ይይዛል።
^ አን.11 ዝግመተ ለውጥ የተከሰተው በሚውቴሽን አማካኝነት እንደሆነ ይታሰባል፤ እነዚህ ነጥቦች በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራሉ።
^ አን.19 በቅርብ የተደረጉ ምርምሮች እንደሚያሳዩት ፕሮቲን ለመሥራት የሚያስችል መረጃ ያልያዘው ረጅም አር ኤን ኤ በጣም ውስብስብ ከመሆኑም በላይ ጤናማ ለሆነ እድገት አስፈላጊ ነው። በዚህ አር ኤን ኤ ላይ እክል መኖሩ እንደ ካንሰር፣ ሶራያሲስና አልዛይመር ለመሳሰሉትና ለሌሎች በርካታ በሽታዎች እንደሚያጋልጥ ተመራማሪዎች ደርሰውበታል። ከዚህ በፊት “አሰስ ገሰስ” ተብሎ ይጠራ የነበረው የዲ ኤን ኤ ክፍል የተለያዩ በሽታዎችን መርምሮ ለማወቅና ለማከም የሚያስችል ቁልፍ ሳይሆን አይቀርም!
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ዲ ኤን ኤ ምን ያህል ርዝመት አለው?
በሰውነትህ ውስጥ ያለ የአንድ ሴል ዲ ኤን ኤ ሲዘረጋ 2 ሜትር ገደማ ርዝመት አለው። በሰውነትህ ውስጥ በሚገኙት በትሪሊዮን የሚቆጠሩ ሴሎች ውስጥ ያለውን ዲ ኤን ኤ በሙሉ ማውጣት ብንችልና የአንዱን ጫፍ ከሌላው ጋር እያያያዝን ብንቀጣጥለው ርዝመቱ ከምድር እስከ ፀሐይ ያለውን ደርሶ መልስ ርቀት 670 ጊዜ እንደሚሸፍን ይገመታል። አንድ ሰው በብርሃን ፍጥነት ቢጓዝ ይህን ርቀት ለመሸፈን 185 ሰዓት ይፈጅበታል።