በቀጥታ ወደ ዋናው ጉዳይ ግባ

በቀጥታ ወደ ርዕስ ማውጫው ሂድ

ተኪላ የሜክሲኮው አምባሳደር

ተኪላ የሜክሲኮው አምባሳደር

ተኪላ የሜክሲኮው አምባሳደር

● ስፔናውያን ቅኝ ገዢዎች በ16ኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ሜክሲኮ በደረሱ ጊዜ አጋቬ ከተባለ ተክል የሚዘጋጀውን ፑልኬ የሚባል የአልኮል መጠጥ ቀመሱ። ይህ መጠጥ ልክ እንደ ቢራ የአልኮል ይዘቱ አነስተኛ ነው። ከዚህም በላይ ፕሮቲን፣ ካርቦሃይድሬት፣ ቫይታሚንና የተለያዩ ማዕድናትን የያዘ በመሆኑ በብዙ አካባቢ የሚገኙ ሰዎች በመደበኛ ምግባቸው ውስጥ ከሚያገኙት በተጨማሪ ለጤና ጠቃሚ የሆኑትን እነዚህን ንጥረ ነገሮች ለማግኘት ሲሉ ፑልኬን እንደ ተጨማሪ ምግብ ይወስዳሉ።

ቀድሞውንም ቢሆን ከምግባቸው ጋር የአልኮል መጠጥ የማቅረብ ልማድ ያላቸው ስፔናውያን ብዙም ሳይቆይ ከአጋቬ የሚገኘውን ፈሳሽ እንደ አረቄ በማውጣት ሜስካል የተባለ ኃይለኛ የአልኮል መጠጥ መሥራት ጀመሩ። ይህ ደግሞ በዛሬው ጊዜ ተኪላ ተብሎ ለሚጠራው መጠጥ መገኘት ምክንያት ሆኗል። በአሁኑ ጊዜ በሜክሲኮ ተኪላ የሚያወጡ በርካታ ድርጅቶች አሉ፤ እነዚህ ድርጅቶች በየዓመቱ 189 ሚሊዮን ሊትር ተኪላ የሚያወጡ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 40 በመቶ የሚሆነው ወደ ውጭ ይላካል።

ሰማያዊ ቀለም ያለው የአጋቬ ዝርያ የሚበቅለው በማዕከላዊው ሜክሲኮ ምዕራባዊ ክፍል በሚገኙት ደረቅ በሆኑ ተራራማ አካባቢዎች ሲሆን በዋነኝነት የሚመረተው በጃሊስኮ ግዛት ባለችው በተኪላ ከተማ አቅራቢያ ነው፤ ተኪላ የተባለው መጠጥ ስያሜውን ያገኘው ከዚህች ከተማ ነው። * የአጋቬ ተክል፣ ምርት ለመስጠት 12 ዓመታት ይፈጅበታል፤ በዚህ ጊዜ ውስጥ ተክሉ ብዙ ማዕድናትን እየሳበ ወደ ውስጡ ያስገባል። ምርቱ የሚሰበሰብበት ጊዜ ሲደርስ የሾለ ጫፍ ያላቸው ቅጠሎቹ ይመለመላሉ፤ ከዚያም ፒና ተብሎ የሚጠራው የአናናስ ቅርጽ ያለው የተክሉ ክፍል ይቀራል። ፒናው በአማካይ 50 ኪሎ ግራም የሚመዝን ከመሆኑም በላይ በውስጡ ከፍተኛ መጠን ያለው ፈሳሽ ይይዛል። አንድ ሊትር ተኪላ ለማዘጋጀት 7 ኪሎ ግራም የሚመዝን ፒና ያስፈልጋል።

ብዙ ሜክሲካውያን የሚወዱት ያልተበረዘ ተኪላን መጠጣት ሲሆን ለጣዕም ሲሉ ጨውና በስሱ የተቆረጠ ኮምጣጤ ይጠቀማሉ። የውጭ አገር ሰዎች የበለጠ የሚያውቁት ማርጋሪታ የሚባለውን የተኪላ ኮክቴል ነው፤ ይህ መጠጥ የሚዘጋጀው የኮምጣጤ ጭማቂና የብርቱካን ጣዕም ያለው አልኮል ከተኪላ ጋር በመቀላቀል ሲሆን ክፈፉ ላይ ጨው በተደረገበት ብርጭቆ ውስጥ የተከሰከሰ በረዶ ከተጨመረ በኋላ የተደባለቀው መጠጥ ገብቶበት ይቀርባል። * ተኪላ 90 በሚያህሉ አገሮች ለገበያ የሚቀርብ በመሆኑ የሜክሲኮው አምባሳደር ተብሎ መጠራቱ የተገባ ነው።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

^ አን.4 በሜክሲኮ ካሉት 136 የአጋቬ ዝርያዎች ውስጥ በርከት ያሉት ፑልኬ እና ሌሎች የአልኮል መጠጦችን ለመሥራት ያገለግላሉ። ይሁን እንጂ ተኪላ ለማዘጋጀት የሚያገለግለው ሰማያዊው አጋቬ ብቻ ነው።

^ አን.5 መጽሐፍ ቅዱስ የአልኮል መጠጥ በመጠኑ መጠጣትን አያወግዝም። (መዝሙር 104:15፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:23) ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ከልክ በላይ መጠጣትንና ስካርን ያወግዛል።​—1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ ቲቶ 2:3